Translate

Saturday, September 21, 2013

ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ

ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ
ለህዝብ የሚታየው ፓትሪያርኩ በተገኙበት ነው በየእለቱ ከ3ሺህ ሰው በላይ ቦታውን እየጎበኘ ነው
በአቃቂ ቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል ፓትርያርኩ በተገኙበት ለህዝብ እንዲታይ መግቢያ መንገድ እስኪሰራ ድረስ የተራዘመ ሲሆን፣ በመስቀሉ ላይ የሳይንስ ምርመራ እንደማይፈቀድ ተገለፀ፡፡
ከሶስት ሳምንት በፊት በፍንዳታ ድምፅና በብርሃናማ ቀስተደመና ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል፣ በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 19 ቀን ለህዝብ ይታያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ፓትርያርኩ የሚገኙበት ስነስርዓት ለማዘጋጀት ጊዜው እንደተራዘመ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎች ተናግረዋል፡፡ መስቀሉ ለህዝብ የሚታየው ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በተገኙበት ስነስርዓት መሆን አለበት መባሉን አስተዳዳሪዎች ጠቅሰው፤ መንገዱ ጭቃ ስለሆነ ጠፈፍ ብሎ ለመኪና እስኪስተካከል ድረስ ቀኑ መራዘሙን ገልፀዋል፡፡ ቀኑ ገና እንዳልተወሰነና ለፓትሪያርኩ ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው ያሉት የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች፤ ስነስርዓቱን ህዳር 11 ቀን ለማካሄድ እንደታሰበ ጠቁመዋል፡፡
ከአዲስ አበባና በአቅራቢያዋ ከሚገኙ አካባቢዎች በየእለቱ ከ3ሺ በላይ ሰዎች ቦታውን እየጎበኙ መሆናቸውን የገለፁት የቤተክርስቲያኗ መጋቢ ሃዲስ ፍሰሃ፤ እኛም በየእለቱ ከ15 ጊዜ በላይ ስለ ተከሰተው ተዓምር ገለፃ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ መስቀሉ ባረፈበት ሳር ላይ እንዲሁም ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ የተነሱ ፎቶዎችን የያዘ ካርድ ታትሞ ለምዕመናን በ10 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በፎቶግራፍ ላይ የሚታየው መስቀል በሰው የተሰራ የዕደ ጥበብ ውጤት እንደሚመስል በመጥቀስ ከሰማይ ወረደ መባሉን የሚጠረጥሩ መኖራቸውን በተመለከተ መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፣ እውነቱን የሚያውቀው ፈጣሪ ነው ብለዋል፡፡
በምድራችን የተሰራ የሚመስል መስቀል ከሰማይ ሊወርድ አይችልም የምንል ከሆነ፣ በምድራችን የምናረባው አይነት በግ ለአብርሃም ከሰማይ ወርዶለታል የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል መጠራጠር ይሆናል ብለዋል መጋቢ ሃዲስ ፍስሃ፡፡ የመስቀሉን ስሪት እንዲሁም መስቀሉ አረፈበት የተባለውን ሳርና አፈር ለመመርመር ሃሳብ ተነስቶ እንደሆነ ተጠይቀው መጋቢ ሃዲስ ሲመልሱ፤ “ይህ መስቀል የቤተክርስቲያኒቱ የክብር መገለጫ ነው” በማለት ተቃውመዋል፡፡
እስካሁን በስፍራው የተፈፀመውን ተአምር ሰምተው የሚያደንቁ እንጂ በመስቀሉና በቦታው ላይ እንመራመራለን የሚሉ ምሁራን አላጋጠሙኝም ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ “እንዲህ ያለ ጥያቄ ያላቸውም ካሉም፣ የማይሞከር ነው” ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ቦታውን እንፈትሻለን፣ የወረደውን መስቀል እንመረምራለን ለሚሉ የሳይንስ ባለሙያዎች ፈፅሞ አይፈቀድም ብለዋል፡፡ መስቀሉ ከሰማይ ከመውረዱ አስቀድሞ ራዕይ ታይቶኛል የሚል ሰው እስካሁን አላጋጠመን ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ያቋቋሙት አባት ግን፣ ቦታው የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ እንደሚሆን በራዕይ እንደታያቸው ተናግረው ነበር ብለዋል፡፡
addis admas

No comments:

Post a Comment