Translate

Friday, June 30, 2017

አርቲስቶቹ ሚዲያ ላይ ነበራቸው በተባለ ተሳትፎ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው


(በጌታቸው ሺፈራው)
ሰገሌ ብሊሱማ ቄሮ ኦሮሚያ (የኦሮሚያ ወጣቶች ድምፅ) በሚባል ሚዲያ ዜና እና ቃለ መጠይቅ ሰርተዋል እንዲሁም ዜና አንብበዋል የተባሉ 4 አርቲስቶች እና ሌሎች 3 ግለሰቦች የሽብር ክስ ቀረበባቸው፡፡ በእነ ኦሊያድ በቀለ የክስ መዝገብ ስር ክሱ የቀረበባቸው አርቲስቶች ኦሊያድ በቀለ (1ኛ ተከሳሽ)፣ ሞይቡል ምስጋኑ (2ኛ ተከሳሽ)፣ ኢፋ ገመቹ (4ኛ ተከሳሽ) እና ኤልያስ ክፍሉ (7ኛ ተከሳሽ) ሲሆኑ ቀነኒ ታምሩ (3ኛ ተከሳሽ)፣ ባይሉ ነጮ (5ኛ ተከሳሽ) እና ሴና ሰለሞን (6ኛ ተከሳሽ) ከአርቲስቶቹ ጋር ዜና እና ቃለ መጠይቅ ሰርታችኋል፣ እንዲሁም ዜና አንብባችኋል ተብለው የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በእነ ኦሊያድ በቀለ ክስ መዝገብ ስር ሁለት ክሶችን ያቀረበ ሲሆን ዛሬ ሰኔ 23/2009 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ክሱ ተሰምቷል፡፡ አንደኛ ክስ በ1ኛ እና በ4ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾቹ በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል በሚል ሰገሌ ብሊሱማ ቄሮ ኦሮሚያ (የኦሮሚያ ወጣቶች ድምፅ) በተባለ ሚዲያና በህቡዕ እንቅስቃሴ በመሳተፍ የኦነግን አላማ ለማሳካት ማሴር ማቀድና ማነሳሳት የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡
በሁለተኛ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ ፣5ኛ፣6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7/1 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ‹‹ሰገሌ ብሊሱማ ቄሮ ኦሮሚያ (የኦሮሚያ ወጣቶች ድምፅ) ለተባለ ሚዲያ በፅሁፍ ዜና በማዘጋጀት፣ የተዘጋጀ ዜናን ሪከርድ በማድረግ ውጭ ላሉት የኦነግ አመራሮችና አባላት በመላክ በእነሱ አማካኝነት ለተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገፆች እንዲሰራጭ በማድረግ ህዝቡ ወደ አመፅ እንዲገባ አነሳስተዋል›› ሲል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር አርቲስቶቹ ቀስቃሽ ሙዚቃ በመዝፈን፣ ዩቲብና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲለቀቅ በማድረግ እንዲሁም የሌሎች ግለሰቦችን ሙዚቃ በማዘጋጀት ህዝብን አነሳስታችኋል የሚል የክስ ዝርዝር የቀረበባቸው ሲሆን የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለሀምሌ 7/2009 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment