Translate

Saturday, June 24, 2017

አንዳርጋቸው ጽጌ የጽናታችን ና የቁርጠኝነታችን ዓርማ ነው!!!


የንቅናቄያችን መስራችና ዋና ጸሀፊ የነበረው ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ በዘረኛው የህወአት አገዛዝ ከየመን አየር ማረፊያ ታግቶ እስር ቤት ከተወረወረ እነሆ ጁን 23 2017 ዓም 3 አመት ሞላው።
ህወአት አንዳርጋቸውን ባገተበት ወቅት የንቅናቄያችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ይሽመደመዳል የሚል ተስፋና እምነት ነበረው። ይህንን እምነቱን ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ በሚፈጸምበት ሰቆቃ ውስጥ ሆኖ እንዲያረጋግጥለትና ነጻነት ናፋቂ የሆነው ህዝባችን ተስፋ እንዲቆርጥ ብዙ ጥሮአል ፤ ደክሟል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በሚከፍለው ግብር የሚተዳደረው የአገራችን ዋናው ቴለቪዥን ጣቢያና ህወሃት ህዝባችንን በፕሮፖጋንዳ ለማደንዘዝ ያቋቋማቸው ሌሎች ሚዲያዎ በሙሉ በመረባረብ ከጓዳችን መታገት ጋር ተያይዞ ግንቦት 7 አከርካሪውን ተመቶአል ፤ ሌሎች የንቅናቄው አመራሮች የአውሮጳና የአሜሪካ የምቾት ኑሮዋቸውን ትተው ወደ በረሃ የመሄዳቸው ጉዳይ የማይታሰብ ነው የሚል ከንቱ ትንበያ ከማራገብ አልፈው የህዝባችንን ቅስም ለመስበር ያመቸናል የሚሉትን የፈጠራ ድራማዎችን በማቀነባበርና በማሰራጨት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ብቻ ሳይሆን ግምቱ የማይታወቅ የአገራችንን ሃብትም አባክነዋል።
ህወሃት ከህዝብ በተዘረፈ ገንዘብና በጠመንጃ ሃይል በተያዘ ሥልጣን ልቡ ያበጠ እብሪተኛ ድርጅት መሆኑን በገሃድ ያስመሰከረው ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌን ለማገት ከተጓዘው ርቀት እና ከወሰደው የድፍረት እርምጃ በተጨማሪ ለነጻነት የሚደረገው ትግል አብቅቶለታል ብሎ ለመደምደም ያሳየው ጥድፊያ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት ትግል ፤ ለፍትህ ለእኩል ነትና ለአገር ባለቤትነት የሚደረግ ትግል መሆኑ መረዳት ያልቻለው የህወሃት አገዛዝ ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ ከአፍላ የወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ የቆመለትና ዋጋ እየከፈለለት ያለው ይህ ክቡር አላማ ከግለሰብ ተክለ ሰውነት በላይ ግዙፍ እንደሆነ አንዳርጋቸውና የትግል ጓዶቹ ጠንቅቀን እናውቃለን።
ወያኔ አገር ውስጥ ያሉትን ተቃዋሚዎች እግር በእግር እየተከተለ ለማዳከም በየቀኑ የሚወስደው የእስር ፤ የእንግልትና የግዲያ እርምጃ አልበቃ ብሎት ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌን ከባህር ማዶ አግቶ ለመውሰድ ለየመን ጸጥታ ሃይል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከፍሎአል። በዚህ የወያኒ የእብሪት እርምጃ የተበሳጨው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘር ፤ ቋንቋና ሃይማኖት ልዩነት ሳያከፋፍለው ‘”እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” በሚል ቁጣ ተነስቶ በአምባገነንነትና በዘረኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ ህወሃት ከአንዳርጋቸው መታገት በኋላ በአመራር እጦት ይበተናል ያለው የነጻነት ትግል ከኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ጋር በተደረገው ውህደትና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመታገል በተፈጠረው ጥምረት መክሸፉን አስመስክሮአል።
ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ በታገተ ሰሞን የንቅናቄያችን አመራር ወደ ምድር ወርዶ ትግሉን ለመምራትና ለመታገል ያስተላለፈውና እየተገበረው ያለው ውሳኔ በጠላት ካምፕ ከፍተኛ መደናገጥን ሲፈጥር በወገን ካምፕ በኩል ከፍተኛ ተስፋንና አለኝታነትን የጫረ ሆኖአል።
የንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አባላት እና ደጋፊዎች በየምንሰበሰብባቸው የስብሰባ አዳራሾችና በየምንሰማራባቸው የትግል መስኮች እየዘመርነው ያለው የ”ላንቺው ነው አገሬ” ግጥም ደራሲ የሆነው ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ የምንታገልለትን አላማ በአጭሩ እንዲህ ሲል በስንኞቹ አስቀምጦአል።
በባርነት ሸክም ጀርባሽ የጎበጠው፣
በባለጌ መዳፍ ክብርሽ የጎደፈው
የስቃይሽ ስቃይ ሰማይ የነደለው
ዓይንሽ እስኪጠፋ ደም ለምታነቢው
ላንቺ ነው ሀገሬ ህይወት የገበርነው፣
ላንቺው ነው ሀገሬ እኛ የምንሞተው፤
ለናዱት አንድነት ላረከሱት ሀገር ፣
ለቀሙን ነጻነት ለጫኑብን ቀንበር፣
መልሱ ሆኖ መጥቷል ደረትን ለአረር፣ እያለ ይቀጥላል።
ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ ይህንን ግጥም በደረሰበት ወቅት በእአምሮ ውስጥ ይመላለስ የነበረው አገራችን የገባችበት አዘቅትና የህዝቦቿ ጉስቁልና እንደሆነ መገንዘብ ከባድ አይሆንም ። ይህንን ለመለወጥ ደግሞ ትግሉ የሚጠይቀው ቁርጠኝነትና የመንፈስ ጽናት ደረጃ እስከምን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦአል።
መላው የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች መሪያችን አንዳርጋቸው ጽጌ በጠላት እጅ የወደቀበትን ሶስተኛ አመት ስናስታውስ እርሱና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቶቻችን እስከዛሬ የከፈሉትንና በመክፈል ላይ የሚገኙትን መስዋዕትነት እያሰብን ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለትን የነጻነት ትግል ከዳር ለማድረስ ያለንን ቁርጠኝነት በድጋሚ በመግለጽ ነው ።
ዛሬ በየእስር ቤት ውስጥ ሆነው በንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ሥም የተለያየ መከራና ስቃይ በመቀበል ላይ ያሉትም ሆኑ በትግሉ ላይ እያሉ ውድ ህይወታቸውን ለዚህ ክቡር ዓላማ የገበሩ ወገኖቻችን የሚካሱት እነርሱ ዋጋ የከፈሉለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ባለን ጽናትና ቁርጠኝነት ብቻ ነው።
የጀመርነው ትግል ምንም አይነት ዋጋ ቢያስከፍለን የኋላ ኋላ በአሸናፊነት እንደሚደመደም ምንም አይነት ጥርጣሬ የለንም። መታሠር፤ መገረፍና መገደል የነጻነት ትግል ማደናቀፍ የሚችል ቢሆን ኖሮ የህወሃት የመንፈስ አባት የሆነው ፋሽስት ጣሊያን እስከዛሬዋ ደቂቃ ድረስ በባርነት ሲገዛን ይኖር ነበር ።
ውድ ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ እና በተለያየ የወያኔ ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ ፍዳችሁን እያያችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን ሆይ! የታሠራችሁበት የብረት ሰንሰለትና የታገታችሁበት የእስር ቤት በሮች የሚበረገዱበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን እኛ የትግል ጓዶቻችሁ እናረጋግጣለን። በአረአያነት ያስተማራችሁን ጽናታችሁና ቆራጥነታችሁ በደማችን ውስጥ ነፍስ እንደዘራ አትጠራጠሩ ።
ዘለአለማዊ ክብር ለነጻነት ስሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖቻችን ሁሉ !
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment