Translate

Monday, September 30, 2013

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ይህንን የማፊያ ቡድን በማፍረስ ታሪክ ይስሩ! በግርማ ሠይፉ ማሩ


ግርማ ሠይፉ ማሩ
በ2005 ዓ.ም የምክር ቤት ዘመን መጨረሻ ላይ የደህንነት መስሪያ ቤቱን በሚኒስትር ደረጃ ለማዋቀር የሚረዳ አንድ አዋጅ ለምክር ቤት ቀርቦ ፀድቆዋል፡፡ ይህ አዋጅ ሲፀድቅ ከነቅሬታዬ ያለኝ ድጋፍ መስጠቴ ይታወቃል፣ ለዚህ አዋጅ ድጋፍ መስጠት የፈለኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከበረሃ ይዘውት የመጡት ልዩ ልዩ አፋኝ ቡድን ስለማይኖራቸው እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩትን አፋኝ ቡድንች ወደ አንድ መዋቅር በማጠቃለል ተጠሪነቱ ከተለያዩ መዋቅሮችና ግለሰቦች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ወደ ተገቢው ማለት ነው) ቁጥጥር በማስገባት ለዜጎች ስጋት ሳይሆን ለዜጎች እና ለሀገር ደህንነት የሚስራ ተቋም ይሆናል በሚል ተስፋ ነው፡፡ ይህ ተስፋዬም ዝም ብሎ ሳይሆን በአዋጁ አንቀፅ 3 “ይህ አዋጅ በመላው ሀገሪቱ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግስታት ደረጃ ሌላ የመረጃና ደህንነት ተቋም  ማቋቋም አይቻልም” የሚል ድንጋጌ በመያዙ ነው፡፡ በመስከረም 19 እሁድ ዕለት አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ “በሰላም” ከተጠናቀቀ በኋላ እጅግ አሰገራሚ የሆነ ተግባር አጋጥሞናል፡፡ ተስፋዬንም ስለአጨለመብኝ ይህን ጉዳይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያውቁትና የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎቱ ኃላፊውን ጠርተው ማብራሪያ እንዲጠይቁ መነሻ ለመስጠት ነው፡፡
የፓርቲያችን ወጣቶች በሰልፉ ላይ ወጣቶችን፣ ሙስሊሙን፤ ክርስቲያኑን፣ ሴቶችን እንዲሁም በግፍ የታሰሩትን ዜጎች በተመሳሌነት ለማሳየት እጃቸውን እና እግራቸውን በሰንሰለት አስረው ከፊት ሆነው ሰልፍ ላይ ሲታዩ ነበር፡፡ ማንነታቸው ያልታወቀ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ከነዚህ ወጣቶች አንዱን ጎትተው ከታክሲ በማውረድ ወደ መኪና ውስጥ ለመጫና ሲሉ በአካባቢው የነበሩ የአንድነት ወጣቶች ደርሰው መውሰድ አትችሉም በሚል ግርግር ሲፈጠር በቦታው ደረስኩ፡፡ በቦታው ደርሼ ይህን የሚፈፅሙትን ሰዎች መታወቂያ እንዲያሳዩኝ ሰጠይቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በአካባቢው የነበሩትን ፖሊሶች (ባለ ኮከብ ማዕረግ ያለቸው ጭምር) አስጠርቼ መታወቂያ እንዲያሰዩን እንዲያደርጉ ቢሞከርም እነዚህን ጉልበተኞች መታወቂያ ሊጠይቅ የሚችል ሞራል ያለው ፖሊስ አጣን፤ ህዝብ በተሰበሰበበት ፖሊሶችን እንዴት እንደሚያደርጓቸው ማየት በእውነት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከፖሊሶቹ አንዱ ጠርቶኝ እነዚህ እኮ ከእኛ አቅም በላይ ናቸው ሲለኝ በቅርቡ በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርቦ ምስክርነት የሰጠው የፖሊስ መኮንን ትዝ ብሎኝ የመንግስታችን ባሕሪ አሁንም ለውጥ እያሳየ ያለመሆኑ እና ፊት ለፊት ከምናያቸው ተቋሞች ጀርባ ሌላ ስልጣን እንዳለ ፍንትው ብሎ ታየኝ፡፡ የሚገርመው በዚያው ዕለት እኔን እያወቁኝ መኪናዬን በግዳጅ አሰቁመው መንጃ ፈቃድ፣ በሚያስገርም ሁኔታ የመኪና ባለቤትነት ደብተር፣ ሰለቦሎ ዕድሳት የማያገባቸውን ሁሉ እየጠየቁ ታዘን ነው በሚል ከገዢው ፓርቲ ጋር በመተባበር ስልፉ እንዳይሳካ  ሲሰሩ የነበሩ ፖሊሶች በሰዓታት ልዩነት መታዊቂያ ያለመጠየቅ ስልጣን ያላቸው ልዩ ዜጎች እንዳሉ አስገንዝበውናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህን ሰዎች ማንነት ማወቅ ከፈለጉ ፎቶና ቪዲዮ በእጃችን እንደሚገኝ ላረጋግጥሎት እችላለሁ፡፡ ሲቪል የለበሱ አፋኞችን ሳይሆን ዩኒፎርም የለበሱ ፖሊሶችንም ቢሆን መታወቂያ መጠየቅና ከወሮበላ ዱርዬ እራሳችን መጠበቅ መብታቸን እንደሆነ ግን ይታወቃል፡፡
በነገራችን ላይ ሰልፉ ከተጠናቀቀ በኋላ እነዚሁ ማፊያ ቡድኖች ፎቶ ይዘው ወጣቶችን በየመንገዱ እያስቆሙ እነዚህን ወጣቶች ማደን እንደያዙ ያረጋገጥን ሲሆን በዕለቱ ለደህንነታቸው ሲባል በአጀብ ወደ ቤታቸው ለማድረስ የቻልን ቢሆንም አሁንም እነዚህ ወጣቶች በምንም ዓይነት ሁኔታ ጉዳት ቢደርስባቸው ሌላ ምክንያት የሌለ እና ይህ የተደራጀ የማፊያ ቡድን የሚሰራው ስራ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያውቁት እፈልጋለሁ፡፡ በማፊያዎቹ በመታደን ላይ ያሉት ወጣቶች ስንታየሁ ቸኮል፣ ዳንኤል ፈይሣ፣ ፋናዬ ወ/ጊዮርጊስ፣ ኤፍሬም ሰለሞን እንዲሁም አበበ ቁምላቸሁ የሚባሉ መሆናቸው እርሶም የዓለም ህብረተሰብም እንዲያውቀት መግለፅ ተገቢ መስሎ ታይቶኛል፡፡ በአደባባዩ ላይ ሲያሳዩ የነበረውም ምስል ይህንን ይመስላል፡፡ ወንጀላቸው ይህ ከሆነ ማለት ነው፡፡


የሰልፉ መሪዎቸ በተምሳሌታዊ አለባበስና ሁኔታ (ከስር ተቀምጠው የሚታዩት  ወጣቶች በደህንነት  ተብዬዎች የሚሳደዱት ናቸው

በሀገራችን የህግ ስርዓት እንዲሰፍን የምናደርገው ጥረት የሚሳካው እንደዚህ ዓይነት አፋኝ የማፊያ ቡድኖች በማሰማራት አይደለም፡፡ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤትም እንዲህ ዓይነት የማፊያ ስራ እንዲስራ ኃላፊነት አልተሰጠውም፡፡ የተሰጡት ኃላፊነቶችና ተግባራት ከባድ በሀገር ላይ የተቃጡ ወንጀሎችን መከታተልና መረጃ መሰብሰብ ይህንንም በህግ አግባብ እንዲፈፅም ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በደርግ የመጀመሪያ ዘመን ተሰፋፍቶ የነበረውን በየቪላ ቤት እና በየመንደሩ አፍነው ወስደው ማሰቃየት በኢትዮጵያ ምድር እንዲቆም የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት አለቦዎት፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስችል ስልጣን ከሌለዎት ለሰብዓዊ ክብር የሚስጠውን ክርስትና እምነት እየተከተሉ ይህንን ስልጣን መያዝ ትርጉም ስለሌለው ለእኛም ተሰፋ ስለማይሆኑን ስልጣን በመልቀቅ ሌላ ታሪክ መስራት ይችላሉ፡፡ ምርጫው የእርሶ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሸንጉሊት ናቸው ከጀርባ የሚያሽከረክር ሌላ ኃይል አለ ለሚሉት ምስክርነት እየሰጡ ነው ብዬ ለመውሰድ እገደዳለሁ፡፡
ይህ በአዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ መዲና የደረሰውን መነሻ አድርጌ የፃፍኩት ቢሆንም በክልልም የፀጥት ክፍል የሚባል ማንነታቸው የማይታወቅ አሳሪዎች አሉ፡፡ የእነዚህን ልዩ የሚያደርገው እስረኛ በአደራ ፖሊስ ጣቢያ ስለሚያስቀምጡ ነው፡፡ ፖሊሶች በአደራ የገቡት መፍታትም ሆነ ፍርድ ቤት ማቅረብ አይችሉም፡፡ በክልል ለማስቃያ የሚሆን የቪላ ቤት እጥረት ስለአለ ሊሆን ይችላል፡፡ ከፖሊስ የበለጠ ስልጣን ግን እንዳላቸው በእርግጠኝነት እንዲያውቁት እፈልጋለሁ፡፡ አዋጁ በፍጥነት በስራ ላይ ውሎ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዋጁ የተሰጡትን ሀገራዊ ተግባር እንዲሰራ እንዲያደርጉ አደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የአንድነት ወጣቶች እነዚህን የማፊያ ቡድኖች በአደባባይ ህግን መሰረት አድርገው ሲያጋልጡዋቸው መመልከት ከምንም በላይ ኩራት የሚሰጥ መሆኑን መግልፅ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁላችንም በቃ ልንል ይገባል፡፡ ታክሲ ውስጥ ያለ ተሳፋሪ ሲቢል ለባሾች እንዲህ ሲያደርጉ ማንነታቸውን መጠየቅ መብቱ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤቱ እነዚህን ቀሽሞች እንደ ሰውር ተከታታይ አሰማርቶ ከሆነ ከአሁን በኋላ እነሱ የሚስጥር ስራ ለመስራት ብቃት የሌላቸው መሆኑ ተገንዝቦ ለሆዳቸው መሙያ የሚሆን ሌላ ስራ እንዲፈልጉ ቢነግራቸው ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን የምልበት ምክንያት በልጅነታችን የማሞ ውድነህን የስለላ መፅሐፍት ለአነበብን እንዲሁም አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የስለላ ፊልም ለሚመለከቱ ወጣቶች የሚመጥን ስአአልሆነ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የሚፈፅሙት ተግባር ተራ የዱርዬ ስራ ስለሆነ ነው፡፡ እኔ ለእንደዚህ ዓይነት ተቋም ላለኝ ክብር እንደዚህ ዓይነት ዱርዬዎች አይመጥኑትም፡፡ ይህ መስሪያ ቤት በእርግጥ የተጣለበትን ኃላፊነት የመወጣት ፍላጎት ካለው (ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግዴታ አለባቸው) መስሪያ ቤቱ በባለሞያ አንጂ በተራ ጆሮ ጠቢና የመንደር ወሬ ለቃሚ መሞላት የለበትም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር 2006 ዓ.ም ተግባራዊ ስራ ለመስራት የሚችሉበት ዘመን እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡ በይፋም ባይሆን በልቦ እና በተግባር የግል አሻራዎን በዚህች ሀገር ላይ ለማኖር መልካም አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን እና የጠላትነት ሰሜት የሚወገድበትን ተግባር በመስራት ነው፡፡ መልካም አዲሰ ዓመት!!!!
ግርማ ሠይፉ ማሩ

No comments:

Post a Comment