Translate

Saturday, May 31, 2014

አገራዊ ስሜት ለምን ይጎድለናል?

በተክሉ አባተ

ከበርካታ ሳምንታት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እየተወያየን ነበር:: ሁሉም ተሳታፊ የተስማማበት ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ ከምንም ጊዜ በላይ እጅግ ከባድ ማኅበራዊ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ነበር:: ለዚህም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂው መንግስት እንደሆነ ቢሰመርበትም ህዝቡም ላለንበት ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ታላቅ አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝ ተወስቷል::እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ለአገርና ለለውጥ ያላቸው ስሜት እንደ በረዶ የቀዘቀዘ እንደሆነ ተነገረ:: ለዬት ያለና ታላቅ አገራዊና ወገናዊ ጉዳይ ሲነገር ህዝቡ ጸጥ ረጭ ብሎ ሰምቶ ሃሳቡን ሳይሰጥ ሹልክ እያለ እንደሚወጣ ሁሉም የታዘበውን እያነሳ ተናገረ:: ብዙዎች ለወገናቸው ጥልቅ ስሜት ስለሌላቸውና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በንቃት ስለማይሳተፉም መንግስት በጭቆናው እንዲቀጥል ሞራልና ጉልበት እየሰጡት እንደሆነም ተጨመረበት::
ከቀናት በኋላ በሌላ መድረክ ፋንታው የሚባል ወንድሜ ለኦስሎ ነዋሪዎች ከላከው ደብዳቤ ውስጥ “ለነገሩ ብዙ ኢትዮጵያዊ ሰው ለብዙ ነገር ስሜት የለውም” የሚል ትችት አገኘሁ:: ይህ በቀላሉ የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነና ውይይት እንደሚያስፈልገው በማመን ጸሃፊውን ቀጥለው በተዘረዘሩት ጥያቄዎች ዙሪያ ልምዱንና እውቀቱን እንዲያካፍለን ተማጸንኩት::
  • ሰው ስሜት የለውም ስንል ምን ማለታችን ነው?
  • የስሜት አለመኖር ምክንያቱና መንስዔው ምንድን ነው?
  • የስሜት አለመኖር የሚያስከትለው ጉዳት ወይም ጣጣ ምንድን ነው?
  • ስሜት-አልባነትን እንዴት ማጥፋት ወይም መቀነስ ይቻላል?
  • ስሜት-አልባነትን ለማጥፋት ወይም ለመቀነስ በሚደረግ ትግል ዋና ተዋንያን እነማን ናቸው?
የስሜት ያለህ!
አቶ ፋንታውም “የኢትዮጵያዊ ስራና ጥልቅ ስሜት አቅም” በሚል ርዕስ ይበል የሚያሰኝ ትንታኔ አቀረበ:: ስሜትን በሁለት ከፍሎ አብራራ:: ሃሳባዊ ስሜት “ከልባችን ለመውደድና በአእምሮአችን ለመረዳት በዙሪያችን በሚከሰቱ ነገሮች ላይ የምናሳየው ጥልቅ ፍላጎትና የምናደርገው ግንኙነት ነው”::ስሜት በልብ ወይም በአእምሮ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሥራ እንደሚገለጥም ምሳሌ እያነሳ አብራርቷል:: የስሜት አለመኖር የሚያስከትለውን መዘዝም ከእድገትና ለውጥ ካለመኖር አኳያ አጠር አድርጎ አንስቷል:: ጽሁፉን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ::
እኔም ፋንታው ባነሳቸው ባብዛኞች ሃሳቦች እስማማለሁ:: በዚህ ጽሁፍ አገባብ ስሜት ማለት በአካባቢያችንና በአገራችን ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በነቃ አእምሮ ተከታትሎና መርምሮ የራስን ግንዛቤ መውሰድ ከዚያም የሚገባውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሆነም እስማማለሁ:: በስብሰባዎችና የውይይትመድረኮች መሳተፍ: የፖለቲካ ወይም የሲቪል ተቋማትን መምራት ወይም አባል መሆን: የራሱና የሌላ ሰው መብት ሲጣስ መቃወም: እድገትና ለውጥ በሚያመጡ ፕሮጄክቶች መሳተፍ ወዘተ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚገለጥባቸው መንገዶች ናቸው::
ምናልባት ጥያቄ ቢኖረኝ ስሜት በሌለው ኢትዮጵያዊ ብዛት ላይ ነው:: እንደ ፋንታው አመለካከት ከሆነ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በቂ ስሜት የለውም:: ይህ ቁጥር እንዴት ታወቀ? አገር ቤት ያለው ወይስ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ነው ስሜት የሌለው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል::
ዳሩ ግን ከምናየውና ከምንሰማው መገመት አይከብድም:: ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቶ የሚወጣው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች የሚገኘው ህዝብ ከበቂና ከተጠበቀው በታች ነው:: ምክንያቱ ደግሞ መንግስትን ከመደገፍ ወይም የጭቆና አለመኖር ሊሆን እንደማይችል ለማንም ግልጽ ነው:: በውጭ አገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንም በዘመናዊ ማህበራዊ የመገናኛ ብዙኃን ስለአገራቸው የሚጽፉና የሚያነቡ ጥቂቱ ናቸው:: ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የውይይትና ክርክር መድረኮች ተዘጋጅተው የሚሳተፉት ጥቂቶች ናቸው:: በሰላማዊ ሰልፍ የሚሳተፉትም እንዲሁ:: በአንጻሩ ደግሞ የሙዚቃ ምሽት ወይም የስፖርት ዝግጅቶች እንዲሁም ሰርግና ልደት በሚደረግበት ጊዜ ያረፍዳል እንጅ የተጠራው ሁሉ ሽክ ብሎ ይገኛል:: ያልተጋበዘውም ባለመጋበዙ ይሰማዋል::
ለመሆኑ አገራዊ ፖለቲካዊ ስሜት የሚጎድለን ለምንድን ነው? ይህ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሌ የሚያነሱት ጥያቄ ነው:: በዝግጅቶቻቸው በቂ ሰው አይገኝምና:: ይህ ጥያቄ ባንድም በሌላም መንገድ ቢነሳም አጥጋቢ መልስ አላገኘም:: አንዳንዶች የዚህ ሁሉ ችግር ህዝቡ ያለው ፍርሃት እንደሆነ ተናግረዋል:: ሌሎች ደግሞ ይህ ዝምታ የኢትዮጵያ ህዝብ የትዕግስቱ መለኪያ እንደሆነ ጽፈዋል:: ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች ችግሩን በፍጹም አይገልጹትም:: የሁሉም ሰው ምክንያቶች ሊሆኑም አይችሉም:: የተጠናከረ ውይይት ቢካሄድ ይህን ችግር መቅረፍ እንደሚቻል በማመን በዚህ ጽሁፍና በተከታታይ ጽሁፎች አገራዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እንዳንከታተልና በሚገባ እንዳንሳተፍ የሚያደርጉ መንስኤዎችንና ምክንያቶችን በዝርዝር ለማየት እሞክራለሁ::
መንስኤዎችና ምክንያቶች
ለአገራዊ ስሜት አለመኖር መንስኤዎችን ከምክንያቶች ለመለየት የተደራጀ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል:: በዚህ ጽሁፍ ግን ሁለቱን አንድ ላይ አድርጌ አቀርባለሁ:: ይህን ማድረጌም የጽሁፌን ዓላማ ከመምታት አያግደኝም:: ይልቁንም አላስፈላጊ ክብደትን ያስወግድልኛል ብዬ አምናለሁ::
በቂ ስሜት ያለመኖር መንስኤዎቹና ምክንያቶቹ ከሰው ሰው ከጊዜ ጊዜ ሊለያዩ ይችላሉ:: ቢሆንም ግን ዋና ሊባሉ የሚችሉትን መገመቱ አይከብድም:: ከማኅበራዊ ህይወቴ ጋር በተያያዘ ከተመለከትኳቸውና ከታዘብኳቸው የስሜት አልባነት መንስኤዎች ወይም ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ዋናዎቹ ናቸው::
ዝንባሌና ፍላጎት
ሰዎች በተፈጥሮአቸውና በህይወት ተሞክሮአቸው የተነሳ ለተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ልዩ ፍላጎትና ዝንባሌ አላቸው:: በመሆኑም ለአገራዊ ጉዳዮች ምንም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ይኖራሉ:: ሌላው ቀርቶ በግል ህይወታቸውም ሲበደሉና መብታቸው ሲጣስም አይገዳቸውም እጅጉን የሚያሳስባቸውና መስዋዕት የሚከፍሉለት ብቸኛው ጉዳይ ሥራቸውና የቤታቸው ነገር ነው:: የተሰማሩበትንም ሥራ የሚመለከቱት ለአገር በሚያደርገው አስተዋጽዖ ጭምር ሳይሆን የደመዎዛቸው መገኛና ማግኛ መሳሪያ በመሆኑ ብቻ ነው::
በዚህ ምድብ ውስጥ በርካታ በትምህርት ብዙም ያልገፉ ሰዎች: ቴክኒሽያኖች: መሃንዲሶች: ፕሮፌሰሮች: ዶክተሮች እና ሌላ ትልቅ ማዕረግና ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችም ይገኛሉ:: እነዚህን ሰዎች አይደለም በማስታወቂያ በአማላጅም ቢሆን ወደ አገራዊ ውይይት መድረክ ማምጣት ከባድ ነው:: ያለው አማራጭ እነዚህ ሰዎች በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ላቅ ያሉና ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ብቻ ነው:: በፖለቲካዊ ውይይት ወይም መድረክ እንዲሳተፉ ማስገደድ ከአለት ላይ ውኃ ለማፍለቅ እንደመሞከር ነው:: በአገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ የሁሉም ሰው ምርጫ ሊሆን አይችልም::
የአቅም ጉዳይ
ቀላል የማይባሉ ሰዎች ደግሞ በአገራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ እምቅ ኃይል ቢኖራቸውም ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ ግምት አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ያደርጋቸዋል:: ራሳቸውን ዝቅ አርገው ስለሚመለከቱ ወጣ ብለው ለመታየት አይፈልጉም:: ውይይቶች በሚካሄዱባቸው ጊዜ ጥሩ ሃሳቦች ቢኖራቸውም ለመጠየቅ ያመነታሉ:: አልፎ አልፎም ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ:: ከብዙ ሰዎች የሚያበረታታ ምላሽ ካላገኙ በሰው እንደተጠሉና እንደተናቁ በመገመት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ:: ከሰዎች የሚያገኙት ግምት አበረታች ስለማይሆን ተሳትፎአቸውን ለመግታት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ:: አገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አስተዋጽዖ ለማድረግ ይህ ነው የሚባል አቅም እንደሌላቸው ራሳቸውን ያሳምናሉ:: በመሆኑም ቀስ በቀስ በታዳሚነት ከሚገኙባቸው መድረኮች ይርቃሉ::
ሌሎቹ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት ሰዎች ተቃራኒ ናቸው:: በእውነትም ጥሩ ሃሳብና ተሞክሮ ቢኖራቸውም የሌላውን ለመቀበል ይቸገራሉ:: ሁሌ የራሳቸው ሃሳብ ብቻ እንዲያሸንፍ ይከራከራሉ:: ይህ ሳይሆን ቢቀር ስብሰባው ወይም ውይይቱ እርባና እንደሌለውና ችሎታ በሌላቸው ሰዎች እንደሚመራ ያወራሉ:: ያስወራሉ:: እንደምንም ብለው ለሚቀጥለው ጊዜ የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ ይሯሯጣሉ:: ካልተሳካላቸውም ሙከራቸውን እንደ ሽንፈት ቆጥረው ከሱታፌ ይታቀባሉ:: ከተሳካላቸው መድረኩ ወይም ፓርቲው የግል ንብረታቸው እስኪመስላቸው ይቆጣጠሩታል:: ሥልጣን እንዲለቁ ወይም እንዲያካፍሉ ወይም የሌላውንም ሰው አስተዋጽዖ ቦታ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ያኮርፋሉ:: ያደረጉት አስተዋጽዖ የተረሳባቸው ይመስላቸዋል:: የመገለል ስሜት ያጠቃቸውና እንቅስቃሴአቸውን ቀስ በቀስ ያቋርጡና በትዝታ መኖር ይጀምራሉ:: ከቻሉም ሲሳተፉባቸው የነበሩትን መድረኮች ወይም ድርጅቶች ይኮንናሉ:: ለማዳከምም ይጥራሉ:: አንዳንዶችም የራሳቸውን ተስፈንጣሪ ድርጅቶች ይፈጥራሉ:: የባሰባቸው ደግሞ የመንግስት ደጋፊና አባል በመሆን ብቸኝነታቸውን ለመቋቋምና ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ይጥራሉ::
//////////// ይቀጥላል ///////////////
ገንቢ አስተያየት ካላችሁ በteklu.abate@gmail.com ላኩልኝ!

No comments:

Post a Comment