Translate

Monday, March 17, 2014

በዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ዝክር፤ በእህቶቻችን ኮርተናል! (ግንቦት 7)

March 17, 2014

Ginbot 7 weekly editorialለዘንድሮው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን መታሰቢያ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው የሩጫ ትዕይንት ላይ ወጣት ሴቶች ባሳዩት ልበ ሙሉነት ኮርተናል። የሩጫውን ትዕይንት አስታከው፣ በአብዛኛው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንደሆኑ የተነገረላቸው ወጣት ሴቶች ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለህሊና እስረኞች መፈታት እና ለሀገር አንድነት ድምፃቸውን ከፍ አድረገው ጮኸዋል፤ ዘምረዋል። እነዚህ ወጣት ሴቶች በሥርዓቱ ምን ያህል እንደተማረሩ በቃላትም በአካል ንቅናቄም አሳይተዋል። ዘረኛውና ፋሽስቱ ወያኔ ግን “ለምን ተቃወማችሁኝ” ብሎ አስሯቸዋል፤ ከፊሎቹም የደረሱበት አይታወቅም። በእህቶቻችን ቆራጥነት ኮርተናል፤ በወያኔ የፈሪ ዱላ ደግሞ ተቆጥተናል። በ1997 እና 98 “የወላጆቻችን ድምጽ ይከበር” ያሉ ሕፃናትን የጨፈጨፈው ወያኔ በ2006 ወጣት ሴቶችን ከማሰቃየት ይመለሳል ብለን አናምንም። ወያኔ እስካልተወገደ ድረስ የፈሪ ዱላው የማይቀር ነገር ነው።

የወንዶቹን ያህል የተዘገበ አይሁን እንጂ በክፉም በደጉም ሴቶች ያልተሳተፉበት የኢትዮጵያ ታሪክ የለም። የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኳን ብናይ በፋሽስት ወረራ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በአርበኝነት ዘምተው አዋግተዋል፤ ተዋግተዋል። በተለያዩ ምክንያቶች መዝመት ያልቻሉት ደግሞ በውስጥ አርበኝነት ተሰልፈው የጠላት ምስጢሮች ለአርበኞች እንዲደርሱ በማድረግ ከፍተኛ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል። ከፋሺስት ወረራ ወዲህ በነበሩ ዓመታት ውስጥም ለፍትህ እና ለነፃነት በተደረጉ ተጋድሎዎች ሴቶች ጉልህ ተሳትፎ ነበራቸው። በተማሪዎች ትግል ውስጥ ለምሳሌ፣ ወጣት ሴቶች በአመራር ደረጃ በመሳተፍ ትግሉን መርተዋል፤ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍለዋል። ከዚያ ወዲህም በነበሩት ዓመታት በኢሕአፓ እና ሌሎችም ድርጅቶች አመራርና አባልነት ተሳትፈው ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ነበሩን። በቅርቡም በምርጫ 97 እንቅስቃሴም የሴቶች በተለይም የወጣት ሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ጉልህ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውና እናስታውሳለን። ለምርጫ ድምጽ መከበር ወጣት ሽብሬ ደሣለኝን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ ከዚያ የበለጡት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዛሬም እንደ ርዕዮት ዓለሙ የመሳሰሉ ጀግኖች በወያኔ ወህኒ ቤቶች እየማቀቁ፤ በየእለቱ ሰቆቃ (ቶርቸር) እየተፈፀመባቸው መሆናቸው በሀዘንና በቁጭት እናስባቸዋለን።
በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊነት በመፈክር ደረጃ አንስተን የምንተወው ጉዳይ አይደለም። የሴቶች ተሳትፎ ያልታከለበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ግቡም አይመታም፤ ቢመታም ዋጋ የለውም።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የተካሄዱትን የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አብዮቶችን በአንክሮ የተከታተለ ማንኛውም ሰው ከሚገረምባቸው ነገሮች አንዱ ሴቶች ያሳዩት ቆራጥነት እና ያካሄዱት ብስለት የተሞላው ትግል ነው። በቱኒዚያ የወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ወጣት ሴቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ የአመራር ቦታ በመያዝ ተሳትፈዋል። በግብጽም የወጣት ሴቶች እልህ ከወንዶቹ በልጦ ታይቷል። አሁን በዩክሬን ውስጥ የምናየው ሀቅም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
የሴቶች በሕዝባዊ አብዮቶች በስፋት መሳተፍ ከቁጥር ማብዛት እጅግ የላቀ መሠረታዊ ጠቀሜታዎች አሉት። ጥቂቶቹን እንደሚከተለው መዘርዘር ይቻላል።
1.ለሴቶች ያልተመቸ ሥርዓት ለማንም አይመችም። ለማኅበረሰብ በጠቅላላ የሚመች ሥርዓት መገንባት ማለት በቅድሚያ ለሴቶች የሚመች ሥርዓት መገንባት ማለት ነው። ይህ ሥርዓት ደግሞ እነሱ እራሳቸው እየተሳተፉበት፤ ከዚያም አልፎ እየመሩትም ነው መገንባት ያለበት።
2.ሴቶች ከወንዶች በላይ ታጋሾች ናቸው፤ ሲያመሩ ደግሞ በቀላሉ አይመለሱም ተብሎ ይታመናል። እናም የሴቶች በተቃውሞ ትግል ውስጥ በብዛት መሳተፍ ሥርዓቱ በሕዝቡ ምን ያህል እንደተጠላ ግልጽ አመላካች ነው።
3.የወጣት ሴቶች በድፍረት ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት ወጣት ወንዶችን ያጀግናል። የወጣት ወንዶች መጀገን ደግሞ ወጣት ሴቶቹን ይበልጥ ያጀግናል። ወጣት ሴትና ወንዶች በእርስ በርስ አርዓያነት ይጀጋገናሉ። እናም ወጣት ሴቶች አምረው ተነሱ ማለት ሁሉም ወጣቶች ሁሉ አምረው ተነሱ ወደማለት ያመራል።
4.የእናቶች መቁረጥ አባቶችን ያነሳሳል፤ የእናትም የአባትም መነሳት ደግሞ መላው ቤተሰብ በሥርዓቱ ላይ እንዲነሳ ያደርገዋል። እናም እናቶች አመረሩ ማለት መላው ቤተሰብ አመረረ ማለት ይሆናል።
5.የሴቶች በትግል አመራር ቦታ ላይ መገኘት በተቃዋሚዎች መካከል ኅብረትን፣ መተሳሰብን ባጠቃላይም ቤተሰባዊ ስሜት ይፈጥራል።
6.ሴቶችና ወንዶች አብረው ሲቆሙ ነው የመተባበር ጥቅም በጉልህ የሚታየው!
የእህቶቻችን በድፍረት ድምፃችሁን ማሰማት ያለው ትርጉም ከድምፃችሁ ከፍታ እና ከቁጥራችሁ በላይ ነው። ዛሬ ጥቂት እንኳን ብትሆኑ ነገ ብዙዎቻችን አርዓያነታችሁን እንድንከተላችሁ ያደርገናል። እናም እህቶቻችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ባሳያችሁን ድፍረት ተበረታተናል። ኢትዮጵያ ብሩህ ራዕይ ያላት፤ ቆራጥነትን የተላበሱ ወጣቶች ያሏት መሆኑን አሳይታችናል። ይህ ትንሽ ጅምር የትልቅ ሕዝባዊ ማዕበል መንገድ አመላካች ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ዘረኛውንንና አምባነኑን ወያኔ ከጫንቃችን ለማውረድ በምናደርገው ትግል የእህቶችና የእናቶች ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ያውቃል፤ ስለሆነም ሴቶች ትግሉን በስፋት እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያደርጋል። ሴቶችና ወንዶች፤ ወጣቶችና አረጋዊያን ሁላችንም የወያኔን ዘረኛ አገዛዝን እንዲያበቃ በጽናት እንታገል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment