Translate

Friday, June 10, 2016

የኖርዲክ ሐገራት አርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ውይይትና ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በኦስሎ ኖርዌይ ተካሄደ፡፡ ጁን 4/2016 የኖርዲክ ሐገራት የአርበኞች ግንቦት ሰባትሕዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ አጠቃላይ ሪፖርት(ዘገባ) ።

Patriotic Ginbot 7 Public Meeting in Oslo
ፕሮግራሙ ለነፃነት በረሐ የወረዱት የንቅናቄው መሪ አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ፣ / ጌታቸው በጋሻው ከቪዥኝ ኢትዮጵያ የክብር እንግዶች እና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከናውኑዋል።
በተለይ  ከኖርዌይ ውጭ ከስዊድን የመጡት የንቅናቄው አባላት እና ደጋፊዎች ለዝግጅቱ ድምቀት ከፍተኛ አስተዋፆ ያደረጉ ሲሆን ከስዊድን ወጣቶች የተገኘውን የሜዳልያ ሽልማት በበረሐ ለሚገኙ ታጋዮች እንዲደርስ ለንቅናቄው ሊቀመንበር ለአርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ  ከስውዲን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር አበርክተዋል።

 በመቀጠልም የፕሮግራሙ አዘጋጆች የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል አበበ ስለ ዝግጅቱ ገለፃ አድርገው በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተለያዩ ሐገሮች ለመጡት አባላት እና ደጋፊዎች ያላቸውን አክብሮት እና ምስጋና አቅርበዋል።
      በእለቱ የተገኙት የክብር እንግዶችም እጅግ ጠቃሚ እና ትምሕርት መቅሰሚያ ንግግሮችን ያደረጉ ሲሆን የመጀመሪያው ተናጋሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው  በጋሻው ከቪዥን ኢትዮጵያ ናቸው።
  ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በኢትዮጵያ ጉዳይ ሰፊ ተሳትፎ ካላቸው በጣት ከሚቆጠሩ የሐገራቸውና የሕዝባቸው ጉዳይ ከሚያንገበግባቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።
  ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ንግግራቸውን የጀመሩት በእለቱ የገቢ ማሰባሰቢያውን ለማጨናገፍ  በወያኔ ተሞክሮ የከሸፈውን ድርጊት በማውገዝ ሲሆን ይህን እኩይ ተግባር እንዲከሽፍ ያደረጉትን የዝግጅቱን አስተባባሪዎች በማድነቅ እና በማወደስ ሲሆን በመቀጠልም እርሳቸው የሚመሩት ቪዝን ኢትዮጵያ ፥እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እና የሚያመጣቸውን ሐገራዊ ፋይዳ እንዲሁም ያደረጋቸውን እና እያደረጋቸው ያለውን ክንውኖች ለሕዝብ እንዲደርስ ለሚያደርገው ኢሳት ያላቸውን ልባዊ አድናቆት በመግለፅ ነበር።
 በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ የተንሰራፋው የወያኔ ዘረኛ ቡድን በኢትዮጵያውያን እና በሕዝቡዋ ላይ የሚያደርሰውን መጠነ ሰፊ ግፍ፣እስር፣ ግድያ እና ዘረኝነት የገለፁት ፕሮፌሰር ጌታቸው ሁሉም በአንድ ካልተባበረ ሐገራችን እንደ ሐገር የመቀጠልዋ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በአፅንኦት አስቀምጠዋል።
 ፕሮፌሰር ጌታቸው :-ፀረ ሕዝብ እና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው ዘረኛው የወያኔ ቡድን በአሁኑ ወቅት በጣም የተዳከመበትና ሐገርን እንደ ሐገር የማስተዳደር አቅም ማጣቱን እና በዚያው ልክ የእውር ድንብሩን ሕዝብ በማዋከቡ ስራ ላይ ቢጠመድም ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ ከዳር እስከ ዳር የሕዝብ አመፅ እያየለ መምጣቱን ገልፀው በእነዚህ ምክንያቶች የትግሉ አይነት እና አቅጣጫ መለወጡን የሚያመላክቱ የተለያዩ ምልክቶችን በማቅረብ ለታዳሚው አስረድተው የአርበኞች ግንቦት ሰባት የትግል እንቅስቃሴ አማራጭ የሌለው የትግል አቅጣጫ መሆኑን በሰፊው አስረድተዋል።
ፕሮፌሰሩ አያይዘውም በምንም አይነት ሁኔታ አናሳ ቡድንን ወይም ጎሳን ብቻ ያካተተ የመንግስት ስልጣን ዲሞክራሲያዊ እና ዘለቄታ ያለው የተረጋጋ ሐገር እና ሕዝብ መፍጠር እንደማይቻል ገልፀው የወያኔ ስርዓት መንኮታኮቱን ያሳያሉ ያሉዋቸውን አብይ ምልክቶች እንደሚከተለው ያስቀመጡዋቸው ሲሆን:-
  እነዚህም ምልክቶች
1-በኢኮኖሚው በኩል ፈፅሞ መውደቁን፣
2-በፖለቲካው በኩል  ወያኔ መናጋቱን
3- የትግሉ መልክ መቀየሩን ለተሰብሳቢው በሰፊው አስረድተው ይህ በሆነበት ሁኔታ ለትግሉ የማይተባበር ለወያኔ መሳሪያ መሆኑ እንደሆነ የገለፁት ፕሮፌሰሩ በኦሮሞ በአማራ፣በሲዳማ እንዲሁም በመላው ሐገሪቱ የሚታዩ የሕዝብ እንቅስቃሴዎችን በተቀናጀና በአንድነት በማድረግ ይህንን ዘረኛ ቡድን ማስወገድ እንደሚገባ ሰፊ ትንታኔ በመስጠት አንድነት አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ ገልፀዋል።
   በተጨማሪም ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር የተጀመረው ውይይት እጅግ በጣም አመርቂ ሁኔታ ላይ እንዳለ ያስረዱት ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው:-
"ኢትዮጵያ ያለ ኦሮሚያ፣ኦሮሚያ ያለ ኢትዮጵያ መኖር አይችሉም" የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ እንሰራለን የሚሉ ሐይሎች ሁሉ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው ጋር መስራት አለባቸው፤የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የመገንጠል ጥያቄ አይደለም፤ ኦሮሞዎች ሐገራቸውን ይወዳሉ ከዚህ ውጭ የሚያወሩ አንዳንድ ፅንፈኞች ስለሆኑ ለነሱ ቦታ መስጠት እንደማያስፈልግ ገልፀው ከድርጅት አመራሮች ጋር ጥሩ መግባባት መፈጠሩን እና ወደፊት ለምትመሰረተው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መሰረትም መሆኑን አስረድተው ንግግራቸውን ቁዋጭተዋል።
       በመቀጠል ፕሮግራሙን የሚመሩት ዶክተር ሙሉዓለም አዳም የአርበኞች ግንቦት ሰባት በኖርዌይ ሊቀመንበር የፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻውን ንግግር አድንቀው በእርግጥ ብዙ አባላት እና ደጋፊዎች አለን ትግሉንም ለመርዳት በየጊዜው ትንሽ ትንሽ ገንዘብ እናዋጣለን ነገር ግን ወያኔዎች አንጉዋጠጡን ስብ እናችንን አጎደፉ ፣መንገድ ላይ አደናቀፉን እያልን በምንቆጭበት በዚህ ወቅት የምናደርገው ነገር ጥቂት ነገር በቂ ነወይ? ብለን እራሳችንን እንድንመረምር ያደርገናል
 ብዙ ምሁራኖች የምቾት ኑሮዋቸውን ትተው እንደ ወጣትነት እድሜያቸው በረሐ ወርደው አሸዋ ላይ እየተኙ ባለበት በዚህ ወቅት እኛ የምናደርጋት ትንሽ መዋጮ በቂ ናት ወይ ብለን ?እራሳችንን እንድንጠይቅ እያደረገ ይልቁንም በእልክ እና በቁጭት ወደፊት ትልቁን ነገር እንድናስብ ያደርገናል።
በእርግጥ አሉ ዶክተር ሙሉ ዓለም :- "በእርግጥ የፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በረሐ መውረድ ትግሉን አጡዞታል" ብለው ነበር የንግግራቸው ማጠቃለያ  የሆነውን አረፍተ ነገር ተናግረው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅንቄ ሊቀመንበር የሆኑትን አርበኛ / ብርሐኑ ነጋን ወደ መድረኩ የጋበዙዋቸው።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋም ወደ መድረኩ ሲመጡ የስብሰባው ታዳሚዎች በድጋሜ በከፍተኛ ጭብጨባ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑም:- ፕሮፌሰር ወይም ምሁር የሚለው መጠሪያ ብዙም አይመቸኝም በኔ አስተሳሰብ ምሁር ማለት መኮፈሻ ሳይሆን ለእውነት የቆመ ነው፣ ምሁር ማለት እውነትን የሚፈልግ ማለት ነው ፣ለሐገር እና ለሕዝብ የሚያሰብ ማለት ነው!! በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት:-
አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑም:- በስብሰባው ላይ የሚያዩትን ከፍተኛ እና ጠንካራ የሴቶች እንቅስቃሴ እንዲሁም በኖርዌይ ያሉ ኢትዮጵያውያኖች ለትግሉ የሚያደርጉትን ከፍተኛ አስትዋፆ ሁል ጊዜ እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።
ፕሮ ብርሐኑ ነጋ ስለ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ከተለያዮ የኖርዌይ መንግስት ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ያዩት እና የታዘቡት ስደት መፍትሄ አለመሆኑን እና መፍትሄው ሐገርን ከዘረኞች ነፃ ማውጣት ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል።
   የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑ  በማያያዝም በአንድ ቀን በኢሳት ላይ የሰሙዋቸው ዜናዎች ሁሉም በስደት ላይ የተመረኮዙ ናቸው፤ ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን ምንድን ነው? ብለን ስናስብ በወያኔ አምባገነኖች የሚደርስብን መጠነ ሰፊ ስቃይ እና ግፍን በጋራ መታገል አለመቻላችን እንደ ማሕበረሰብ እየተዋረድን መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
 አያይዘውም እንዴት ነው? ይህንን ሁሉ መከራ እና ግፍ የተሸከመው፤ ማሕበረሰቡ ለምን በአንድነት ለነፃነቱ አይነሳም? በማለት ጠይቀዋል።
አያይዘውም በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የነፃነት ትግል እንደመንደርደሪያ ያነሱት / ብርሐኑ የደቡብ አፍሪካ ነጮች በቁጥር ከሐገሬው ሕዝብ በቁጥር ትንሽ ናቸው
እንዴት ነው ታዲያ ለረጅም ዘመን አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኖረው ብለን ስንጠይቅ  *የመጀመሪያው የሳይኮሎጅ ጦርነት ነው።
 እናም እኛ ከናንተ ጋር እኩል አይደለንም እናንተ ከኛ ታንሳላችሁ የሚለው ስብከት ጥቁሩን አምኖ እንዲቀበል አድርጎታል።
 *ስለሆነም የቀለም ልዩነቱ በስብእናው ላይ ልዩነት እንዳለው አሳምነውታል።
 በዚህ የተከፋፈለው ጥቁር የራሱ የሆነ ነገር እንዳይኖረው የነጮች ተቀጣሪ እንዲሆን ነው ያደረጉት።
* በመቀጠልም የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ ስርአት ያራምደው የነበረው የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ አካሄድ በስፋት ከተነተኑ በሁዋላ አሁን በሐገራችን ያለው የወያኔ ዘረኛ ቡድን እያራመደ ያለውን አፓርታይድ ስርዓት ጋር በማነፃፀር ሰፊ እና ጥልቅ የሆነ ትንታኔ የሰጡ ሲሆን በመቀጠልም ደቡብ አፍሪካውያን ያካሄዱትን  የነፃነት ትግል በሰፊው የተነተኑት አርበኛ / ብርሐኑ :-ከሕዝባዊ እምቢተኝነት እስከ ትልልቅ የነጮች ተቁዋማት እና በምርቶች ላይ የተወሰደው ምርቶችን ያለመጠቀም ትግል እንዲሁም በምርቶች ላይ የተወሰደው ማእቀብ በተጨማሪም በውጭ የሚኖሩት ዜጎች ያሳዩት የውጭ እምቢተኝነት ትግል ውጤት እንደሆነ  ደቡብ አፍሪካውያንን ነፃ ያወጣቸው ገልፀዋል።    
በመቀጠልም እኛ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት እያደረግን ያለው እንቅስቃሴ ይህንን መሰረት ያደረገ ነው፤ በዓለም ላይ ነፃነት በልመና ተገኝቶ አያውቅም ፤ነፃነታችንን የምናመጣው እኛው ነን ማብራሪያ ከሰጡ በሁዋላ
 አርበኞች ግንቦት ሰባት የሚከተለው የትግል ስልት እንደ ደቡብ አፍሪካ ሶስት አይነት የትግል ዘርፎች እንዳሉት ገልፀው እነዚህም ሶስት የትግል ዘርፎች የሚከተሉት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይኸውም:-
1 ሕዝባዊ እንቢተኝነት በሐገር ውስጥ
2 ሕዝባዊ እንቢተኝነት በውጭ ሐገራት እና
3 በመሳሪያ የተደገፈ የነፃነት ትግል እንደሆነ ለተሰብሳቢው ያብራሩ ሲሆን:-
    / ብርሐኑ እጅግ መሳጭ እና የተሰብሳቢውን ቀልብ በእጅጉ ስቦ የያዘው ንግግር የወያኔ ስርአት በሕዝብ እና በሐገር ላይ የሚያደርሰውን በደል እና ግፍ በተጨማሪም ከዚህ ሁሉ ስቃይ እና መከራ እንዴት እንደምንወጣ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን የትግል መንገድ እጅግ ማራኪ በሆነ መንገድ ለታዳሚው ከማብራራታቸውም በላይ በደቡብ አፍሪካ እና በወያኔ አፓአታይድ ስርዓት መካከል ያሉትን ልዩነቶች እናተጨባጭ ነገሮችን በሰፊው የተነተኑ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ:-
  1- የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት አቀንቃኞች ደቡብ አፍሪካ እንደ ሐገር የመቆየትዋን ነገር በፍፁም ጥያቄ ውስጥ  እንደማያስገቡ፤
-   የወያኔው አፓርታይድ ስርዓት ኢትዮጵያን እንደሐገር እንዳትቆይ እያደረገ እንደሆነና ወያኔ የሐገሪቱን መንግስታዊ ተቁዋማትን በሙሉ እያፈረሰ መሆኑን፤
2- በደቡብ አፍሪካ ግን ምንም አይነት መንግስታዊ ተቁዋማት እንዳልፈረሱ፤
 3-በደቡብ አፍሪካ እስረኞች በምንም አይነት ፍርድ ቤት በፓንት እና ከነቴራ ቀርበው እንደማያውቁ  ነገር ግን በወያኔ አምባ ገነናዊ ስርዓት ግን ፈፅሞ የሰብዓዊ መብትን በጣሰ ሁኔታ እስረኞች ፍርድ ቤት እየቀረቡ መሆናቸውን ለተሰብሳቢው ካብራሩ በሁዋላ:-
ብዙ በደል እና ግፍ እየደረሰብህ የፈለከውን አይነት እርምጃ ወይም የትግል ስልት መውሰድህ ብልህነት ብቻ ሳይሆን አማራጮች የሉህም ሲሉ አማራጮች አለመኖራቸውን ለተሰብሳቢው ካብራሩ በሁዋላ ባለፉት 25 ዓመታት የወያኔ አምባገነናዊ ስርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተገደሉ እንዳሉ ያብራሩት ፕሮፌሰር ብርሐኑ ይህንን የተቃወመ አንድም ምእራባውያን ሐገራት እንደሌለ አስረድተው እራሳችንን ነፃ ማውጣት ያለብን እኛው እራሳችን ነን  በማለት ለተሰብሳቢው በቂ ግንዛቤ ሰጥተው:-
 በአርባ ምንጭ የተደረገው ፀረ ወያኔ ትግል በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች እንደሚቀጥል ያስረዱት አርበኛ / ብርሐኑ ነጋ በሚጠብቀን ዘርፈ ብዙ ትግል ላይ ሁሉም መረባረብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
  አርበኛ / ብርሐኑ ነጋ :- ለነፃነት የሚደረገው ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል እና ይህም በባርነት ከመኖር በእጥፍ እንደሚሻል አስረድተው ሐገራችን አደጋ ላይ ነች ችግሩን በስደት የምንወጣው አይደለም ትግሉ ምርጫ የሌለው እውነት ነው በማለት ሐገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ እጅግ ልብ በሚነካ እና የእናት ሐገር ክብርን ለማስጠበቅ በተነሳሳ የጀግንነት ስሜት በሐገራችን እየተፈፀሙ ያሉትን ግፎች በሰፊው ካብራሩ በሁዋላ "ለነፃነት በመሞት ለሐገራችን ክብርን ማጎናፀፍ አለብን በማለት ንግግራቸውን የቁዋጩ ሲሆን የስብሰባው ታዳሚዎችም በታላቅ ጭብጨባ ድጋፋቸውን እና ያላቸውን አክብሮት ቁዋጭተዋል።
      በመቀጠል ታዳሚን በድንገት ያስደመሙት በስብሰባው ላይ በድንገት የተገኙት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሉ በወያኔ እስር ቤት መስዋእትነት እየከፈሉ ያሉት የአርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እህት / ብዙ አየሁ ፅጌ ሲሆኑ ተሰብሳቢውም ሲያያቸው በወያኔ እስርቤት የሚገኙትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በማስታወስ በእንባ የተራጨ ሲሆን / ብዙአየሁም ለአርበኛ ብርሐኑ ነጋ ያላቸውን አክብሮት እና አድናቆት በመግለፅ ብዙዎች የሞቱላትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ስጦታ አበርክተውላቸው ስለ ወንድማቸው አርበኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የፃፉትን ተሰብሳቢውን በእንባ ያራጨ ግጥም አንብበው ሲጨርሱ ተሰብሳቢው ያለውን አክብሮት በታላቅ ጭብጨባ ገልፆላቸዋል።
 የእለቱን ስብሰባ እጅግ ልዩ የሚያደርገው የኢሳት ብርቅየ ጋዜጠኞችን ገሊላ መኮንን  ከአምስተርዳም እና መታሰቢያ ቀፀላን ከለደን ጨምሮ ከተለያዩ የሰሜን አውሮፓ ሐገሮች የንቅናቄው አባላት እና ደጋፊዎች በብዛት   በመገኘት የስብሰባው ተሳታፊ ሆነዋል፡  በእለቱ የቀረበውን የአርበኛ / ብርሐኑ ነጋ፣ የአርበኛ አንዳርጋቸው ፅጌ እና የአርበኛ መአዛው ምስልን የያዘውን የፎቶ ግራፍ  ጨረታ ለማሸነፍ የተደረገው ከፍተኛ  ፉክክር ሲሆን ለእናት ሐገሩ ክብር ምንም ነገር ቢጠየቅ ወደ ኋዋላ የማይለው የኢትዮጵያዊው የሐገር ፍቅር ስሜት እና አንድነት የተንፀባረቀበት መሆኑም ጭምር ነው።
Patriotic Ginbot 7 Public Meeting in Oslo
የጨረታውም አሸናፊ / ብዙ አየሁ ፅጌ ሲሆኑ ኖርዌይ ላሉ ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አድናቆት በመግለፅ ጨረታውን ስጦታ የሰጡ ሲሆን የኖርዌይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶክተር ሙሉ ዓለም  አዳም ደግሞ ለስዊድን የንቅናቄው አባላት ስጦታ አበርክተውታል።
  በእለቱ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአጠቃላይ ድምሩ 800,162 ክሩነር  የተገኘ ሲሆን  በእጣ የቀረበው ላፕቶፕ አሸናፊም ላፕቶፑን ለንቅናቄው ስጦታ አበርክቱዋል።
ይህ ታሪካዊ ስብሰባ ከመጠናቀቁ በፊት ከስብሰባው ታዳሚዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች የአርበኞች ግንቦት ንቅናቄ ሊቀመንበር አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በቂ ማብራሪያ እና ገለፃ ካደረጉ በሁዋላ ፕሮግራሙ እጅግ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቁዋል።

ኢትዮጵያችን በክብር ለዘላለም ትኖራለች!!!!!!


No comments:

Post a Comment