Translate

Wednesday, June 5, 2013

የግንቦት 25ቱን አገራዊ ሰልፍ ተከትሎ መንግስት ያንጸባረቀውን ሴራ ተኮር አቋም አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ!

ግንቦት 27/2005
ድምፃችን ይሰማ
ባሳለፍነው እሁድ አገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ወንጀሎችን ለመቃወም በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ ስነስርአት መካሄዱ977861_10200726226811999_641498735_o ይታወሳል። የተቃውሞ ሰልፉ አጀንዳ አድርጎ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል መንግስት በሀይማኖት ላይ በጣልቃ ገብነት እየፈጸመ ያለውን ኢ-ህገ መንግስታዊ በደል እንዲያቆም የሚጠይቅና የታሰሩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም እንዲፈቱ የሚተይቅም እንደነበር ይታወሳል። በሰልፉ ላይም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ልክ እንደሌላ ሀይማኖት ተከታይ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ሁሉ ተሳትፎ ያደረጉና የጋራ ድምጻቸውን ያሰሙ መሆኑን ከሰልፉ ስነስርዓት መረዳት ተችሏል፡፡ ምንም እንኳን የዚህ መግለጫ አላማ ሰልፉን አስመልክቶ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠት ባይሆንም ሰልፉን ተከትሎ ከመንግስታዊ አካላት የተሰጡ ፈር የለቀቁና በሴራ የተሞሉ ግብረ መልሶችን አስመልክቶ ግን መሰረታዊ የመነሻ ነጥቦችን ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

በዋነኝነት ከሰልፉ በኋላ መንግስት ማተኮር የፈለገው የህዝበ ሙስሊሙን ከ18 ወራት በላይ የዘለቀ ሰላማዊ የመብት ትግል ማጣጣል መሆኑ ግልጽ ሆኗል። ካሁን ቀደም ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ የህዝበ ሙስሊሙን ሃይማኖታዊ ጥያቄ ሌላ መልክ ለማላበስና ፖለቲካዊ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ተሞክሯል። መንግስት ‹‹ዓላማቸው ፖለቲካዊና እስላማዊ መንግስት የማቋቋም አጀንዳ ነው!›› በሚል ከተአማኒነት የራቀ ውንጀላ ትግላችንን ለማጣጣል መሞከሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ከጉዟችን እንደማይገታን ያለፉት ግዚያት ምስክር ናቸው። የግንቦት 25ቱን ሰልፍም ተንተርሶ ለማድረግ የሞከረውና የተገኘው ውጤትም ይኸው ነው። በዚህም ‹‹የጥቂቶች›› እያሉ የሚያንጓጥጡት የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ትግል እንደተፋፋመ እና ቁጥር አንድ መልስ ያላገኘ ሃገራዊ አጀንዳ መሆኑን በምላሳቸው እንዲመሰክሩ ሁኗል፡፡ ይህ መልስ ያላገኘ የህዝብ ጥያቄ ያለመፍትሄ ሊያልፉት እንደማይችሉም መረዳታቸውን ለህዝባችን አስረድተውልናል፡፡ ሌላው ደግሞ ሙስሊሞች እንደአገር ዜግነታቸው ከአገሪቱ ዜጎች ጋር በአንድነት የሚያሰሙትን የመብት ጥያቄ እና እንደሙስሊምነታቸው ለሚደርስባቸው በደል የሚያሰሙትን ድምፅ በማደበላለቅ ‹‹ዱሮውንም ጥያቄያቸው ፖለቲካዊ ነበር!›› የሚል አቋም ለማንጸባረቅ ሞክረዋል። ይህ በፍጹም ሊሳካ የማይችል ክፉ ምኞት መሆኑን ቀድሞ እንደተረዱት ብናውቅም አሁንም ደግመንና ደጋግመን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን።
ከግንቦት 25 ሰልፍ በፊትም ትግላችንን ለማጠልሸት ‹‹ሶማሊያ››፣ ‹‹ናይጄሪያ›› እና ‹‹ማሊ›› እያለ ሲረግጥ ተጠልፎ የወደቀ ባዶ ፕሮፖጋንዳ መገለጫው ሆኗል፡፡ በዚህም በተለያዩ ግዜያት እርስ በርሳቸው ፍፁም ከማይገናኙ ጉዳዮች ጋር ጥያቄያችንን ለማስተሳሰር መሞከር መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በመርህ ሳይሆን በአጋጣሚ የምንመራ ነን ለሚል ትችት መንግስታዊ ክብርን ባልጠበቀ መልኩ እራስን ማጋለጥ እንደተመረጠ ያሳያል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ከሐምሌ 2003 አንስቶ እየደረሰበት ያለውን በደል ለመቃወም የጀመረው ህዝባዊው የ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› ትግል አንዳችም ፖለቲካዊ ዓላማ ያዘለ አይደለም። ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄ ብቻና ብቻ ነው! እስካሁንም ከዚሁ የመብት ትግል ምህዋር ውጭ የተጨመረ አንዳችም ጥያቄ የለም! ይህንን ሆን ብለው ራሳቸውን ከህዝባዊው እውነታ ለመሰወር ከፈለጉ የመንግስት ባለስልጣናት በስተቀር ዓለም በሙሉ ተረድቶናል። ባለድርሻ አካላት ሁሉ ጥያቄያችንን ተረድተዋል። የመንግስትን በሸፍጥ የተሞላ ፕሮፓጋንዳም ንቆ የተወ እንጂ የተቀበለ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ የለም። ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትም ጉዳዩን ተረድተው መንግስታዊው ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጠይቀዋል። በመሆኑም መንግስት ጥያቄያችን ፖለቲካዊ አድርጎ ለማሳየት የሚደክመው ድካምና የባለስልጣናቱ ፕሮፖጋንዳ መንግስትን ለዳግም ኪሳራ የዳረገ መሆኑን መላው ኢትዮጵያዊ በይፋ እንዲረዳ እድሉን የሰጠ ሆኖ አልፏል!
ሰልፉን ተከትሎ የተንጸባረቀው ሌላው አደገኛ መንግስታዊ አቋም ህዝበ ሙስሊሙን ከሌላው ማህበረሰም ሆነ ሃገራዊ አጀንዳዎች ነጥሎ ለማውጣት ሙከራ መደረጉ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ የመብት ጥያቄዎቻቸውን አስመልክቶ ያደረጉትን ሰልፍ ምስል በማዛባትና የሙስሊሙን ተሳትፎ ብቻ ነጥሎ በማውጣት ልክ እንደወንጀል መቁጠር፣ ሙስሊሙ በአገሪቱ ጉዳይ እንደማያገባውም ሆነ ሌሎች በሙስሊሙ ጉዳይ እንደማያገባቸው አድርጎ መሳል ለህዝቦች ቆሚያለሁ ከሚል መንግስት የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር ነው። የዜጎቹን ህዝባዊ መስተጋብር ለማቀጨጭ የሚሞክር መንግስት ከፍ ያለ ስህተት እየሰራ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል። ህዝበ ሙስሊሙ በውዲቷ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውና የነበረው ህዝባዊ መስተጋብር ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ከዚህም ሆነ ከቀደሙ መንግስታት የቀደመ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአገሪቱ ውስጥ ያለን ህዝባዊ መስተጋብር የትኛውም መንግስት ሊሸልመንም ሆነ ሊነጥቀን የማይችለው የውልደት መብታችን መሆኑን አጠንክረን ልንገልጽ እንወዳለን!
በግንቦት 25 የተደረገውን ሰልፍ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በሚገባ ሽፋን ሰጥተው መዘገባቸው ይታወሳል። የዘገቡት ደግሞ በርካታ የመብት ጥያቄዎችን እንዳነሳ አገራዊ ሰልፍ እንጂ የሙስሊሞችን ጥያቄ ብቻ ነጥለው አይደለም። መንግስታዊዎቹ በተለይም ኢቴቪ እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግን ከሰልፉ ጥያቄዎች አንዱ የሆነውን የሙስሊሙን አጀንዳ ብቻ መዝዘው በማውጣት አሳፋሪ ሚዛን የመስረቅ ተግባር ፈፅመዋል፡፡ ይህን ያደረጉት ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው። አገሪቱ ውስጥ እየተፈጸመበት ባለው የመብት ጥሰት ቅሬታ ያለው በሙስሊሞች ዘንድ (ያውም አክራሪዎች በለው በሚጠሯቸው ዘንድ) ብቻ እንደሆነና ሌላው ህብረተሰብ ምንም ችግር እንደሌለበት አስመስሎ ለማቅረብ ነው። ሰልፉን አስመልክተው መግለጫ የሰጡ ባለስልጣናት ‹‹ሲሸመድዱት የከረሙ›› ያስመሰለባቸውን የተጠና መልስ ከሙስሊሙ ትግል ጋር አስታከው መስጠታቸው ትግላችን የህልውና መሆኑን ተረድተው አሁንም ከትከሻችን ላይ ሊወርዱ አለመፈለጋቸውን የሚያሳይ ነው። የህዝበ ሙስሊሙን አጀንዳ ከሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ማምለጫና መሸሸጊያ አድርጎ መጠቀምም ከአንድ መንግስታዊ አካል የማይጠበቅ ተግባር ነው። ያልተሳካ እና ሊሳካ የማይችል ከንቱ ሙከራ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል። ተቃውሞውን ከመንግስታዊ ሚዲያዎች ውጭ በዚህ አይነት ምስል ያንጸባረቀ የለም። መንግስታዊ ሚዲያዎች ደግሞ በተደጋጋሚ ውሸታቸው ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያጡትን ተአማኒነት መልሰው ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል። በመሆኑም የፕሮፓጋንዳ ሙከራው መና መቅረቱን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። በተቃራኒው መንግስት ይህንን መሰል ምስል የማጣመም ስትራቴጂ መከተሉ ካሁን በፊትም በሙስሊሞች ላይ ሲፈጽመው የነበረው ርካሽ የፕሮፓጋንዳ ሙከራ እንዲጋለጥ ያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው። በአይናቸው ስር ሲፈፀም ያዩትን አገራዊ ሰልፍ የአወሊያ ቅጥያ አድርጎ ማቅረቡ ካሁን በፊትም በሙስሊሙ ላይ ተመሳሳይ አጣሞ የማቅረብ ሙከራ ሲያደርግ የቆዩ መሆኑን ብዙሀን እንዲረዱ አድርጓል። የህዝበ ሙስሊሙ ትግልም በከፍተኛው እርከን ላይ እንደሚገኝ እና በድል ዋዜማም እንደሆነ በተዘዋዋሪ ነግረውናል፡፡
መንግስት የሙስሊሙን ጉዳይ አግዝፎ ለመሳል የሞከረበትን የግንቦት 25ቱን ሰልፍና ያነሳቸውን ጥያቄዎች በጸረ ህገ መንግስትነት ፈርጇል። ይህን እንደሰበብ በማድረግም በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በተዘዋዋሪ መንገድ ተሞክሯል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የመብትና የሃይማኖታዊ ህልውና ትግል በሐይል ለማስቆም መሞከር ሃገራዊ እና ታሪካዊ አጸፋው የከፋ መሆኑን ግልጽ ለማድረግ እንወዳለን። የሚሊዮኖችን የመብት ጥያቄ በሀይል ለመፍታት ማሰብ የሚታሰብ መንገድ አይደለም። ጥያቄዎቻችን ሃይማኖታዊ፣ ትግላችንም ሰላማዊ ነው! ለሰላማዊ ትግልን ተገቢውን ትኩረትና መፍትሄ መስጠት ከተደጋጋሚ የፖለቲካ ክስረትና ህዝባዊ መቃቃር ያድናል፡፡ ትግላችን መብታችን እስኪከበር ድረስ ሰላማዊ ሆኖ ይቀጥላል! ለዚህም አንዳችም ጥርጥር የለንም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment