Translate

Tuesday, July 12, 2016

መንግስት የጎንደሩን የሕዝብ ቁጣ ያቀጣጠሉት ኤርትራ ከመሸጉ ኃይሎች መመሪያ እየተቀበሉ ነው ሲል ከሰሰ


(ዘ-ሐበሻ) የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስተባበሪዎችን ለማሰር ከትግራይ የመጡ ደህንነቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ ተጀምሮ; በጎንደር የሕዝቡ ቁጣ አይይሎ ከተማውን መቆጣጠሩንና አንገዛም ማለቱ መዘገቡ ይታወሳል:: በዚህም ጉዳይ መንግስት በሰጠው ምላሽ “በኤርትራ ከመሸጉ ሀይሎች መመሪያ በመቀበል የተከፈተ ነው” አለ:: መንግስት በራድዮ ፋና በኩል እንዳለው “በሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ኩርባ አካባቢ የሚያልፉ የህዝብና የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ተኩስ በመክፈት ጥቃት በመፈፀም የህብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሲያደርጉ የነበሩትን አስሬያለሁ” ብሏል::

የራድዮ ፋና ዘገባን እንደወረደ ያንብቡት:-
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 5፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኤርትራ ከመሸጉ ፀረ ሰላም ሀይሎች መመሪያ በመቀበል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደርና በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞኖች ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉና ዝርፊያ የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
Gonder 12የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ኤርትራ ውስጥ መሽገው ከሚገኙ የፀረ ሰላምና አሸባሪ ሀይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና መመሪያ በመቀበል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ቁርቢ አካባቢ እንዲሁም ትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ ደንሻና አካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።
በአከባቢዎቹ በጦር መሳሪያ በመታገዝ ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በአንድ ሰላማዊ ሰው ላይ ግድያ መፈጸማቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
እንደዚሁም አንደ ሌላ ግለሰብን አፍነው ከወሰዱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት በገንዘብ ሲደራደሩ መቆየታቸውም ነው የተመለከተው።
በተለይም በሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ኩርባ አካባቢ የሚያልፉ የህዝብና የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ተኩስ በመክፈት ጥቃት በመፈፀም የህብረተሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሲያደርጉ የነበሩ መሆናቸውን ነው ግብረ ሃይሉ የጠቆመው።
ግብረ ሃይሉ ይህንንም በመረጃና በማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ሀምሌ 05 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ጠዋት አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ከመካከላቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች ግብረ ሃይሉ ላሰማራቸው የፀጥታ ሃይሎች እጅ ላለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ነው ያመለከተው።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሴቶችንና ህፃናትን ከለላ በማድረግ በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች ላይ የመሳሪያ ተኩስ በመክፈትና ቦንብ በመወርወር ጉዳት ያደረሱ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፥ የጉዳቱን መጠን በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ ግብረ ሃይሉ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment