Translate

Thursday, April 21, 2016

በጋምቤላ የተጨፈጨፉት ዜጎች ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን ማነጋገሩን ቀጥሎአል


ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓም በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች የተገደሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የአለምን ትኩረት በሳበት በዚህ ወቅት፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ምንም አይነት መግለጫ አለማውጣቱ ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለጥቃቱ አፋጣኝ መልስ አለመስጠቱ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከባድ የሆነውን አገራዊ ጉዳይ ትተው ወሳኝ ላልሆነ ስብሰባ ስዊድን መገኘታቸው ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረ ነው። 


መንግስት 208 ሰዎች በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ ከ70 በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም 102 ህጻናት እና ሴቶች ተጠልፈው መወሰዳቸውን ሲገልጽ፣ ኢሳት ደግሞ ጋምቤላ ውስጥ ያሉ ታማኝ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ የሟቾች ቁጥር 230 መድረሱን እንዲሁም ተጠልፈው የተወሰዱት ደግሞ 143 መድረሳቸውን ዘግቧል። አስከሬን የማሰባሰቡ ሂደት የቀጠለ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጾ ነበር። በአሜሪካ የሚገኙ የኑዌር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ በደቡብ ሱዳን የዜና አገልግሎት ድረገጽ ላይ ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ደብዳቤ፣ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ 280 ሰዎች መገደላቸውንና 150 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን በመግለጽ፣ ከመንግስት በኩል ለወላጆቻችን፣ ልጆቻችን ዘመዶቻችን አስፈላጊው የደህንነት ጥበቃ ሳይደረግ እንዴት ራሳችንን እንደ ኢትዮጵያዊ ልንቆጥር እንችላለን በማለት ጠይቀዋል። 
የንዌር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በደብዳቤያቸው በመከላከያ ሰራዊት ምላሽ እና በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ ያላቸውን ጥርጣሬም ገልጸዋል። 
ጥቃቱን የፈጸሙት 4 ሺ የሚሆኑ በደንብ የታጠቁና የተደራጁ ሃይሎች መሆናቸውን፣ 280 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የተገደሉትም 12 ሰአት በፈጀ ጦርነት መሆኑን ገልጸው፣ ድርጊቱ ሲፈጸም የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ይመለከት ነበር የሚለው መረጃ ትክክል ነበር ወይ ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩን ጠይቀዋል። 
“የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም የት ነበር? ጦርነቱ 12 ሰአታት ያክል መቆየቱ እየታወቀ የተጠለፉትን ኢትዮጵያውያንን ፈጥኖ ለማዳን መከላከያው ለምን ተሳነው? በተለይ ደግሞ ጋምቤላን ከንዌር ዞን የሚያገናኘው መንገድ ከ ግማሽ ሰአት በላይ እንደማይወስድ እየታወቀ፣ ከላሬ እስከ ማዲንግ ቀበሌ ያለው ቦታም ሰፊ አለመሆኑ እየታወቀ ፣ ወገኖቻችንን ሲፈጁዋቸው ለምን ፈጣን ምላሽ ሳይሰጥ ቀረ ? በማለት ጥያቄያቸውን ያከታተሉት የኑዌር ተወላጆች፣ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ፣ ሳይወል ሳያድር አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ልጆቻችንንና ሴቶቻችንን ሊያመጣልን ይገባል ብለዋል። 
የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናቱ ደህና እስከሆኑ ድረስ ለዜጎቹ እንደማይጨነቅ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት የኑዌር ኮሚኒቲ አባላት፣ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸም ፣ መንግስት ለዜጎቹ ተቆርቁሮ የወሰደው እርምጃ እንዳልነበር ገልጸዋል። ከ9 አመታት በፊት ሙረሌዎች በንጎር ቀበሌ፣ ከ7 አመታት በፊት ደግሞ በፓልቦል ቀበሌ እርምጃ ሲወስዱ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እርምጃ አለመውሰዳቸውን በማስረጃነት ያቀርባሉ።
የክልሉ መንግስት ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በጻፈው ደብዳቤ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር በጭፍጨፋው እጁ እንዳለበት በዝርዝር የገለጸ በመሆኑ፣ ጠ/ሚኒስትሩ ለደቡብ ሱዳን መንግስት ግልጽ ደብዳቤ በመጻፍ ዜጎቻችን እንዲመለሱ እንዲሁም አስፈላጊ እርምጃ በመውሰድ ጥቃቱ እንዳይደገም ማድረግ ይገባዋል ብለዋል። 
ተመሳሳይ ጥቃቶች በቦሊም ኩም ወረዳ ማንጎግ ፣ ቻቲየር፣ ባኒየራል፣ ማዲያንግ ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በአኝዋክ ዞን ጆር እና ሌሎችም አጎራባች ቀበሌዎች ሲፈጸሙ ምንም እርምጃ አለመወሰዱን ያወገዙት የማህበረሰቡ አባላት፣ መከላከያው አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ለማዬት እየጠበቅን ነው በማለት ደብዳቤያቸውን ቋጭተዋል።
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉክ ቱት ጥቃቱ ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓም ሲፈጸም እንደነበር በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው፣ በእነዚህ 20 ቀናት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምን ይሰራ ነበር የሚል ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ፣ በኢህአዴግ የአካባቢው ፖሊሲ ላይ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ እያደረገ ነው። ከግጭቱ በሁዋላ የአካባቢውን ተወላጆች እየተነሱ ወደ አንድ አካባቢ እንዲሰባሰቡ መደረጉን ተከትሎ፣ የሚለቀቀውን መሬት ማን ይወስደዋል? የሚል ጥያቄም እያስነሳ ነው። 
የደቡብ ሱዳን መንግስት ምንም አይነት መግለጫ አለመስጠቱም ሌላው አስገራሚ ነገር ሆኗል። ምንም እንኳን የኢህአዴግ መንግስት፣ በማያገባው ገብቶ የደቡብ ሱዳንን መንግስትና የሪክ ማቻርን ጦር እጃቸው የለበትም በማለት ተሽቀዳድሞ መግለጫ በማውጣቱ ፣ የደቡብ ሱዳንን መንግስት መግለጫ ከማውጣት ቢታደገውም፣ ድርጊቱ በራሱ ዜጎች የተፈጸመ በመሆኑ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለሟች ኢትዮጵያውያን ሀዘኔታውን መግለጽና ወንጀለኞችንም ይዞ እንደሚያስረክብ በአደባባይ መናገር ነበረበት በማለት ኢትዮጵያውያን ወቀሳ ያቀርባሉ። 
አሰቃቂው ጥቃት በተፈጸመ ማግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር ወደ አውሮፓ ለስብሰባ መጓዛቸው በኢህአዴግ መንግስት ላይ ተጨማሪ ትችት እንዲሰነዘር እያደረገ ነው። ወንጀለኞችን በመያዝና አሳልፎ በመስጠት በኩል በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን መንግስታት መካከል የዲፐሎማሲ ስራ መስራት ሲችሉ፣ በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ስብሰባ ላይ ለመገኘት መመጣታቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ህይወት ደንታ እንደሌላቸው ማሳያ ነው በማለት አንዳንድ ወገኖች ትችት ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ የመገናኛ መንገዶች ባደረጉት ግፊት መንግስት የሃዘን ቀን ቢያውጅም፣ ሟቾቹ ምንም የሚዲያ ሽፋን ሳይሰጣቸው እንደተራ ግድያ በቤተሰቦቻቸው እንዲቀበሩ መደረጉ ፣ መንግስት ድሮውንም ሰይፈልግ በግፊት የሀዘን ቀን ለማወጁ ማረጋገጫ ተደርጎ ተወስዶአል። 
አንዳንድ ወገኖች መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱ የዜጎቹን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን ባለማስጠበቃቸው ይቀርታ ይጠይቁ ሲሉ፣ ሌሎች ወገኖች ደግሞ፣ የራሱ መንግስት ያላከበረውን ህዝብ የውጭ አገር መንግስት እንዲያከብረው መጠበቅ የዋህነት ነው በማለት መንግስት እስካልተለወጠ ድረስ የኢትዮጵያውያን ስቃይ አያቆምም ይላሉ።

No comments:

Post a Comment