Translate

Wednesday, March 12, 2014

አሸባሪዎቹ የጣይቱና የሚኒሊክ ሴት ልጆች

ቹቸቤ

Arrested Semayawi party members and supportersየሰማያዊ ፓርቲ ቢጫ ለባሽ ወጣት ሴቶች መታገታቸውን ሰምተን ነበር። አንጋፋው ክስ ደግሞ እናትና አባታቸውን ጮክ ብለው መጥራታቸው መሆኑ ሲነገረን የጥፋታቸው ልክ ታሰበን። የትግራይ ናፃ አውጪዎችና ለነርሱ ለመታዘዝ ፈቃዳቸውን ያሳዩ ገባሪዎች በሙሉ ለተልዕኮ ትምህርት የማይመቹትን እነ ባዮሎጂንና ኬሚስትሪን ዞር አላሉባትም። በርካቶቹ የራሳቸውን ስም ከረሱ የቆዩ ስለሆኑ ዘር በጅምላው እንጂ ቤተሰብ በነጠላው አይገባቸውም። እናም እነዚህ ወጣቶች የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን ማለታቸው አሸበራቸው።

ትንሽ እወቀት ያለን እኛ ግን በመጀመርያ ሴቶች ወላጅም አዋላጅም መሆናቸውን እናውቃለንና የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን ቢሉ አይደንቀንም። እንዲያውም “ጎሸ ሰው ጫካ በቀል አጉራ ዘለል ሲሆን ነው እንጂ የመጣበትን ሲያውቅ ጥሩ ነው።” ብለን ያደነቅን እናቅፋለን የወደድን ለጋብቻ እንጠይቃለን። ወጉ እንደዚህ ነዋ! በጋብቻ ተደራጅቶ የሚኒሊክና የጣይቱን ስም ማቆየት ስለምን ያስፈራል? ዘር መተካት ደግ ነው እንላለን። እንዴ ፌዴራሎች ጠለፋ ይሆን እንዴ የፈፀሙት?
ቢሆንም ልካቸውን ያውቁታልና በሚኒሊክና ጣይቱ በሚሸበሩትም አንፈርድም። ግንቦት ሃያ የተወለዱት ራሳቸውን የፋብሪካ ውጤት አድርገው ስለሚቆጥሩ ተጋዳላይ ድርጅት እንጂ እናትና አባት እንዴት ሊኖረው ይችላል ብለው የመቆጣት መብታቸውንና የማስፈራራት አቅማቸውን ተጠቅመዋል። እናም ድንጋይ ሰባሪ ቅሎቹ ወይም ባለጊዜዎቹ እነዚህን የሚያማምሩ የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆችን ተመሳስለው የገቡ ጠጉረ ልውጦች ብለዋቸዋል።
ነገር ግን በቁም ነገር የክሶች ሁሉ ክስ ተብሎ በታሪክ መዝገብ እንዲሰፍር  የክስ መዝገብ ቅጂው ሊቀመጥ የሚገባው ሰነድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንግዲያው የሙሶሎኒና የግራዚያኒ ወይም የሳሊኒ ነን እንዲሉ ይጠበቅባቸው ነበር እንዴ? በማለት ቁጣዬን ሳሰማ አንድ እውቀት ዘልቆ የገባው ጓደኛዬ “… ወይ ቹቸቤ ወይ አልገባህ ወይም ግራ ተጋብተህ ይሆናል እንጂ እነሱ ከመስመርዋ ዝንፍ አላሉም አዎ አንድና አንድ ነገር ብቻ ለሙሶሎኒና ግራዚያኒ ነው የሚሉህ አራት ነጥብ።” ብሎ ሲናገር የመለስ መንፈስ ያደረበት ይመስል ነበር። ቀጠለና “… ሃይለማርያም ኢየሱስና መለስ ተምታቶበት ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ ሲል የምትሰማው ትንሽ የተጋነነ ነው” ብሎ ሳቅ እያለ በረድ ሊያደረግኝ ሞክሯል።
እና ካልጠፋ ውሸት ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ በሆነበት አገር የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ነን እያሉ ሮጡ ማለት የሩጫ ዝግጅት ላይ ሩጫን ሁከት ፈጠራ ማድረግ የሚያስቅ ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝንም ነው። እነዚህ ወጣቶች ተጠርጥረው አልተያዙ ሲሮጡ ሸንቆጥ የሚያደርጉ ቃላትም አብረዋቸው ከሮጡ መረጃው ያው ነው የሚሆነው። ሩጫ ደግሞ እንደዚህ ነው አንዳንድ ሰው ያልበዋል፣ አንዳንድ ሰው ቁና ቁና ያስተነፍሰዋል ለመታሰቢያ ገንዘብ ለመሰብሰብያም ይሮጣል። እነዚህ ቆነጃጅት ደግሞ ጮክ ብለው አሰቡ ይህንንም አላልንም ብለው አልካዱም የምን ምስክር ያስፈልጋል? እርግጥ ነው ቁመናቸው ያምራል ግን አስፈሪ ጡንቻ አላየሁባቸውም ምን ይሁን ብለው ነው ምስክር የሚያስፈራሩት? እንዲያውም ምስክሮቻቸው ያሉትን መልሰው ሲያሰሙ “ወይኔ ጉዴ አንቺም ሰምተሽ ነበር? ደስ ሲል” እስቲ ድገሚው ይሉ ይሆናል እንጂ። በመጀመርያ አገር እንዲሰማ አይደል እንዴ ጮክ ብለው የተናገሩት? እዚያ መንደር የቂል ክምር ነው ያለው? እኔ እምለው ባንዳነት በ’ጂን’ ይተላለፋል እንዴ? ተጋዳላዮች በአረቄው ማለቴ አይደለም በዘር ግንድ ለማለት ነው። የባንዳ ልጆች ተደራጅተውብን ሚኒሊክን አሸባሪ ፋይል ውስጥ ጨመሩት።
የዘር ግንድ እኮ እውነትም አስገራሚ ነው። የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆች ዛሬን ድረስ የባንዳ ልጆችን ማሸበራቸውና ማስጨነቃቸው ይደንቃል። “… እንኳንም አደባባይ ወጥተው አየናቸው እንዲያውም ትንሽ የፈዘዝነው ከባንዳ ተኝተን ይሆናል….” የሚሉ ወንዶች መነቃቃትም እየታየ ነው። እኛም በሩቅ ያለነው እንዲህ እንላለን የሚኒሊክና የጣይቱ የሀገር ወዳድና የጀግና ኢትዮጵያውያን ዘር ይብዛልን። አሜን በሉ!

No comments:

Post a Comment