Translate

Saturday, May 24, 2014

በኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞች የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ወሰኑ


eritrean refugees
በሺህ የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች የፕሬዚዳንት ኢሳያስን አስተዳደር በትጥቅ ትግል ለማስወገድ ጠመንጃ ካነሱ ተቃዋሚዎች ጋር ለመቀላቀል መወሰናቸውን ሱዳን ትሪቢውን ገለጸ። ውሳኔው የተላለፈው ኤርትራ ለ23ኛ ዓመት ድል በዓልን ተንተርሶ ነው።

ሱዳን ትሪቢውን እንዳለው የኤርትራን ስደተኞች መግለጫ በመጥቀስ እንደዘገበው ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አገሪቱን በአንድ ፓርቲ “በረግጠህ ግዛው” አስተዳደር ላለፉት 23 ዓመታት ገዝተዋል። ተያይዞም የአስመራው አገዛዝ በአገሪቱ ዴሞክራሲን፣ የሰብአዊ መብትን፣ ነጻነትን ማጎናጸፍ ባለመቻሉ ስርዓቱ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት መስማማታቸውን አመልክቷል።
“ከነጻነት” ማግስት የኤርትራ ተወላጆች እጣ ፈንታቸው ስደት፣ መሰወር፣ ጭቆና፣ እስር፣ ውርደት፣ ማስፈራራት እንደሆነ በመግለጫቸው ያመለከቱት ስደተኞች፣ “የኤርትራ ምድር እንጂ ህዝቦቿ ነጻ አልወጡም” ብለዋል። ጨቋኙ የኤርትራ አገዛዝ አሁንም በዜጎቹ ላይ አረመኔያዊ ተግባሩን ስለገፋበት ጊዜው በህብረት ወታደራዊ ርምጃ የሚወሰድበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሜይ 22፣ 2014 የወጣው የሱዳን ትሪቢውን ዜና ከላይ በተጠቀሱት ምሬቶች ሳቢያ በኮሌጅ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም ትግሉን ጠመንጃ በማንሳት እንደሚቀላቀሉ ማረጋገጣቸውን አመልክቷል።
“በዲሞክራሲያዊ መርህ የሚመራ መንግስት በኤርትራ በተአምር ይመሰረታል ብለን መጠበቅ አንፈልግም” ማለታቸውን የጠቆመው ሱዳን ትሪቢውን፤ ባለፉት አስር ኣመታት የኤርትራ የጦር ሰራዊት አባላት፣ የባህር ሃይል፣ ጨምሮ በ100 ሺህዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና የመን መሰደዳቸውን ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የአዲስ አበባ ተወካይ የሆኑትን ኪሱት ገብረእግዚአብሔርን ጠቅሶ ዜናው እንደ ገለጸው እስከ ሚያዚያ (ኤፕሪል) መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት የኤርትራ ተወላጆች 92,460 መሆናቸውን ዘግቧል፡፡
በአማካይ ቁጥራቸው 2000 የሚጠጋ የኤርትራ ዜጎች በየወሩ የኢትዮጵያን ድንበር እየተሻገሩ እንደሚገቡ፣ እነርሱም ከ18 – 50 ዓመት እድሜ ያላቸው ሁሉ እንዲሳተፉ የሚያስገድደውን ብሔራዊ ውትድርና የሚሸሹ መሆናቸውን ያመለከቱት ሃላፊ፣ ስደተኞቹ ከአስገዳጁ የወታደራዊ አገልግሎት ሌላ የፖለቲካ ጭቆና ሽሽት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያሰድዳቸው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment