Translate

Wednesday, July 27, 2016

ምስለ – ብአዴን

ብአዴን የብረት አከሉ ህዝባዊ አመጽ መሀንዲስ?

gondar uprising
ለፖለቲካ ስልጣን ሁለተኛነት ሁሌም የሚጫወተዉ ብአዴን፤ ኢሕኢፓ በገጠመው የመበታተን አደጋ ለኢሕዴን ጥንሰሳ ምክንያት የሆነው የበለሳ ንቅናቄውን በመጀመር ብዙዎች ወደ ደርግ ሲኮበልሉ፣ እልፎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ ‹‹ጥቂቶች ቆራጦች›› ህዳር 11/1973 ዓ.ም በህወሓት አጋፋሪነት ኢሕዴንን እንደመሰረቱ በግነታዊ ቃላት የታጀበው የድርጅቱ ታሪክ ያትታል፡፡

የዘመናዊው አርበኛ (ኢሕአፓ) ኃይል በደርግ፣ ሻዕብያና ወያኔ ታክቲካል ህብረት ውልቅልቁ በወጣበት ሂደት ውስጥ የተፈጠረው ኢህዴን ደርግን ለመጣል ካደረገው ወታደራዊ አበርክቶ ይልቅ የፖለቲካ አበርክቶው እጅግ ላቅ ያለ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በተለይም በሰሜን ምዕራብ፣ ደብረታቦር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሰሜን ሸዋን የመሳሰሉ የደርግ ጠንካራ ወታደራዊ ቤዞች የነበሩትን ቦታዎች ሰብሮ ለመግባት የኢሕዴን ውስን ሰራዊትና አመራሮች የየአካባቢውን ህዝብ በማግባባት (በመደለል) ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በድህረ ደርግ ጊዜ ክልሉን የሚመራው ኢሕዴን (ከዚህ በኃላ ብአዴን) የወቅቱ ከፍተኛ አመራሮች የዘር ሃረግ ከኤርትራ እስከ ሲዳማ፣ ከትግራይ እስከ ሐረር ድረስ የሚጣቀስ የነበረ ከመሆኑ አኳያ ድርጅቱ በክልሉ የተቀመጠ ምድብተኛ የፖለቲካ ጉዳዮች ተላላኪና አስፈፃሚ ነበር፡፡ በ1987 ዓ.ም አዲሱ ቋንቋ ተከሩ ፌደራሊዝም ህገ-መንግስታዊ እውቅና አግኝቶ የክልል ድንበር ማከላከል ስራ (ሴራ) ሲሰራ ድርጅቱ ‹‹እወክለዋለሁ›› ያለውን ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎቹን በሚያስጠብቅ መልኩ ሊቆምለት አልቻለም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው የክልል ድንበር አከላለል ጉዳይ ነው፡፡ የወሎ መሬት ተቆርሶ ለትግራይ ክልል ከመሰጠቱ ባሻገር በለምነቱ የሚታወቀው የወልቃይትና አካባቢው መሬት የአካባቢውን ነዋሪ የቀደመ ታሪካዊ ዳራ፣ ባህል፣ ቋንቋና ሥነ-ልቦናዊ ገጽታ ሳይጠና የህዝቡን ፍላጎት በሚጋፋ መልኩ ለክልላዊ ጂኦ-ፖለቲካልና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሲባል ወልቃይት በትግራይ ክልል ሊጠቃለል ችሏል፡፡ ይህን ለመስለው ኃላፊነት ለጎደለው ፖለቲካዊ ሴራ ተጠያቂው ህወሓት ብቻ ሳይሆን ከህወሓት ጀርባ ረዘም ያለ እጃቸውን በጉዳዩ ላይ በማስገባት አጀንዳውን የደገፉት የወቅቱ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችም በታሪክ ተወቃሽ ናቸው፡፡ በተለይም ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስሞን፣ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ዳዊት ዮሐንስ፣ ዮሴፍ ረታ፣ ታደሰ ካሳ፣ በታሪክ ቀዳሚ ተወቃሾች ናቸው፡፡
ብአዴን በዝግመተ ለዉጥ መስመር …
ከድህረ-ደርግ ጀምሮ የብአዴንን ፖለቲካዊ የሥልጣን ጉዞ በሶስት የጊዜ ማዕቀፍ ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ ማዕቀፍ ከ1983 እስከ 1997 ድረስ ያለውን ሰፊ ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ በዚህ ጊዜ ድርጅቱ ራሱን ለፖለቲካዊ ሽያጭ  ያቀረበ ቢሆንም የድርጅቱ ቁንጮ አመራሮች ‹‹ቱሪስት›› የሚል ቅፅል ስም የተሰጣቸው በመሆኑና ከክልሉ ውጪ ባሉ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ በተከታታይ ይደርስ ለነበረው ጥቃት ተከላካይ ሆኖ ባለመገኘቱ ድርጅቱ በክልሉ ተወላጅና በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ዘንድ በጥርጣሬ አይን ሊታይ ችሏል፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬ በፌደራልና በክልሉ ከፍተኛ ሥልጣን የተቀጡት ገዱ አንዳርጋቸው፣ አለምነው መኮንን፣ ደመቀ መኮንን፣ አያሌው ጎበዜ፣ አህመድ አብተው፣ አምባቸው አምሳሉ (ዶ/ር)፣ ተስፋዬ ጌታቸው፣ ብናልፍ አንዷለም፣ ወዘተ የመሳሰሉት አመራሮች በድህረ ደርግና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ድርጅቱን የተቀላቀሉበት ጊዜ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ ማዕቀፍ በፖለቲካው የአካዳሚክ አለም አድርባይነት በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ምን እንደሚመስል ከመማር ይልቅ ብአዴን ቤት ውስጥ በተግባር የሚታየው ይበልጥ ያስተምር ነበር፡፡ የወቅቱ የፖለቲካ አመራሮች ለህወሓት የፖለቲካ መሀንዲሶች በማደግደግ ረገድ የሚቀድማቸው አልነበረም፡፡ ለታማኝነታቸውም የሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካ ሥልጣን ሹመት አያጡበትም ነበር፡፡ በተለይም በ1993ቱ የህወሓት ዳግማዊ ህንፍሽፍሽ መለስ ዜናዊን ‹‹ከዘመናዊ ጥብቅ የትግራይ ብሄርተኝነት›› አቀንቃኞች ከእነ ተወልደ ወ/ማርያምና ስየ አብረሃ ‹የፖለቲካ ሃሳብ› የበላይነት በመታደጉ ረገድ የእነ አዲሱ ለገሰ ድጋፍ ከተወራለት በላይ ነበር፡፡ ለመለስ ባሳዩት ታማኝነት የሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካ ሥልጣናቸዉ ይበልጥ መተማመኛ አገኘ፡፡andm_top_memebers
ሁለተኛዉ የጊዜ ማዕቀፍ ከምርጫ 97 ማግስት እስከ አቶ መለሰ ህልፈት (2004) ድረስ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ይህ ጊዜ የብአዴንን ቀጣይ የፖለቲካ ዝማሜ የሚወስኑ ፖለቲከኞች በአባልነት የተቀላቀሉበት ጊዜ ነው፡፡ ምርጫ 97 ብአዴን ‹‹በሚመራዉ›› ክልል ሙሉ በሙሉ የተሸነፈበት የምርጫ ጊዜ መሆኑ ይታወሳል፡፡ አዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ውስጥ በመሸጉት በእነ ህላዊ ዮሴፍ ሃሳብ አመንጪነት በበረከት ስሞን ስትራቴጂስትነት በእነ አያሌው ጎበዜ አስፈፃሚነት የብአዴን አባላት ቁጥር ከመቶ ሺህዎች ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ እንዲደርስ አደረጉ፡፡ ከዚህ ግዜ ጀምሮ ድርጅቱ የተቃውሞ ድምፅ ምሽግ መሆን ጀመረ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ በአባላት ምልመላ ዘመቻዉ የተካተቱ አዳዲስ የድርጅቱ አባላት በ1998 እና በ1999 የክረምት ወራት በተሰጡት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስልጠናዎች ወደ ዝቅተኛና መካከለኛ አመራርነት ሊሳቡ ችለዋል፡፡ እነዚህ አመራሮች በመሬት ቅርምት፣ በስመ ንብረት ዝውውር፣ በገቢ ግብር አሰባሰብና መሰል የዝርፊያ ቦታዎች የ‹‹ድርሻቸውን›› ከዘረፉ በኋላ በክልሉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ለምን? እንዴት? የሚሉ ያልተለመዱ ‹አፋጣጭ› ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ከክልሉ ዉጪ በሚኖሩ አማርኛ ቋንቋ  ተናጋሪዎች ላይ የሚደርሱ በደሎችን፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ የትግራይና አማራ ክልል የድንበር ማካለል ጉዳይና ሌሎች ተያያዥ ነገሮችን በተለያዩ መድረኮች በማንሳት የብአዴንን ከፍተኛ አመራሮች ማፋጠጥ ጀመሩ፡፡ ምናልባትም በዚህ ግዜ እነ በረከት ስሞን ድርጅታቸው የተቃውሞ ምሽግ እየሆነ መምጣቱ ሳይገለጽላቸው አልቀረም፡፡
በሁለተኛው የጊዜ ማዕቀፍ ድርጅቱን በአባልነት ተቀላቅለው ወደ ዝቅተኛና መካከለኛ አመራርነት የተሳሰቡት አመራሮች በየ መድረኩ የሚያነሱትን ተቃርኖ ያዘለ ሀሳብ  በማፈን ረገድ ከኢህዴን ምስረታ ጀምሮ ከነበሩት ከፍተኛ አመራሮች በላይ በድህረ-ደርግ ጊዜ ብአዴንን የተቀላቀሉት የድል አጥቢያ መሪዎች እነ ደመቀ መኮንን ቀዳሚ ነበሩ፡፡ እስከ ሁለተኛዉ የጊዜ ማዕቀፍ ድረስ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ሀሳብ ግልብጥብጥነትና ለመለስ ዜናዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች በማደግደጉ ረገድ የሚቀድማቸው እህት ድርጅት አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ ሁለተኛው ትውልድ የብአዴን ሰዎች ክልሉን መምራት ጀምረው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እንደ አያሌው ጎበዜ ያሉ ለዘብተኛ አመራሮች ህዝባዊ ዝንባሌ ማሳየት የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡
ከፖለቲካ የሥልጣን ጉዞ አኳያ በሶስተኛ የጊዜ ማዕቀፍ ሊጠቃለል የሚችለው ጊዜ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ህልፈት በኋላ እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያቅፍ ይሆናል፡፡ ብአዴን በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ አሮጌ ቆዳውን ገፎ ለመውጣት የተውተረተረበት ጊዜ ቢኖር ሶስተኛው የጊዜ ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡ በርግጥ በሁለተኛው የጊዜ ማዕቀፍ (ከምርጫ 97 እስከ አቶ መለሰ ህልፈት ጊዜ ድረስ) አዳዲስ አመራሮችን ወደ ከፍተኛው ስልጣን ማማ ያወጣ ቢሆንም አድርባይነቱ ተከትሏቸው ስለመጣ ከአቻዎቻቸው ጋር ትክሻ ለትክሻ መጋፋት አልቻሉም ነበር፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግን ፖለቲካዊ መዋቅርና አካሄድ በቀየረው የመለስ ዜናዊ ህልፈት ዋና ተጠቃሚ የሆነው ሚዛን አስጠባቂው ደኢህዴን ቢሆንም ብአዴን የአድርባይነቱን ካባ ገፎ ለመጣል የተውተረተረበት ጊዜ ነው፡፡ ድርጅቱ የድንገቴ ሥልጣን ምኞቱን (የጠ/ሚኒስተርነት ቦታ) ባያሳካም በፖለቲካ ሥልጣን ደረጃ ሁለተኛነቱን ለማስጠበቅ ችሏል፡፡ በርግጥ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን የሚያህል ወሳኝ የመረጃ ቦታ በምንግዜም የበላዩ ህወሓት ተነጥቆ በነባር ታጋዬ ፍሬ ህይወት አያሌው ተወክሎ ታኮ ላይ መቀመጡና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ሲታዩ የወቅቱን የድርጅቱን ትክሻ ተጋፊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተው ይሆናል፡፡
የሆነዉ ሆኖ ከፖለቲካ ሥልጣን ጉዞ አኳያ የብአዴን ዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች በሁለተኛዉ የግዜ ማዕቀፍ የጀመሩት የፍንገጣ ዝማሜ በሦስተኛዉ የግዜ ማዕቀፍ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰቱ ፖለቲካዊ ክስተቶች አኳያ ይበልጥ መጎልበት  ቻለ፡፡
የድህረ መለሱ ህወሓት በቻለው መጠን የፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያውን አሳክቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስተር ቦታው በብአዴን አይያዝ እንጂ በሚዛን አስጠባቂው የደኢህዴን መያዙ የሚያመጣው ስጋት እንደሌለ ተረድቷል፡፡ ታንክና ባንኩን ጠቅልሎ በመያዙ የልብ ልብ የሚሰማው ህወሓት በብአዴን ቤት የዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮችን ፖለቲካዊ ፍንገጣ በደህንነት መዋቅሩ በኩል ቢረዳውም “ከስኒ ማዕበልነት” እንደማይሻገር ገምቶ ነበር፡፡ ይሁንና ችግሩ ውሎ አድሮ ድርጅታዊ ራስ ምታት እንደሚሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መረዳት ችሏል፡፡ በተለይም በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ያሉት የብአዴን ዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች ህዝባዊ ዝንባሌ ማሳየታቸው፣ በአካባቢው የጦር መሳሪያ የታጠቀው ህዝብ ሰፊ መጠን ያለው መሆኑ፣ የጦር መሳሪያ የታጠቀዉ የአካባቢው ህዝብ በክልሉ ካቢኔ ይሁንታ ህጋዊ ፈቃድ እንዲሰጠው መደረጉ፣ ይህን ተከትሎ የጦር ማሳሪያ ግብይቱና ዝውውሩ ከህቡዕነት ወደ ይፋዊነት እየወጣ መሄዱ፣ የወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት ጥያቄ ከህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ ወደ ከረረ ፍጥጫና ግጭት መሸጋገሩና በጉዳዩ ላይ የብአዴን ዝቀተኛና መካከለኛ አመራሮች ድጋፍ ማሳየት መጀመራቸዉ፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ መቋጫ ያላገኘ መሆኑ፣ የትግራይና አማራ ክልል ድንበር (የ‹ግጨው› ቦታ ይገባኛል ጥያቄ) ማካለል ጉዳይ ፍሬ አልባ መሆኑ፣ በሰሜን ምዕራብና አካባቢው እየታየ ያለው የታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴ መጠናከርና፣ በአካባቢዉ የአውራጃዊነትና ብሄርተኝነት ዝንባሌ በተለይም ትግሬ-ጠል ባህሪ መታየት መጀመሩ፣… የብአዴን ዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች ፖለቲካዊ ፍንገጣ ታክሎበት የኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረት እንዲጠብ አድርጎታል፡፡ ከዚህም ባለፈ በቀጣይ ለሚፈጠረው ኢ-ተቀልባሽ ህዝባዊ እምቢተኝነት  ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ይገኛል፡፡andm12
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክልሉን የሚመሩት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች አልፎ አልፎ የሚታይባቸውን የአፍ ወለምታ በሽታ ሳንዘነጋ ህዝባዊ ስሜት በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሴ አለሜ፣ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ንጉሴ ጥላሁንን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ህዝባዊ ዝንባሌ ያለው ተፅዕኖ በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ህዝባዊ ዝንባሌ ለድርጅቱ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች የሚፈጥረውን ሥነ-ልቦናዊ መነቃቃት ልብ ይሏል፡፡
በክልሉ ያለው የጦር መሳሪያ ህጋዊ ፈቃድ እንዲያገኝ መደረጉ የቁም ቅዠት የፈጠረባቸው የህወሓት አመራሮች ጉዳዩን 180 (አንድ መቶ ሰማንያ) አባላት ባሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ላይ አንስተውት ነበር፡፡ በወቅቱ የህወሓት ሊቀመንበር የሆነዉ  አባይ ወልዱ የብአዴን አመራሮችን ሲወቅስ ‹‹በገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የክልሉ ካቢኔ የሰሜን ምዕራብ /የሰሜን ጎንደርን ህዝብ የጦር መሳሪያ በነፍስ ወከፍ እያስታጠቀ ይገኛል፡፡ ገዱ ራሱን ከሲቪል አስተዳደር ወደ ጀነራልነት ቀይሯል›› በሚል ወቀሴታ አዘል ክስ ለምክር ቤቱ ቢያቀርብም የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምላሽ ‹‹አዎ እኔ ለክልሌና ለህዝቤ ጀኔራል ነኝ! የአካባቢውን ህዝብ የቆየ ባህላዊ ወግና ልማድ ባንዴ መቀየር ስለማንችል ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የያዙ ሰዎች ይፋዊ ምዝገባ ተደርጎ ህጋዊ እንዲሆን አድርጌያለሁ›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የድህረ መለሱ የኢህአዴግ ምክር ቤት ለስድብ ሩብ ጉዳይ በሆኑ የቃላት ውርጅብኝ ታጅቦ እንደሚካሄድ የሁለቱ ወደረኛ አመራሮች የቃላት ልውውጥ አስረጅ ምሳሌ ይሆናል፡፡
በመለስ የኢህአዲግ የአመራር ዘመን ህወሓት በአማራ ክልል ላይ የነበረውን የጣልቃ ገብነት ሚና የሚገድብ አዲስ አመራር ከብአዴን ጓዳ እየወጣ ያለ ይመስላል፡፡ የገዱ አንዳርጋቸው ካቤኔ አካሄድን ለመረመረ ሰው ‹‹ክልሉን ለእኛ ተውልን!›› የሚል ምላሽ ለህወሓት እየሰጠ እንዳለ ሊያስተውል ይችላል፡፡
በቀደመው ጊዜ ‹‹ጥቁር አማሮች›› እና ‹‹ቱሪስት›› በሚል ክልሉን መወከልም ሆነ መምራት አይችሉም በሚል ሲብጠለጠሉ የነበሩ ነባር የኢህዴን/ብአዴን ከፍተኛ አመራሮች በጤና መቃወስ፣ በእድሜ መግፋትና በመተካካት ለሁለተኛው የብአዴን ትውልድ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን አስረክበዋል፡፡ በኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ድርጅታዊም ሆኑ አገራዊ አቅጣጫዎች/ጉዳዮች በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንደሚወሰኑ ይታወቃል፡፡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ ከአራቱም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በሚመረጡ ዘጠኝ ዘጠኝ አመራሮች በድምሩ በሰላሳ ስድስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይወከላል፡፡ በዚህ ከፍተኛ ሥልጣን ባለዉ ኮሚቴ ውስጥ ብአዴንን ወክለው በአሁኑ ሰዓት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሆኑት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሥም ዝርዝር የሚከተለውን ይመስላል፤-
  1. ደመቀ መኮንን
  2. ገዱ አንዳርጋቸው
  3. አለምነው መኮንን
  4. ብናልፍ አንዷለም
  5. ተስፋዬ ጌታቸው
  6. አህመድ አብተው
  7. ከበደ ጫኔ
  8. ካሳ ተክለብረሃን
  9. አምባቸው መሰለ (ዶ/ር)
ከእነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ የትጥቅ ትግሉን በ1970ዎቹ አጋማሽ በልጅነቱ ኢህዴንን ከተቀላቀለው ካሳ ተክለብረሃን ውጪ ስምንቱም የድል አጥቢያ መሪዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት በህወሓት የተወከሉት ዘጠኝ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚዎች፡-
  1. አባይ ወልዱ
  2. ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)
  3. አዜብ መስፍን
  4. አዲስ አለም ባሌማ (ዶ/ር)
  5. ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር
  6. ጌታቸው አሰፋ
  7. አለም ገብረዋህድ
  8. ቴድሮስ አድኅኖም (ዶ/ር)
  9. በየነ መክሩ፤ ናቸዉ፡፡
ከህወሓት የፓሊት ቢሮ አባላት ውስጥ በትጥቅ ትግሉ ተሳትፎ ያላደረጉት አለም ገብረዋህድ እና ቴድሮስ አድኅኖም ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሰባቱም ሥራ አስፈፃሚዎች ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በልዩ ልዩ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የሥልጣን ቦታዎች የነበሩ ነባር ተጋዮች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ ተነስተን ህወሓት በመተካካት ድርቅ ተመርቷል ማለት እንችላል፡፡ በየትም አገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት መረጃ ዋና ዳይሬክተር የሆነው ጌታቸው አሰፋ ህወሓትን ወክሎ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ፖለቲካውን እንዳሻው ይዘውረው ጀምሯል፡፡
ወደ ዋናው ነጥብ ስንመለስ ብአዴን ለሁለተኛው ትውልድ የፖለቲካ ስልጣኑን አሻግሯል፡፡ ስልሳ አምስት አባላት ባሉት የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንደ በረከት ስሞንና ታደሰ ካሳ ያሉ ነባር ታጋዮች ቢኖሩም በአብዛኛው የሁለተኛው ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ በአንጻሩም ቢሆን ከአራቱም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በተሻለ መልኩ የሴቶች ተሳትፎ የሚታይበት የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
የሐምሌ ፀሐይ ከወደ ብአዴን?
የድህረ-መለሱ ኢህአዴግ በብዙ መልኩ ፖለቲካዊ መዋዥቅ ይታይበታል፡፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርቆት የስርዓቱ መገለጫ ሆኗል፡፡ የኢህአዴግ ቁንጮ አመራሮች በቁሳዊ ህይወታቸው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መሳፍንቶችና የደርግን የአየር በአየር ነጋዴ አስንቀውታል፡፡ ከዚህም ባለፈ በመንፈስ ሁነኛ የገዥ መደብ ንቃተ ህሊና ተላብሰዋል፡፡ ተራማጅ የፖለቲካ ሀሳብ ያረጠበት ድርጅት ውንብድና መገለጫው ሆኗል፡፡ እስከ መለስ ህልፈት ድረስ ህወሓት በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች አዛዥ ናዛዥ ነበር፡፡ ድህረ መለስን ተከትሎ በተፈጠረው የፖለቲካ አሰላለፍ ግን ከብአዴን ብርቱ ሙግት የገጠመው ይመስላል፡፡ ኦህዴድ የብአዴንን መንገድ ለመከተል የሞከረ ቢመስልም የኦሮሚያን ተቃውሞ ተከትሎ እየተፈጠሩ ባሉ ብጥብጦች ‹‹ጸረ ሰላም ኃይሎችን ለመከላከል›› በሚል ሰበብ ከህወሓት መዳፍ ላይ ተመልሶ ወድቋል፡፡ በማዕከላዊ መንግስቱ በኩል ያለውን ፖለቲካዊ ተሳትፎ አጉኖ ለማሳየት አቅም ቢያጥረውም ብአዴን የሚመራውን ክልል ከህወሓት ጣልቃ ገብነት ለማዳን የሄደበት መንገድ የተሳካ ይመስላል፡፡gondar uprising
“የህወሓት የበላይነት ይብቃ!” የሚለው የብአዴን ዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች ጥያቄ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መነቃቃት ሊፈጥር ችሏል፡፡ በተለይም ከግለሰብ ፖለቲካዊ ገጽታ አኳያ ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ በክልሉ ህዝብ የተጠላው ደመቀ መኮንን ለሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጥሩ ትምህርት የሰጠ ይመስላል፡፡ የዚህ ጉዳይ ቀዳሚ ትምህርት ወሳጅ ገዱ አንዳርጋቸው ሲሆን፤ እርሱን ተከትለው አሰላፋቸውን እያስተካከሉ ያሉ የክልሉ ካቢኔ አባላት ቀጣይነት እያሳየ ላለው የኢህአዴግ ፖለቲካዊ ኪሳራ ተጨማሪ በር ከፋች ሆነዋል፡፡ በፌደራል ደረጃ የሥልጣን ባለቤት የሆኑት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች እንደ ክልሉ ባለስልጣናት ህዝባዊ ዝንባሌ የሚያሳዩ ባይሆንም በጊዜ ሂደት ፖለቲካዊ መዋዋጥ የሚፈጥሩበት እድል ሰፊ ነው፡፡ የእነርሱ ጭንቀት ፖለቲካዊ ዋስትና የሚሰጣቸው ኃይል መኖሩ ላይ ነው፡፡ እንደ ገዱ አንዳርጋቸው ያለ የብአዴን አመራር በአካሄዱ ማህበራዊ መሰረቱን እያስፋ መጥቷል፡፡  በዝቅተኛና መካከለኛ አመራሮች ዘንድ ተወዳጅነትን ከማትረፉ ባሻገር በክልሉ ህዝብ ዘንድ በቀና አመለካከት ለመታየት የሚያስችለውን ህዝባዊ ዝንባሌ መርጧል፡፡ ግዜ የሚገልጠዉ ተጨባጭ እዉነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡
ብአዴን የብረት አከሉ ህዝባዊ አመጽ መሀንዲስ?
የወልቃይት አማራ ብሄርተኝነት ጥያቄ በሰሜን ምዕራብ የብአዴን መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ ብአዴን ከህወሓት ጋር እየፈጠረ ላለው ፖለቲካዊ ግፊያ ኃይል ሰጪ ሆኗል፡፡ የትግራይና አማራ ክልል አዋሳኝና አቅራቢያ ወረዳዎች ታች አርማጭሆ፣ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣… ወረዳን የሚያስተዳድሩ የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ለወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት ጥያቄ መቀጣጠል የራሳቸዉን ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የህወሓት የደህንነት መዋቅር ያዉቃል፡፡
ለወልቃይት የአማራ ብሄረተኝነት ጥያቄ መቀጣጠል የተደረገዉ ድጋፍ ጎንደር ከተማ ድረስ ዘልቆ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በህዳር ወር 2008 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲያደርጉ የከተማ አስተዳደሩ ፍቃድ ሰጥቷል፡፡ ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ የሆነዉን ጉዳይ በጉልበት ካልፈታሁ ብሎ የተነሳዉ ህወሓት ያለ ክልሉ መንግስት እዉቅና አምስት የተመረጡ የኮሚቴዉን አባላት ሐምሌ04/2008 ምሽት ጎንደር ከተማ ላይ ለመያዝ ባደረገዉ ዘመቻ አታላይ ዛፌ፣ ጌታቸዉ አደመ እና መብራቱ ጌታሁን የተባሉ የኮሚቴዉን አባላት በቁጥጥር ስር ሲያዉል፤ አቶ ገብረ እግዚአብሄር የተባለ የኮሚቴዉ አባል በአካባቢዉ ህብረተሰብ ትብብር ሊያመልጥ ችሏል፡፡
col demeke
ኮለኔል ደመቀ
በማግስቱ ኮለኔል ደመቀ ዘዉዱን ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 በተለምዶ ‹ደሳለኝ ት/ቤት› አካባቢ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ለማፈን የተደረገዉ ጥረት በኮሎኔሉ እምቢተኝነት ከፌደራል የጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን ጋር የተኩስ ልዉዉጥ በማድረግ ራሱን ለመከላከል ያደረገዉ ጥረት በከተማዉ ነዋሪ ድጋፍ ተችሮት እንዲሁም ከወልቃይት-ዳንሻና አካባቢዉ አንድ መቶ ሃያ የሚሆኑ የኮለኔሉ አጋሮች በሦስት F.S.R የጭነት አይሱዙ መኪና 135 ኪ.ሜ በማቆራረጥ ጎንደር ከተማ ድረስ በመግባት የኮለኔል ደመቀን ቤት የከበበዉን የፌደራል የጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን ከከተማዉ ህዝባዊ ጦር ጋር በመተባበር ባደረሱት ጥቃት፤ የአካባቢዉ ምንጮች ከመንግስት በኩል የሟቾች ቁጥር ከ20 ይበልጣል ቢሉም የፌደራሉ ‹‹መንግስት›› ባመነዉ መረጃ መሰረት 9 የፌደራል፣አንድ መከላከያ እና አንድ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ (በወቅቱ የተሰጠዉን መስመር ስቶ ወደ ዋናዉ የውጊያ ቦታ በመግባቱ ሊሞት እንደቻለ የአካባቢዉ ምንጮች ይጠቁማሉ) በድምሩ 11 የሰራዊቱ አባላት እንደተገደሉ፤ ከሲቭል ደግሞ 5 ሰዎች እንደሞቱ፤ በተጨማሪም 9 የሰራዊቱ አባላት ቁስለኛ እንደሆኑ የሚታወስ ነዉ፡፡
ሀምሌ 05/2008 ቀኑን ሙሉና የምሽቱ አጋማሽ ድረስ በህዝባዊ ጦርና በፌደራል የጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን በተጨማሪነት የሰሜን ምዕራብ 24ኛ ክፍለ ጦር አዘዞ- ጭልጋ ምድብተኛ የመከላከያ ሰራዊት አጋዥ በሆነበት ሁኔታ መደበኛ ዉጊያ ሲካሄድ፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ የሰሜን ጎንደር ዞንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የፖሊስ አባላት ዉጊያዉ ይካሄድበት ከነበረዉ (ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18) ቦታ በቅርብ ርቀት ጉዳዩን ከመከታተል በዘለለ እንደ መንግስታዊ አካል የወሰዱት አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዮ ላይ ለዘብተኛ አቋም ማሳየታቸዉ ህዝባዊ ዝንባሌ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለሁለት ቀናት በቆየዉ በብረት ለተደገፈዉ ህዝባዊ አመጽ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም ሆነ የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶች ጉዳዮን ዳር ይዞ ከማየትና አልፎ አልፎ ራሳቸዉን ለመከላከል ካደረጉት ጥረት ዉጪ ህዝባዊ ጦሩን ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት የለም፡፡ ይህ ጉዳይ የሚያመለክተዉ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ‹‹የኃይል እርምጃ እንዳትጠቀሙ!›› የሚል ትዕዛዝ በርግጥም እንደተላለፈ ጥቁምታ ይሰጠናል፡፡gondar selam bus
ለሁለት ቀናት በዘለቀው ብረት አከል ህዝባዊ አመጽ ሁለት የፌደራል ፖሊስ መኪናዎችና የሰላም ባስ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ ሲወድሙ ሌሎች የንብረት ጉዳቶችም ደርሰዋል፡፡ ይህን በመሰለዉ መሬት አንቀጥቅጥ ህዝባዊ አመጽ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም ሆነ የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊሶች ጥጋቸዉን ይዘዉ አመጹን መመልከታቸዉ የህዛባዊ አመጹን ተራዛሚነት የሚሹ የብአዴን ዝቀተኛ፣ መካከለኛ እልፍ ሲል ደግሞ ከፍተኛ አመራሮች እንዳሉ ተጨማሪ ጥቁምታ ይሰጠናል፡፡
የአካባቢዉ ምንጮች እንደሚያረጋግጡት ኮለኔል ደመቀ ዘዉዱ በዕለቱ ማምለጥ የሚችልበት እድል የነበረ ቢሆንም ‹‹የታሰሩት የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ካልተፈቱ የእኔ ማምለጥ ጓዶቼን መካድ ይሆንብኛል›› በሚል በህዝባዊ ጦር አጃቢነት ለዞኑ የልዩ ኃይል ፖሊስ ዋና ኃላፊ ኮማንደር ዋኘዉና ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተቀባ ተባባል በኃላፊነት ‹‹ለተሻለ የህግ ከለላ›› አደራ ተሰጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ ከህዝባዊ ጦሩ የተሰጠዉን ኃላፊነት የተረከቡ አመራሮች ‹‹ኮለኔል ደመቀ ዘዉዱን ለትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ ለፌደራሉ መንግስት አሳልፈን አንሰጥም፡፡ ለዚህም ኃላፊነት እንወስዳለን›› በሚል ኮለኔሉን ከህዝባዊ ጦሩ ተረክበዋል፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚሆነዉ ዉድቅ መንግስት (failed state) ባላቸዉ ደቡብ ሱዳን አለያም ሱማሊያ አይደለም ለአፍሪካዊያን ምሳሌ የሆነ ‹‹ጠንካራ መንግስት›› አለ ተብሎ በሚታመንባት ኢትዮጵያ ውስጥ ነዉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ድርድር ጀርባ  ክልሉን የሚመሩት የብአዴን ከፍተኛ ባለሥልጣናት እጃቸዉ የለም ብሎ ማመን ቂልነት ይመስላል፡፡ በዞንና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ያሉ መካከለኛ አመራሮች የትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ኃይል አከል ግፊት ሳያሸብራቸዉ ‹‹ኮለኔሉን አሳልፈን አንሰጥም›› በማለት በህዛባዊ ጦሩ ፊት ቃል መግባታቸዉ ከእነዚህ መካከለኛ አመራሮች ጀርባ ያለዉ ፖለቲካዊ መተማመኛ ምን ያህል እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡gondar building
በፌደራል ደረጃ ያሉ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ከሐምሌ 08-09/2008 ድረስ ጎንደር ከተማ ላይ ከዞኑና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ያደረጉት የምክክር ስብሰባ ከትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ ከፌደራሉ መንግስት ፍላጎት አኳያ ዉይይቱ ፍሬ አልባ  ሆኖ ቀርቷል፡፡ በነገራችን ላይ የትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ምንም ልዩነት የላቸዉም፤ ያዉ ጠቅላዩ ህወሓት ነዉ፡፡ ኮለኔል ደመቀ ዘዉዱን ከጎንደር ከተማ በኃይል አፍኖ መዉሰድ የማይቻል ሆኗል፡፡ ከብረት አከሉ ህዝባዊ እምቢተኝነት ጀርባ የብአዴን ዝቅተኛ፣ መካከለኛና የዉስን ከፍተኛ አመራሮች ደጀንነት ጮክ ብሎ ይታያል፡፡ የወትሮዉ የህወሓት የበላይነት አማራ ክልል ላይ ላይ በተለይም ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የማይታሰብ ሆኗል፡፡
ጀብደኝነት ለህወሓታዊያን ብቻ የተሠጠ አድርገዉ የሚያስቡት የህወሓት አመራሮች ከብአዴን በኩል እየገጠማቸዉ ያለዉ ፖለቲካዊ ግፊያ ቀላል አይመስልም፡፡ በቀደሙት ‹‹ቱሪስት›› የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ የተሰራዉን ስህተት ለማካካስ የሚጥረው ሁለተኛዉ የብአዴን ትዉልድ ብረት አከል ህዝባዊ አመጹን በደጀንነት መደገፍ ዘመን የፈቀደዉ የህዝባዊ አመጽ ምህንድስና አስመስሎታል፡፡ የህወሓት አመራሮች ነጻ አዉጭነታቸዉ የማይቆም ሂደት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ፡፡ ብሶት እነርሱን ብቻ ወልዶ እንደ ቆመም እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ ግና፤ ብሶት ዛሬም ሌሎችን እየወለደ እንደሆነ ኤርትራ በርሃን ማስታወስ ሳይጠበቅብን ስምንት የጭንቅ ወራትን ከተሻገረዉ የኦሮሚያ ህዝባዊ አመጽ በተጨማሪ የሰሜን ምዕራቡ ብረት አከል ህዝባዊ አመጽ አስረጅ ምሳሌዎች ይሆኑናል፡፡ በተለይም የሰሜን ምዕራቡ ብረት አከል ህዝባዊ አመጽ ወደ ከተማ ላይ የሽምቅ ዉግያ በመቀየር የከተማ አብዮቱ ወደ ሌሎች ትልልቅ የአገሪቱ ከተሞች እንዲስፋፋ የሚያደርግበት (ብቸኛ) የቢሆን ዕድል ሰፊ ነዉ፡፡ ይህን የቢሆን ዕድል ይበልጥ የሚያጠናክረዉ ጉዳይ የሰሜን ምዕራብና አካባቢዉን የሚመሩት የብአዴን አመራሮች (ከፍተኛ አመራሮችን ሳንዘነጋ) ህዝባዊ ዝንባሌ ማሳየትና በቀጠናዉ ቲማቲም የመግዛት ያህል ቀላል እየሆነ የመጣዉ የጦር መሳሪያ ግብይትና ዝዉዉር መኖሩ ነዉ፡፡ እናም በቀጣይ የሚፈጠረዉን የከተማ ላይ የሽምቅ ዉግያ ማህበራዊ መሰረት በማስፋት ከተማ አቀፉን አብዮት ኢ-ተቀልባሽ ያደርገዋል!!
‹ያለ ደም ስርየት የለም!›
በሙሉዓለም ገ.መድህን

No comments:

Post a Comment