Translate

Thursday, November 16, 2017

የመቀሌው ሽኩቻና የህወሃት የውድቀት አፋፍ

ክንፉ አሰፋ
TPLF Mekelle meeting
መቀሌ ወሩን ሙሉ ውጥረት ውስጥ ከርማለች። ከተማዋ ላይ እየወረደ ያለው ዶፍ የሚያባራ አይመስልም። የህወሃቶቹ የዘንድሮ መሰባሰብ ለጤና እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ሰዎቹ እንደወትሮው “በሃገር ጉዳይ ላይ” ለመዶለት ወደ መቀሌ አልተጓዙም። ቀደም ሲል ጠላታችን ድህነት ነው ሲሉን ነበር። አሁን ግን በለሁለት ተቧድነው አንዱ ሌላውን ጠላት ሲል ይሰማል።

በግል ጸብ ለሁለት መሰንጠቃቸው የአደባባይ ምስጢር ይሁን እንጂ፤ እርቅ እና ሰላም በአጀንዳቸው ውስጥ አልተካተተም። ሃገሪቱ የገባችበትን ችግር ወደጎን ትተው፣ “አንተ ሌባ – አንቺ ሌባ” ሲባባሉ እንደከረሙ ነው እየተሰማ ያለው። ይህንን የማይታረቅ ቅራኔ ይዘው አብረው ስለማይዘልቁ የአንዱ ቡድን ማሸነፍ ግድ ይላል።
በዚህ ‘ታሪካዊ’ ስብሰባ የሙስና እና የሌብነት ፋይሎች ተጠርዘው ቀርበዋል። ህወሃቶች አፍ አውጥተው “በስብሰናል”ም ብለዋል። እንደ አጀንዳ በቀረቡ በነዚህ የክስ ፋይሎች ላይ ድምጽ ተሰጥቶባቸዋል።
ስብሰባውን እየረገጡ የወጡት ወንጀል ሲዶለትባቸው የነበሩትና “ተሸናፊ” ህወሃቶች ናቸው። በሃብታቸው ብዛት “ቀዳማዊት እመቤት” የተባሉት አዜብ መስፍን የመጀመርያው ስብሰባ ረጋጭ መሆናቸውን ሆርን አፋየርስ ከውስጥ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።
አዜብ ተከትለው ስብሰባውን እየረገጡ የወጡት የነ ስዬ አብርሃን ጽዋ ይቅመሱ አይቅመሱ ገና ባይታወቅም፣ ዛቻውና ጥርስ መናከሱ መቀጠሉን ግን የመቀሌ ምንጮች ገልጸዋል።
ወሩን ሙሉ መቀሌ ላይ ከትመው ሲጠዛጠዙ ውለው ሲጠዛጠዙ መሰንበታቸውን እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል። ግምገማው ቀድሞ እንደሚያደርጉት አንዱ ባንዱ ላይ ጣት መሰባበቅን አልፎ፣ በተራ ስድብ እና ዘለፋ የታጀበ ነው። አጀንዳቸው ብሄራዊ ጉዳይ ቢሆን ባልከፋ ነበር። እጅግ የሚያሳፍረው ጸቡ እኔ እበልጥ፣ የግል መሆኑ ነው። ሌቦች የሚጋጩት ሲሰርቁ ሳይሆን ሲካፈሉ ነው ይባል የለ።
አቶ ሀብቶም ገ/እግዚያብሄር የህወሃቱ ድረገጽ በሆነው አይጋ ፎረም ላይ ኢህአዴግ ያለበት መንታ መንገድ እና የሀገራችን እጣ ፈንታ! በሚል የለቀቁት ያልተለመደ ጽሁፍ ከወዲያ እየነደደ ያለውን እሳት ይጠቁመናል። አይቴ ሃብቶም ስለዛሬው መግማማትና የሌቦች ፖለቲካን ክፉኛ ይኮንናሉ። ዛሬ ብቸኛው የመክበሪያ መንገድ ወይ የመንግስት ስልጣን መያዝ ወይ ከመንግስት ባለስልጣን መጠጋት እሳቤ መሆኑን እና ለዚህም ሙሉ ተጠያቂው ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ነው ይላሉ።
እርግጥ ነው። በህወሃት ውስጥ ሽኩቻ እና መጠላለፍ አዲስ አይደለም። የከዚህ ቀደሙን ተመክሮ እንዳየነውም፤ ስብሰባ ረግጦ መውጣት ለችግሮቹ መፍትሄ አልሆነም። ከ16 አመት በፊት እነ አቶ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ስዬ አብርሃ፣ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳኤ የመለስን ሰነድ አንቀበልም ብለው ስብሰባ ረግጠው ነበር። እነ ስዬ በወቅቱ አብዛኛ ድምድ ነበራቸው። ግና ማኬቬሊያዊው መለስ ቀደማቸውና እንደወጡ በዚያው ቀሩ።
አሁን መለስ የለም። ጸቡም የውስጥና የርስበርስ ብቻ አይደለም። ሽኩቻው ከሕዝብ ጋርም ነው። ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር። የከረረው ክፍፍል ከህዝብ እንቢተኝነት ጋር ተደምማሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ታምራት ገለታን መጠየቅ አያስፈልግም።
ፋይዳ ላይኖረው፣ እንዲሁ ሲቀያየሩ መሰንበታቸው “ስልቻ ቀልቀሎ…” ይሁን እንጂ፣ የኑሮው ውድነት፣ ከጣና ኬኛ ፖለቲካ እና የሼኩ ያልጠጠበቀ መታሰር፣… ተደማምሮ ለውጥ ፈልጎ ለተነሳው ኃይል በር መክፈቱ ግልጽ ነው።

No comments:

Post a Comment