Translate

Saturday, November 4, 2017

ህወሀቶች በማያቋርጥ ስብሰባ ውስጥ ናቸው / መሳይ መኮንን/

ህወሀቶች በማያቋርጥ ስብሰባ ውስጥ ናቸው። ልዩነታቸው ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ መጥቷል። የበላይነት ይዟል የተባለው በስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድን ከሳሞራ የኑስ ላይ ወታደሩን የመንጠቅ ሙከራው የተሳካ ባለመሆኑ አንዳቸውም አንጃ ገዝፎ መውጣት ተስኖት በር ዘግተው መጠዛጠዛቸውን ቀጥለዋል። መጨረሻቸው አጓጊ ይመስላል። ቦታ እየቀያየሩ የቀጠሉት ህንፍሽፍሽ ለኢትዮጵያ መፍትሄ ለማምጣት እንዳልሆነ ይታመናል። ከችግር ፈጣሪ መቼም የመፍትሄ ሀሳብ አይፈልቅም። የመለስ ዜናዊ አይነት ብልጣብልጥና ሴረኛ መሀላቸው ባለመኖሩ አንደኛው አንጃ ነጥሮ የመውጣትና ሌላኛው ደፍልቆ ለማንበርከክ ያለው እድል እጅግ ጠባብ ነው። ዝሆኖች ሲጣሉ ጥሩ ነው።

የህወሀቶች ህመም መድሃኒት ያለው አይደለም። ፈውስ የለውም። ጠራርጎ ሊወስዳቸው ከሚችል ጽኑ ህመም ጋር እየሰቃዩ ለመሆናቸው በርካታ ክስተቶችን ማሳየት ይቻላል። አንዱና ዋና የኦህዴድ ሰሞንኛ እንቅስቃሴ ነው። አንዳንዶች ቲያትር ነው፡ ያለህወሀት ፈቃድ ኦህዴድ ስንዝር መራመድ አይችልም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። እኔም ይህን አስተያየት ሙሉ በሙሉ ውድቅ የማደርገው አይደለም። ነገር ግን ህወሀት ከገባበት ማጥ፡ ከተዘፈቀበት አረንቋ፡ ከሚያሰቃየው ጽኑ ህመም፡ ስር ከሰደደው የእርስ በእርስ ፍጥጫ አኳያ ከተወሰደ ህወሀት ለማሴር፡ ቲያትር ለመስራት አቅም ያለው አይመስለኝም። ህወሀት ተዝረክርኳል። ሀገሪቱ ዝናብ እንዳበላሸው ሰርግ መላ ቅጧ የጠፋባት የሆነችው ያለምክንያት አይደለም።
ለህወሀት መዳከም ትልቁ ማሳያ አባወራው መብዛቱም ነው። ለውጭ ዲፕሎማቶች ግራ እስኪያጋባ ድረስ የትኛው አለቃ፡ የትኛው አዛዥ እንደሆነ አይታወቅም። የአራት ኪሎው ቤተመንግስት ያዘዘውን የካዛንቺሱ መንግስት የሚሽርበት፡ የመቀሌው አለቃ የወሰነውን፡ የአዲስ አበባው ቡድን የሚያፈርስበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሰንብቷል። የውጭ ሀገራት ዲፖሎማቶች ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ከየትኛው አካል ጋር እንደሚነጋገሩ አያውቁትም። ባለፈው የቃሊቲን እስር ቤት ለመጎብኘት አዲስ አበባ የገቡት ዲፕሎማቶች ከአቶ ሃይለማርያም ፍቃድ አግኝተው ቃሊቲ ሲደርሱ በሌላኛው ቡድን ቀጭን ትዕዛዝ ጉብኝታቸው ተከልክሏል። የቅርብ ጊዜው የአቶ በቀለ ገርባ የዋስ መብት ውሳኔ የተሻረውና በኋላም የታገደው በዚሁ ምክንያት ነው።
አረናዎች ዛሬ በመቀሌ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍም የህወሀትን አቅም ማጣት ከሚያሳዩ ክስተቶች አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ። ህወሀት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዲኖረው ፈጽሞ አይፈቅድም። ''መስመሪ ህወሀት መስመሪ ህዝበ ትግራይ እዩ'' የሚለው የእነመለስ ዜናዊ ዶክትሪን በትግራይ ምድር መቼም ህወሀትን የሚቀናቀን ፓርቲ እንዲኖር የሚፈቅድ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ሌላ ነገር እንዲያስብ ከቶም አይፈለግም። ህወሀትን እንደብቸኛ አዳኝ እንዲቀበል የህወሀት መዝገብ ውስጥ በስውር ተጽፏል። ከሌላው የኢትዮጵያ አከባቢ ይልቅ ትግራይ ለብዝሃነት ፊት ተነፍጓታል። ለአማራጭ ሀሳቦች እድል አልተሰጣትም። ህወሀትና ህወሀት ብቻ ትግራይ ምድርን ይሞሏት ዘንድ የህወሀት መጽሀፍ ቅዱስ ይደነግጋል። እናም አረናዎች ከነችግሮቻቸው ለትግራይ ህዝብ ያልተለመደ ድምጽ ለማሰማት የሚፍጨረጨሩት የህወሀትን መዳከም ተከትሎ ነው። ዛሬ በመቀሌ አረናዎች ይዘው የወጡት መፈክር የህወሀትን ዶክትሪን የሚወግዝ ነው። ''ህወሀትን ህዝቢ ትግራይን ዝተፈላለዮ 'ዮም'' - የትግራይ ህዝብና ህውሀት አንድ አይደሉም ነው ትርጉሙ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለስልጣናት ሀብት እያሸሹ ነው። የአንድ ስርዓትን የመቃብር ጉዞ ከሚያሳዩት አንዱ ይሀው የሀብት ሽሽት አሁን በስፋት እየታየ ነው። ህወሀት ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስ ተከትሎ በየቦታው የትግራይ ተወላጆች በስብሰባ ተጠምደዋል።በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ ለውስጥ የትግራይ ተወላጆችን መሳሪያ ማስታጠቅ መጀመሩንም የሚሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። የትግራይ ባለሀብቶች የወረሯቸው ትልልቅ የንግድ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዘዋል። ስጋት የገባቸው ባለሀብቶቹ ከሀገር ቤት ይልቅ እንቅቃሴአቸውን በባህር ማዶ አድርገዋል። በተለይ በበላይነት የተቆጣጠሩት የሪል ስቴት ቢዝነስ የቁልቁለት ጉዞ ለይ እንደሆነ ይነገራል። ብዙዎች ለመሸጥ እየሯሯጡ ቢሆንም የሚገዛቸው አላገኙም። ገንዘቡ ሌላው እጅ እንዳይኖር በማድረጋቸው የሚሸጡትን የሚገዛ አቅም ያለው ባለሀብት ለገኝ አልቻለም። በሌላው እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ነገሮች መከሰታቸው ይሰማል።
የኦህዴድ ጉዳይ
በዚህ ውጥንቅጥና ትንፋሽ በሚያሳጣው ፍጥጫቸው ውስጥ ሆነው ህወሀቶች የኦህዴድን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሞክረዋል። ግን የቻሉት አይመስልም። ኦህዴድ ከተሰመረለት ተሻግሮ ተጉዟል። ከጠርሙሱ ወጥቷል። በባለፈው ጽሁፍ እንደገለጽኩት የኦህዴድ አዲሱ እርምጃ የህወሀት ቲያትር ነው የሚል እምነት የለኝም። ህወሀት ተልፈስፍሶ ለማሴር አቅም ከየት ያገኛል? ቲያትር ለመስራት ይቅርና ለማሰብም እኮ አቅም ይጠይቃል። እነለማ ከማንም በላይ የህወሀትን ስስ ብልት ያውቁታል። በደህንነት መስሪያ ቤት አብረው ለሩብ ክፍለዘመን ገደማ እንደመቆየታቸው ህወሀትን አብጠርጥረው የሚያቁ ናቸው። እነለማ የህወሀት ትንፋሽ ሳስቶ፡ ጉልበቱ ዝሎ፡ አንድ ሀሙስ እንደቀረው እየተገነዘቡ በህወሀት ሴራ ተጠልፈው ቲያትር ይሰራሉ ለማለት በጣም ይከብዳል። ህዝብ ከዳር እስከዳር ተነቃንቆ የህወሀትን መንግስት ወንበር በነቀነቀበት በዚህን ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ እነለማ የህወሀት ድራማ ተዋናይ ለመሆን የሚፈቅዱ አይመስሉኝም።
ከባህርዳሩ የእነለማ ጉዞ ይልቅ የእምቧጭ አረምን ለመንቀል የኦሮሞ ወጣቶች ያደረጉት ዘመቻ ቀልቤን ገዝቶታል። ዛሬ ባህርዳር ላይ በሙዚቃ ዝግጅቶችና በጥናታዊ ወረቀቶች እየተካሄደ ያለው የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ኮንፈረንስ የካድሪዎች ጋጋታ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። የኦህዴድና የብአዴን እፍ ያለ ፍቅር ይልቅ የሁለቱ ኢትዮጵያውያን ልጆች የአንድነት ስሜት ትርጉሙ ከፍተኛ ነው።
ምንም እንኳን ኦህዴድ ከህወሀት አንጻር የሚገዳደር አቅም እየፈጠረ ቢመጣም ሜዳውም ፈረሱም ሊለቀቅለት አይገባም። መሪዎቹ ወንጀለኞች ናቸው። በመጨረሻው ሰዓት ሃጢያታቸውን የሚያሰርይላቸውን መንገድ ቢጀምሩም የመሪነትና የትግሉ የአርበኝነት መድረክ ሊሰጣችው የሚገባ አይመስለኝም። በጎ ተግባራቸውን ማወደስ እንጂ መሪ ሆነው ህዝብ ለለውጥ እንዲያበቁ ተስፋ እንዲጣልባቸው ማደረግ ተገቢ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ትግል ባለቤት ኦህዴድ እንዲሆን መፍቀድ ትልቅ የታሪክ ስህተት ነው። ኦህዴድ የራሱን የተበላሸ ታሪክ የሚያነጻበትን እድል ከመስጠት ያለፈ የመጪው ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪ ተዋናይ እንዲሆን የሚደረገው ሩጫ አደጋው ከፍተኛ ነው። ሌላው ቢቀር በኦህዴድ አስፈጻሚነት ባለቁት በሺዎች የኦሮሞ ልጆች ደም መቀለድ ነው። ኦህዴድን ማንገስ የእነዚያን ውድ ወገኖቻችን መስዋዕትነት ማራከስ ነው የሚል እምነት አለኝ።
የባህርዳሩ ኮንፍረንስ ብዙም ያልማረከኝ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረግው ስብሰባው ላይ ባሳለፈው ውሳኔ ነው። ቃል በቃልም ባይሆን ''በአባል ድርጅቶች መሃል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የእርስ በእርስ የመገናኛ መድረኮች በማመቻቸት ትግሉን በአዲስ ምዕራፍ መቀጠል'' የሚል ውሳኔ በዚሁ የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ተላልፏል። በግልጽ ቋንቋ ይህ ውሳኔ የባህርዳሩን ኮንፈረንስ የሚመለከት ነው። በዚህም አያበቃም። በቀጣይ የህውሀቱ ሊቀምንበር አይተ አባይ ወልዱ ከ1ሺህ በላይ ልዕካንን አስከትሎ ባህርዳርና አዳማ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ከሆነ የፖለቲካ ግርግር እንጂ ብዙዎቻችን እንዳወደስነው አንዳች አዲስ የለውጥ አየር እየመጣ አይደለም።
ኦህዴድ ወደ ባህርዳር ከማቅናቱ በፊት የራሱ ኮንፍረንስ አድርጓል። በወቅቱም ኦህዴድ እያደረገ ያለው ያልተለመደውን መስመር የምር እንድንወስድለት አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርግ አሳስበን ነበር። ነገር ግን የተለመደው የካድሬዎች ኳኳታና ግርግር ሆኖ ተጠናቋል። እነለማ የግል ስብዕናን ከማሳመር ያለፈ ለሰሯቸው ሀጢያቶች ማካካሺያ የሚሆኑ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ይጠበቃል። በብልጭልጭና ለታይታ ፍጆታ በሚሆኑ ግርግሮች የትም መዝለቅ አይችሉም። ይህ ሲባል እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ዋጋ የለውም ለማለት አይደለም። ከምንም እንደሚሻል መመስከሩ ተገቢነት አለው። በተለይ እነለማ በሚያስተዳድሩት የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትወርክ እየተላለፉ ያሉ ፕሮግራሞች ትልቅ ውዳሴና ምስጋና የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ስሜት ይገዛሉ። ተስፋ ይሰጣሉ።
እንደእኔም ሆነ አንዳንዶች እየገለጹት እንዳሉት ባለፉት 25 ዓመታት በህወሀት አቀናባሪነትና ፈጻሚነት፡ በኦህዴድ ተባባሪነት የተገነቡት የጥላቻ ግድግዳዎች እንዲፈርሱ ጊዜው አሁን ነው። እነለማ ይህን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ከኮንፈረንስና ስብሰባ ግርግሮች ባለፈ ወደመሬት የወረደ፡ ህዝቡ ውስጥ ዘልቆ የሚገባ የለውጥ መስመር በአፋጣኝ መዘርጋት አለበት። ለምሳሌ የአኖሌ ሀውልት እንዲፈርስ ማድረግ አንዱ አወንታዊ እርምጃ ነው። በእኔ እምነት የአኖሌ ሀውልት በአንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ለሚገለጸው ታሪክ እንኳን የሚመጥን አይደለም። የሚሉት የታሪክ ጠባሳ ተፈጽሞ ቢሆን እንኳን የጥላቻ ሀውልት መትከል መዘዙ ለትወልድ የሚተርፍ ነው። ክቡር የሆነውን የሰው ልጆ የሰውነት ክፍል በዚህ መልኩ አደባባይ ላይ መስቀል ለማንንም ትምህርት አይሆንም። እናም ይህን ጥላቻን ብቻ የሚያሳየውን ሀውልት ማንሳት ከእነለማ ቡድን የሚጠበቅ አንዱ እርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ
ወስኗል። ቆርጧል። ከእንግዲህ ወለም ዘለም የለም። በየትኛውም ቅርጽና መልክ የሚመጣን የህወሀትን መንግስት አገዛዝ አይፈልገውም። ለጥገናዊ ሳይሆን ለስርነቀል ለውጥ መስዋዕት ለመሆን ተዘጋጅቷል። ህወሀትን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዲያየው አይፈቅድም። በአራቱም አቅጣጫዎች የሚሰማው ድምጽ አንድ ዓይነት ነው ''ወያኔ በቃን''!!!!
የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው። ከእንግዲህ ለየትኛውም የማዛናጊያና ማታለያ እንቅስቃሴዎች እድል መስጠት አይስፈልግም። ህወሀት ቆዳ ቀይሮ እንደሚመጣ መጠበቅ አለበት። ተስፋ የሚቆረጥ ስርዓት አይደለም። ከመቃብር አፋፍ የተጠጋ ህወሀት እንዳያዘነጋው ነቅቶ መጥበቅ አለበት። እነለማ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ከሺህ ተግባራት እንደአንዱ መውሰድ እንጂ ብቸኛ የለውጥ ሃይል አድርጎ ልብን መክፈትና የወደፊትን መስመር አሳልፎ መስጠት ታሪካዊ ስህተት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

No comments:

Post a Comment