Translate

Saturday, May 31, 2014

ለውጥን ፈልገን ለውጥንም ፈርተን በጭራሽ አናመጣውም

ዳዊት ዳባ

Revolution coming to Ethiopia
የለውጥ አስፈላጊነት ላይና ወያኔ መራሹ መንግስት ይበቃው ዘንድ ባብዛኛው ዜጋ ከተቻለ የሚለው እንዳለ ብዥታ የለም። ይህ ፍላጎት የብዙ ስረአቱ ውስጥ ያሉ ዜጎችም ጭምር መሆኑን የተለያዩ መረጃዎችን ጨምቆ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል። በርግጥ የለውጡ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙና አይቀሬነቱን የሚያውቁ ነገር ግን ለውጡ የተረጋጋና ችግሮች ያልበዙበት እንዲሆን ይረዳል ብለው አገዛዙ ድርሻ በሚያደርግበት እንዲከወን የሚመኙ አሉ። ፈራ ተባ እያሉ ሀሳቡን አንዳንዴ ያነሱታል። ይህ ሀሳብ ክፋት ባይኖረውም ጥሩ ምኞት ብቻ ነው የሆነው። በትንሹ እንኳ ተቀባይነት እንዲያገኝ አይደለም እንዲሰማ ለማድረግ አገዛዙ ጉልብት አልሰጠው እያለ ብለጭ ድርግም ይላል። አውቆ የሚያደርገው በሚመስል ገና እነዚህ ጥሩ አሳቢ ዜጎች ቁምነገሩን ሲያነሱት አገዛዙ አንጀት ቁርጥ የሚያስደርግ ሰማይ ሰማይ የሚያካክል አጋረዊ ጥፋቶችን አከታትሎ እየፈጸመና እያላገጠበት ያስቸግራል። ለምን ብሎ ለሚጠይቅ?። ቀንደኛ ለሆኑት የስርአቱ ሰዎች ከኛ በላይ ይህ መንገድ እንዳማያዋጣቸውና እድሜያቸውን ማሳጠር ብቻ እንደሆነ አሳምረው ስለሚያውቁ ነው። እውነት ለመናገር ትክክልም ናቸው። የትኛውም ለውጥ የሚመጣበት መንገድ የመጨረሻ ውጤቱ ለነሱ መቶ በመቶ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። አስፍተንና እርቀን አስበን፤ ሆደ ሰፊ ሆነን፤ ይቅር ብለናል ብለን መጫኛ ነክሰን ብንለምንም ልንሳምናቸውና ሀሳብ እንዲቀይሩ ለማድረግ አይቻለንም። የሰሩትን ያውቁታል። ስለዚህም ላልቆረጡ ይቁረጥ።
እነሱ ገፍተን እንዲሸሹ እንድናደርጋቸው ነው የሚጠብቁት። ያም ሆኖ አዙረንና በጥልቀት ስላላየነው ነው እንጂ ለውጡ ላይ ይገጥሙናል ብለን የምናስባቸውን ችግሮች በማስቀረት ረገድ ለውጡ ላይ ድርሻም አደረጉ አላደረጉ ቅንጣት ታህል የሚጨምሩትም የሚቀንሱትም ነገር የለም። እንደውም ያወሳስቡታል። በሌላ በኩል ለለውጥ የቆመው ክፍል ከምር ይህን ቁም ነገር አሳስቦት መላ ላድርግበት ቢል መፍትሄ ሊያበጅለት የማይችል አይደለም። የሚካበደውን ያህልም በጭራሽ አስቸጋሪም አይደለም። የዚህ ክፍል ዋን ትኩረት መሆን የነበረበት ይህ ነበር።
ለውጥ ሊመጣ ነው። አዎ ለውጡ እየመጣ ነው። እንዲሁ በምንም አይነት ለውጥን ፈርቶ ትግሉን በማለዘብ ማዘግየት ይሆናል እንጂ ይገጥሙናል የምንላቸውን ችግሮች ማስቀረትም አይቻልም። ይህን አይነት አሳብ በድጋሚ ግራ የገባን መሆናችንን ብቻ ነው የሚያሳየው። እንደውም ችግሮች ገዝፈውን ተወሳስበው በሗላ መፍትሄ ልንሰራላቸው የማይቻለን ማድረግ ብቻ ይሆናል። እየታየ ያለውም ይሄ ነው። እስካሁን ማሸነፍ አቅቶንና ወያኔን ፈርተን አሁን ደግሞ ለውጡን ፈርተን እድሜ አንቀጥልላቸው። በዛ ላይ የተገኘውን ያህል እድሜ ማግኘቱን እንሱም የሚፈልጉት ነው። ምክንያቱም በሚያገኙት እድሜ ደግሞ ችግሮችን በመፈልፈል፤ በማግዘፍና በማወሳሰብ ፈርተን ይቆዩ ይሆን? እንድንል ይጠቀሙበታል።
አገዛዙን ማሸነፍ ትግል ነው። አገዛዙን ማሸነፍ መሰዋትነት የሚሻ ነው። ለውጡን ሉአላዊነታችንን የማይነካ በማይከፋፍለንና በማያገዳድለን፤ ሁሉ ደስተኛ በሚሆንበት መንገድ መከወን ግን እንደማየው ትግል ልናደርገው ካልፈለግን ትግል በጭራሽ አይደለም። ትግልም ቢባልም አውዳሚ ትግል አይደልም። አውዳሚ የሆነ መተጋገልንም በዋናነትም አያሻም። የሚፈልገው ፍቃደኝነትን፤ አስፍቶ ማሰብን፤ ተጨባጩን ያአገራችን ሁኔታ ማጥናትንና፤ አማካኝ የሚያስማማ መፍትሄ አምጦ መውለድንና ማስቀመጥን ነው። ለሁሉም በጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያያትንና መስማማትን ብቻ ነው። በዚህ ጽሁፍ ትግል ያልኩት ሲቀነቀን የማየው በሂደቱ ሉአላዊነታችንን ሊጎዳ የሚችል ፤ ደም የሚያፋስስና አውዳሚ የሆነውን ነው። ያሁኑ ደግሞ እንደከዚህ በፊቱ በድርጅቶችና በተከታዬቻቸው መሀል የሚደረግ አይደለም። በህዝቦች መሀል የሚደረግ እንደሆነም ስለማውቅ ነው። አዲሱ ትውልድ ከሰማና ግድ ካለው ነው እንጂ የአቢዬት ልጆች ታላለቆቻችን ዛሬም ከማይታረቅ ቅራኔ፤ ከመስመር ልዩነት ከሚል ታስቦት የወጡ አይመስለኝም እንደሚከብዳቸው አውቃለው።
ይህ ግልጽ በሆነበት ነው አገዛዙን ነገ ለመጣል ባሰበ በሙሉ ሀይላችን መግፋቱን ለደቂቃም ማቆም ግን የለብንም የምለው። ለምን ቢባል ከላይ ከሰጠሁት ምክንያት በተጨማሪ ለውጡን ችግሮች የማይኖሩበት ማድረጉ ድሮ ድሮ መሰራት የነበረበት ነው። በቀላሉም አዎ በቀላሉ ሊሰራ የሚችል ውዝፍ የቤት ስራ ነው። ወዝፈንዋል። ያም ሆኖ የተጀመረው ትግል በሚጨምርበት በተጓዳኝ በቀላሉ ሊሰራ የሚችል ደግሞ ነው። ሁለት ሲደመር ሁለት ይሆናል አይነት መፍትሄ ካላልን። ስለማይቻል መቶ ፐርሰንት ሁሉም የሚደሰትበትና ፍፁም መፍትሄ ለማምጣት ካላሰብን። የጋራ መፍትሄ መስራቱ ላይ ድርሻ አላደርግም ብሎ ርካሽ ፖለቲካ ሊሰራበት የሚያሰላ ድግሞ ካልተነሳ። ሂደቱ ህክምና መጀመር መሆኑ ቀርቶ አንድ ክኒን በመዋጥ ከሁሉም አይነት መሀበረሰባዊ ችግሮቻችን ባንዴ ለመፈወስ አይነት ያላሰበ ካልሆነ። ቢቻል ጥሩ ነበር ከአለም ላይ የመጀመርያዎቹ እንሆን ነበር። በየትኞቹም አገሮች እንደኛው ቸግሮች መኖራቸውም መፍትሄ ላይ መስራቱም ቀጣይ ሆሌም የሚኖር ሂደት ነውና። አላማው ውስን በዋናነት ሽግግሩን ሰላማዊ ማድረግ ደም የማያፋስስና የአግር ደህንነትን ማረጋገጡን ብቻና ብቻ ታሳቢ አድርጎ ከተሰራበት።
አሁን የትኞቹም ድርጅቶች ከላይ የገለጽኩትን አይነት ድም አፋሳሽን አውዳሚ ትግል ውስጥ ሳይገቡ ሽግግሩን እናሳካለን ብለው ሊያሳምኑኝ፤ ሊያሳምኑም የሚችሉ የሉም። ለዚህም ነው ለውጥ እጅግ አስፈሪ የሆነው። ካላችሁ እጃችሁን አውጡና አሳምኑን። ያለበለዚያ አንድ ድርጅቶች ፕሮግራማችሁን በማስፋትና ተጨባጩን ያገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በይበልጥም ለውጡን የሚሸከም ማድረግ። ሁለት በቶሎ በጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብላችሁ የዝች አገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ጋር ሁሉ አግላይነት በሌለበት ተወያይታችሁ ፍጽም ባይሆንም በሁሉም ዜጎች ዘንድ ማለፊያ ተደርጎ የሚወሰድ ስምምነት መቋጨት ብቻ ነው መንገዱ። ከሁለቱ አንዱን እንኳ ሳታደርጉ በርግጠኝነት በየትኛውም መንገድ የሚመጣ ለውጡን አውዳሚ ትግል ውስጥ ሳይከተን በሰላም ልታሻግሩን በታአምር ካልሆነ አይቻልም። ሳይቻል ቀርቶ ለሚደርሰው ውድመት ደግሞ ሀላፊነት አለባችሁ።
እንዲሁ እውነት እውነት እላችሗለው ይህን ካላደረጋችሁ በቀጣይም ዲሞክራሲያዊ መንግስት አዝች አገር ላይ አሁንም አይመጣም። ዜጎች ይህን ቁምነገር አጽኖት ሰጥተን እንየው። ብዙዎች በዘር የተደራጁ ድርጅቶች ዲሞክራሲን ሊያመጡ አይችሉም ይላሉ። ይህ ግልጽ ነው አይችሉም። እነሱም ባዛ ወይ በዚህ ዘር ተደራጅተው ለሁሉም የሚሆን ዲሞክራሲ ብቻችንን ሆነን እናመጣለን ብለው አላሰቡም። አይሉምም። ከዚህ በሗላ አይመጡምም። መነሳት ያለበት በዘር አልተደራጀንም የሚሉት ወደስልጣን ሲመጡ ይህ ሁሉ የዘር ድርጅት፤ የመብት ጥያቄና፤ ጥልቅ ሴሚትና ፍላጎት ብንን ብሎ ይጠፋል ወይ የሚለው ነው?። መንግስት ስሆኑ ሊመልሱት ወይ ሰላማዊ መፍትሄ ሊሰሩለት ከሆነ አደጋ ባለው በሳት ውስጥ ዛሬ ለምን እናልፋለን?። በኔ እይታ ሀሳባቸው ያ ቢሆን ዛሬውኑ ይመልሱት ወይ በሁሉ ተቀባይ መፍትሄ አሁን ይኖራቸው ነበር።
መታወቅ ያለበት ነገ ዲሞክርያሲያዊ ለመሆን ስትሞክሩ ጥያቄው በነፃ መድረክ ፋፍቶ በሚሊዬኖች ይቀጥላል። ሲትጨፈልቁትና ሲታፍኑት አንባገነን ሆናችሁ ማለት ነው። ለማፈንና የተወሰነ አመት ደግሞ ለማስኬድ በገፍ መግደልንም ስለሚሻ ገዳይ አንባገነን ትሆናላችሁ ማለት አይደለም ወይ?። ይህን ደግሞ ከዛሬው አምርሬ እቃወማለው። መብት የሚከበረብት ከማለት መብትን መበለቱ መፍትሄ አይደለም?። ለኔ ያው አመል የሆነው ወዛድር ላባደር አድካሚ ሙግት ነው። አንድ ሚሊዬን ሆነው ሲጠይቁ የግለሰብን መብት ማክበር የመንግስታችን መሰረት ስለሆነ እናንተ ደግሞ ብዙ ስለሆናችሁ ወይ ያፍንጫችሁ ቅርጽ ስለሚመሳሰል ተለያይታችሁ ጠይቁ ሊባል ነው ማለት ነው።
በዚህ ምክንያት ተሰሚነት ያላቸው ተስፋም የማደርግባቸው የበዙትን ተቃዋሚ ድርጅቶች አሁን የያዙትን ወይ መፍትሄ የሚሉትን መንገድ ፈርቼዋለው። ፍራቻዬ በቀጣዬ ምርጫ ከስትራተጂ አኳያ አዋጭ ሆኖ ስላልታየኝም ነው። ያሸባሪ ህጉ ላይም ሆነ ያአባይ ጉዳይ ላይ ተቃዋሚዎች ካገዛዙ ጋር ካደረጉት ክርክር በቀጣይ በመጪው ምራጫ ከገዛዙ ጋር የሚኖሩ ከርክሮች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ስለወኩም ነው። ኮሌታ ይዞ ግርግዳ አስደግፎ የመሰለ ቁርጥ ያለ መልስ የሚሹ ጥያቄዎችን እንጠብቅ።
አሁን ያለውን ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላል መቃወም እንጂ መነሻ የሚሆን እንኳ አከላል የለም። ይዘውም ወደምርጫው አይገቡም። ውለዱ ግን ይኖራል። ቆያይቶ ቢሰራም ቆይቶ መምጣቱ በራሱ ኒይውትሮል ቦንብ ነው። በዛ ላይ ለሚሸነሽነውና ለሚለያየው ዜጋ ለምን እንዴት እንደሚጠቀምው ማስረዳቱ ካቅምና ከመድረስ አኳያ እግዚአብሄር ከናንተ ጋር ይሁን ነው የምለው። ተችሎም ተቀባይነት ማግኘቱ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው።
ድርጅት የግለሰቦች ስብስብ ነው። የኛ ድርጅቶች ደግሞ የስብጥራዊነት ችግር አለባቸው ። በቅርበትና በመተዋወቅም ነው። በንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ፖሊሲና እቅድ የሚወጣው ካለው ነባራዊ ሁኔታና አሸናፊ ማድርጉ ተሰልቶ ሳይሆን የሚመኙት፤ እንዲሆን የሚፈልጉትና ትክክል ነው ብለው ሚያስቡት ተፅኖው በበዛበት ይመስለኛል። አሁን አሁን አፈናውም ሚና እያደረገ እንዳለ እያየው ነው። ለዘጠና ሚሊዬን ያንድ አገር ልጆች ብንሆንም ልዬነትና የተለየ ብዙ…. ላለን የሚሆን ፖሊሲና እቅድ አለመቀመሩ በሗላ ብዙ አጣምረው የሚያዩ፤ ድምጽ የሚነፍጉ፤ አልፈውም የሚታገሉ አብዝቶ ይፈጥራል። ስለዚህ አሁን አሁን ያለውን አከላለል መንካቱ ትርፉ ኪሳራ ማጨድ ብቻ ሆኖ ነው የሚታየኝ። ለምርጫ ብቻ ሳይሆና ለሌች የትግል አማራጮችም በይበልጥም ለህዝባዊ አመጹም ሁሉ ድርሻ እንዲያደርግ ሳይሆን መሄዱ የሚፈለገውን ጉልበት አያመጣም። አሁን ያለው አከላል አይነካ የምለው ግን በዋናናት ዲሞክራሲያው በሆነ ስርአት ውስጥ ጠቃሚና ጎጂነቱ መጀመርያ መታየት ስለሚገባው ነው። መፍትሄ ብለን በቀጣይ የምናስኬደው ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ የልጆች ጫወታ መሆንም ስለሌበትም ነው። መሬት ላራሹ የወያኔው የዘር ፖለቲካ አይነት ስር ነቀል ለውጥ ከትርፉ ኪሳራው ትልቅ መሆኑን ስለማውቅም ነው።
ቆም ተብሎ እንደገና ይታሰብበት የምለው እየገሰገሰ በአለው ለውጡ በግርግር ያገር ሉአላዊነት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ። ከላይ የገለጽኩት አይነት አውዳሚ ትግል ውስጥ የማይከተን፤ ለዘውም በዜጎች መሀል። ትግላችንን ካገዛዙ ብቻ ጋር የሚያደርግና ጉልበት የሚያስገኝልን መፍትሄ ስላልሆነ ነው። በቀጣይም እንዳልኩት ዲሞክራሲን ያለችግር ለመተግበር ስለማያስችልም ነው። የመብት ጥያቄዎች ሊለጠጥ የሚችልበት የመጨረሻው ደረጃ ድረስ እንደው አንዴ ተለጥጧል። በቀጣይም ሁሌም ጥያቄዎች ብሶቶች ይኖራሉ። ከዚህ በሗላ የሚመጡትን ለመመለስ ካሁኖቹ አይከበዱም። ደግሞም ይኑሩ። አይኑሩምም አልልም። ጤናማም ነው። በአጠቃላይ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ የትግል አግባብ የሚቀጥሉበትን መንገድ ማበጀት እንደሚቻል ስለማውቅ። የተያዘው አያያዝ ወደዛ የሚገፋ ስላልሆነም ነው። ከዚህ መለስ መገንጠል የሚለውን የእብዶች ሃሳብ የሚያከስምና የወያኔን አንቀጽ 39 መሰረዝ ላይ መስማማት ላይ መድረስ በቀላሉ እንደሚቻል ስለማውቅ ነው። ባንዲራዉ ላይ ያስቀመጡትን አንባሻም ከድል በሗላ በክብር ማንሳቱም ላይ። ኢትዮጵያዊነታችንን በየወንዙ እየቆምን መጠየቁ መፍትሄ የማይሆነውን ያህል ለሁሉ ችግር ኢትዬጵያዊነት መልስም አይመስለኝም። ለኔ ወሳኝ ሰዎችችን እንጂ ኢትዬጵያዊነት የማይሸከመው የመብት፤ የማንነት.. እነዲሁ ፍላጎትና የማያስተናገድው ብሶት…የለም ብያለው። ብንወድቅ የሚያወድቁን አንድና አንድ ወሳኝ ሰዎቻችን ናቸው።
እንደገና ባግባቡ ይታሰብበት የምለው አሁን ካለኝ አጠቃላይ ያገራችን ፖለቲካ መረዳትና አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ከላይ የገልጽኳቸውን በወርቅ ሚዛን ሊመዘኑ የሚገባቸው አገራዊ ፋይዳዎች ዛሬ መፍትሄ ተብሎ የሚቀርበው ሀሳብ ውስጥ በመነሻ ደረጃ እንኳ ያስገባና የታሰበበት ሆኖ ስላልታየኝ ነው። የተያዘው አማራጭ ለውጥን ሳንፈራ መታገል እንዳላስቻለን እያየው ስለሆነም ነው። በዜጎች መሀል የበለጠ መጠላላትን መፈራራት በየቀኑ በሚያድግ ሲፈጠር ስላየሁ ነው።
የመብት ጉዳይ ላይ ሁሌም የትል ወገብ ነው ያለን ለማጣዎች ነን። ይባስ ብሎ ዛሬ ጠበን ስለተነሳን ከራሳችን እንዳንቃረን፤ ፈርተንና ድንጋጤም አለበት የሰሞኑን የስምንት አመት ህጻን ጨምሮ የንጹፈን ዜጎቻችንን ፍጅት ጠንከር ብለን መቃወም እንኳ አልቻልንም። እንደውም ደጋግመን ገድለናቸዋል። ለምን በዲዲቲ ከሚሉ ጀምሮ ዱላ ይዞ የሆነ ሰው አስገድዶ ያጻፋቸው የሚመስሉ የድርጅት የመግልጫዎች ጋጋታ፤ የዘር ፖለቲካ ነው። ዘረኞች ናቸው የትንታኔ መአት …ብቻ ሁሉም ስህተትም አሳዛኝም አስተዛዛቢም ነበር።
ለኔ የተፈጁት ኢትዬጵያዊያን ናቸው። ኦሮሞዎች ናቸው። የደሀ እናት ልጆች ናቸው። ዘመዶቼ ናቸው። ባታወቋችው ነው እንጂ ይህቺ አገር የሂወትና የደም መሰዋትነት ግድ ባላት ጊዜ ታላላቆቻቸው ሁሌማ የበዛ መሰዋትነት የከፍሉ ናቸው። የፈጇቸው የትግሬ ወያኔዎች ናቸው። የፈጇቸው ደስታን ስለሚሰጣቸው ነው። ጦርነትን ሰርተን ያህዬች ብለሀት መሆኑ ነው። በቀጣይም ምርጫ ብለው ሲሸነፉ ሊፈጅ ስላሰቡ ነው። ምርጫ የሚባል ነገር የለም ያባት ነው። እንደምትሸነፍ እያወክ ምርጫ ብሎ መግደል ያህያ ካልሆነ ሌላ ምን ይባለል። ለማንኛውም የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄያቸው ጥርት ያለ የመብት ጥያቄ ነው። ጥያቄያቸው ጥርት ያለ ህጋዊ ጥያቄ ነው። የዘር ፖለቲካ የደረግነው ተሳደድንና ተገደልን አይደለም ተሰደብን ብለው መቃወማቸው ትክክል ሲሆን አባቶቻችን መሬታቸው በዘረኛ በትግሬ ወያኔዎች እየተቀማ ባሬላ ተሸካሚ ለምን ይሆናሉ ብለው ጠየቁ ብለን ሙግት የገጠምን፤ የከፋንና ትንታኔ ያበዛን ጊዜ እኛ ነን። መወገዝ ባለበት ደረጃ ያወገዝንና ድምጻችንን ያሰማን ኢትዬጵያዊ ግዴታችንን ነው የተወጣነው። የሚያኮራን ነው። ወደተነሳሁበት።
እድሜ ለገዢዎቻችን ጫካ ቆይተው መጥተው ወደሗላ መልሰውን እንጂ የዛሬው መፍትሄ ያኔ ሊተገበር የሚችል ነበር። ላሁኑ አስተማማኙ መፍትሄ አሁን አንገብጋቢ ወሳኝና ግድ የሚል ፖለቲካዊ አቋም በመያዝና ጠጠር ያሉ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላማዊ ሽግግርን አረጋግጦ በቀጣዩ በጊዜ ሂደት በመሀበረሰብ ጠቅላላ እድገትና ማእከላዊ መንግስቱን በማጠንከር፤ በማስተማር መሄዱ አዋጭ ነው። የየትኛውንም ዜጋ የፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖር መብትም ሆነ የዘር ሀረግና የትውልድ ቦታ እያጣሩ ማፈናቀል በህግ አግባብ በቀላሉ ልክ ማስገባት የሚቻል ነው። ከሁሉ በላይ ይታሰብበት የምለው እንደዜግነቴ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ድምፄን ማሰማትና የተሻለ የምለውን የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረብ ግዴታ ስላለብኝም ነው። ጉረኛም ቢያስመስለኝ ሽግግሩን ችግር የሌለበት የሚያደርገውንና በጋራ የሚያታግለነን እንዲሁ የማያጠላላ መፍትሄ ካዛም ከዚህም ወገን ያለውን ሀሳብ አይቼ እኔም እንኳ መሀል ያለ መነሻ መፍትሄ ባንድ ገጽ ላይ አጣፍጬ ማስቀመጥ ስለምችልም ነው።
ከዛ ውጪ ጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪክ ላይ በቻ በመንተራስ መፍትሄ መስራት አይቻልም። ትናንት ላይመለስ ሞቷል። ይቁረጥ። ስድብና ንቀትን የሚገለጽባቸውን አገላለፆችን እየፈበረኩ መቀስቀሱም ሆነ አንዱን ዘር ሴጣን በዳይ፤ዘረኛ፤ ጠይ፤ ጨቋኝ በማድረግ ፍፅም ውሸትና መሰረት የሌለው ዘመቻ ማካሄድ መፍትሄ መስሎን እያደረግነው ካለን አይደለም። {የምምለስበት ቢሆንም እነዚህን አገላለጾች ብዙ ጊዜ ስንናገርም ሆነ ስንፅፍ የምንጠቀመው አውቀን ለርካሽ ፖለቲካችን እንዲያመችና ለሌሎች ያለንን ጥላቻ ለማሳየት አስበን አሳስተን ነው።} ይህ የሚደረገው ይህን ወይ ያንኛውን ክፍል በማሸማቀቅ ዝም ለማሰኘት ታስቦ ነበር ። የጅሎች መላ ስለሆነ አይሰራም። በዚህ ከቀጠለ ግን የሚያስፈጅ ወይ የሚያፈጃጅ መሆኑን ግን ማወቅ ሁሉም አለበት። እንደውም መልካም አሳቢ ዜጎች ሁሉ እየወጣን ወገንታዊ ሳንሆን ሀይ ካላልነው ሽግግሩን ያከብዳል። ለአብሮነታችንም አደጋ ነው። እዚህ ሀላፊነት የጎደለው ጸያፍ ተግባር ላይ ድርሻ የምታደርጉትን በሙሉ አጥብቄ አወግዛለው። ይህ በተደራጀና በተቀናበረ መንገድ የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች በግልፅ ያሳያሉ። በዚህ እውነት ፅሁፌን አበቃለው።
ዳዊት ዳባ
Dawitdaba@yahoo.com

No comments:

Post a Comment