Translate

Sunday, July 31, 2016

የጻድቃን “መፍትሔ ሃሳቦች” – ልመና? ጥገና? ወይስ ህወሃት ቁጥር 2?

(ርዕሰ አንቀጽ)

which one

የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና አለአግባብ ለመበልጸግ ያሰቡ አውሮጳውያን በአሜሪካ አካባቢ ያሉትን አገሮች በጥጥና በሸንኮራ አገዳ እያለሙ መጠነሰፊ ሃብት ለማጋበስ በሰላም የሚኖሩ አፍሪካውያንን በግፍ እያጋዙ ዓለማችን እስካሁን ዓይታ የማታውቀውን ዓይነት የባርነት ሥርዓት ለበርካታ ዓመታት አካሂደዋል፡፡ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ በግፍ የተጋዙት ወገኖች በመንገዳቸው ያሳለፉት መከራና ከዚያም ለማሽን እንኳን የሚሰጠው ዕረፍትና ጥገና እነርሱ ተነፍገው ለመቶዎች ዓመታት ከምንም ጋር የማይወዳደርና የማይነጻጸር ሰቆቃ አሳልፈዋል፡፡ የዚህ መራራ ግፍ ውጤት አሁንም አብዛኛውን የዓለማችንን ክፍል እየናጠው ነው፡፡

በዚህ አስከፊ ዘመን በባርነት ሥር የሚማቅቁት እንደ ንብረት ይቆጠሩ ስለነበር በምርጫ አይሳተፉም ነበር፡፡ ሆኖም ካላቸው ከፍተኛ የህዝብ ብዛት አኳያ ባሪዎችን አስቆጥረው በርካታ የምክርቤት ወንበር ለማግኘት የተመኙት የደቡብ ፖለቲከኞች አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው አንድ ባሪያ እንደ 3/5 ሰው ይቆጠር የሚል ድርድር ላይ ደርሰው ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ከአምስት ባሪያ ሁለቱ ለቁጥር አይገቡም፤ መኖራቸው አይታወቅም፤ ምንም ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰቆቃ የበዛባቸው ግፉዓን በየጊዜው የሚችሉትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ እጅግ በርካታ የሕይወት መስዋዕትነት ተከፍሎ ነጻነት ይፋ ቢሆንም በአሜሪካ የሚገኙ ጥቁሮች ግን አሁንም ስልታዊ የዘር ጥቃት ሰለባዎች ናቸው፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ለነጻነት እጅግ ውድ የሆነውን ህይወታቸውን የከፈሉ ያልተዘመረላቸው በርካታ ጥቁሮች እያሉ አሁንም የባሪያ ሥርዓት ከማስወገድ ጋር የችግሩ ጠንሳሾች የሆኑት ነጮች የመፍትሄው ፈር ቀዳጆችና ፋና ወጊዎች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ማልኮም ኤክስ እንደ ወንበዴና ወሮበላ ተደርጎ ታሪኩ ሲጎድፍ ወረቀት ላይ ፊርማቸውን ማስፈራቸው እንደ ታላቅ ውለታ ተቆጥሮ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን የባርነት አስወጋጅ “መሲህ” ተደርገው ይወደሳሉ – ያለ እኛ አይሆንላችሁም የማለት ያህል ነው – ከማንዴላ ጋር ዴክላርክ እንደሚጠቀሱት፡፡ ችግር ፈጣሪውም መፍትሄ አምጪውም – ተወቃሽም ተሞጋሽም – ነጮች ናቸው፡፡
ይህንን ጉዳይ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም፡-
ከጌቶቻቸው በጥንቃቄ የተማሩት ህወሃቶችም እንደ ዓቅማቸው ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሲውተረተሩ 25ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ሲሻቸው እንደ ነጻ አውጪ፤ ሲሻቸው ደግሞ እንደ ቅኝ ገዢ እንደ አቅሚቲ ሁሉንም ለመሆን ወጉ አይቅርብኝ ሲሉ መታዘብ የሚችል ሁሉ ላለፉት ዓመታት ሲያስተውላቸው ሰንብቷል፡፡ ከበረሃ ወጥተው ስለ ልምላሜ፤ በትግል ስም ወደር የሌለው ግፍ ሲሰሩ ቆይተው ስለ ህግ የበላይነት፤ ፊደል በቅጡ ሳይቆጥሩ በድንቁርና ተሸብበው ስለ ዕድገትና ብልጽግና ስሌት፤ ቤተሰባቸውን እንኳን በቅጡ የመምራት ብቃት ያላሳዩ ምግባረ ብልሹዎች ስለ አገር አስተዳደር፤ ለረሃብተኛ የተላከ እህል ሸጠው በሰው ህይወት ላይ የቀለዱ አጭበርባሪዎች ስለ ግልጽነትና ተጠያቂነት፤ አገር ለመገነጣጠል በነጻ አውጪ ስም ሲነግዱ የኖሩ የበረሃ ወሮበሎች ስለ ሉዓላዊነት፣ ስለ ፌዴራላዊ አወቃቀር ከበሮ ሲደልቁ፤ … አይተናል! ሰምተናል! ታዝበናል! ህወሃቶች ሁሉንም እስኪበቃን አሳይተውናል፡፡
በማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ /ማገብት/ አዋላጅነት በሻዕቢያ የተደቀለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር /ህወሃት/ በነጻ አውጪ ስም አገር መግዛት በጀመረበት ጊዜ ለእርሱ የበረሃ ራዕይ የሚለውን፤ ለኢትዮጵያ ግን ትውልድ የሚጨርስ ነቀርሳ የሆነውን ችግር ተከለ፡፡ ራሱን መሪ አድርጎ በሾመው መለስ ለማኝነት በዓለም እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተባበሩት መንግሥታት ፊት ቀርቦ አገር እንድትገነጠል በይፋ ለመነ፤ ሰዎችን እንደ እህል በዘር ጆኒያ ሰፈረ፤ በሰላም አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስበርሱ አጋጨ፣ ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቀለ፤ መሬት ነጠቀ፤ ዜጎችን አዋረደ፣ አሰረ፣ ገረፈ፣ አሰቃየ፣ ገደለ፣ ጨፈጨፈ፣ … በመላው ኢትዮጵያ የማይጠፋ እሳት ለኮሰ፤ አሁን እሳቱ ራሱን የሚበላበት ሰዓት ላይ ደረሰ! አሁን መግቢያ መውጫው ሲጠፋ እስካሁን ማንም ሰው ምንም ዓይነት ሃሳብ ሳያቀርብ የኖረ ይመስል በጻድቃን ህወሃቶች “የዕርቅና ተሃድሶ” ምልጃ መቅረቡ አስገርሞናል፡፡ ግን አንሰማም አንልም፡፡
በኢትዮጵያ የተከበሩ የሚባሉትን እንደ ሽምግልና ያሉትን ተቋማት ያለልክ ያዋረደው ህወሃት 25ዓመታት በየቦታው የለኮሰው እሳት ራሱን ሊበላው በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ “ዕርቅ፤ ሰላም፤ ፍቅር፤…” እያለ መሆኑ ከውስጥም ከውጭም እየተሰማ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሰሞኑን የተለቀቀው የጻድቃን ገ/ትንሳኤ “የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች!” በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጽሁፉ በቀድሞ የህወሃት መሃንዲስ የተጻፈ ከመሆኑ ሌላ በይዘት ይህ ነው የሚባል አዲስ ነገር መጠቆሙ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም ስለ ሕገመንግስት የሚያወራው ክፍልና ከዚያ ጋር በተዛማጅ የቀረቡት ሃሳቦች ነገደ ጎበዜ የዛሬ 12ዓመት አካባቢ ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ የጠቆሙትን ዋቢ ሳይጠቅስ የተጻፈ ነው ተብሎለታል፡፡
“የመፍትሔ ሃሳብ” ጠቋሚ ነው ባሉት ጽሁፍ ላይ ጻድቃን በርካታ ነገሮችን ለማስፈር ሞክረዋል፡፡ በአንድ ወገን ህወሃት በበረሃ ያደረገችውን ትግል እያሞገሱ በሌላ ደግሞ “የኢትዮጵያን ችግር በኢህአዴግ መዋቅሮች ታጥረን መፍታት አንችልም” በማለት እርስበርሱ የሚጣረስ ሃሳብ በማቅረብ ህወሃትን ትተው ኢህአዴግን እንደ አንድ ችግር ፈጣሪ ተቋም አድርገው አቅርበውታል፡፡ በአገሪቷ ላይ አለቅጥ የተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት፣ … በመለስ አነጋገር “የመበስበስ” ውጤቶች መሆናቸውን ሆን ብለው የዘነጉት ይመስል አሁን ለሚታው ችግር ምንጭ አድርገው አትተዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ህገመንግሥቱን “እናምልከው” የማለት ያህል ደጋግመው አወድሰውታል፡፡
ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ስማቸው “ጻድቃን” ባይሆን ኖሮ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎች በጽሁፋቸው ላይ ባሰፈሯቸው ሃሳቦች ይኼኔ ማዕከላዊ ገብተው www.freetsadkan.com የሚል እርሳቸውን የማስፈታት ዘመቻ ተጀምሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ህወሃት አገዛዝ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ህገመንግሥታዊ መብታችን ይከበር፤ እንዲያውም ሌላ ጥያቄ የለንም ህወሃት/ኢህአዴግ ህገመንግሥቱን ብቻ ያክብርልን በማለት የጻፉ፣ የተናገሩ፣ ህዝብ ያደራጁ፣ የታገሉ፣ … እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ተሰውተዋል፤ ተረሽነዋል፤ ለስቃይ ተዳርገዋል፤ ከዚህ የተረፉት አብዛኛዎቹ ደግሞ “አሸባሪ” ተብለው እስር ቤት እየማቀቁ ነው፡፡ “ድምጻችን ይሰማ” በማለት ዘመቻ የጀመሩት ሙስሊሞች ቀዳሚ ጥያቄ ህገመንግሥቱ ይከበር እንደነበር እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡ ጻድቃን በተመሳሳይ ሲሉት ግን ከሽብር ወደ “ጽድቅ” ይቀየራል፤ ርኩሰቱ ይቀደሳል፡፡
የህወሃት “ጄኔራልነትን” ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንቱንም ጠቅልለው የያዙት ባለሃብቱ ጻድቃን ስለ ትግራ ተወላጆች በርካታ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡ እነ ሰየ አብርሃን ወደ ወኅኒ የወረወረው ህንፍሽፍሽ የኋላ ሰለባ የሆኑት ጻድቃን በዚህ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያተኮረው ንግግራቸው ስየ አብርሃ ከእስር በተለቀቁ ቀናት ውስጥ “በትግራይ ህዝብ ላይ ተስፋ አትቁረጡ” በማለት ቪኦኤ ላይ ያደረጉትን ተማጽንዖ የሚያስታውስ ሆኗል፡፡
በጽሁፉ ላይ ሌሎችን በርካታ ነጥቦችን እያነሱ ዝርዝር ትንታኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ላሁኑ በዚሁ እናብቃና ሃሳባችንን እናቅርብ፡- የጻድቃን “የመፍትሄ ሃሳቦች” ጽሁፍ (የቃላት ግደፈቶቹን ሳናንሳ) ከዚህ በፊት በተደጋሚ በቅንነት ከቀረቡት ጋር ሊወዳደር የሚችል ባይሆንም እንደዓቅሚቲ የተሰነዘረና አዎንታዊ ሃሳብ ያነገበ በመሆኑ ሊጤን ይገባዋል እንላለን፡፡ ሁሉንም ነገር በጭፍን ከመቃወም ይልቅ ተቃዋሚ ኃይላት በጽሁፉ ላይ በመመርኮዝ ህወሃትን የመገዳደሪያ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይገባቸዋል ለማለት እንወዳለን፡፡
የጻድቃን ትንታኔ እና የመፍትሄ ሃሳብ በህንፍሽፍሹ ወቅት ክትባት ተሰጥቷቸው የደነዘዙትን፤ የተወገዱትን፤ የላሉትንና የመከኑት የቀድሞ ህወሃቶች በዕድሳትና በስልት ወደ መንበሩ ለመመለስ ይሁን ወይም ተምሬበታለሁ ከሚሉት በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በኩል ከህወሃት አንጋሾች የተላከላቸው ይሁን በውል የታወቀ ነገር ባይኖርም መፍትሔዎቹን በቅንነትና በእውነተኛ መንፈስ ያቀረቧቸው ከሆኑ እንደ አንድ ቆራጥ ጄኔራል የመሪነቱን ቦታ በመጨበጥ ወደ ፍልሚያው በፊት አውራሪነት እንዲዘምቱ ሃሳብ እናቀርባለን፡፡ ይህ ሲሆን አመራሩን የሚደግፉ የሚበዙበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፤ የእውነተኛ ለውጥ ተስፋ ይፈነጥቃሉ፡፡ ከዚህ ካለፈ ግን “ወታደር ሲጠግብ የፖለቲካ ተንታኝ ይሆናል” ከማስባል በላይ አይሆንምና ውጤቱ ክሽፈት ይሆናል እንላለን፡፡

No comments:

Post a Comment