Translate

Wednesday, September 6, 2017

በምስራቅ ሐረርጌ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተወረወረ ቦምብ በርካቶች ቆሰሉ

(BBN) በምስራቅ ሐረርጌ ሜኢሶ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተወረወረ ቦምብ በርካቶች ቆሰሉ፡፡ ከስፍራው የተገኘው መረጃ እንደጠቆመው፣ ቦምቡ የተወረወረው በአካባቢው ጥቃት እያደረሰ በሚገኘው የሶማሊያ ክልል ልዩ ኃይል አማካይነት ነው፡፡ የሶማሊያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ባለፉት ተከታታይ ቀናት በምስራቅ ሐረርጌ ሜኢሶ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል መንግስትም ሆነ ከፌደራሉ መንግስት ምንም ዓይነት ከለላ ያላገኘው የአካባቢው ነዋሪ፣ ባለው አቅም ራሱን ከጦሩ ለመከላከል የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ ራሱን ለመከላከል እያደረገ ባለው የአጸፋ ምላሽ የተቆጣው የሶማሊያ ልዩ ኃይል፣ ቦምቡን በትምህርት ቤቱ ላይ እንደወረወረው ከአካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ድርጊቱን ‹‹የበቀል እርምጃ›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የእጅ ቦምቡ ወደ ትምህርት ቤቱ ከተወረወረ በኋላ በርካቶችን ያቆሰለ ሲሆን፣ በጽኑ የቆሰሉት ደግሞ አምስት ህጻናት መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሌሎችም የጥቃቱ ሰላባ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመራው እና ከህወሓት ትዕዛዝ የሚቀበለው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል፣ በምስራቅ ሐረርጌ በተለይም ሜኢሶ በተባለው ከተማ ጥቃት ማድረስ ከጀመረ ረዥም ጊዜ ሆኖታል፡፡ ሆኖም በህወሓት የሚመራው መንግስት ጥቃቱን ለማስቆም ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ ነዋሪዎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ያለበት የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም፣ ነዋሪዎቹን ከሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ጥቃት ለመከላከል ባለመፈለጉ፣ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ ይገኛል፡፡ ዛሬ በትምህርት ቤት ላይ የተወረወረውን ቦምብ ተከትሎ አካባቢው ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡

No comments:

Post a Comment