Translate

Friday, May 24, 2013

ሰበር ዜና፣ የሰማያዊ ፓርቲ የግንቦት 17ቱን ሰልፍ ወደ ግንቦት 25 አስተላለፈ


ECADF – የሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ሲል ጠርቶት የነበረውን የሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ ለአዲስ አበባ አስተዳደር በደብዳቤ ለማሳወቅ በሞከረበት ወቅት የከተማው አስተዳደር ሀላፊዎች ሆን ብለው ደብዳቤውን አንቀበልም በማለታቸው የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የአይን እማኞች በተገኙበት ደብዳቤውን በአንዱ የከተማው አስተዳደር ቢሮ ውስጥ እጠረጴዛ ላይ አኑረው እንደወጡና በህጉ መሰረት የሰላማዊ ሰልፉን ከጠራው አካል በኩል መደረግ ያለበት ሁሉ ስለተደረገ ፓርቲው በያዘው ፕሮግራም መሰረት ሰልፉን ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት እንደሚያካሂድ አሳውቆ ነበር።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰልፉን ፈቀደ
የሰማያዊ ፓርቲ ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ለአዲስ አበባ አስተዳደር በደብዳቤ ለማሳወቅ በሞከረበት ወቅት ደብዳቤውን ለመቀበል አሻፈረኝ ብለው ሲያንገራብዱ የዋሉት የከተማው አስተዳደር ሀላፊዎች ዘግይተው የሰማያዊ ፓርቲ ባሳወቀው ቀንና ቦታ ሰልፉን ሊያካሂድ እንደሚችል ለፓርቲው በቀጥታ በተጻፈ ደብዳቤ አሳወቁ (እኛም የዚህን ደብዳቤ መልዕክት በሰበር ዜና ይዘን ወጥተን ነበር)። የሰማያዊ ፓርቲም ይህንኑ ደብዳቤ እንደተለመደው በፌስ-ቡክ ገጹ ላይ አትሞታል። (የደብዳቤውን ይዘት ለመመልከት እዚህ ይጫኑ።)

የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን አስተላለፈ
ብዙም ሳይቆይ የሰማያዊ ፓርቲ ለግንቦት 17 ጠርቶት የነበረውን ሰልፍ ወደ ግንቦት 25 ማስተላለፉን አስታወቀ። ይህን አስመልክቶ የሰማያዊ ፓርቲ አጭር መልዕክት እንዲህ ይነበባል፣
ከአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ በዛሬው እለት በተሰጠ ገለጻ መንግስት 50ኛውን የአፍሪካ ህብረት በአል ለማክበር በአሁኑ ግዜ ከፍተኛ የጸጥታ ሰራተኞች መድቦ በመስራት ላይ በመሆኑ ከፓርቲው የቀረበልንን ጥያቄ ለማስተናገድ የጸጥታ ሰራተኞች እጥረት አለብን ብለዋል ፡፡ይህም በመሆኑ የተቃውሞ ሰልፉ ቀንና ቦታ እንዲለወጥ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም የዚህን ጥያቄ ተገቢነት ከሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ስነስርአት አዋጅ ቁጥር 3/1983 አንጻር በመመርመር ተገቢ ሁኖ ስላገኘው የተቃውሞ ሰልፉ ግንቦት 25/ 2005 ዓ.ም. በኢትዮ-ኩባ አደባባይ ከጠዋቱ 4 ሰአት- 8 ሰአት እንዲሆን በመወሰን ከመንግስት የእውቅና ማሳወቂያ ደብዳቤውን ተቀብሏል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ማሳወቂያ ቅጽ ላይ በሰፈረው መረጃ መሰረት የተላለፈው የሰላማዊ ሰልፍ እሁድ ግንቦት 25፣ 2005 ከጠዋቱ 4 ሰዓት መነሻውን ግንፊሌ ከሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት አድርጎ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ እና ቸርቸር ጎዳናን ይዞ መድረሻውን ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ያደርጋል።
semayawi party protest call june

No comments:

Post a Comment