Translate

Monday, June 3, 2013

በህዝብ አቆጣጠር አሁን ጨዋታው ተጀመረ!

ወደ "ሻርኮቹ" ይቀጥል!! (ርዕሰአንቀጽ)

shark


ሙስናው ላይ የተጀመረው ዘመቻ ሙስናን በስንጥር የሚያሰኝ ቢሆንም አቶ መለስ ያልደፈሩትን ሰፈር አቶ ሃይለማርያም ነክተውታልና በኢህአዴግ ታሪክ የሙስናን ሰፈር በማንኳኳት ግንባር ቀደሙ ሰው ያደርጋቸዋል። እኛም ጅምሩ መልካም ነው እንላለን። ግን ጥያቄም ማሳሰቢያም አለን። ለማንኛውም በህዝብ አቆጣጠር አሁን ጨዋታው የተጀመረ ይመስለናል።

በሙስና የተጠረጠሩ ነጋዴዎች፣ ደላሎች፣ አቀባባይ የተባሉና የመንግስት ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ከተሰማ ጀምሮ ህዝብ በስፋት እየተቸ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተደላደለውን ሙስና ህዝብ ጠንቅቆ ከነባለቤቶቹ ያውቃል። ይረዳል። ያሸታል። ባለፈ ባገደመ ቁጥር ለድህነቱ ማስታገሻ ያላምጣቸዋል።
ሙስና ሲባል ሙስና ነው። ወንጀል ሲባል ወንጀል ነው። ህግ መተላለፍ ያስጠይቃል። አሁን እንደሚታየው ግን የጸረ ሙስናው ዘመቻ ሰፈር የለየ ይመስላል። ዋናዎቹ “ሻርኮች” አልተነኩም። ዋናዎቹ “የማበስበሻው ባህር” ፊታውራሪዎች አሁንም እያገሱ ነው። እነዚህ አገር ወዳድ የሚመስሉ  የሙስና መፈልፈያ ማሽን አምራቾች ለምን ዝም ተባሉ? የህዝብ ጥያቄ ነው? የምስኪን ዜጎች ጥያቄ ነው። በተለይም “ጠቁሙኝ እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት ለተናገሩት አዲሱ መሪ፡፡
በኢትዮጵያ በትዕዛዝ ንብረታቸውን የተነጠቁ፣ በደል ደርሶባቸው ፍርድ እናገኛለን ብለው ወደ ህግ አምርተው በትዕዛዝ የተበየነባቸው፣ በባለጊዜዎች መመሪያ ቅርስና ርስታቸውን የተነጠቁ፣ ተራ የቀበሌ ጭቃ ቤት ሳይቀር የተዘረፉ፣ የነፍስና የወንጀል ጉዳዮች ውስጥ መዘፈቃቸው እየታወቀ ክስ የማይመሰረትባቸውና በወንጀል ተጨማልቀው አገሪቱ ላይ የነገሱ ስለመኖራቸው መነገር ከጀመረ ያው የኢህአዴግን የስልጣን ዘመን ያክል ቆይቷል።
ፍርድና ርትዕ እንዲጓደል ብር ከባንክ በትዕዛዝ ተበድረው በፌስታል የሚረጩ፣ እዳ በሚጮህበት ሆቴሎቻቸው ውስጥ አልኮሆል እያራጩ “የገበያ ወሲብ” የሚያሻቅጡ፣ የሰው ትዳር የሚደፍሩ፣ አስፈራርተውና አስገድደው አህቶችና እናቶችን ከትዳራቸው የሚለዩ፣ ቤተሰብ የሚበትኑ፣ ቀና ብላችሁ ለምን አያችሁን በሚል እስከ ነፍስ ማጥፋት የሚደርሱ ማፍያዎች ፍርድ ቤቱንና የፍትህ ደጅ ዙሪያ ገባውን ቁልፍ ተረክበው አገሪቱን እየጋለቡዋት ነው የሚለው ዜና ተብሎ፣ ተብሎ ያለቀለት የማይሸፈን የአደባባይ ጉዳይ ነው።
“ግብር ለምን ክፈሉ እንባላለን” በሚል የስርዓቱን ቁንጮዎች በመያዝ ባለስልጣናትን ከሃላፊነታቸው የሚያስነሱ፣ ግብር የሚጠየቁበትን ሰነድ ቢሮ እያሰበሩ የሚዘርፉ፣ ሰነድ የሚያጠፉ፣ ለሰሩት ወንጀል በህግ ሲጠየቁ የህግ አካሄዱን በመመሪያ የሚያሳግዱ፣ በራሳቸው ፊርማና ማህተም “በትዕዛዝ ክስ አዘጋን” ብለው ለየጋዜጣው መግለጫ የሚበትኑ ወረበሎች ስለመበራከታቸው መለፍለፍ ከተጀመረ አንድ ጠ/ሚኒስትር አልፈው ሁለተኛው ተተክተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደብዳቤ እያጻፉና ትዕዛዝ እንዲተላለፍላቸው እያደረጉ የንግድ ውድድሩን ያዛቡ፣ ህግ አክብረው የሚሰሩትን ዜጎች ከገበያና ከውድድር እንዲገለሉ ያስደረጉ፣ ኢትዮጵያን “ለጠቅላይ “ሊጫወቱባት የሚዳዳቸው ወረበሎችን ያላካተተ የጸረ ሙስና ዘመቻ ከቶውንም ተቀባይነት እንደሌለው ህዝብ እያወጋ ነው።
የፍትህ ሚኒስትሩ ከሃላፊነት መነሳታቸውን ተከትሎ የፍርድ ሂደት ያዛቡ፣ መረጃ የቀረበባቸውን ክሶች ያሳገዱ፣ በመመሪያና በተለያዩ ንክኪዎች ህግ እንዲሰቀል ያደረጉ አቃብያነህግ እንደሚታሰሩ ሰምተናል። ምርመራው በሰነድ የተደገፈ ስለመሆኑ ይፋ ሆኗል። ይህንን ዜና የሰሙ “አዋራው ጨሰ፤ በህዝብ አቆጣጠር ጨዋታው ተጀመረ” እያሉ ነው።
ፍትህ ተጓድሎባቸው የአቤቱታ ፋይላቸው የተዘጋባቸው የጨዋታውን መጀመር ሲጠብቁ ነበር። በህይወት ጉዳይ ሻርኮቹን ከሰው ፋይላቸው የተቀረቀረባቸው አሉ። ሻርኮቹን በህግ በመጠየቃቸው ብቻ እስር ቤት የተቀረቀሩ አሉ። ፍትህ እንዲዛባ አድርገው የራሳቸውን ያልሆነ ንብረት የወሰዱ አሉ። ንብረታቸውን ተዘርፈው ልመና የወጡ አሉ። ሚስቶቻቸውን ተቀምተው እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡ አሉ። ብዙ ለጆሮ የሚቀፍ ወንጀል የሰሩና የሚጠየቁበትን ፋይል ያሳገዱ መጨረሻቸው ምን ይሆን? በግፍ የሞቱ ደማቸው ይጮሃል። በግፍ በልማት ስም ቤቷ የፈረሰባትና ለባለጊዜ ስፍራ የለቀቀች ደቃቃ እናት የጣር ድምጽ ይሰማል። ህግ ጎድሎባቸው፣ አቤት የሚሉበት ያጡ ወገኖች ሮሮ ከልክ አልፏል። በፖሊስ፣ በአቃቤ ህግ፣ በዳኛ፣ ከዛም በላይ በ”ተላላኪ ባለስልጣኖች” ትዕዛዝ መብቶቻቸውን የተገፈፉ የፍትህ ያለህ እያሉ ዓመታት አስቆጥረዋል።
አሁን በእኛ ሰዓት አቆጣጠር ጨዋታው ተጀምሯል። በህዝብ ሰዓት አቆጣጠር ጨዋታው ተጀምሯል። ኳሷ አደገኛ ቀጣና ውስጥ ናት። የተነቁ ፋይሎች፣ የታገዱ ጉዳዮች፣ የታደፈኑ የፍትህ ጉዳዮች ከልክ በላይ ናቸው። አሳፋኞቹም እዛው ኢህአዴግ ደጅ አረፍ እንዲሉ የተደረጉትን ጨምሮ በየደረጃው አሉ። አብረው የሚነግዱም አሉ። እነዚህን ሁሉ አልፈው መሔድ ከተቻለ ጨዋታው በትክክል በህዝብ የሰዓት አቆጣጠር ተጀምሯል። አለበለዚያ ግን የህዝብና የመንግስት አቆጣጠር ተለያይቷል። አንዱ ሲተኛ አንዱ ይነቃል። ሳይገናኙ ይተላለፋሉ።

No comments:

Post a Comment