Translate

Tuesday, April 19, 2016

በጋምቤላ የሟቾች ቁጥር 230 መድረሱንና ከ140 በላይ ህጻናትና ሴቶች መወሰዳቸውን የአካባቢው ምንጮች ገለጹ


ሚያዚያ ፲፩(አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው አርብ፣ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓም በጋምቤላ በከፍተኛ ሁኔታ የተጣቁ ወታደሮች በኑዌር ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸሙት ጥቃት፣ መንግስት እንኳን ባመነው፣ 208 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ100 በላይ ቆስለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ተወስደዋል፣ ከ2 ሺ ያላነሱ የቀንድ ከብቶችም ተወስደዋል።የአካባቢው አስተማማኝ ምንጮች እንደሚሉት ዋናው ጥቃት በተፈጸመበት በጅካዎ እና በላሬ መስመር ብቻ እስከዛሬ ቀን ድረስ የ230 ሰዎች አስከሬን ተገኝቶአል። ተጠልፈው የተወሰዱት ህጻናት ቁጥር ደግሞ 143 ደርሶአል። በማኩዌ አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ ገና እየተጠራ በመሆኑ፣ የማቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ይሆናል ሲሉ እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል። ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ሰፍረው የሚገኙ ዜጎችን መንግስት ወደ ጋምቤላ ከተማ እየወሰዳቸው መሆኑንም ምንጮች አክለዋል። በመከለከያ ቦታ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአንዳንድ አካባቢዎች ዛሬ ቅኝት ሲያደርጉ ታይተዋል።

መንግስት ድርጊቱን ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኙ የሙርሌ ጎሳ አባላት እንደፈጸሙት በመግለጽ፣ የደቡብ ሱዳንን መንግስትም ሆነ የአማጺውን የሪክ ማቻርን ሰራዊት ከወንጀል ነጻ አድርጎአቸዋል። ይሁን እንጅ መንግስት የደቡብ ሱዳንም ሆነ የአማጺው ሃይሎች ከድርጊቱ በስተጀርባ እጃቸው የለበትም በሚል ተሽቀዳድሞ የሰጠው መግለጫ ሌላ የመነጋገሪያ ርዕስ ከፍቶአል። የደቡብ ሱዳን መንግስትና አማጽያኑ ራሳቸው “እጃችን የለበትም” ማለት ሲችሉ፣ መንግስት የእነሱ ወኪል ሆኖ መግለጫ ለመስጠት ለመን ቸኮለ?”በሂደት ከሁለቱ ሃይሎች አንደኛው ከጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለበት ቢታወቅ ፣ መንግስት ምን ሊል ነው? “ የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። “ መንግስት እንደሚለው ድርጊቱ ተራ ዝርፊያ ቢሆን ኖሮ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወይም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው አማጺ ሃይል ታጣቂዎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከላከል አይችሉም ነበር ወይ? መከላከል እንኳን ባይችሉ ለኢትዮጵያ መንግስት አስቀድመው መረጃ በመስጠት መንግስት እንዲዘጋጅ ማድረግ አይችሉም ነበር ወይ? “ የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግስት ሰዎችን እስካሁን አሳልፎ ለመስጠት አለመቻሉም ለጥርጣሬው ተጨማሪ ምክንያት ሆኖአል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የጋምቤላ ነዋሪዎች በመንግስት በኩል የተሰጠውን መግለጫ አይቀበሉትም። ድርጊቱ በሙርሌ ጎሳ አባላት ተፈጽሟል ብለው ለማመን እንደሚቸገሩም ይናገራሉ። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም “ ድርጊቱ ከሌሊቱ 10 ሰአት እንደተፈጸመ የተገለጸ ቢሆንም፣ በእለቱ ግን በጅካዎ አካባቢ ከጡዋቱ 2 እስከ 3 ሰአት ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ ሄሊኮፕተር በአካባቢው በወታደራዊ ቅኝት ሲያደርግ ነበር፣ ታዲያ 2 ሺ ከብት ዘርፈው ሲሄዱ ወይም ብዛት ያላቸው ሰዎች ግድያውን ፈጽመው 40 እና 50 ኪሜ በእግራቸው ተጉዘው ምንም ነገር ሳይደረስባቸው ደቡብ ሱዳን ሊገቡ አይችሉም፤ የተጠለፉትም ህጻናት ይህን ያክል ኪሜ በእግራቸው ሊጓዙ አይችሉም” ካሉ በሁዋላ፣ ከሁሉም በላይ አካባቢው ሜዳማ በመሆኑ፣ ተዘረፉ የተባሉት እንስሶችን በሄሊኮፕተር ማየት ይቻል ነበር” ሲሉ ያክላሉ። “ከሰአታት በሁዋላ በአካባቢው የተገኙት ወታደሮች ገዳዮችን ባያገኙዋቸው እንኩዋን የተዘረፉትን ከብቶች ማግኘት ይችሉ ነበር፣ ይህ እንዴት ሳይሆን ቀረ?” በማለት ጥያቄ ያነሳሉ።
ከሁሉም በላይ ጠርጣሬያችን ያጎላው ደግሞ ከላሬ እስከ ፉኝዶ ባለው እጅግ ሰፊ መሬት በአንድ ጊዜ እና በተመሳሳይ ሰአት ጥቃት ተፈጸመ የሚለው ዜና ነው። ረጅሙን ድንበር አቋርጠው፣ እጅግ ሰፊ በሆነው አካባቢ ተንቀሳቀስው ጥቃት ፈጽመው በእግራቸው እንዴት ሊያመልጡ ይችላሉ የሚሉት ነዋሪዎች፣ ይህ የማይሆንና የማይመስል ነው ይላሉ።
ሌላው የሚያነሱት ጥያቄ “መንግስት 61 ታጣቂዎችን መግደሉን ካስታወቀ፣ ሌሎች እንዴት ሊያመልጡ ቻሉ? የተገደሉትስ የየትኛው ወገን ናቸው? ታጣቂዎች ከተገደሉስ እንስሶችን ማን እየነዳ ወሰዳቸው? ከብቶቹስ እንዴት አልተገኙም፤ የሟቾች አስከሬንስ እንዴት አይታይም? ተገደሉ የተባለበት ቦታስ የት ነው?” የሚል ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄዎችን ከማንሳት ባሻገር ፣ የራሳቸውን መላምትም ያቀርባሉ። ጥቃቱ ተፈጸመበት በሚባለው አካባቢ፣ በስልጣን ላይ ያለውን የክልሉን መንግስት የሚቃወሙ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱበታል በሚል መንግስት ተደጋጋሚ የሄሊኮፕተር ቅኝት ሲያደርግ መሰንበቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ምናልባትም ድርጊቱ በደንብ ተቀናብሮ የተፈጸመ ሊሆን እንደሚችል ቢግልጹም፣ ድርጊቱን የፈጸመውን ክፍል ግን በትክክል ለመናገር አልደፈሩም።
በአሁኑ ሰአት በጋምቤላ ዋና ከተማ ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ሲናገሩ፣ በፉኝዶ አካባቢ ደግሞ ሰራዊቱ ወደ ካምፑ ተመልሶ መግባቱን ይገልጻሉ።
ኢሳት የመከላከያ ሰራዊቱ ከአዲስ አበባ ትእዛዝ እስከሚጠብቅ እንዲሁም፣ የሎጂስቲክስ በተለይም የመኪና አቅርቦት በማጣቱ፣ መኪኖችን ከእርዳታ ድርጅቶች ተውሶ ወደ ድንበር መንቀሳቀሱን፣ ታማኝ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ገልጾ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መንግስት በማህበራዊ ሚዲያው የደረሰበትን ጫና ተከትሎ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሀዘን አውጆአል። ይሁን እንጅ በዚሁ እለት፣ በሌሎች አገራት እንደሚደረገው ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ጋምቤላ በመሄድ፣ ሟቾቹን በወታደራዊ ስነስርአት በክብር እንዲቀበሩ ያድርግ አያድርግ የታወቀ ነገር የለም። መንግስት ጥቃቱን ተከትሎ የኢትዮጵያን ህዝብም ይቀርታ አልጠየቀም፣ አንዳንድ ወገኖች፣ ድንበር ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ስራው በመሆኑ፣ ለተፈጸመው ጥቃት ግንባር ቀደም ተጠያቂው መንግስት ነው እያሉ ነው። በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉት መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ መንግስትን ሙሉ በሙሉ ተጠያቄ አድረገዋል
መንግስትን በሁለገብ ትግል ለመጣል የሚንቀሳቀሰው አርበኞች ግንቦት7ትም እንዲሁ፣ ተጠያቂው ወያኔ ነው ብሎአል።
አርበኞች ግንቦት 7 ህወሃት ሥልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ በጋምቤላ ክልል ነዋሪ በሆኑ ወገኖቻችን ላይ እንዲህ አይነት የጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ብሎአል። “ በ1996 የህወሃት ልዩ ጦር የተሳተፈበት የዘር ማጥፋት ወንጀል በአኝዋክ ተወላጆች ላይ ተካሂዶ ከ400 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸው መቀጠፋቸውን፣ በክልሉ የሚካሄደውን የመሬት ቅሚያ የተቃወሙ፤ ከአያት ቅድሜ አያቶቻችው የወረሱትንና እትብታቸው ከተቀበረበት በሃይል አንፈናቀልም ያሉ በርካቶች ተገድለዋል ፤ ተደብድበዋል፤ ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል። ከእስርና ከስደት ያመለጡ በርካቶችም በገዛ መሬታቸው ለአዳዲሶቹ ባለሃብቶች ጭሰኛ ሆነዋል አለያም ለጎዳና ተዳዳሪነት “ መዳረጋቸውን አስታውሷል።
“ወያኔ “ማንነታቸው ያልታወቀ” የሚላቸው እነዚህ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው 40 እና 50 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገብተው ምንም መሣሪያ ባልታጠቁ ወገኖቻችን ላይ እንዲህ አይነት ጭፍጨፋ ሲፈጽሙ የአገር ዳር ድንበር ለመጠበቅ የተቀጠረው መከላኪያ ሠራዊት አንዳችም የአጸፋ እርምጃ እንዳይወስድ ካምፕ ውስት ተዘግቶ እንዲቀመጠ የተደረገው ለምንድነው?የጥቃት ፈጻሚዎቹ ማንነትና የመጡበት ቦታ እንኳ በትክክል እንዳይታወቅና ተድበስብሶ እንድቀርስ የተፈለገው በምን ምክንያት ነው? የአገር ዳር ድንበርና የዜጎችን ደህንነት በአስተማማኝ የሚጠብቅ በሌለበት የአካባቢው ህዝብ ከጥንት ጀምሮ እራሱንና ንብረቱን የሚከላከልበት ነፍሰ ወከፍ መሣሪያ እንዲፈታ ማድረግ ለምን አስፈለገ?የሚሉ ጥያቄዎች ከጭፍጨፋው በስተጀርባ የወያኔ እጅ እንዳለበት ማሳያ ናቸው፣ ብሎአል።
“ድንበር ተሻግሮ ጥቃት ፈጸመ የተባለው ታጣቂ ” ጋምቤላ ውስጥ የሚካሄደውን የመሬት ቅርመታ የሚቃወሙትን ለማዳከም ሆን ተብሎ የጋምቤላንና የጎረቤት ሱዳን ዜጎችን ለማጋጨት ከሚጠነስሰው ተንኮል ውጭ ሊሆን አይችልም። በክልሉ የሰፈረው የአገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ ከ208 በላይ ዜጎችን የጨፈጨፉ ታጣቂዎች ከመቶ በላይ ንጹሃን ዜጎችን አግተው በሰላም ወደ መጡበት መመለስ መቻላቸው ለዚህ ዋቢ ምስክር ነው። “ ብሎአል።
አርበኞች ግንቦት 7 በዜጎቻችን ላይ ለደረሰው ለዚህ የጭፍጨፋ ወንጀል ተጠያቂ የሆኑ የወያኔ መሪዎች ህግ ፊት እንዲቀርቡ የጀመረውን ሁለገብ ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል ብሎአል።

No comments:

Post a Comment