Translate

Friday, June 23, 2017

ይድረስ ለትግል አባቴ አንዳርጋቸው ጽጌ

የአርበኛ  ታጋዩ ትውስታ
ተ—ጠ—ቀ—ቅ!!
Andargachew Tsige is Ethiopian
ለፍትህ፣ለእኩልነት፣ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ለሰባዊ መብት ልዕልና መጠበቅ፣ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ—ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው ለሰጡ ሰማዕታት ጓዶቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እናድርግላቸው!! —-ይበቃል!!
ታች!!

ለተሰው ጓዶቻችን ያደረስነውን የህሊና ጸሎት ከደመና በታች አያስቀርብን እያልኩ፣ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ልግባ። በቅድሚያ ግን ከዝች ወረቀት ላይ የሰፈረችው መልዕክት ወይም ትዝብት አሊያም ትውስታ ልበላት የኔና የኔ ብቻ ናት!! ግድፈት ካሳየሁም ከወዲሁ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ። በዚህ ከተግባባን ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ይዣቹህ ልንጎድ፦
ብዕሬን ከጣቶቼ አዋድጄ፣ ከነጩ ወረቀት ጋር አቀናጅቼ እንዴት ሃሳቤን ምሉዕ አድርጌ መግለጽ እዳለብኝ ግራ ገብቶኛል። ሆህያት አነሱብኝ፣ ቃላቶች ኮሰሱብኝ፣ ያንተን ስብዕና፣ተከለ ቁመና ለመግለጽ የሚመጥኑ ሃረጋት፣ ዐረፍተ-ነግሮች፣ አንቀጾች ባወጣ ባወርድ ሁሉም ዝቅ አሉብኝ። ግን እንደ ምንም ብየ እነኝህን ሆህያት ባይመጥኑህም አጠራቀምኩኝ። ቃላትን ከቃላት አጋጭቼ ፣ሃረጋት ሰርቼ፣ ዐረፍተ ነገር መስርቼ፣ እነኝህን አንቀጾች ፈጠርኩ።
በእርግጥ አንተ ውዳሴ እና ዝማሬ እደማትሻ ጠንቅቄ አውቃለሁ። በርሃ ላይም ደጋግመህ ነግረህናል። ልናመሰግንህ፣ ልናግዝህ ስንል እንኳን “በሉ ዝበሉ ምንሰርቼ!፣ አልደከመኝም! እራሴው ነው የማደርገው” ትለን ነበር። ሁልጊዜም ከማውራት ይልቅ ስራን ነው የምታስቀድመው። <<ንድፈ ሃሳብንና ተግባርን አቀናጅቶ የሚጓዝ ሰው ደስ ይለኛል>> ትለን ነበር። <<ጋሼ>> ብለን እንኳን እንድንጠራህ አትፈቅድልንም።
ዛሬ ግን ጋሼ እንድልህ ፍቀድልኝ። በእርግጠኝነት ጋሼ ብዬ በመጥራቴ ቅር እንደማትሰኝብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እናም ጋሼ አንተና ጥቂት ጓዶችህ የዘራቹትን የነጻነት ንጹህና ምርጥ ዘር ዛሬ አምሮበታል!! እጅግ አብቧል!! ፍሬውንም በቅርብ ጊዜ ታየዋለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ስታስተምረን፣ ስትመክረን፣ ስታወያየን <<ታጋይ ከአቅሙ በላይ በሚገጥሙት ሁኔታዎች ምክንያት ይማረካል፣ ይቆስላል፣ ይሰዋል—ግን ትግሉ ይቀጥላል!!>> ትለን ነበር። እናም ልክነህ ጋሼ። አባባሉስ <<ታጋይና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል>> አይደል የሚባለው።አንተን ቢያስሩህም፣ ቢገርፉህም፣ የተለያዩ ሰቆቃዎችን ቢፈጽሙብህም—ትግሉን አላሰሩትም!!
ያነጽከን!! የቀረጽከን!! ያንተ አርበኛ ታጋይ ልጆችህ አደራህን ዝንፍ ሳናደርግ ትግሉን አስቅጥለነዋል። እናም እልፍ ሁነናል!! በእያንዳዱ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መግባት ችለናል። ጠላታችን ተንቀጥቅጧል!! ፈርቷል!! ርዷል!!! በዚህም እንኳን ደስ አለህ
በእርግጥ አንዳንድ የኔ ብጤ ግብዞች እንዴት በእስር ቤት እየተሰቃየ እንኳን ደሳለህ ይለዋል የሚሉ አይጠፍም። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከመከራ፣ ከፍዳ ነጻ ለማውጣት ብዙ ግፍና ሰቆቃዎች ተፈጽመውበታል። የሚፍጸሙበት ሰቆቃዎች አይሰሙትም ነበር። እንዲያውም በእሱ ላይ ሰቆቃ የሚፈጽሙበትን <<አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው>> እያለ ጸሎት አድርሶላቸዋል።
አንተም ጋሼ ስለኢትዮጵያዊያ መከራና ፍዳ ስትል ከወጣትነትህ ጀምረህ አሁንም ድረስ እድሜ ሳይገድብህ፣ እርጅና ሳይጫጫንህ መስዋእትነት ከፍለሃል! እየከፈልክም ትገኛለህ።ነገርግን እየከፈልከው ያለው መስዋዕትነት መና አለመቅረቱን እና  በሰውነትህ ላይ ካለው ቁስል ይልቅ የወጠንከው ትግል እየጎመራ መሄዱ የበለጠ እረፍት እንደሚሰጥህ ስላወኩ ነው እንኳን ደስአለህ ያልኩህ።
ሲጀመር እውነት እንናገር ከተባለ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለው የኑሮ መናወጥ፣ የነጻነት እጦት፣ የፍትህ መጥፋት፣ የመብቶች መረገጥ፣ ስደት፣እስራት፣ ግርፋት፣የግፍ ሞት— እንደሌሎች እያዩ እንደማያዩት፣ እየሰሙ <<ጀሮ ዳባ ልበስ>> እንደሚሉት አልሆንም ብለህ እንጂ፤ የደመቀ ትዳርህን! የሞቀ ኑሮህን—ዕንቡጥ የአብራክህን ክፋይ ልጆችህን ጣል እርግፍ አድርገህ ትተህ፣ ለመቻል የሚከብደውን ችለህ በርሃ የወረድከው። አብዛኛው ሰው እንደ ምድራዊ ገነት የሚመለከተውን የምዕራቡ ዓለም ኑሮ ረግጠህ፣ ከምቾትና ከድሎት ይልቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቀደምከው። ዛሬ ላይ ሁነህ ነገን አይተሃል። እናም ጋሼ ላደረክልን ነገር ሁሉ እናመሰግንሃለን። ያንተ ቁስል ለራስህ ባይሰማህም ለእኛ ለታጋዮቹ ግን አጥንታችን ድረስ ዘልቆ በመግባት ይሰቅስቀናል።
በጊዜው ይገርመኝ የነበረው የመንፈስ ጽናትህ!! የማይናወጠው ጥንካሬህ!! እኛ ወጣቶቹ እንኳን ደከመን ስንል አንተ ግን አንድም  ቀን <<ኧህ!>> ብለህ ያለማወቅህ ነው። ያን ተራራ!! ያን ቁልቁለት!! ያን አቃቅማ!! ያን እሾህና እንቅፋት ችለህ፣ በዚያ ዳገት ሃያ ሃያ  ሊትር ውሃ የሞሉ ሁለት ጀሪካኖችን፣ በግራና ቀኝ እጆችህ አንጠልጥለህ ስትወጣ ትንፋሽህን ከፍ አድርገህ ስትተነፍስ አይቼህም፣ ሰምቼህም አላውቅም። በእርግጠኝነት አልደክምህ ብሎም አይደለም። እኛም ሰዉ መሆንህን እና ሰባዊ ባህሪያትን መላበስህን እንረዳልን። ግን ለዓላማህ ስትል ሁሉንም ነገር ዋጥ አደረከው። የሚሰማህን ሁሉ እንደማይሰማህ ቆጠርከው። የደፈረሰ ውሃ አብርኸን ጠጥጠተሃል። ተረኛ አስመጋቢ ሆነህ እንጀራ ጋግረህና ወጥ ሰርተህ አብልተህናል። የሆነውን ሁነሃል። አፈር ላይ ተኝተህ ድንጋይ ተንተርሰሃል። ክብር!! ለአንተ ለትግል አባታችን ይሁን እላለሁ። ጋሼ እኛ ልጆችህ አንድም ቀን እንኳን ዘንግተንህ አናውቅም። ሁሌም በውስጣችን ታትመህ አለህ። አስተምሮትህ በህይወት እስካለን ድረስ ይኖራል። እኛ ብናልፍም  ከትውልድ ወድ ትውልድ ይተላለፋል።
ዛሬ እስርቤት ውለሃል። ያ ትወጣው ትወርደው የነበረውን ዳገት ዛሬም ለመውጣት ለመውረድ እግርህ ይፈልገው ይሆናል፣ እንደ አይንህ ብሌን ትሳሳላቸው የነበርካቸውን ታጋይ ልጆችህን፣ አይንህ ይራብ ይሆናል ግን በእርግጠኝነት ጋሼ ስጋህ የሚፈልገውን ሽቶ በይሆናል ቢቀርም፣ መንፈስህ ግን ከእኛ ጋር ነው!! የእኛ መንፈስም ካንተጋ ነው!! ስጋህን ነውጂ ማን መንፈስህንና ልብህን ቆልፎ አስቀርቶት?
ቆለፍነበት አሉ ስጋ ብቻ አግተው
የልቡን መብረሩን ማን? በነገራቸው።
እናም ጋሼ አምባገነኖች እንደ ቅዠታቸው የነጻነት ቀንዲሎችን በማሰር፣ በመግደል የተጀመረው ትግል የሚዳፈን ቢሆን ኖሮማ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ቀንበር ነጻ ባልወጣች ነበር። ኔልሰን ማንደላ በሮቢን ደሴት ጠባብ ክፍል ውስጥ ለ27 ዓመታት ታሰረ! ተሰቃየ!። ይባስ ተብሎም አሜሪካ ድርጅቱንና መሪዎቹን በሽብርተኝነት ባህር  መዝገብ ውስጥ አሰፈረች። ግን የሆነው ሌላ ነው። ትግሉ አይነቱን እየቀየረ በመላው ደቡብ አፍሪካ እንደ ሰደድ ዕሳት ተቀጣጠለ። የማንዴላ መታሰር ሺ ማንዴላዎችን አፈራ። አፓርታይድም ተገረሰሰ። ።
ሼ ምንም እንኳን ወያኔ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን አፍሶ  የመን ድረስ በመዝመት አንተን ቢያግትም፣ ያንተ መታገት ሺ አንዳርጋቸው ጽጌዎች እንዲ ፈጠሩ ምክኒያት ሁኗል። ለሃገሩ ዘብ የሚቆም፣ መብቱን ለማስመልስ ህይወቱን አስልፎ ለመስጠት የቆረጠ <<እኔም አዳርጋቸው ጽጌ ነኝ>> ያለ ትውልድ አፍርተሃል።
ይሁን እንጂ ጋሼ አንተ የደማህላትን፣ እንደ ክርስቶስ ስቃይና መከራ የተቀበልክላትን ኢትዮጵያን ለመናድ፣ ንደውም የራሳቸውን ስውር ዓላማ ለማሰካት ጥቂት ሃይሎች ከግራም ከቀኝም መኖራቸውን ሳልደብቅ እነግርሃለሁ። ግን በመሪዎቻችን ሆደ-ሰፊነትና ብስለት፣ በእኛ በአባላቶች ጠቢብነት ከሁሉም ሃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት ብቻ ሳይሆን የጋራ አገራችን በጋራ ገንብተን ለመጓዝ በልበሙሉነት እየተንቀሳቀስን ነው። በዚህም የስውር ጥቅም አሳዳጆችን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቃቸው እና እርቃናቸውን እንዲቀሩ እያደረግን ነው።ባስተማርከን አስተምህሮት፣ በሰጠኸን አዳራ፣ ባስገባህን ቃልኪዳን፣ ባወረስከን ጽናት ኢትዮጵያ ከጨቋኞች መድፍ ወጥታ!! ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተመስርቶ፣ ሁሉም ልጆቿ በዕኩልነት የሚኖሩባት አገር እስከምትሆን ድረስ፣ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ እመነን ጋሼ አናቅማማም!! ወደኋላ አንልም!!
የአርበኛ  ታጋዩ ትውስታ

No comments:

Post a Comment