Translate

Tuesday, May 21, 2013

ወ/ሮ ትዕግስት ከታገቱበት ሲና ተለቀቁ!!


በዶላር ወደ ሲና፤ በዶላር ወደ ሸገራብ

tigist gebre


የሱዳን፣ የኤርትራና የግብጽ ዜግነት ባላቸው ራሻይዳዎች ታፍነው ወደ ሲና በረሃ የተወሰዱት ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ ካይሮ መግባታቸው ታወቀ። ወ/ሮ ትዕግስት ቅዳሜ ረፋዱ ላይ ካይሮ የገቡት አጋቾቹ እንዲሰጣቸው ከጠየቁት 25 ሺህ ዶላር በድርድር 15 ሺህ ዶላር ተከፍሏቸው ነው።

ዜናውን በሰሙ ማግስት “የወ/ሮ ትግስት የርዳታ እጆች” በማለት ተሰባስበው የነፍስ አድን ዘመቻውን ከጀመሩት መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሰብለ ደምሴ በተለይ ለጎልጉል እንደተናገሩት ወ/ሮ ትዕግስት ከአሰቃቂው የሲና በረሃ ወጥተው ካይሮ የገቡት ከአራት ወራት በኋላ ነው።
አጋቾቹ ወ/ሮ ትዕግስትን በ10 ሺህ ዶላር እንደገዙ በመግለጽ 25 ሺህ ብር ካልተከፈላቸው እንደማይለቁና የሰውነት ክፍላቸውን በመሸጥ ያወጡትን ወጪ እንደሚሸፍኑ ይደራደሩ እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ገነት “አስቀድመን 10 ሺህ ዶላር ከፈልን። ቀሪውን 5 ሺህ ዶላር ወ/ሮ ትዕግስት አገር ቤት ያሏቸው ከብቶች ተሽጠውና ከያለበት ተለቃቅሞ እንደሚከፈል በመግለጽ ተደራድረን ከተስማማን በኋላ ክፍያውን ፈጸምን” ብለዋል።
ሱዳን ሸገራብ በሚባለው ሰፊ የስደተኞች ጣቢያ ከባለቤታቸውና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ ጥር 22 ቀን 2005 ዓ ም ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም በካምፕ ውስጥ ከሚገኘው ቤታቸው  በግምት ሰላሳ ሜትር ሳይርቁ ራሻይዳዎች አፍነዋቸው እንደወሰዷቸው ጎልጉል መዘገቡ ይታወሳል
ወ/ሮ ሰብለ ደምሴ፣ ወ/ሮ አዜብ ሮባና ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ጸጋዬ ሰብዓዊነት ረፍት ነስቷቸው ባካሄዱት ዘመቻ ከተለያዩ ቤተክርስቲያናት፣ በጉዳዩ ሃዘን ከገባቸው ወገኖች፣ በተሰበሰበ ገንዘብ ወ/ሮ ትዕግስት ህይወታቸው ሳያልፍ ከዕገታው ነጻ መሆናቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረ ያስረዱት ወ/ሮ ሰብለ፣ “ነፍስ ለማዳን በተደረገው ጥሪ የተባበሩ ሚዲያዎች፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ሁሉም ዓይነት የህብረተሰብ ክፍል በህብረታችን ስም ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን። ወ/ሮ ትዕግስትና ባለቤታቸውን አግኝተናል። ሃዘናቸው በወገኖቻቸው ርዳታ ተለውጦ የደስታ እንባ አንብተዋል። እኛም ተደስተናል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ግን” አሉ ወ/ሮ ሰብለ “ግን ብዙ ወገኖች በተመሳሳይ ችግር ላይ እንዳሉ ስናስብ አሁንም እረፍት የለንም። በምንኖርበት ሁሉ በተለያዩ መንገዶች ድርጊቱ የሚፈጸምበት ቦታ ላይ ያሉ ባለስልጣኖች እንዲህ ያለውን አስነዋሪና ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት እንዲያስቆሙ ትግላችንን መቀጠል አለብን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ወ/ሮ ትዕግስት አሁን ህክምና እየተደረገላቸው ስለሆኑ ሲያገግሙ ለሌሎች ትምህርት ይሆን ዘንድ፣ በቀጣይ በትብብር ድምጻችንን ለማሰማት የሚያተጋንን ቁምነገር እንዲካፍሉ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ወ/ሮ ትዕግስት ከሲና በረሃ መልስ ያጋጠማቸውንና በትክክል የተመለከቱትን ለወገኖቻቸው እንደሚያካፍሉ የገለጹት ወ/ሮ ሰብለ ህብረታቸው ዝርዝር ጉዳይ የያዘ የምስጋና መልዕክት አዘጋጅቶ እንደሚያሰራጭ ገልጸዋል።
አፋኞቹ ራሻይዳዎች ናቸው። ራሻይዳ የቆዳቸው ቀለም ጠየም ያለ የሱዳን፣ የኤርትራና የግብጽ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ቀደም ሲል ከሶስት እስከ አራት ሺህ ዶላር እየተቀበሉ በደላላ አማካይነት ስደተኞችን በሲና በረሃ ወደ ግብጽ ያሻግሩ ነበር። እስራኤል በሲና በረሃ ወደ ድንበሯን ዘልቀው የሚገቡበትን የስውር መንገድ ስትዘጋው ራሻይዳዎቹ የገቢ ምንጫቸው ተዘጋ። ገንዘብ የለመዱት ወንበዴዎች የንግዱን ስልት ቀየሩና ሰው ማፈን ጀመሩ። አፈናውንም ከሚያካሂዱባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ድንበር አቋርጠው የሚጓዙትን አድፍጠው በመያዝ፣ ስደተኞችን ከስደተኛ ካምፕ አፍኖ በመውሰድ፣ ከሌሎች አፋኞች ስደተኞችን በአነስተኛ ገንዘብ በመግዛት እንደሆነ በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።
በደላሎች እስራኤል ለመግባት ጉዞ ከጀመሩት ወገኖች መካከል ስንቶቹ በሲና በረሃ ሟምተው እንደቀሩ መረጃ የለም። ከሱዳን ምድር ወጥተው ግብጽ በመሻገር ሲና በረሃ እንደ ከብት ተበልተው የሚጣሉት ወገኖች ስቃይ ለሰሚው ግራ ነው። ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ መከራ ከቀን ቀን እየተባባሰ ነው። አሰቃቂ ዜናዎች መስማት ለየእለቱ የሚያስፈልገን መሰረታዊ ጉዳይ እስኪመስል ተለመዷል። ይህ አሳሳቢ ጉዳይ “እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል” የሚለው የሁሉም ወገን “ዳር ቋሚዎች” ጥያቄ ነው፡፡
የ12 እና የ 1 ዓመት ከስምንት ወር ልጅ ያላቸው ወ/ሮ ትዕግስት ታፍነው በነበረበት ወቅት ባለቤታቸውን በስልክ እንዲያነጋግሩ ይደረጋሉ። ባለቤታቸውም ይሰቃያሉ። እግራቸውና እግራቸው መካከል ብረት ተደርጎባቸዋል። ይደበደባሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው ባለቤታቸው የተጠየቁትን ገንዘብ ባስቸኳይ እንዲከፍሉላቸው ለማስጨነቅ ነው። ባለቤታቸው እንደተናገሩት “ምንም አማራጭ የለኝም። የተጠየቀውን ገንዘብ ማግኘት አልችልም። ልጆቼ ወደፊት ሲጠይቁኝ ለምኜ አቃተኝ ለማለት እየለመንኩ ነው። ባለቤቴ ግን ምንም ማድረግ እንደማልችል ታውቃለች፤ ባይሳካልኝና ነጻ ባላወጣት አትቀየመኝም… ” በማለት ለቪኦኤ መናገራቸው ይታወሳል።
የ12 ዓመቷ ልጃቸው ሱፊ “እኛንም እንዳይወስዱን ስለምንፈራ ከቤት አንወጣም” በማለት  ከቪኦኤ ለቀረበላት ጥያቄ ልብ የሚነካ shagrabመልስ ሰጥታ ነበር፡፡ “እናቴን አፈኗት” ያለችው ህጻን የበርካታዎችን ልብ እረፍት ነስታ ነበር። ወ/ሮ ሰብለ “እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሲቃ የተሞላበት ጉዳይ እየሰማን በውጪ ያለን ወገኖች እንዴት 30 ሺህ ዶላር (በወቅቱ የተጠየቀው) ማዋጣት አቃተን” ሲሉ በመገረም ጠይቀው ነበር። ወ/ሮ ትዕግስት ገብሬ ቢተርፉ ለሌሎች በማስተማር ተመሳሳይ ችግር በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እንዳይደርስ የማድረግ ስራ ይሰራል የሚል እምነት እንዳላቸው ወ/ሮ ሰብለ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ወ/ሮ ትዕግስት ከካይሮ ወደ ነበሩበት ሰፊ የስደተኞች ካምፕ ሸገራብ ይመለሳሉ። መቼ እንደ ሆነ ባይገለጽም ከታፈኑበት ምድር፣ በስደት ከሚኖሩበት ሸገራብ ቤተሰቦቻቸውን ተቀላቅለው ኑሮን ይቀጥላሉ ወይስ … ? (Photo: BBC)

No comments:

Post a Comment