Translate

Thursday, May 1, 2014

ወያኔ የሚፈራው ምርጫ ወይስ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (አመጽ)

ወያኔ የሚፈራው ምርጫ ወይስ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (አመጽ)የወያኔ የሚፈራው ምርጫ ወይስ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (አመጽ)

ተስፋዬ ዘነበ(ኖርዌይ በርገን)
በዚች አለም   በሕዝቦቻቸው ላይ የሚፈነጩ አምባገነኖችን ለማስወገድ የሚደረጉ ሕዝባዊ  እንቅስቃሴዎች ሁሉ የወያኔ ዘረኛችን  ለምን ሲያስደነብራቸውና በፍርሃት ሲያሸማቅቃቸው  እንደሚኖር  የሁሉም ሰው ጥያቄ ነው፡፡ የህውሃት ዘረኛ ቡድን በሕዝብና በሃገር ላይ የሚያደርሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት  ወይም ውድመት በተለያየ መንገድ ሕዝቡ ቅሬታውን ቢያሰማም እራሱ ለፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግር መፍትሄ ከመሻት ይልቅ የሕዝቡን ብሶት ለማዳፈን ሀላፊነት የጎደለው   ተግባራትን እየፈፀመ ሃገርን የመበተን ስራውን ቀጥሎበታል፡፡

በአዋጅ የተደነገጉ የሕዝብን አሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን እየሸረሸሩና አዋጅን በተራ መመሪያ እየሻሩ  የስቃይ ቀንበሩን ያከብዱበታል ፡፡በየትኛውም ሁኔታ ማለትም የሰብአዊ መብቱ የተረገጠውን፣ የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል ስላለ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታየ የሚሰቃየውን የነፃነት ታጋይ፣ በስርዓቱ ብልሹና የተዝረከረከ አሰራር በኑሮ ውድነት እየማቀቀ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ለጥያቄው ተገቢውን መልስ ወይ መፈትሄ ከመስጠት ይልቅ በተራ ካድሬያዊ ዲስኩር ከላይ ለዘረኛው ስርዓት ቃል አቀባይ ከሆነው ጠ/ሚ ተብዬው እስከ ልማታዊ ጋዜጠኛ ነን እስከሚሉት ድረስ በርሃብ ለጠወለገው ምስኪን ሕዝብ ጥጋብን፣ በገዛ ሃገሩ ፍትህ አጥቶ ለሚሰቃየው ፍትሃዊነትን እንዲሁም ሰብአዊ መብቱ ተገፎ ነፃነቱን ለተነጠቀው ሕዝብ ዴሞክራሲን ነጋ ጠባ ይሰብኩታል፡፡
ይህው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ስለፈጠረው ሃገራዊ ቀውስ ብዙ ብዙ  ቢባልም የዚህን መርዘኛ ስርዓት ሰንኮፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ ለመጣል ከምርጫ ይልቅ ሕዝባዊ እምቢተኝነት(አመጽ) ስለመሆኑ ስርዓቱ በሚያሳየውና ከሚሰጋባቸው ነገሮች ለመረዳት ይቻላል፡፡
እንደሚታወቀው በተደጋጋሚ የተካሄዱት ምርጫዎች ከምርጫ 97 ውጪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለወያኔ መሳሪያ ከመሆን ወጪ የስርዓቱ የአፈና መዋቅር ተቃዋሚዎችን የሚያወላዳ አልነበረም፡፡ ይህ ማለት ይካሄዱ የነበሩ ምርጫዎች በህውሃት ዘረኛ ቡድን በተጠና የአፈና እንዲሁም በዋነኝነት ምርጫን  ምርጫ ሊያሰኙ የሚችሉ ገለልተኛ ተቋማት በጠቅላላ በስርዓቱ መዋቅር የተዋጢና የተተበተቡ በመሆናቸው ለመገናኛ በዙሃን ሸፋንና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ መደለያ ካልሆነ  በስተቀር ምርጫው ሳይጀመር ውጤቱ የታወቅ እንደ ነበር ከማንም የተሰወረ አደለም፡፡ ስለሆነም የህውሃት ቡድን አምስት አመት ጠብቆ የሚመጣ ምርጫ  ከላይ እንደተጠቀሰው ለአንዳንድ ግብአት ይጠቀምበት እንደሆን እንጂ ምርጫ ስለተቃረበ እንቅልፍ የሚያጣ አይመስልም ምክንያቱም የምርጫ አስፈጻሚ አካላት እስከ ፍትህ ስርዓቱ በእጁ ናቸውና፡፡
የልቁንም ለዚህ እኩይ ስርዓት የራስ ምታት የሚሆንበትና ሰላም የሚነሳው ሕዝባዊ እምቢተኝነት(አመጽ) ነው፡፡ በቃ የሚል ትውልድ ግፍና በደል ያንገሸገሸው ሕዝብ ለመሆኑ ማሳያ ይሆኑ ዘንድ አንዳንድ ነጥቦች እናንሳ፡፡
ከአመታት  በፊት ቱኒዚያዊው ሙሃመድ ቡዋዚዝ የቢን አሊን አንባገነን መንግስት በሃገሩ በቱኒዚያና በሕዝቧ ላይ የሚያሳደረውን ዘርፈ ብዙ ችግር በመቃወም እራሱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ ካቃጠለ በሗላ ቱኒዝያን ጨምሮ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ የመን፣ እስካሁንም በነወጥ ውስጥ ያለች ሶሪያ የደረሰውን ሕዝባዊ እምቢተኝንትና በየሃገሩ የተለኮሰው አመጽ የወያኔን ዘረኛ ቡድን ያስፈራውና ያሸማቀቀውን ያህል አምስት አመት ጠበቆ የሚካሄደው የየስሙላ  ምርጫ አላሸበረውም፡፡
ይህንንም ለመገንዘብ በዛን ወቅት ሟቹ መለስ ዜናዊ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ማየት የበቃል፡፡ በመጀመሪያ የአረብን አለም አብዮት የሚዘገቡ አለም አቀፍ የመገናኛ ቡዙሃንን ማፈር ቀዳሚ ተግባሩ ነበር ሆኖም መረጃው በተለያየ መንገድ ሕዝብ ጋር መድረሱን የተረዳው ሟቹ ጠ/ሚንስትር የሕዝብን መንፈስ ለመሳብና ቤሔራዊ ስሜትን ሰቅጦ ይይዝልኛል ያለውን መላ ምቱ ዘየደ ባይሳካም ኤርትራን ለመውረር መዘጋጀቱን ማወጅ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው አብዮቱ የኢትዮጲያንም በር እንዳያንኳኳ ካለው ከልክ ያለፍ ፍርሃት ነበር፡፡ ሆኖም ሕዝብ ኖሮውን እንጂ የወረራ ዲስኩር ችላ እንዳልው ሲረዳ  በኤኮኖሚም በፖለቲካ እንዲሁም ሃገራችን ያላትን መልካም የውጪ ገንኙነት የላገናዘበ በተጨማሪም በባለሞያዎች በቃ ጥናትና ምርምር ያልተደረገበትን እስካሁንም ዘርፈ ብዙ ችግር አዝሎ የሕዝብ ኪስ የራቆተውን የአባይ ግድብን እንካችሁ ብሎ ሻማ  አለን፡፡ የሟቹን አላማ ይህኛው  በተወሰነ መጠን አሳካለት ሆኖም አብዮት የፈራው ወይም ሕዝባዊ እምቢተኝነትን የፈራው የህውሃት ዘረኛ ቡድን የማይገፋ እዳ ለሃገርን ለሕዝብ ትቶ ችግሩን ፍርሃቱ ፈታበት፡፡
በተጨማሪ ይህው ዘርኛ ቡድን በአለም ዙሪያ የተደረጉ የተሳካላቸው ምርጫዎችን እያነሳ የሰጋበት ግዜ አይታወስም፡፡ በአንጻሩ ምርጫ ያጭበረበሩ አምባገነኖችን ሕዝብ ሲቃወምና ድምጹን ለማስመለስ የሚያደርገውን የነፃነት ትግል አሉታዊ መልክ ሰጥቶ ባዘጋጃቸው የፖለቲካ ተንታኝ ተብዬዎች ውግዝ ከማርዮሰ ሲያስብላቸው ይውላል፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚካሄዱ ሕዝባዊ እቢተኝነት(አመጽ) ከማውገዝ ወደ ሗላ ብሎ የማያቀው ይህ ስርዓት ሰሞኑን ዘጋቢ ፊልም መስራት በማይሰለቻቸው ልማታዊ ጋዜጠኞቹ ይቀርብ የነበረው የዚሁ የፍርሀትና እራሱን እየከፈነ ያለው ያበቃለት የህውሃት ዘረኛ ቡድን ቅዠት ነው፡፡
ቅዠቱ የቀለም አብዮት ይልና ከብርቱካናማው የዩክሬን አብዮት ጀምሮ ቬንዙዌላ የድርሳል አጠቃላይ ምልከታው አብዮት ወይም ሕዝባዊ እምቢተኝነት  የሚከናወነው ሕዝብ ፈልጎት ሳይሆን ከምህራባዊያን እዲሁም በምህራባዊያን ሃገራት ከሚኖሩ ዜጎች ፈላጊት የሚመነጭ ነው ይለናል ኸረ እንደውም እነዚሁ ምህራባዊያን የማይፈልጓቸውን መንግስታት የሚያሶግዱበት አንዱ መሳሪያ ሕዝባዊ አመፅ ነው በማለት ይቀጥላል፡፡ ሌላው የሚገርመው  የ 97 ምርጫን ተከትሎ ሕዝብ የተቀማ ድምጹን ለማሰመለስ ያደረገውን እንቅስቃሴና ንጹሃን ወገኖቻችንን በዚሁ ዘረኛ ቡድን የተነጠቅንበት ትህይንትም እንደ ዘጋቢ ፊልሙ አገላለጽ በሌሎች ሃገራት እንደተደረገው ሁሉ በምህራባዊያንና በነዚሁ ሃገራት በሚኖሩ ዜጎች የተቀነባበረ እንደሆነ ያትታል፡፡ የሚገርመው ታዲያ ወያኔን ይህንን ያህል ዘመን በሕዝብ ጫንቃ ላይ ያስቀመጡት እነሱ ምህራባዊያን ሆነው ሳለ ሰጋቱን ምን እንዳመጣው ነው፡፡
ሕዝብ ለሚያቀርበው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ የፍትህ ጥያቄ እንዲሁም የዴሞክራሲና የነፃነት ጥያቄ ጀርባ ሰጥቶ በትምክህት መካፈስ በቃኝ ለሚል ለውጥ ፍላጊ ትውልድ እሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ ነው፡፡ የህውሃት ዘረኛ ቡድን አሁን የትያያዘው መንገድ ይህው ነው፡፡
ምን ያለበት ምን አይችልም እንደሚባለው የትም ይሁን የት መሰል የአመባገነኖችን ዙፋን የሚያነቃንቅ ሕዝባዊ አመጽ የሕውሃት ቡድን እራስ ምታት ነው፡፡ ሕዝብንም በመከፋፈልና በመለያየት የተጋው ፍርሃቱን ለማብረድ ነው፡፡ በተረፈ አምስት አመት ቆጥሮ የሚመጣን ምርጫ ያውም 99.6% ሊሰርቅበት የሚችል ለእርሱ በእርሱ የተከፈተ የምርጫ ስርዓት ያሰጋዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በፍርህት የሚያርደውም የሚያሶግደውም ሕዝባዊ እምቡተኝነት(ሕዝባዊ አመጽ) ነው፡፡ በተለይ አሁን ስርዓቱ በስብሶ እራሱን በገነዘበት ሰዓት ሊቀብረው የሚችል በኢትዮጲያዊነት ጥላ ስር በአንድነት የተደራጀ በቃ በሎ ነፃነቱ የሚያውጅ ተውልድ ነው!!!
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment