Translate

Thursday, June 1, 2017

ከቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ (በኤፍሬም ማዴቦ)

በኤፍሬም ማዴቦ (እዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ያለዉ ሃሳብ ሁሉ ዬኔ ዬኔና የኔ ብቻ ነዉ)
Téwodros II was the Emperor of Ethiopia from 1855
ዕለቱ ሰኞ ነዉ . . . .  ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓም። እቺ ቀን “ መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ የሴቱን አናዉቅም፥ ወንድ አንድ ሰዉ ሞተ” ተብሎ የተገጠመላት ቀን ናት። እቺ ቀን ኢትዮጵያ ዘለዓለማዊ ጀግናዋን ያገኘችበትም ያጣችበትም ቀን ናት። እቺ ቀን ቴዎድሮስ የሞተብንም የሞተልንም ቀን ናት . . . .  አዎ ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ኢትዮጵያ መስዋዕትነትንና ባዶነትን፥ ተስፋና ተስፋ መቁረጥን፥ ቁጭትንና ሀሴትን አንድ ላይ ያስተናገደችበት ቀን ነዉ። እሲቲ አማክሩኝ እቺን ቀን ምን ልበላት? የቀን ቅዱስ ብዬ እንዳላወድሳት የአንድነታችን ጀማሪ የሆነ ሰዉ ሙሉ ራዕዩን ሳናይለት አለግዜዉ የተለየን በዚች ቀን ነዉ።
  የቀን ጎደሎ ብዬ እንዳልረግማትም የኩራታችን ምንጭ የሆነች ቀን ናት። እቺ ቀን እንግሊዞች የአበሻ እጅ ሊይዙ መቅደላ ጫፍ ላይ ወጥተዉ አፍረዉ የተመለሱባት ቀን ናት . . . . “ገደልን እንዳይሉ ሞተዉ አገኟቸዉ፥ ማረክን እንዳይሉ ሰዉ የለ በጃቸዉ፥ ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸዉ፥ ለወሬ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸዉ”  እስቲ አንዴ በምናባችሁ ወደኋላ ሂዱና  . . . . አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ለእንግሊዞች እጃቸዉን ሰጥተዉ ቢሆኖ ኖሮ ብላችሁ አስቡ . . . . በስመ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ! የናንተን አላዉቅም እኔ እንኳን ላስበዉ አስባለሁ ስል ጨነቀኝ። አያችሁ እንኳን እጅ መስጠት ስለ እጅ መስጠት እንዳናስብ የሚያደርግ ከብረት የጠነከረ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ስላጎናጸፈን ነዉ መይሳዉን የምንወደዉና የምናከብረዉ። ይህንን አፄ ቴዎድሮስ ያወረሱንን ስነልቦና ነዉ ዛሬ “ኢትዮጵያዊነት” እያልን የምንጠራዉ። ይህ ስነልቦና እጅ አለመስጠት ነዉ፥አለመሸነፍ ነዉ፥ ተስፋ አለመቁረጥ ነዉ፥ በዘር፥ በቋንቋና በሀይማኖት አለመለያየትና አለመከፋፈል ነዉ . . . . ይህ ስነ ልቦና አንድነት ነዉ። ይህ ስነልቦና ጀግንነት፥ መስዋዕትነት፥ ጽናት ፍቅርና መተሳሰብ ነዉ። እነዚህ ሁሉ ቴዎድሮሶች ናቸዉ ቴዎድሮስም እነዚህን ሁሉ ነዉ።
ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓም ያ አስራ ሦስት አመት ሙሉ ቁጭ ብድግ እያለ የታዘዘለት ህዝብና ሰራዊት ቀርቶ አንድነቷንና ትልቅነቷን የተመኘላት ኢትዮጵያ እራሷ አፄ ቴዎድሮስ ላይ ያደመችበት ቀን ነበር። ቤተክርስቲያን አይንህን ላፈር ብላቸዋለች። ሊነግስ ያሰፈሰፈዉ ምድረ ራስና ደጃዝማች ንጉሰ ነገስቱ ሞቱ የሚባል ዜና ለመስማት አስፍስፏል። የጋይንቱ ጀግና ገብሪዬም ንጉሰ ነገስቱን ሳይሰናበት እስከወዲያኛዉ አሸልቧል። ጋፋት አሰርተዉ መቅደላ ድረስ ያስጎተቱት “ሴባስቶፖል” ምንተ እፍረቱን አንዴ ተኮሶ በቃኝ ብሏል። መቅደላ አፋፍ ላይ እንኳን የሰዉ ድምፅ የነፋስ ሽዉታም አይሰማም። ያ ሰራዊት የጨፈረበት፥ አዝማሪ የዘፈነበት፥ ጀግና የፎከረበት፥ የጦር ዕቅድ የወጣበትና መኳንንቱ ግብር የበላበት የመቅደላ አፋፍ ህይወት የሌለበት ይመስል ጭጭ ብሏል። ሰኞ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓም መቅደላ አፋፍ ላይ የሚሰማ ብቸኛ ድምፅ ቢኖር አንድ ብቻዉን ከወዲህ ወዲያ የሚንጎራደድ ሰዉ ዱካ ብቻ ነዉ። አዎ የአንድ ሰዉ ዱካ. . . . የቴዎድሮስ ዱካ. . . .  የ“አንድ ለእናቱ” ዱካ! የዚያ አንድ ያደረጋትን አገር የሚሰናበት ሰዉ ዱካ፥ . ያ ዘመነ መሳፍንትን በቃ ያለ፥ ኢትዮጵያዊነትን የተከለ፥አንድነትን ያመጣልን ሰዉ ዱካ!
አፄ ቴዎድሮስ ገና ኢትዮጵያን ተሰናብተዉ አልጨረሱም ነበር “ንጉስ ሆይ”  . . .  . “ንጉስ ሆይ” እያለ የሚጣራ ሰዉ ድምፅ ከሩቁ ሲሰሙ። የሰዉየዉን ማንነት ባያዉቁም ይዞላቸዉ የመጣዉ መልዕክት ግን ገብቷቸዋል  . . . . ማነህ አንተ ብለዉ ተጣሩና ወታደሩ “ንጉስ ሆይ” ብሎ የዋጠዉን ትንፋሽ ሳያወጣ . . . .  በቃ! በቃ!  . . . . በቃ አዉቄዋለሁ አትንገረኝ ብለዉት ወደ መጡበት ተመለሱ። ብዙም ሳይቆይ አንድ ድምፅ መቅደላን አንቀጠቀጣት። የአፄ ቴዎድሮ የመጨረሻ ድምፅ፥ ለትዉልድ የተላለፈ የአደራ ድምፅ፥አትበታተኑ የሚል ድምፅ፥ ለእንግሊዝ እጅ አትስጡ የሚል ድምፅ  መቅደላን አንቀጠቀጣት  . . . . . . . . .“አንቺ እማማ ስሚኝ . . . ስሚኝ አንቺ እማማ . . . ትዝብት ዉረሺ ከዚህ ሌላ ሳይመሽ እንዳስነጋሽብኝ ሳይነጋ እንዳስመሸሽብኝ” የሚል ወዳጅና ጠላት ለዩ፥ አገር ለጠላት አታሳዩ የሚል የወቀሳና የትዝብት ድምፅ መቅደላን አንቀጠቀጣት። ከዚህ ድምፅ በኋላ አፄ ቴዎድሮስ ወደ አፋቸዉ የገባ እንጂ ከአፋቸዉ የወጣ ምንም ነገር የለም።
መይሳዉን የኖረበት ዘመን ሰዉ አልተረዳዉም፥ ቢረዳዉማ ኖሮ አብሮት ይጓዝ ነበር እንጂ ወራሪ ጠላት ይዞበት አይሄድበትም ነበር። ቴዎድሮስን አንድ ያደረጋት ኢትዮጵያ አልተረዳችዉም፥ ብትረዳዉማ ኖሮ እቺ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሌላ ፍጹም ሌላ ኢትዮጵያ ትሆን ነበር። ቴዎድሮስን ቤተክርስቲያናችንም አላወቀችዉም፥ ቄሱና ቀሳዉስቱ የቴዎድሮስን ራዕይ ያኔ አዉቀዉለት ቢሆን ኖሮ ዛሬ በህይወት ያለ ጳጳስ ተሽሮ ካድሬ ጳጳስ አይሆንም ነበር። አንጥረኛዉና የብረት ሰራተኛዉ የቴዎድሮስን ራዕይ አልተረዳለትም ቢረዳዉማ ኖሮ ዛሬ ወናፍ ለማየት ቤተ መዘክር ነበር የምንሄደዉ። ገበሬዉ የመይሳዉን ራዕይ አላወቀለትም ቢያዉቅማ ኖሮ የዛሬዉ ገበሬ እርፍ ጨብጦ ሳይሆን መሪ ጨብጦ ነበር የሚያርሰዉ። ዛሬ እኛም ብንሆን የቴዎድሮስን ዝናዉን ነዉ እንጂ ራዕዩን ገድሉን ነዉ እንጂ አላማዉን አላወቅንለትም። ብናዉቅማ ኖሮ ከወሬ ስራ እናስቀድም ነበር፥ ብናዉቅማ ኖሮ ጡንቻችንን ጠላት ላይ እንጂ ወዳጅ ላይ አናሳርፍም ነበር። አዎ አፄ ቴዎድሮስን ብናዉቃቸዉ ኖሮ ጠላት አስቀምጠን ወዳጅ ለማጥፋት አንደራጅም ነበር። ቴዎድሮስን ብንረዳዉ ኖሮ ተለያይቶ የብቻ ቤት መስራት ከአንድነት አይበልጥብንም ነበር። የቴዎድሮስን ራዕይ ብንረዳ ኖሮ እንደ ቴዲ አፍሮ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን እንጂ የዘመነ መሳፍትን መከፋፈልና ትንሽነት አንሰብክም ነበር።
የአፄ ቴዎድሮስ ራዕይና ወይን አንድ ናቸዉ- ጥሩነታቸዉና ጣዕማቸዉ የሚታወቀዉ ዘመን ሲቆጥሩ ነዉ።  ባለፉት አንድ መቶ አመታት ዉስጥ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነትን አንግበዉ የተነሱ መሪዎች፥የኪነት ሰዎችና ደራሲያን ኢትዮጵያዊ ጀግንነትን፥ መስዋዕትነትንና አንድነትን በንግግራቸዉ፥ በዜማቸዉና በስነጽሁፍ ስራቸዉ ዉስጥ የገለጹት አፄ ቴዎድሮስን በመጠቀም ነዉ። ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ኢትዮጵያ ዉስጥ የትልቁን የመሳሪያ ፋብሪካ ስም “ጋፋት” ብሎ የጠራዉ “ሴባስቶፖል” ትዝ ብሎት ነዉ። ፀጋዬ ገ/መድህንና ብርሀኑ ዘርይሁን ኢትዮጵያዊ ጀግንነትንና መስዋዕትነትን ለመግለጽ መቅደላ መድሃኔ አለም ቤተክርስቲያን ሄደዉና መቃብር ቆፍረዉ አፄ ቴዎድሮስን ማናገር ነበረባቸዉ። ወላድ በድባብ ትሂድ ኢትዮጵያ ዛሬም ጀግኖቿን፥ ዛሬም ትላልቅ ልጆቿን የሚዘክሩና ዛሬም አንድነቷን የሚሰብኩ ብርቅዬ ልጆች አሏት። ከእነዚህ ብርቅዬ ልጆች ዉስጥ ድምጻዊ፥ ገጣሚና የዜማ ደራሲ ቴድሮስ ካሳሁን አንዱ ነዉ።
ቴዲ አፍሮ የህወሓት ዘረኞች “ኢትዮጵያዊነት”ን አጠፋነዉ ባሉ ቁጥር ኢትዮጵያዊነት እንኳን እነሱ ትናንሾቹ “ትልቅ ነን” ባዮችም ሞክረዉት አልጠፋ ሲላቸዉ የተውት ሲገፉት የሚጋፋ ሲቆርጡት የሚያቆጠቁጥና እንደ አፈታሪኩ ወፍ እንደ “ፊኒክስ” ሞተ አበቃለት ሲባል ከሞተበት ተነስቶ መኖሩን የሚያዉጅ የታሪክ አለት፥ የዘመን ሚስጢርና የጽናት ምልክት መሆኑን በአለም አደባባዮች ላይ የዘመረ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያዊነት ጠበቃ ነዉ። ቴዲ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊነት እሱ እራሱ ሚስጢር የሆነ ሰዉ ነዉ። ለዚህ ይመስለኛል አንዳንዶቻችን ቴዲ ለምን “ኢትዮጵያ” ብሎ እንደሚጮህ ያላወቅንለት። “ትዝብት ዉረሺ” ብሎ የተሰናበተንን ቴዎድሮስን የማይረዳ ሰዉ “ጉራ ብቻ” ብሎ እቅጩን የነገረንን ቴዲ መረዳት አይችልም። ኢትዮጵያዊነትን ለመረዳት የሁለቱን ቴዲዎች ስብከትና ከ”ቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ” ያለዉን ዘመን መረዳት ያስፈልጋል። ቴዎድሮስንና ቴዲሮስን ለመረዳትም ኢትዮጵያዊነትን መረዳት ያስፈልጋል። ዛሬ ይህንን ያልተረዱ ሰዎች ናቸዉ ይህ ድንቅ የኪነት ሰዉ ላይ ላዩን ሙዚቃ እያሰማን ዉስጥ ዉስጡን ግን “ኢትዮጵያን አድኑ” ብሎ ያስተላለፈዉን ትልቅ መልዕክት ወደ ጎን ትተዉ ቴዲ ይበልጣል ጥላሁን ይበልጣል እያሉ የራሳቸዉን ለዛ ቢስ ዘፈን የሚዘፍኑት። እስቲ እግዜር ያሳያችሁ ሰዉ ወርቅና ሰም ቀርቦለት ምን ቢሆን ነዉ ወርቁን ትቶ ሰሙን ካላፈስኩ እያለ ግብግብ የሚፈጥረው! ቴዲ የኢትዮጵያ ወርቅ ነዉ . . . . . ቴዲን ለመረዳት ሰምና ወርቅ ለይቶ ማየት የግድ ነዉ።
የአፄ ቴዎድሮስን የመቅደላ መልዕክት የዛሬዎቹ ትናንሾች መስማትም ማሰማትም አይፈልጉ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የአፄ ቴዎድሮስን የአደራ ቃል አትስማ ቢሉት ይናገራዋል፥ አትናገር ቢሉት ይጽፈዋል፥ አትጻፍ ቢሉት ይዘፍነዋል፥አትዝፈን ቢሉት ያንጎራጉረዋል። ሸመንደፈሩ ቴዎድሮስ ካሳሁን ይህንን ድምጽ ሰምቶታለ፥ጽፎታል፥ ተናግሮታል፥ ዘፍኖታል፥ እስር ቤት ሆኖ አንጎራግሮታል። ለዚህ ነዉ ቴዲን የምንወደዉ። ቴዲን የምንወደዉ የቴዎድሮስን ትዝታ ስለቀሰቀስብን ብቻ አይደለም። ቴዲን የምንወደዉ “ኢትዮጵያዊነት” ጥብቅና አጥቶ ሲወንጀል ያለ ምንም ፍርሃት የ“ኢትዮጵያዊነት” ጠበቃ እኔ ነኝ ያለ ሰዉ ስለሆነ ነዉ። ቴዲን የምንወደዉ ያንን የመቅደላ አፋፍ የአደራ ድምጽ ያለምንም ፍርሃት ይዞልን ስለመጣ ነዉ።
ቀኑ፥ ወሩና አመተ ምህረቱ ትዝ አይሉኝም- ቦታዉ ግን በፍጹም አይረሳኝም – አስመራ ሲኒማ “ኦዲዮን” አዳራሽ ዉስጥ ነዉ። እራቴን ከበላሁ በኋላ አዳራሹ ዉስጥ ገብቼ ቦታ የያዝኩት በግዜ ነዉ። የድራማዉን መጀመር የሚናፍቀዉ አዳራሹን የሞላዉ ሰዉ አሁንም አሁንም አዳራሹን በፉጩትና በሆታ ያናጋዋል። ከምሽቱ ሰባት ሰአት ተኩል ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በወታደራዊ ዪኒፎርም ያሸበረቁ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አዳራሹ ዉስጥ መግባት ጀመሩ። ሜጄር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ፥ ብርጋዴር ጄኔራል ታዬ ባለኬር፥ ብርጋዴር ጄኔራል ቁምላቸዉ ደጀኔ እና ኮሎኔል ተስፋዬ ትርፌ በወቅቱ አስመራ ዉስጥ ከማዉቃቸዉና በተለያየ አጋጣሚ ተገናኝተን ካናገርኳቸዉ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ በቅርብ ከማዉቃቸዉ የኢትዮጵያ ብርቅዬ የጦር መኮንኖች ዉስጥ አንዱ ናቸዉ። ጄኔራል መርዕድ አባት ሆነዉ መክረዉኛል፥የበላይ ሆነዉ አዘዉኛል፥እንደ ጓደኛ አጫዉተዉኛል። ብዙዎቹን የኢትዮጵያ ጀግኖች በስም ነዉ የማዉቃቸዉ፥ ጄኔራል መርዕድ ግን እጃቸዉ እጄን ሰዉነታቸዉ ሰዉነቴ ነክቷል፥ ትንፋሻቸዉ ሞቆኛል ንግግራችዉ መስጦኛል ምክራቸዉ ስንቅ ሆኖኛል።
ትዕይንት ስንት እንደሆነ ለግዜዉ ትዝ አይለኝም ብቻ መጋረጃዉ ተከፍቶ ትዕይንቱ ሲጀመር ባልቻ አባነብሶ ሁለት እጃቸዉን የፊጥኝ ታስረዉ ቁጭ እንዳሉ ምድረ ሶላቶ ከብቦ ለጣሊያን ታማኝ ይሁኑና ለሞሶሊኒ ገብሩ እያለ ይሳለቅባቸዋል። ባልቻ እሺም እምቢ ከአፋቸዉ አልወጣም። አባነብሶን የጨነቃቸዉ  . . . . ለሚኒልክና ለጣይቱ የኢትዮጵያን ነገር ምን ብዬ እነግራቸዋለሁ የሚል ለራስ ሳይሆን ለአገር የመጨነቅ ሃሳብ ነበር። ይህን ግዜ ነበር አብራር አብዶ ያቺን ቀጭን ብትሩን ይዞ ወደ አዳራሹ ብቅ ያለዉ። አብራር አብዶ በዚያ ቅላቱ መድረክ ላይ ሲወጣ መድረኩን ማቅላት ነበረበት- እሱ ግን ድሮዉንም የደበዘዘዉን መድረክ ጭራሽ አጨለመዉ። በተለይ ያቺን ቀጭን በትር ወደ ባልቻ አባነብሶ እየቀሰረ  . . .  የጣሊያንን በመሰለ የተኮላተፈ አማርኛ. . . ባልቻ አባነብሶ ይኼ ኖ  . . . . እሱ ደካማ ሽማግሌ ኖ እያለ በአድዋዉ ጀግና ላይ ሲያሾፍ ሲኒማ ኦዲየን አዳራሽ ሰዉ አልባ ይመስል ጭጭ አለ።  አንገቴን ቀና አድርጌ ዞር ዞር እያልኩ ስመለከት ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጠ ይመስል ሁሉም ሰዉ አጎንብሷል። ለምን አያጎንብስ የጀንነታችንና የአንንኩኝ ባይነታችን ምልክት የሆነ ጀግና በነጭ ነጫጭባዎች ተከብቦ . . . . .  ደካማ ሽማግሌ ነዉ ሲባል! አብራር አብዶን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከነበርኩበት ግዜ ጀምሮ እወደዋለሁ። አስመራ ሲኒማ ኦዲዮን ዉስጥ ግን አብራር እራሱ ያነሳሳዉ ስሜቴ አመክኖዬን ቀማኝና አብራር አብዶ ሙያዉን በሚገባ ስለተወጣ ለግዜዉም ቢሆን የምወደዉን አብራርን ጠላሁት።
ፊቴን በሁለት እጆቼ አበስ አበስ አደረኩና አሁንም ካጎነበስኩበት ቀና ስል የሲቃና የእልህ ድምፅ ተሰማኝ። ይህ ድምፅ ከአብራር አብዶ አፍ  . . . .  ደካማ ሽማግሌ ኖ . . . .  የሚል ቃል በወጣ ቁጥር እየበረታ ሄደ። ማነዉ ብዬ አዳራሹን መቃኘት ጀመርኩ። ፊታቸዉን በሁለት እጃቸዉ ሸፍነዉ ከእሳቸዉ በፊት ኖረዉ ላለፉ ጀግና ሰዉ ክብር የሚያለቅሱት የዚህኛዉ ዘመን ጀግና ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ነበሩ። እኔን ጨምሮ አዳራሹ ዉስጥ የነበረዉ ሰዉ ሁሉ ዕምባ በዕምባ ሆኗል። ጀግናን በደምብ የሚረዳዉ ጀግና ነዉና የጄኔራል መርዕድ ዕምባ ግን መቆሚያም ያለዉ አይመስልም ነበር። ድራማዉ ተፈጽሞ ከአዳራሹ ስወጣ ጄኔራል መርዕድ ሌላም ነገር ሞክረዉ ነበር ሲባል ሰማሁ- እሱ አይጠቅመንምና ልተወው። ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ የቴዎድሮስን አደራ ለቴድሮስ ያቀበሉና ከቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ ባለዉ የታሪክ ቅብብሎሽ ዉስጥ አንዱን ትልቅ ምዕራፍ የጻፉ ሰዉ መሆናችዉን ሳልናገር ባልፍ ግን የሳቸዉ ብቻ ሳይሆን “ቃልኮ የእምነት ዕዳ ነዉ” ያለዉ የመቅደላዉ ጀግና አጽምም ይወጋኛል። ኢትዮጵያዊነት ከምንም ከማንም በላይ ነዉና የራሴ ጀግኖች አጽም ከሚወጋኝ የህወሓት ጥይት ወግቶኝ እኔም እንደነ ጄኔራል መርዕድ ባሸልብ ምርጫዬ ነዉ።
ከቴዎድሮስ እስከ ቴዎድሮስ የተሰበከዉ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ሆኖ ሳለ ለምንድነዉ እኛ የአገር አጀንዳ ጥለን የመንደር አጀንዳ ያነገብነዉ? ምንድነዉ ኢትዮጵያዊነትን አስረስቶ ጎጠኝነትን ያስወደደን? የአገራችን አንድነት ላልቶ እያየነዉ ለምንድነዉ የግል ቤታችንን ለመስራት የምንሯሯጠዉ? እኔ ሞቼ “አናንተ ኑሩ” የሚል ትዉልድ ጠፍቶ እናንተ ሞታችሁ “እኔ ልኑር” የሚል ስስታምና ሞራሉ የላሸቀ ትዉልድ እንዴትና ለምን ተፈጠረ? ተምሮ የማያነብ ምሁር፥ ሳያነብ የሚጽፍ ተማሪ አሁንማ ጭራሽ ያልተጻፈ የሚያነብ ትዉልድ እንዴት ሊኖረን ቻለ? ሳያስብ የሚናገር መሪ፥ ሳይወያይ የሚወስን ፓርላማ፥ ለምን አሰብክ ብሎ የሚፈርድ ዳኛ፥ ምስክር የሚያሰለጥን አቃቤ ህግ ከዬት የመጣ ጉድ ነዉ? ዉሸት ሲነገር አሜን ማለት፥ ጓደኛ ሲገደል ከንፈር መጥጦ መሄድ፥ አገር ስትዋረድ አላየሁም ማለት፥ዳር ድንበር ሲደፈር ጭጭ ብሎ ማየት፥አንድነት ላልቶ መለያየት፥ ኢትዮጵያ ስትፈርስ የራስ ጎጆ መስራት ከየት የመጣ ባህል ነው? ምንድነዉ በኢትዮጵያዊነትና በጎጠኝነት በትልቅነትና በትንሽነት መካከል የሚያዘልለን? ለምንድነዉ በአንድነታችን ላይ የተጋረጠዉን አደጋ ለማዳን ህልማችን ተለያይተን መደራጀት የሆነዉ? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አግኝተንና ወደኋላ ተመልሰን ጉዟችንን እንደገና ከ”ሀ” ካልጀመርን የባርነት ኑሯችን ይቀጥላል። የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ በአገራችን ዉስጥ ሚሊዮን ችግሮችን ፈጥሯል- አንድም ቀን ችግራችንን ሲፈታ ሲፈታ ግን አልታየም። ታድያ ይህንን እያወቅን ለምንድነዉ ከጥላቻና ከልዩነት ፖለቲካ የማንላቀቀዉ? የኔ አቋም ከላይ የዘረዘርኳቸዉ ችግሮች ሲፈጠሩ እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል አይደለም፥ አቋሜ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገዉ ትግል እኔ የመጀመሪያዉ ሰዉ እሆናለሁ የሚል ነዉ። በኢትዮጵያዊነቴ የማንም ሰዉ ወይም ቡድን ጠላት መሆን አልፈልግም ደግሞም አይደለሁም . . . . የማንም ሰው ጥቃት ሰለባ መሆንም አልፈልግም! የምታገለዉ ነጻነት አግኝቼ የሌሎችን ነጻነት ለማክበር ነዉ።
አፄ ቴዎድሮስ አንድ ያደረጓትን አገር ሳይኖሩባት ሞቱ፥ ጸጋዬ ገ/መድህን የአገሩን አንድነት እንደሰበከ ከአገሩ ወጥቶ በሰዉ አገር ሞተ፥ ብርሀኑ ዘርይሁን ስለ አንድነታችን እንደጻፈ እሱም ብዕሩም ጭጭ አሉ። “አንድነት” ብለዉ ዕድሜ ልካቸዉን  የጮሁት ጄኔራል መርዕድ ንጉሴና ጓደኞቻቸዉ ኢትዮጵያን ጥሎ በፈረጠጠ ሰዉ ተገደሉ። ዛሬ ኢትዮጵያ እሷንም ታሪኳንም በማይወዱ ሰዎች እጅ ሲትወድቅ ደግሞ መቼም ኢትዮጵያ ምን ግዜም የቁርጥ ቀን ልጃ አታጣምና ቴዲ አፍሮ የሚባል የኪነት ሰዉ ተነሳ። ቴዲ “ያስተሰርያል” ብሎ ሰበከ ሀጢያታችን በዝቶ ታየዉና፥ “ጥቁር ሰው” ብሎ ዘመረ ድል ናፈቀዉና፥ አሁን ደሞ “ኢትዮጵያ” ብሎ ከዳር ዳር ጮኸ የቃል ኪዳናችን ማሰሪያዉ ኢትዮጵያዊነት ነዉና!  ለመሆኑ ይህ ከቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ ጀግኖች የሞቱለት፥ የቅኔ ሰዎች የተቀኙለት፥ የዜማ ሰዎች ያዜሙለት፥ ጸሐፊያን የጻፉለት፥ ከያንያን የከወኑለት “ኢትዮጵያዊነት” ማለት ምን ማለት ነዉ? . . . . . ምንድነዉ ኢትዮጵያዊነት? ሰምቶ ለሚገባዉና ገብቶት ለሚሰራ ሰዉ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ነገር ነዉ . . . .  “ኢትዮጵያዊነት” ሲለመልም ሁላችንም የምንጠለልበት ሲጠወልግ ሁላችንም የምናለመልመዉ የጋራ ቤት ነዉ። ኢትዮጵያዊነት እሺም ነዉ ኢትዮጵያዊነት እምቢም ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ጽናት ነዉ፥ ኢትዮጵያዊነት ኩራት ነዉ፥ ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ዘመን ያስቆጠረ የታሪክ ማህደር ነዉ፥ ኢትዮጵያዊነት የወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ከ”ቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ” የነበረ አሁንም የሚኖር ማንም ሊያቆመዉ የማይችል የታሪክ ክስተት ነዉ። አሜን!  ቸር ይግጠመን።
ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር

No comments:

Post a Comment