Translate

Tuesday, April 12, 2016

ወያኔ መንግስት የኮምፒውተር መረጃዎችን መጥለፍ፣ መበርበር፣ መሰለል የሚያስችል ህግ አረቀቀ

መንግስት እንደፈለገ የግል የኮምፒውተር መረጃዎችን መጥለፍ፣ መበርበር፣ መሰለል፣ ኦን ላይን መፈለግ የሚያስችለውን ህግ አርቅቆ ለፓርላማ አቅርቦአል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ኮምፒውተር ወይንም የኮምፒወተር ስርዓት ምንነት ሲያብራራ በሶፍትዌር እና ማይክሮቺን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ የዳታ ፕሮሰሲንግ፣ ክምችት፣ ትንተና፣ ስርጭት፣ ግንኙነት ወይንም ሌሎች ሂሳባዊ ወይንም አመክኖአዊ ተግባራትን የሚያከናውን ማንኛውም መሳሪያ ነው ይለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የኮምፒውተር ወንጀል በፈቃድ እና ለፈቃድ እንደሚከናወን ይጠቅሳል፡፡ በዚሁ መሠረት በሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችና መርማሪዎች ወይም ሌሎች በተፈቀደላቸው አካላት፣ በፍ/ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ የኮምፒውተር ስርሰራ አያስቀጣም ይላል፡፡ ሌሎች ባልተፈቀደላቸው ወገኖች የይለፍ ቃልና ሌሎችን የደህንነት አጥሮችን ሰብሮ መግባትና ክፍያ የሚጠይቁ የኮምፒውተር አግልግሎቶችን ያለክፍያ መጠቀም እና የመሳሰሉ ድርጊቶች እንደሚያስጠይቁ አስቀምጦአል፡፡
ፖሊስ በረቅቅ አዋጁ መሰረት የኮምፒውተር ወንጀል ለመፈጸሙ ወይም እየተፈጸመ ስለመሆኑ በቂ ጥርጣሬ ሲኖር በወንጀል ሕግ ሥነሥርዓት በተደነገገው መሠረት ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ሊይዝ ከመቻሉም በተጨማሪ ምርመራ ያልጠጠናቀቀ ከሆነ እስከ አራት ወራት ጊዜ ድረስ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ መውሰድ እንደሚችል ደንግጎአል፡፡
በተጨማሪም ፖሊስ ለወንጀል ምርመራ ዓላማ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ከፍርድ ቤት ፈቃድ በማውጣት ማንኛውንም የኮምፒውተር ሥርዓት፣ ኔትወርክ፣ ወይም ኮምፒውተር ዳታ ከርቀት ወይም ከቦታው በአካል በመገኘት መበርበር ይችላል ይላል፡፡
ወንጀሎቹን የሚያከብዱ ሁኔታዎች በተመለከተ ረቂቅ አዋጁ እንደሚለው የግለሰቦችን የኮምፒውተር ስርዓት ዳታ ከማጥቃት ጀምሮ ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ ተቋማት የኮምፒውተር ስርዓቶችና ኢላማ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው ብሎአል፡፡ ቅጣትን በተመለከተም ለአብነት ያህል የአንድ ተቋም ድረገጽ ቢጠቃ ከአምስት እስከ አስር ኣመት እስራትና ከብር 50 ሺ አስከ 100 ሺ ብር መቀጮን ይጥላል፡፡ በቁልፍ መሰረተ ልማት ላይ ከሆነ የገንዘብ ቅጣቱ ከ100 ሺ እስከ 200 ሺ የእስር ቅጣቱ ከ10 አስከ 15 ኣመት ይደርሳል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በተለይ ክፍያ የሚጠየቅባቸው የኮምፒውተር አገልግሎቶችን ያለክፍያ መጠቀም እንደወንጀል መደንገጉ ሰሞኑን ኢትዮቴሌኮም በቫይበርና መሰል አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ሊጥል ነው የሚሉትን ዘገባዎች የሚያጠናክር ሆኖአል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከሳምንት በፊት በፓርላማ ተገኝተው የኦሮሚያ ግጭት ተከትሎ በመንግስት ላይ የሳይበር ጥቃት መሰንዘሩን ተናግረው ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ከወር በላይ ትዊተርና ዋትስ አፕ የሚባሉት ዘመናዊ መረጃ የመለዋወጪያ መንገዶች በተለይ በኦሮምያና በደቡብ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ ተዘግቦአል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከወራት በላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሙሉ ለሙሉ የትዊተርና ዋትስ አፕ ተጠቃሚዎች አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ብሉምበርግ የዜና ወኪል ዘግቧል። የስማርት ሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በትዊተርና በፌስ ቡክ ሜሴንጀር መልእክቶችን መለዋወጥ እንዳልቻሉና ደንበኞች በኢትዮ ቴሌኮም መማረራቸውን ገልፀዋል።
በአንቦ ዩንቨርሲቲ ወሊሶ ካንፓስ መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ”ሁሉም የሞባይል ዳታ አገልግሎቶች ከአንድ ወር በላይ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦብናል” በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አስረድተዋል። ኢትዮ ቴሌኮምና የገዥው ፓርቲ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ችግሩ ከተለመደው የመስመር ችግር ጋ የተፈጠረ ነው በማለት ሲያስተባብሉ፣ የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ሃላፊ ሌስ ሌፍኮው ደግሞ በኢትዮጵያ ከሚታየው የሀሳብ አፈና ጋር እንደሚያያዝ ተናግረዋል፡፡
ከ20 ሚሊዮን በላይ በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ የአለማቀፍ እርዳታ እየተለመነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ መንግስት ለህዝብ የሚደርሱ መረጃዎችን ለማፈን በሚሊዮኖች ገንዘብ ያወጣል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብበታል፡

No comments:

Post a Comment