Translate

Monday, September 25, 2017

የህወሃት አጀንዳ + የዘር ፖለቲካ + የሜንጫ ፖለቲካ – መጨረሻው ተያይዞ …

የኢትዮጵያ ህወሓት ሰራሹ “ፌደራሊዝም” ወደ ተፈራው ቀውስ እየተንደረደረ መሆኑንን የሚያሳዩ የዜና ዘገባዎች የተሰሙት ገና ከጅምሩ ነበር። በርካታ ባለሙያዎችና የተቀናቃኝ ፖለቲካ መሪዎች በተደጋጋሚ ስጋታቸውን ቢገልጹም ተቀባይነት ሊያገኙ ባለመቻላቸው የጎሣና የብሄርተኛነት በሽታ እያደር ኢትዮጵያን እየበላት አሁን ያለችበት ደረጃ አድርሷታል።

ችግሩ አለመስማትና አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ዓላማ ያለው፣ በቅጥረኝነት አገሪቱን የማፈራረስ ተልዕኮ የማሳካት ጉዳይ በመሆኑ የመከሩ፣ የዘከሩ፣ ያስጠነቀቁ፣ ስጋታቸውን አደባባይ ያወጡ ዜጎች ወንድ ሴት ሳይባል ተፈጅተዋል። አገሪቱ ምትክ የሌላቸውን ልጆቿን እንድትከስር ተደርጋለች። ግድያውና አፈናው ብቻ ሳይሆን መላውን የአገሪቱን ህዝብ እርስ በእርስ ጎሣና ጎጥ ለይቶ እንዲናከስ እየተወተወተና እየተገፋ አገሪቱ ቆዳዋ በልጆቿ ደም እንዲለወስ ሆኗል።
ዛሬ ከየአቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎች፣ የዜና ዘገባዎችና ገለልተኛ የሚባሉ ሪፖርቶች እንዲሁም የራሱ የችግሩ ባለቤት ሚዲያ የሚያሰራጩት ሁሉ እረፍት የሚነሳ፣ እንቅልፍ የሚከለክል፣ ጉዞው ወደ “ሚፈለገው” መድረሻው መቃረቡን የሚያመላክት ነው። አገሪቱ በቂም ነፍራ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የደም ጠረን እንደ ከርቤ የሆነላቸው፣ ሃሳባቸውና ሂሳባቸው የሰመረላቸው ሆኖ የሚሰማቸው ጥቂቶች፣ የደም ጠኔያቸውን በጥጋባቸው ልክ እየተጋቱ በማሽካካት ላይ ይገኛሉ።
አሁን በኢትዮጵያ ዝምታ የሚታየውና “ሰላም ሰፍኖበታል” የሚባለው የትግራይ ክልል ብቻ ቢሆንም ከአማራ ክልል ጋር ያለው የድንበር፣ የመሬት ቅሚያና የማንነት ጥያቄ አድሮም ቢሆን ችግር እንደሚሆን ስለጉዳዩ እናውቃለን የሚሉ እየገለጹ ነው፤ እያስጠነቀቁ ነው። በተለይም አዲስ ተሰርቶ አየር ላይ የዋለው የኢትዮጵያ ካርታና የትግራይ ይዞታ፣ የአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች በትግራይ ክልል ውስጥ እንዳሉ ተደርጎ የሚሰጠው ትምህርት እጅግ አነጋጋሪ፣ ምክንያት ያልቀረበበት፣ ዓላማው ምን እንደሆነ በይፋ ማብራሪያ ያልተሰጠበት፣ ለሰሚውና ለተመልካቹ ሁሉ ግልጽ ምልክት እየሆነ ነው። “ለምኑ?” የሚሉ ካሉ “አይቼሽ ነው ባይኔ ወይስ በቴሌቪዥን” የሚለውን ሙዚቃ መስማቱ በቂ ነው።
ድንገት ሞተሩ የጠፋበት መለስ “ታላቅ ነበርን፤ ታላቅ እንሆናለን” በማለት “እንኳን ከናንተ ተፈጠርኩ” ለሚለው “ምርጥ ህዝብ” እንደተናገረው፣ ትግራይን ወሽመጥ አበጅቶ ባለድንበርና ባለ ሰፊ የእርሻ መሬት ባለቤት ለማድረግ አማራ ክልልን ማንነቱን፣ መሬቱን፣ ስብዕናውን፣ ታሪኩን፣ ተራራውን፣ ወንዙን … የቀረ ነገር የለም ሁሉንም ዘርፈው ወደ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ተለጥጠዋል። ድንበር አበጅተው ከሱዳን ጋር እንደ አገር እየተደራደሩና ለነገ የማይነቀል የመሰላቸውን ቀውስ ልክ እንደ ጌቶቻቸው እየቀበሩ ነው።
ሲጦዝና ሲላላ ቆይቶ ወደ ብረት ፍልሚያ የዞረው ይኸው የአማራ ክልል ችግር ዱር ቤቴ ባሉትና በመንግስት በኩል የተለያዩ የድል ዜናዎች ቢቀርቡበትም መጨረሻው አለየለትም። ገለልተኛ ወገኖች እንደሚሉት የአማራ ክልልና ህወሃት/ኢህአዴግ ተፋተዋል። ራሱ ብአዴንም ተቧድኖ ከሁለት አልሆን ብሎ በውዳቂነት ተመድቦ በኪሳራ እየዳፈቀ ነው። በበታች አመራሮቹ ዘንድ የመንሸራተትና የመክዳት አዝማሚያ እየታየ ነው። ፍጹም የተነጠሉም አሉ። ይህ በአማራ ክልል ጥፍጥፍ ፓርቲ ዘንድ ላይ ያለው ችግር መላ ሳይበጅለት በያዘው የፖለቲካ አቋምና፣ በተቋቋመበት መርህ መሰረት መቀጠለ አልቻለም። ድርጅቱ ነባር አባላቱን እያባረረ አዲስ ቢተካም ወዲያውኑ በአመለካከከት “ጥራት” መዛሉን ከአገዛዙ የሚወጡ መረጃዎች ራሳቸው የሚያረጋግጡት እውነት ሆኗል
በመፈቃቀር ላይ የተመሰረት አንድነት” በሚል ኩልና ቀለም እየተቀባ ሲራገብ የነበረው የጎሣ ፖለቲካ፣ መለስ የቀባው የቁጩ ኮስሞቲክስ ታጥቦ ዛሬ ጎሰኝነት በየአቅጣጫው ደም እያራጨ ነው። ደም እያቃባ ነው። ቂምና ጥላቻን እያዘነበ ነው። ቀደም ሲል በተለይም ምስኪን የአማራ ክልል ተወላጆች ተመረጠው እንደ ባዕድ በግፍ ከኖሩበት ቀዬና ካፈሩት ንብረት እየተነጠሉ ተጣሉ። ይኸው ኮስሞቲክሱ የተራገፈበት የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ቀመር እያደር ብሶበት ህይወት እየበላ ነው። ምንም የማያውቁ ህጻናት አገር ይመራሉ በሚባሉ ሰዎች ከመማሪያ ክፍል ውስጥ ሆነው ፊደል እየቆጠሩ “ከክልላችን ውጣ” የሚል ደብዳቤ እንዲታደላቸው መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ሲጀመር መባረርና መፈናቀል “የመዝናኛ ዜና” ነበር። አንዳንዶች የመፈናቀልን ዜናና ሰለባዎቹን እያዩ በድል አድራጊነት ስሜት ያሽቃብጡበትም ነበር። የዛኔ መቆሚያ ያልተበጀለት ይህ ችግር በጎንደር የትግራይ ተወላጆች ላይ ሲደርስ “ካሳ” ተጠየቀበት። እንመራዋለን ለሚሉት ህዝብ ደንታ የሌላቸው የግዢ ፖለቲከኞችና ፓርቲያቸው “ካሳ” ቆጣሪ፣ የራሱን ወገኖች አሳሪ፣ የራሱን ድንበር አስረካቢ፣ በራሱ መጪ ትውልድ ላይ ጋላቢ እየሆኑ ከህዝብ ተለዩ፣ እያደር ተተፉ። ከመተፋትም በላይ … ይህ የውስጡ ነው።
ትናንት “አማራ ውጣ” እያሉ ሲያንቧርቁ የነበሩ “የሜንጫ” ፖለቲከኞች፣ ትናንት “ነፈጠኛ ሃ በኡ” ሲሉ የነበሩ የእንግዴ ልጅ ፖለቲከኞች፣ ትናንት ሽማግሌዎች፣ ህጻናት፣ ሴቶች እድሜ ልካቸውን ከኖሩበት ቀዬ እየተዘረፉና እየተደበደቡ ሲባረሩ፣ ባዕድ ሲባሉ ሲስቁና የድል አድራጊነት ስሜት ደማቸውን ሲያንተከትከው የነበሩ፣ ትናንት ስለመፈናቀል ክፋት ሲነገራቸው “ጥሪ አይቀበልም” በሚል ጆሯቸውን የጠረቀሙ፣ ዛሬ የመፈናቀልን ጣጣና እርግማን እየሰበኩ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በየትኛውም መመዘኛ ከሶማሌ የተፈናቀሉ ውድ ዜጎችን ከሌላው ክልል ከተፈናቀሉ ውድ ዜጎች ማነጻጸር አይፈልግም፤ ሕዝብ አይነጻጸርም። አላማውም አይደለም። ወደ ጉዳያችን ስመለስ የኛ ዋንኛ ዓላማ፣ ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ በግድ ጥላቻን እየጋቱ ለሚያጫርሱት “የመከኑ ፖለቲከኞችን” አካሄድ ከህወሓት ባልተናነሰ ሊወነጀሉ እንደሚገባ ለማመልከት ነው።
አንዲት እናት ሶስት ልጃቸውን ጥለው እቅፋቸው ላይ ያለችውን ይዘው ሽሽት ገቡ። የተጫኑበት የጭነት መኪና የተኩስ እሩምታ ሲወርደበት በእግር መሄድ ግድ ሆነ። ከረዥም ጉዞ በኋላ ከሶማሌ ክልል ወጥተው “ኦሮሚያ ክልል” ሲገቡ የታቀፉት ልጅ በህይወት የለም። ይህ በማህበራዊ ገጾች ይፋ የሆነና በምስል የተደገፈ ሃቅ ነው። ይህ “ለገጀራ” አምላኪ ፖለቲከኞች የድላቸው ፍሬ ነው፤ የስብከታቸውና የቅስቀሳቸው ሁሉ ውጤት ነው። ለጉዳዩ ዋና አራማጅና በዓላማ ለሚንቀሳቀሰው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) መሪዎች በትክክለኛው የማባላት ፖለቲካ ላይ መሆናቸውን የሚያረጋገጡበት የመኖራቸው ዋስትና ነው። የትግራይ ህዝብ ይህንን ጉዳይ እንዴት እንደሚያየው ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መረጃ የለውም። ራሱን ከዚህ አይነቱ የወንበዴዎች ቡድን እንዲያርቅ በተደጋጋሚ መክረናል።
በአወዳይ በአሰቃቂ ሁኔታ የተሰየፉት የሶማሌ ክልል ወገኖች ደምና ስቃይ ምን ዓይነት ደስታ እንደሚያጎናጽፍ ለእኛም ሆነ፣ ኅሊና ላላቸው ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው። ይህንን ድርጊት ሁሉም በያለበት ሲያወግዝ የትግራይ ምሁራንና ነዋሪዎች ጸጥ ማለታቸው ደግሞ ከሁሉም በላይ አስደንጋጭ ይሆናል።
ኃይለማሪያም ደሳለኝ “ልቤ ደምቷል” ሲል አንድም ሰው ሳይቀር በጉዳዩ እጁ ያለበት እንደሚቀጣ ሲናገር መስማት ከደረሰው አደጋ በላይ ዘግናኝ ነው። ሲጀመር ኃይለማሪያም የሚደማ ልብ የለውም። የሚደማ ልብ ቢኖረው ኖሮ “ተልዕኮ አስፈጻሚ” ሆኖ “የመከላከያ ሰራዊት ነጻ እርምጃ እንዲወስድ አዝዣለሁ” አይልም ነበር። ኃይለማሪያም ከሚስቱ ጋር በቤተመንግስት “አበባየሽ ሆይ” ሲዘፍን፣ አወዳይ ሕዝብ እየታረደ ነበር። እርሱ በግ መግዛቱና ዱለት መብላቱን ሲናገር ከሶማሌ ክልል ወገኖች እየታጨዱና እየተባረሩ ነበር። እርሱ ቁርጥ ሥጋ ለጨጓራው እንደሚስማማው ሲንተባተብ፤ የአወዳይ ሕዝብ አንጀቱ በህወሓት “ሠራዊት” እየተዘረገፈ ነበር።
ስለ እምነት መናገር ደግ ባይሆነም፣ አንድ አምላኩን ለሚያውቅ፣ አንድ “ኢየሱስን አገለግል ነበር” ለሚል ሰው፣ አንድ ወጣቶችን ፖለቲከኛ እንዳትሆኑ እመክራለሁ እያለ ሲያስተምር ለነበረ ሰው፣ በታላቅ የወንጌል መነቃቃት ስብሰባ ላይ በመገኘት አዋራ ላይ ተንበርክኮ “ይቅርታ አይገባኝም” እያለ ሲያለቀስ ለነበረ ሰው፣ ሳይራብ፣ ሳይደኸይ፣ ምንም ሳይጎድለበት … እንዲህ ባለ የደም አዙሪት ውስጥ መነከሩ አስገራሚ ነው። የኃይለማሪያም ብቻ ሳይሆን ባለቤቱና መላ ቤተሰቦቹ እንዲሁም አባል ነኝ የሚላት (የሐዋሪያት) ቤተክርስቲያን አመራሮች እንደ እግዚአብሔር ቤተሰቦች ሊያውግዙት፣ ሊኮንኑት አልሰማ ካለ ሊለዩት በተገባ ነበር። እዚህ ላይ የኃይለማሪያምን “የመከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ አዝዣለሁ” እና የኬኒያን የሌብነት ምርጫ እንዲደገም የወሰነው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የመሐል ዳኛ “ባደረኩት ውሳኔ ላይ ሃይማኖቴ ተጽዕኖ አድርጎብኛል” ማለታቸውን ለሚሰማ ጉዳዩ ከሃፍረትም፣ ከውርደትም በላይ ይሆናል (የመሐል ዳኛው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤ/ክ አባል መሆናቸውን ልብ ይሏል)። ከራሱ በላይ የሚፈራውና የሚያመልከው ፈጣሪ እንዳለ ከልቡ የሚያምን ሰው ይህ ዓይነት ውሳኔ ዕለታዊ ተግባሩ እንጂ ጀግና የሚያስብለው እንዳልሆነ የእምነቱ አስተምህሮ ነው። እንደ ኃይለማርያም ዓይነቱን በገሃድ ወጥቶ የሚገስጽ አንድ ሐዋሪያ የሐዋሪት ቤ/ክ ማጣቷ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው። ይህንን ጉዳይ ለሃይለማሪያም ቤተሰቦችና አባል ለሆነበት ቤተ ክርስቲያን በመተው ወደተነሳንበት እንመለስ።
ከላይ በተደጋጋሚ “የሜንጫ/የገጀራ ፖለቲካ” በማለት ስለደጋገምነው ጉዳይ እንመለስ። የአቶ ወርቁ ልጅ የበደኖ ነዋሪ ነበር። ከበደኖ የተፈናቀለው ገና በጠዋቱ ነው። መለስ ስለ ጎሣ ፖለቲካ አፉን መክፈትና በመትፋት ሲጀመር ነው። ይህ ወጣት ከሙሉ ቤተሰቦቹ ጋር ወደ ወበራ የሸሸው። በበደኖ አባቱን አጣ። አቅመ ደካማ እናቱንና ታናናሽ እሀቶቹን ይዞ ወበራ ገባ። አማራነቱ ከተወለደበትና ካደገበት አሰደደው።
ይህ ስሙን ሙሉ በሙሉ የማንጠቅሰው ወጣት በየደቂቃው ይዘገንነዋል። በየደቂቃው በዘገነነው ቁጥር አንገቱን ይሰብቃል። አንገቱን ወደኋላ አዙሮ ይመልሰውና የሆነ ነገር ይነክሳል። በቃ በየደቂቃው ይህንን ያደርጋል። ለምን? ምክንያቱም የእስላሚክ ኦሮሞ ታጣቂዎች አንገቱን በሜንጫ ከኋላ ስለቆረጡት ነው። ከዚያም አንድ ኦሮሞ የጤና ረዳት ደርሳለት ህይወቱ ተረፈ። ታሪኩ ባጭሩ ይህ ነው። ጠባሳውና ፍርሃቱ አሁን ድረስ ያርደዋል። በደኖ ብዙ ግፍ ተሰርቷል። ጊዜና እውነት ሲጋጠሙ ብዙ ይባለለት ይሆናል።
የሜንጫ ፖለቲከኞች የሟቹ የአባ ጃራ ፍልፈሎች ናቸው። አባ ጃራ የኢስላሚክ ኦሮሞ መሪ ነበር። አሁን እሱ ከሞተ በኋላ እጅግ ስሙ የናኘውና በሜንጫ የሚምለው ደግሞ ጃዋር መሐመድ ነው። ጃዋር መሐመድ በራሱ አንደበት “በሜንጫ አንገቱን እንቆርጠዋለን” ብሎ ሲያሽካካ የነበረና ምራቁን በወጉ ያልዋጠ ወጠጤ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ነው። እዚህ ላይ እስልምና እምነትን ለመንካት ሳይሆን በሰላማዊው የሙስሊም ህዝብና እምነት ውስጥ የሚሰራውን ድራማ ለማሳየት ነው።
ጃዋርን የውጭ ሚዲያዎች በተለይም ዘ ጋርዲያን የጃራ ምትክ ሲል እጅግ ተሰሚነት ያለውና በቅርቡ ገኖ የወጣ እንደሆነ መዝገቡ ያታወሷል። ዘ ጋርዲያን ይህንን አለም አላላም የጃዋር መሐመድ አካሄድ ትኩረት እየሳበና የአጠቃላይ የዲያስፖራውን ትግል ይዞ ገደል እንዳይገባ ፍንጮች አሉ። የሙስሊም ወገኖች “ድምጻችን ይሰማ” ትግል መስመር እየያዘ ባለበት ወቅት ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሄዶ እንዲቀዛቀዝ የሆነበትን፤ በቅርቡ ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ኀብረት ራሱ ህወሓትን እያራደው በነበረበት ጊዜ የተከሰተውን የማምከኛ ሥራ ማስታወሱ ግድ ይላል።
ከውጪ ከሚነዳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅጥ አልባ መሆኑ ጋር ተዳምሮ የእነ ጃዋር መሐመድ ፖለቲካ ለህወሃት ጥሩ አጋጣሚ እየፈጠረ እንደሆነ ሰከን በማለት ቆም ብሎ ለማሰብ ለሚፈልግ ብዙም የሚቸግር አይመስለንም። በምን ጉዳይ እንደሚለያዩና እንደሚስማሙ በውል ለይተው የሚያውቁና የሚያስረዱ የጠፉበት የዲያስፖራው ፖለቲካ ሁሉንም ጉዳይ በዜሮ እንዳያጣፋው ጎልጉል ያሳስባል። በሌለ ልዩነት የሚባሉት ታጋዮችም ሆኑ ፖለቲከኞች ከልፍለፋ በመውጣት ሰክነው ዙሪያቸውን እንዲመረመሩ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ አበክሮ ይመክራል።
ዛሬ ዓለምን የሚያንቀርቅቧት ኃይሎች መባላት ሲፈልጉ ወይም አንድን ኃይል ከሥልጣን ለማስነሳት ሲፈልጉ በተለይ ከሴፕቴምበር 11 በኋላ “ታፔላ” መለጠፍ ብቻ ከበቂ በላይ ምክንያታቸው ነውና “ታፔላዋን” መጠንቀቅ የሚቻለው ከመክለፍልፍ ፖለቲካ መውጣት ሲቻል ብቻ ይሆናል። ማንም ሆነ ማን መስከን ካልቻለ በአሁን ሰዓት በሁሉም መንገድ አደገኛ ድጥ አለ። ምስኪን የሆነውን ደሃውን ህዝብ ማየትም መልካም ይሆናል። እነ ሕዝቅኤል ገቢሳና ሌሎችም ይህንን “የሜንጫ ሒሳብ” በጥንቃቄ ቢያሰሉት መልካም ነው። አገሪቱ በደም እንድትጨቀይ የሚያደርግ የተበታተነ ሩጫ ዋጋ ያስከፍላል፤ ዋጋው “ነጻ እናወጣዋለን” የሚባለውንም ሕዝብ አብሮ እንዲኖር የሚያደርግ ለመሆኑ ዋስትና የለውም። ለመጋደሉ የወያኔዎቹ ሴራና ቅስቀሳ ከበቂ በላይ ነው። (የመግቢያ ፎቶ: Addis Standard)

ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው

No comments:

Post a Comment