Translate

Friday, November 3, 2017

ብሱን እየገሰጠርን ከላችንን እናውልቅ (በነጋ አባተ)

በነጋ አባተ
Professor Berhanu Nega
1) ከዓመት በፊት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በዋሽንግተን ዲሲ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ንግግሩን በቀጥታ ስርጭት ከተከታተልኩ በኋላ “ብርሃኑ እንደቸርችል እኛ እንደ እንግሊዞች” በሚል ርዕስ ስር አንድ መጣጥፍ ማቅረቤን አስታውሳለሁ። ዘንድሮ በሲያትል ዋሽንግተን በተደረገው ስብሰባ የፕ/ሩን ንግግር ፊት ለፊት ቃል-ተአካል ተገጣጥመን ስለሆነ ብዙ ነገሮችን ለማስተዋል እድል አግኝቻለሁ። እንደ ዜጋ ከዚህ በፊት ደጋግሜ  ባቀረብኳቸው መጣጥፎቼ አንኳር አንኳር ናቸው የምላቸውን ፍሬ ሃሳቦች እየሸረከትኩ ወደ አንባቢዎቼ አምጥቻለሁ። በመክሊቴ ቆሜአለሁ ብዬም አስባለሁ። የቀረቡትን ሃሳቦች ወደ አትሮኑ አስጠግቶ ማድቀቅና ማላም ደግሞ  የፖለቲካውን መዘውር ለመያዝ የሚያታትሩት ወገኖች ድርሻ ይመስለኛል።

መጥፎ አጋጣሚ ሆነና ይህን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት በዚህ ጊዜ ደግሞ በየጣራችን ስር በእንባ የሚያራጨንን፤በትካዜ ድባብ ከታዛችን የሚለጥፈንን ተደራራቢ ሃዘን ከኢሊባቦር፤ ከካማሽ አካባቢዎች ተቀብለናል ። አዎ የኢትዬጵያ ምድር እስከ አርአያም የደረሰ ከውኃ እንባ እስከደም እንባ ፈስሷል…….!። በህወኃት ባለሟሎች ሴራ የሚገፋው ይህ ማዕበል ምድራችንን የደም ከል እያለባሳት ነው። እኛንም የት ተነስተን የት መርገጥ እንዳለብን ሚዛን የሚያሳጡ ተግዳሮቶች እየገጠሙን ነው።
በምድር ዘመን ጥቂት ቆይታው ከዘመኑ በላይ የሰራውና ነገሮችን አርቆ የማየት ልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ነበረው ተብሎ የሚነገርለት  Randolph Bourne / ራንዶልፍ ቦርነ / “ War is the health of the state” በሚል ርእስ ስር  በጻፈው ዝነኛ ጽሁፉ እንዲህ ብሎ ነበር “የመንግስታት ሰዎች በረብ የለሽ ምክኒያት ጦርነት ያስነሳሉ ያንጊዜ  ግን እነርሱ መፍካት ይጀምራሉ። ጀግኖች ተብለው የሚሾሙ ይበዛሉ። ሌሎች የመደብ ትግል ጩኽቶች ግን ፀጥ ይላሉ። ወጣት ወንዶችም በየጦርሜዳው  እንደጧፍ ይቀልጣሉ።”  እውነት ነው። ይህ አጥፊ ዘዴ በዕብዶች ቤተ መንግስት እንደጉበና በጓዳ በኩል ጉብ ብሎ መታየቱ የተለመደ ነው እሱ ነዋ እረፍታቸው!። ለሚያሽከረክሯቸው አጋንንቶች የደም ግብር ካልሰጡ ያምሷቸዋል እንቅልፍ የላቸውም። ይህ ልክፍት ደግሞ ዘመን፤ ተራራ፤ድንበር አይወስነውም ተመቻችተው ለተገኙለት እንደ ዛር ነው ይጎመራል።
እንዲህ ዓይነት በህዝብ ላይ የሚደረግ ፌዝና ቁማር ናላውን ያዞረው ሌላኛው በለንደን የሚታታመው ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው  Paul Fussell’s እንዲሁ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ አካባቢ “The great war and modern memory” በሚል ሼንቋጭ ገቢረ-ቅኔ ርዕስ ስር ባቀረበው መጣጥፍ እንዲህ ነበር ያለው። ግሩም ርዕስ!።
“ምን ማድረግ እችላለሁ?
በዚህ ታላቅ የምሬት ቀንስ ተራው ህዝብ ምን ሊፈይድ ይችላል?
ደስተኛ እና ፍልቅልቅ መሆን?…… ( አሁንም ከህሊናው ጋር ይሟገታል)
አንተ ግን በጦርሜዳ ስለሚዋደቁ ጓደኞችህ በድፍረት ፃፍ። ተራና ከንቱን ሃሜት አትድገም፤ መሰረት የሌለውን አሉባልታም አትስማ ደግሞም ከሄግ በላይ አዋቂ ነኝ ብለህ አታስብ……..
ብቻ  ምን አለፋችሁ ይሟገታል እናም ጸሃፊው ግራ ተጋባ ብዕሩ ከህሊናው መንገራገጭ የተነሳ ተንተፋተፈች፤የሚመዛቸው ሃረጎች  ከወዲያ ወዲህ የሚወዛወዙ መሰሉ። ምክኒያቱም ከሃምሌ እስከ ጥቅምት 1916 ብቻ በጦርሜዳ የተሰውት የእንግሊዝ ወታደሮች ብዛት ከ300 ሽህ በላይ ነበር። ህዝቡ ግን ከሁኔታውና ከሃዘኑ ሩቅ ይመስላል በሃገሪቱ በልዩ ልዩ ስፍራ ሆን ተብለው በሚደረጉ ዝግጅቶች በመታደም ጊዜውን ያሳልፋል ይባስ ብሎም ጦሩን በበላይነት የሚመራው ጀኔራል ዳግላስ ሄግ ማርሻል ተብሎ ተሾመ፤ተሸለመ። እውሸት ነግሶ ነገር በዕብዶች ሲደበላለቅ ዘመነ ግርንቢጥ ይሉሃል ይህ ነው። ለዚህ ጋዜጠኛ  ከየጦር ሜዳው የሚደርሱት መረጃዎች ሌላ በህዝቡ መሃከል የሚከናወነው ሌላ እናም እውነትን የምትተነፍሰው ነፍሱ አየር ላይ ተንጠለጠለች።
በሽበታቸው ደርዝ የማይገኙትን የእኛን ሃገር የነፍስ ጎረምሶቻችንንና የህወሃት ፊታውራሪዎችን እንመልከት። መራራን ነገር በህዝብ መሃከል ሲሰሩና ሲበትኑ እንዲህ ዓይነትን ታላላቅ ድግሶች፤ ኮንሰርቶች አዕምሮአችንን ለማደንዘዝ እንደሚጠቀሙ ማስተዋል ተገቢ ነው። ያኔ የሼሁ ኖቶችም ከህሊናቸው ለራቁ ነጭ ለባሽ የኪነጥበብ ሰዎች መመንዘር ይጀምራሉ። አዎ! ደፋሮቹና የሉሲፈር ምሩቆቹ የህወኃት ሰዎች ሆን ብለው በመቆመር በህዝብ ላይ የሃዘንን ናዳ ከናዱ በኋላ ወዲያው በቁስሉ ላይ ሌላ እንጨት ልከው ሃዘኑን በሃዘን ያቆሳስሉታል። እንዲያውም በእንዲህ ባለ ሰሞን ዘረኝነታቸውን ያጎሉታል። በደም የጨቀዩ እጆቻቸውን ዘርግተው ለከርስኪ ለገጽኪ እያለ ከሚኖረው የሆድ እድምተኛና ከቀለም ከተጣላው የጦሩ ክፍል ወደ መድረክ እየጎተቱ በማምጣት ሹመት በሹመት ድግስ በድግስ ያደርጉታል።
አንዳንድ ጊዜ ለሹመት ወደ አደባባይ ከፍ የሚያደርጓቸውን ሰው መሰል ሰዎች ስመልከት ለፋሲካ የተዘጋጁ የእርድ ከብቶች ይመስሉኛል ሲጠሩ ከተፍ ብለው ዓይናቸውን ከማቁለጭለጭ ውጭ ለምን? እንዴት? ብለው ለመጠየቅ አቅም ያላቸው አይመስሉም ነገ መልሰው ሲቀሟቸውም እንዲሁ አይጠይቁም። ሲደመድሙም በአስረሽ ምችው ያቀልጡታል። በዚህ ጊዜ ነው እውነተኛ ጸሃፊዎችና  የኪነጥበብ ሰዎች የሚፈተኑት፤ ለምን? ስራቸው የምስክርነት ሰራ ነውና !። እናስ ጸሃፊው ምን ብሎ ይጻፍ? ዜመኛውስ ምን ብሎ ያዚም? ከህሊና ጋር ተጣልቶ ከዕብዶች ጋር በዕርኩሰት መዋሰብ ? ወይስ ለእውነት መስክሮና ከህሊና ጋር ታርቆ መቆም? ምርጫው ሰው በመሆን እና ባለመሆን የሚደረግ ምርጫ ነው። እያልኩ ያለሁት የደደቢቱ ዛር ሰከን የሚለውና ፈረሶቹም እረፍት የሚያገኙት ለጌታቸው በሚያቅርቡት የደም መስዋዕትና  አንጀታችንን እየፋቀ ከሚወጣው እንባችን ስር ነው።
የወቅቱ ድባብ የሚነግረን ሁላችንም ሃገራችን ወደየት እንደምታመራ እርግጠኞች ያልሆንበት፤ ሊሞት አፋፍ ላይ የደረሰውንና አቅሙ ከድቶት የሚንጠራወዘውን ይህንን አስከፊ ስርዓት ለመግፋት አቅም ያላዳበርን መሆናችንን በገሃድ የወጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እውነቱ ላይ ቆመን ስንነጋገር አሁን ባለንበት ሁኔታ ወያኔ በመንበሩ ላይ የተቀመጠው አቅም ሰላለው ሳይሆን በእኛ አቅም ማጣት ብቻ ፈሩ ህወኃት እየተንገዳገደም ቢሆን መቆሙን ነው። ሃገርና  ህዝብም  የመንግስትነት ባህሪ በሌለው ጨካኝ ቡድን ስል ጥፍሮች እየተገሸለጡና መድኅን ያጡ የሰቆቃ ዋይታዎችንም እያደመጥን ግን ደግሞ መድረስ ያልቻልንበት ጊዜ ላይ ነን። ፤ ቡድኑ   ለ27 ዓመታት በጎነጎነው ሴራ ተጠላልፎ የወደቀበት ስዓት ላይ ነው ያለነው። ይህንን አቅም ማጣቱን እንዳይታወቅበት ደግሞ በአጨናባሪ ስልቱ  የመስዋዕት በጎችን ማዘጋጀትና ድግስ ደግሶ ችርስ ማለት ቀጣይ ትዕይንቶቹ እንደሚሆኑ  መገመት አያዳግትም። “አለን ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ለማለት ነዋ”። እንንቃ!!! እኛ ወደ እኛ  እንመልከት በተራ ሙገሳ ተልካሻ ስዕብናን ለመገንባት ደፋ ቀና ከማለት ይልቅስ እውነትን እየተነጋገርን ከልብ በሆነ መተሳሰብ  እጅ ለእጅ እየተያያዝን የምሬታችንን ዘመን ብናሳጥረው ይበጀናል።
እዚህ ላይ ልድገመው ወቅቱ አንዳችን በአንዳችን ላይ አቃቂር የምናወጣበት ጊዜ ሳይሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገርን  ከጥፋት ህዝብን ከመከራ ለመታደግ የምንሮጥበት ጊዜ ላይ ነን። ሁላችንም መሪዎችልንሆን አንችልም። ሁላችንም ፊተኞች ልንሆን አንችልም። ይህ ወቅት ሃገርንና ህዝብን ከጥፋት ለማዳን የምንተጋበት ጊዜ እንጅ፤ ለግል ዝና ላይና ታች የምንልበት ጊዜ ላይ አይደለንም። የራስን ዝናና ጥቅም በማስቀደም እኔ ከሌለሁበት ሁሉም ነገር ገደል ይግባ ዓይነት ከአህያዋ አስተሳሰብና አባባል ላይ የቆምን ወገኖች ብንኖር ፈጥነን እንንቃ። ከእንሰሳነትም ወደ ሰውነት እንመለስ። አይናችንን ከራሳችን ጥቅምና  የወንበር ምኞት ላይ አንሰተን እጆቻችንን ለመልካም ስራ እየዘረጋን በመንፈሳችን ኤሎሄ የምንልበት ወቅት ላይ ነን። እናስተውል ሁሉም በሃገር ነው!
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ ፕ/ሩ  በሲያትሉ ንግግራቸው ወቅት በኤርትራ ስለተካሄደው ጉባኤ ለተሰብሳቢው በሚገባ መልኩ ገልጠዋል። ጉባኤው ብዙ ነገሮችን የዳሰሰ፤ አሰራሮችንም እንደገና ያነጠረ እንደሆነ ነግረውናል። እንደ ንግግራቸው በጉባኤው የተከናወኑትን ስራዎች እንደ አንድ መርከብ መስየዋለሁ። ድርጅቱ በገነባው በዚህ መርከብ ውስጥ አራት ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉትና እነርሱም ሁለቱ ከናፊ፤ ሁለቱ ደጋፊ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ከዚህ በፊት ስለአርበኞች ግንቦት ሰባት ያለኝን  ድጋፍና ለመሪዎቹ ያለኝን አክብሮት አቋሜን በግልጽ ገልጫለሁ ትላንትና እንዳልኩት ዛሬም እደግመዋለሁ የድርጅቱ አባል ግን አይደለሁም። ድርጅቱን የምደግፈበት ዓቢይ  ምክኒያቶች ግን አሉኝ። አንደኛው የድርጅቱ መሪዎች የመረጡት የትግል መስመር በጋለ የሰይፍ ስለት ላይ በጫማ በላመ እግር የመራመድ ያክል ለምጣጭ ቢሆንም እንኳን ለዚያ ያሳዬት ቁርጠኝነት ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ አግ 7 አሁን ካሉን የተቃዋሚ ኃይላት መካከል በክብ ዙሪያ እግሮቹን ለመትከል ጥረት የሚያደርግና የተሻለ ብቃት ያለው  ድርጅት በመሆኑ ነው ። የአግ7 መሪዎችንም ሆነ ድርጅቱን ለመቃወም እነርሱ የሄዱበትን መንገድ መሄድ ያስፈልጋል። እንኳን እንደ አግ7 ዓይነት ጠንካራ ድርጅታዊ አወቃቀር ያለውን ድርጅት ይቅርና በቅንነትና በእውነት ለተነሱም ይሁን ለሚነሱ አዳዲስ ድርጅቶችም ቢሆን አንደኛው የሌላኛውን የነጻነት ትግል እስካልጎዳና ወያኔያዊ ተልዕኮ እስከሌለው ድረስ መደገፍ ይገባናል ብዬ አምናለሁ። ይህን ስል ግን የአግ7 መሪዎቹና ድርጅቱ “ምልዑ በኩሉሄ “ ናቸው እያልኩ አይደለም። ይሁን እንጅ የሄዱበት መንገድ ሩቅ ነውና የሚጠበቅብን ክንዳቸውን መደገፍ ነው።  ይልቅስ በማይሆን  አታካራ ጊዜአችንን ከምናጠፋ ሃገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝበን አግ7 በገነባው መርከብ ላይ ያልተደፈኑ ብሶችን እየገሰጠርን የድላችንን ጊዜ ብናፋጥን  ይበጀናል ለማለት ነው።አሁን ያለንን አቅም ሳንወሻሽ ከመረመርን ሁላችንም  አግ7  ወደ ጀመረው ጅምር ስራ በአንክሮ ልንመለከት የሚያስገድደን ጊዜ ላይ ነን። አዎን በዚህ አግ7 በገነባው ጅምር የመርከብ ውቅር ላይ ሁላችንም እጆቻችን አንስተን ልንረባረብ ይገባናል!።
ሁላችንም እንደምናውቀው በኖህ ዘመን በምድሪቱ ላይ የጥፋት ውኃ ከሰማያት በታዘዘ ጊዜ ኖኅ ከመለኮት ድምጽ ተካፋይ ስለነበር በደረቅ መሬት ላይ መርከብ ለመስራት ከእንጨትና ከብረት ጋር ትግል ገጥሟል። በሌላ በኩል ሰዎች ከልክ ባለፈ መረንነት ይታመሱ የነበረበት ዘመን ነው ይባስ ብሎም ወደ ኖህ መጥተው አንተ እብድ ይህንን የሰማይ ስባሪ ያክል መርከብ የምትሰራው  ለምንህ ነው ብለው አንባረቁበት፤ጮኹበትም። እርግጥ ነው እብድ ይሰኛል  ሰው  እንዴት በደረቅ ምድር ላይ መርከብ ይሰራል? ግራ የሚያጋባ ነው። ግን ከሚታየው ዓለም ወጥቶ ወደ ማይታየው መንፈሳዊ ዓለም መዝለቅና የዘመኑን ሃሳብ ተናጥቆ ማምጣት መንፈሳዊ ጀግንነትን ይጠይቃል። እውነቱ ይህ ነው ወይ ከመለኮት ጥበብ ጋር መመሳጠር ወይ መንፈሳዊ ጀግኖችን ማቅረብ።
አሜሪካኖቹ አፍሪካውያንን በተለይም እኛን በሚመለከት ያላቸውን አቋም ለጊዜው ተወት እናድርገውና እነርሱን በተመለከተ ግን ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ያላቸውን የልብ ክፍትነት ሳይ እቀናለሁ። ሁላችንም በስም የምናውቃቸው የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን የተናገሩትን ልጥቀስ “ It is impossible to rightly govern a nation without God and the bible” ብዙዎቹ የአሜሪካ ፕሪዚዳንቶች እግዚአብሄርን በተመለከተ የተናገሩትን ለመጥቀስ ጊዜ የለም እንጅ አስገራሚ አስገራሚ ንግግሮች አሏቸው። አሁንም ድረስ ለመንፈሳዊ ነገር ትኩረት መስጠታቸውን የምታወቁት በሆሊይውድ የሚመረቱትን መንፈሳዊ ፊልሞች መመልከት በቂ ነው። አሁንም እንኳን  ነገ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ይገጥመናል ብለው  ይሰጋሉ እናም መፍትሄ ነው ያሉትን ለማዘጋጀት ይደክማሉ። ክብዙዎች ጥቂቶችን ለመጥቀስ The day after tomorrow, Left Behind, The independence day and Close encounters ናቸው። በተለይም  ክሎዝ ኢንካውንተርን ሙቪ ስንመለከት መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በሰዎች ህይወት እና በሃገር ደረጃ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል እንረዳለን የኖኅ ህይወትም ወለል ብሎ ይታየናል። ጆርጅ ዋሽንግተን እንዳሉትም ሃገርና ህዝብ በአዕምሮ ብቻ እንደማይመራ በምንኖረባት ምድር መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት እንዳለ ልብ እንድንል ያስችለናል።
ከንጉስ ኃ/ ስላሴ ጀምሮ ወደ ኋላ የነበሩትን መሪዎች ስንመለከት ከህዝብ የሚመጡትን ሃሳቦችም ሆነ መንፈሳዊ መልዕክቶችን በፈሪሃ እግዚአብሄር ለመቀበል ልባቸው ክፍት ነበር። ሌላው ሳይቀር እረኛ ምን አለ? ብለው ይጠይቁ ነበር። ይህ እረኛ ምን አለ የሚለው ባህላዊ ቅርስ ደግሞ ክርስቶስ በቤተልሄም በተወለደ ጊዜ የመላዕክቶችን ዜና የሰሙትና የምስራቹን ይዘው ወደ ከተማ የገቡት እረኞች ስለነበሩ ከዚያ ታሪካዊ አመጣጥ ጋር ተያይዞ  የመጣ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለእረኞች መለኮታዊ ነገር ይገለጥላቸዋል ተብሎ ይታመናል። አባቶቻችን ይህንን ያክል ሄደው ለመስማት ልባቸው ክፍት ነበር። እኛ ግን ስልጣኔ መስሎን የእኛ የሆነውን ሁሉ ናድነው። እንደ ምሳሌ ስናነሳ ጋሽ መስፍን ( ፕሮፌሰር) በዚህ በኩል ሃገር በቀሉን የትምህርት ስርዓት መናድ እንዳልነበረብን በንስሃ መልክ ሲናገር ሰምቼአለሁ። መሪዎቻችንን እንደጋሽ መስፍን ያሉ መጭውን ማስተዋል የሚችሉ ሰዎችን ምክር ቢሰሙ ኖሮ ዛሬ በእንዲህ ዓይነት እጅና እግሩን ባጣ ውድቀት ላይ አንገኝም ነበር። ጆሮ ያለው ይስማ ነው።
ለማንኛውም ከዚህ ቀደም እንዳልኩት  እንደ አግ7 አይነት ህዝባዊ አደራን የተቀበሉ ንቅናቄዎች ከህዝብ የሚመጡትን ጠቃሚ ምክሮች የምታስተናግድ ትንሽ መስኮት ማዘጋጀት አንዳለባቸው በድጋሜ ለማሳሰብ ነው።  በሁለት አቅጣጫ ይጠቅመናል አንደኛውና ቀዳሚው ድርጅቱን በበለጠ ህዝባዊ ባህሪ እንዲላበስ ያደርገዋል። ሁለተኛው ደግሞ የአግ7 መሪዎች ያላዬትን ለማየት ሌላ ተጨማሪ ዓይንን መጠቀም ነው። ይህ የህዝብን ሃሳብ ያለመቀበል የልብ ድንዳኔ ደርግን ያጠቃ ብሎም ህወኃትን የገደለ አዚም ነውና ይህንን የአምባገነን ባህሪ አብሮን እንዳይሻገር ከወዲሁ ልንቀብረው ይገባል። ማርከሻው ደግሞ በባህላችን ትልቅ ስፍራ የነበረውን የመከባበር ዘንግ ማንሳት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መሪዎች ለህዝብ ጆሮን ካልሰጡ፤ ህዝብ በቅንነት ለመሪዎቹ ካልተገዛ ሃገርም ሃገር አይሆን ህዝብም ከመከራ እንባ አያባራ።
ፕ/ሩ በሁለት ትላልቅ የማህረሰብ አምዶች ላይ የገባቸውን ያክል ማብራሪያ ሰጥተዋል በቤተ ዕምነቶችና በኪነጥበብ ጉዳይ!። ወደ ማብራሪያቸው ጠልቄ አልገባም መሆን ስላለበትና አግ7 ገንዘቡ ማድረግ ስላለበት ነገር ብቻ  ግን ልናገር። እዚህ ላይ አንባቢያንን አንዴ ቆም ላድርግና አንድ ጉዳይ ላይ ትንሽ እንድናስብ  ልጋብዝ እስኪ ከዚህች ዓለም መንፈሳዊነትና ኪነጥበብ ቢወሰዱ ይህች ዓለም ምን ትመስላለች?። ከአዕምሮአችሁ ጋር ልተዋችሁና ልቀጥል።
መንፈሳዊ አባቶችን ስለማማከር፦ መንፈሳዊ አባቶችን ስንል የሁሉንም ቤተ እምነት መሪዎችን የሚያጠቃልል ስብስብ ማለታችን ነው። የምንኖረው በ22 ኛው ክ/ ዘመን ነውና አንዱን ዕምነት ከሌላው በማበላለጥ አንዲትም ጋት ፈቀቅ ማለት አይቻለንም ዘመኑን መረዳት ደግሞ የግድ ይላል። አንዲት ሃገር የቤተ እምነቶችን  ምሰሶ ነቅላ ከጣለች ልትረጋጋ አይቻላትም ምክኒያቱም ወደንም ብጠላንም፤ገባንም አልገባንም የምንኖርባት ዓለም ከመንፈሳዊው ዓለም ተፅዕኖ ነፃ አይደለችም። በአዕምሮአችን ብቻ የማንመልሳቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉና መንፈሳዊውን ዓለም የሚያስተውሉ ሰዎች ያስፈልጉናል። እርግጥ ነው ያለንበት ዘመን ሉሲፈር ጉልበት ያወጣበት ዘመን በመሆኑና በቤተ እምነቶችም ያሻውን የሚፈጽምበት ጊዜ ላይ ስለሆንን እውነተኛ መንፈሳዊ ሰዎችን ማግኘት ይቸግር ይሆናል። ግን አሁንም በዚህ ክፉ ዘመንም ቢሆንም እንኳን እነዚያ እውነተኞቹ አባቶች አሉ። ይህንን በሚመለከት ለአግ7  ስራ ማብዛት እንዳይሆን እንጅ ከየእምነት ቤቶቹ የተውጣጣ አንድ የመማክርት ጉባኤ ክንፍ ቢኖረው ድርጅቱ ውበት ፤ሞገስ ይደረብለታል እንጅ ኪሳራ የለውም። የተረጋጋ ሰው አይደለም የምንለው ዶናልድ ትራምፕ እንኳን መንፈሳዊ አማካሪዎች አሉት ከእነርሱ  ውስጥ አንዷ ፓውላ ዋይት ናት።
በዚህ አጋጣሚ ኢትዬጵያ በመለኮት ያላትንና  ሁለት የማውቃቸውን ምስክርነቶች ለአንባቢዎቼ ላካፍላችሁ ወደድኩ። እርግጥ ነው መንፈሳዊ ነገር አዋቂ ነን ለሚሉት ሰዎች ሞኝነት እንደሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ቢነግረንም የምናውቀውን ከመግለጥ ግን ወደኋላ አንልም።  ከተወለድኩበት ከተማ ከጎንደር ሳልወጣ አንድ አባት ከዋልድባ ገዳም የግል መልዕክት ሲኖራቸው በመንፈስ እየተነዱ ወደ ጎንደር ይመጡ ነበር። ከጥቂት ጉደኞቼ ጋር ሆነን ሁለት ታላላቅ ጉዳዬችን ከአንደበታቸው ሰምተናል። አንደኛው መልዕክታቸው በ1978 ዓም ነው “ይህ መንግስት” አሉ የደርግን መንግስት ማለታቸው ነው “ የሚወድቀው በ1983 ነው” አሉን ። በጊዜው ለመልዕክቱ ምንም ትኩረት አልሰጠነውም ነበር ምክኒያቱም ሊሆንም ላይሆንም ይችላል በሚል ማለት ነው።  ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጡ በጣም ተጎሳቁለውና አዝነው አገኘናቸው ዘመኑ በ1981 ዓ.ም ነበር። እናም ያለማቋረጥ ያለቅሳሉ “ምንድነው ምን ሆኑ ብለን?” ጠየቅናቸው። ከጥቂት ቆዪታ በኋላ መልሳቸውን ነገሩን “ በኢትዬጵያ ምድር ላይ አንድ ታላቅ መልዓክ ቆሞ አየሁ። ፊቱን ወደ ሰሜን ዞሮ መልዓኩ ያለማቋረጥ ያለቅሳል ከዓይኑ የሚወጣው እንባም የደም እንባ እንጅ የውሃ እንባ አልነበረም። ሰውነቴ ተጨነቀ፤ ምነው ለምን ታለቅሳለህ? ብዬ ስጠይቀው ‘ስለኢትዬጵያ አለቅሳለሁ” ብለው እለቅሶአቸውን ቀጠሉ። ሲጨርሱም “በሉ እግዚአብሄር ከእናንተ ጋር ይሁን እንግዲህ በምድር አንገናኝም” ብለውን ተለያየን ከዚያ በኋላም አልተገናኘንም። እኒህ አባት ወደ ዚያኛው ዓለም የተሻገሩ ይመስለኛል። መልዕክቶችን ግን በጥንቃቄ እንመልከታቸው።
ሌላውና ሁለተኛው መንፈሳዊ ሰው  ዴሬክ ፕሪንስ ይባላሉ በዓለም አቀፍ የወንጌል አገልግሎት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሰው ናቸው። እኒህ ሰው ስለ ፆምና ጸሎት በፃፉት መጽሃፋቸው እንደገለጡት “ለጥቂት  ቀናት ኬንያ ውስጥ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ሆነን በፆምና በጸሎት ነበርን ወቅቱ (በኢትዬጵያ አቆጣጠር በ1965 ዓም አካባቢ ነበር) በጸሎታችን ወቅት አንድ ራዕይ ወደ እኛ መጣ ። ከሱማሊያ አቅጣጫ  ጥቁር ሙሉ ልብስ የለበሰና ከላይ ቀይ ካባ የደረበ አንድ ሰው ወደ ኬንያ  በፈረስ እየጋለበ ይመጣ ጀመር። ለጊዜው በፀሎት የነበርነው ሰዎች የግዚአብሄር መንፈስ ፍቺውን እንዲያበራልን መጸለይ ጀመርን የእግዚአብሄር መንፈስም የኮምኒዝም መንፈስ ነውና ጸልዪ አለን እኛም ተግተን መጸለይ ጀመርን ያ በከፍተኛ ፍጥነት ሲጋልብ የነበረው ሰው ፊቱን ወደ ኢትዬጵያ ዞረ ኢትዬጵያ ውስጥ ምን እንደሆነ አይተናል” ይሉናል። ጆሮ ያለው ይስማ ነው!!!። እነዚህ መንፈሳዊ መልዕክቶች በኔ ዘመን የተፈጸሙ በመሆናቸው ለአንባቢያን አቀረብኳቸው እንጅ በመጽሃፍ ቅዱስ መንፈሳዊ አባቶች መንፈሳዊ መልዕክቶችን  ይዘው ወደ ሃገር መሪዎችና ወደ ህዝብ ይመጡ እንደነበር ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። በቅዱስ ቁርዓንም ይህ ሁኔታ እንደሚኖር እገምታለሁ። አሁንም ጆሮ ያለው ይስማ ነው!!!።
2) የኪነጥበብ ድርሻ፤- የብዙ ሰዎች ችግር ወደ ስልጣን ማማ ሲመጡ ሁሉን የሚያውቁ ይመስላቸዋል  ይህ በሽታ ደግሞ እኛን ኢትዬጵያውያንን በጣም ጎድቶናል። ታውቂው የኪነጥበብ ሙያተኛ ወዳጄ ጋሽ መርዓዊ  ስጦት ያጫወተኝን ላካፍላችሁ ወደድኩ። ጋሽ ተስፋዬ ገሰሰ የብሄራዊ ቲአትር ስራ አስኪያጅ በነበረበት ጊዜ የደርግ ሰዎች ለአንድ ዝግጅት ይጣደፋሉ ለገሰ አስፋው ወደ ብሄራዊ ብቅ ይልና እንዲህ አድርጉት ፤ በዚህ አውጡት በዚህ አግቡት ማለት ሲጀምር ጋሽ ተስፋዬ ብድግ አድርጎ  “ለገሰ ሙያውን ለኛ ተወው ለመቼ እንደምትፈልጉን ብቻ ንገረን” ብሎ እንዳሰናበተው አጫውቶኛል። በፖለቲካው አካባቢ የዜግነት ድርሻችሁን ለመወጣት ደፋ ቀና የምትሉ ወገኖች ይህንን ሙያን ለባለሙያው የመስጠትን ባህል ለታሳድጉ ይገባል።  የተሃድሶውን ዘመን ታሪክ ( Renaissance Period) የሚያውቅ ሰው ኪነጥበብን  በተራ ባህላዊ ልማድ ምዘና ተነስቶ ቀልድና ዋዛ አያደርግም። እናም ትግሉን በማጠናከር አንፃር ኪነጥበብ የራሷን ሚና እንድትጫወት ሜዳውን በማስፋት አሁን ከተሞከረው በላይ ብዙ መሰራት እንዳለበት አምናለሁ። የአንድ ሊደርሽፕ ትልቁ ችሎታው ደግሞ ሁሉን ሰራ በተወስኑ ሰዎች ለመስራት መሞከሩ ላይ ሳይሆን ሰዎችን በሞያቸውና በስጦታቸው ማቆሙ ላይ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ ትግሉ በየሙያ ባለቤቶቹ ሲታሽና ሲፈተግ ገለባው የወጣለት ልብ አድርስ ስራን እንድናይ ይረዳናል። እናም በኔ አቅጣጫ የመርከቡ ክፍል ግድግዳ ሳስቶ ይታየኛልና ይታሰብበት ባይ ነኝ። በተረፈ ግን ለኢትዬጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ የምለው ቢኖር ሁላችንም አግ7 በገነባው መርከብ ላይ በየገጣችን እየተመለከትን የሳሳ ነገር ቢኖር ብሱን እየገሰጠርን የድላችንን ቀናት እናቅርብ የሚል ነው። የአግ7 ሰዎችም በልበ ሰፊነት ሜዳውን የማስፋት ሰራ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ። ስደመደም ሙሉጌታ ሉሌ ከጠቀሳት የመጽሃፍ ቅዱስ ልዋስና ጽሁፌን ልጨርስ “ ሰልፍ የጀግና ነው ድል ግን የግዚአብሄር ነው”። አበቃሁ።

No comments:

Post a Comment