Translate

Thursday, November 16, 2017

”እኛ ደህና ነን፣ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፣ የሚፈጠር ነገርም አይኖርም” ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻው የመንግስቱ ኃይለማርያም ባለቤት

Mengistu Haile Mariam
Mengistu Haile Mariam, Ethiopian army officer and head of state (1974–91)
መሳይ መኮንን
የቢሮ ስልኬን አነሳሁ። ወደ ሀራሬ ደወልኩ። ከወዲያ ማዶ ትህትና የተሞላበት የእመቤት፣ የወይዘሮ፣ የእናትነት ግርማ ሞገስ የተላበሰ ረጋ ያለ ድምጽ ተሰማኝ። ይሄን ድምጽ አውቀዋለሁ።

”ጤና ይስጥልኝ ማን ልበል?”
”ጤና ይስጥልኝ ወ/ሮ ውባንቺ ቢሻው። መሳይ እባላለሁ። ከኢሳት ዋሽንግተን ቢሮ ነው የምደውለው።”
”እሺ የእኔ ጌታ። ደህና ናችሁ?”
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስለምደውል አልረሱኝም። ትህትናቸው ይገድላል። ለጠብ የመጣን በፍቅር ማርኮ ይመልሳል። የቀድሞዋ ቀዳማይ እመቤትን ዘመን አልቀየራቸውም። ርቀት አለወጣቸውም። ደርበብ ያሉ ኢትዮጵያዊ እመቤት። ወ/ሮ አዜብ መስፍን ትዝ አሉኝ። ማወዳደር ይከብዳል።
የደወልኩት የዙምቧቡዌው መፈንቅለ መንግስት በኮነሬል መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ የሚፍጥረው ተጽእኖ ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ይዤ ነበር። መፈንቅለ መንግስቱ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በግልና በቢሮ ስልክ በርካታ መልዕክቶችን ተቀብዬአለሁ። በማህበራዊ መድረኮች የሚደረጉትን አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንብቤአለሁ። በአንድም ይሁን በሌላ ከኮነሬል መንግስቱ ወዳጆችም ይሁን ነቃፊዎች የሚሰነዘር ጥያቄ ነበር። እንደ ቢቢሲ አማርኛ ያሉ ደግሞ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የኮነሬሉ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለው የውይይት አጀንዳ ከፍተዋል። በእርግጥ ጥያቄው የእኔም ነበር። ለዚያም ነው ስልክ የደወልኩት።
”እኛ ደህና ነን። ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። የሚፈጠር ነገርም አይኖርም።”
”እንደው ኮነሬል መንግስቱን ላናግራቸው እችላለሁ?”
”አይ እሳቸው ለጊዜው በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አይፈልጉም። መስጠት ሲፈልጉ እኔ ራሴ እደውልልዎታለሁ። ይቅርታ እንግዲህ የእኔ ጌታ”
”አመሰግናለሁ ወ/ሮ ውባንቺ። እግዜር ይስጥልኝ።”
ተሰናበትኳቸው። ድምጻቸው በቀላሉ ከጆሮ አይጠፋም። ባለቤታቸውን አንቱ እንደሚሏቸው አውቃለሁ። ወደ ወንበሬ ተመለስኩና መረጃዎችን ማገላበጥ ጀመርኩ። ነገሩ ሌላ ሆነ። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች የቅርብ አማካሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ አገኘሁ። ከአንድ ዓመት በፊት በወጣ ዘገባ ላይ ኮ/ል መንግስቱ የተናገሩትን ላነበበ ይሄ ክስተት በቅርበት ሊመጣ እንደሚችል ይገምታል።
ኮ/ል መንግስቱ የዚምቧቡዌ ጦር ጄነራሎችን ከሰፊው የእርሻ ማሳቸው ድረስ እየጠሩ ያማክሯቸዋል። በተደጋጋሚ። ዚምቧቡዌ ከሙጋቤ በኋላ ምን መሆን እንዳለባት አቅጣጫ ያሳዩት እሳቸው መሆናቸው ይነገራል። የጄነራሎቹ የቅርብ ሰው ናቸው። ወታደራዊው ክፍል ስልጣኑን እንዲይዝና ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን በክብር እንዲያሰናብት የመከሩት እሳቸው ናቸው። በጥቅሉ ከሰሞኑ የዚምቧቡዌ ፖለቲካዊ ክስተት ጀርባ የኮ/ል መንግስቱ እጅ እንዳለበት የሚያሳዩ አስተማማኝ መረጃዎች አሉ።
እናም ኮ/ሉ ምን ሊሆኑ ይችላሉ ብለው በስጋትም ይሁን በደስታ አንዳች ነገር ሲጠብቁ ለነበሩ ከዚህ በላይ መልስ አያገኙም። ለነገሩ ኮ/ል መንግስቱ ውለታቸው ለዚምቧቡዌ ህዝብ እንጂ ለሮበርት ሙጋቤ አይደለም። መንግስት ቢቀያየርም ለውጥ አይኖርም።

No comments:

Post a Comment