Translate

Friday, June 19, 2015

እርዱን ፍረዱልን አንልም፤ በነፃነት ተጋድሎአችን አይግቡብን!


Ethiopian author Tsegaye Gebremedihn Arayaበመካከለኛዉ ምስራቅ ዝነኛ የሆነዉ ጋዜጠኛ ድንቅ የስነጹሁፍ ሰዉም ነዉ። በኮሎኔል ጋማል አብዱልናስር የቅርብ ሰዉነትነትና አማካሪነትም ይታወቃል። ሖስኒ ሙሃመድ ሃይከል እንደዳቦ የሚገመጡ መጻሕፍትን በመጻፉ፥ ከመካከለኛዉ ምስራቅ ባሻገር የእንግሊዝ አንባቢዎቹ የጹሁፎቹ እስረኞች ናቸዉ። አሁንም በጋርዲያን ጋዜጣና በስፔክቴተር መጽሄት የሚወጡ መጣጥፎቹ እንደጆን ላካሬ ልብወለድ መጻሕፍት የሚያማልሉ ናቸው። በእኛ በኩል ከዚህ ደራሲ-ጋዜጠኛ The Sphinx and the Commissar መጽሃፉ በቀልድም በቁም ነገርም የተጠቀሰ አንድ አጭር ‘ኤፒሶድ’ ለመዋስ እንወዳለን።
ሐይከል እንደጻፈው ከሰባቱ ቀን የአረቦችና የእስራኤል (1967) ጦርነት ማብቂያ አካባቢ የግብፁ መከላከያ ሚኒስትር ማርሻል ፋዉዚ ሰፋ ያለ የጦር መሳሪያ ሸመታ ሊስት ይዘዉ ወደ ሞስኮ ይሄዳሉ። በክሬምሊን የተቀበሉአቸው የሶቪየቱ የመከላከያ ሚኒስትር ማርሻል ግሬችኮ ነበሩ። በሰባቱ ቀን የሞስኮ ቆይታቸዉ ወቅት እስራኤል ስላወደመችባቸዉ ታንኮች፥ ኤፒሲዎች፥ አውሮፕላኖች – ስለማረከችባቸዉ ስፍር ቁጥር የሌለው የጦር መሳሪያዎች አንስተው እነዚያን እንዴት መተካት እንደሚቻል ሲነጋገሩ ሰንብተዋል።

በዉይይቱ ፍጻሜ ላይ ሁለቱ ማርሻሎች ብቻ ሳይሆኑ በሁለቱም ልዑካን ቡድኖች ዉስጥ አባላት የነበሩ የሁለቱም አገሮች ሹማምንት መለኪያ በማጋጨት “ናዝድራቬ ናዝድራቬ” ሲባባሉ ቆይተዉ የሶቪየቱ የመከላከያ ሚኒስትር የማሳረጊያ ንግግር ያደርጋሉ። የፖለቲካ ባህል ስለሆነ የሶቪየት ኅብረት ቀይ ሰራዊት የጀርመን ናዚዎችን እንዴት እንዳሸነፈ፤ አገሩን ብቻ ሳይሆን መላውን ምስራቅ አዉሮፓን ለድል እንዳበቃና ፒፕልስ ዲሞክራሲዎችን እንዴት እንዳቋቋሙ ደሰኮሩ። ከዚያም ማርሻሉ “አሁንም ከግብፅ ሰራዊት ጎን ተሰልፈን ጽዮናውያንን “እንደመስሳለን! እናሸንፋለን!” ብለው መለኪያ አጋጩ። መፈክር ቀረበ፤ ተፎከረ። (የልዑካን ቡድን አባላት ሆናችሁ ወደሞስኮ የሄዳችሁ ሁሉ የተከታተላችሁት ስነ-ስርዓት ሁሉ ተከናወነ። እንደምታዉቁት በስራ ሰአት በቢሮዎች የሚሾመው ቮድካ፥ ኮኛክ፥ ቪኖ ወዘተ ልክ የለዉም። ትንሽ የአካል ጥንካሬ ከሌለዎ የመጠጡ መጠን አለመኖር ሳይታሰብ ጉድ ያፈላል። ለማንኛዉም ፉከራዋም አለች።)
ትርዒቱ አላለቀም። የሶቪየቱ ማርሻል የግብጹን ማርሻል አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ አጅበው በመሄድ በመጨረሻ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተሰጣጡ። የግብፁ መከላከያ ሚኒስትር ለጊዜው መሳሪያ ጭነው ባይመለሱም፤ መስፈሪያ ሚዛን የሌለው ተስፋ ተሸክመው ሊሄዱ ነዉ። ያንን ተስፋ ከመሳፈራቸው በፊት እንደገና ለመስማት ፈለጉና፤ “ዛሬ ጠዋት የገቡልን ቃል ልቤን አሙቆታል” ይላሉ። በዚህ ጊዜ የሶቪየቱ አቻቸዉ “የቱ ነው ልብዎን ያሞቀው?” ሲሉአቸዉ ፋውዚ “ከእናንተ ጎን ተሰልፈን ፅዮናውያንን እንወጋለን፥ ያሉትን መጥቀሴ ነዉ” ይሏቸዋል። የሶቪየቱም ማርሻል እዚህ ላይ ሲደርሱ “ያንንኮ የጠቀስኩት ‘አንድ ለመንገድ’ ይሆንዎታል ብዬ ነዉ። “One for the Road አያዉቁም?” አሉአቸዉ ይባላል። ማሾፍ ወይም እንደፈረንጆቹ “bluff” ማድረጋቸዉ ኖሯል።
ባለፈው ወር ላይ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) ረዳት ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ የሚወስድ ተልዕኮ ነበራቸውና ወደዚያው ዘልቀው ተመልሰዋል። ለምን ነበር የሄዱት? ተብሎ የሚጠየቅ አይመስለኝም። በዚያ አካባቢ ትልቅ የጦርነት ቋያ አለ። በአረቢያን ፔኒንሱላ ያለውን አልቃይዳ እንዲከላከል ተመድቦ የነበረዉ የየመኑ ፕሬዚዳንት አብደላ ሳለህ፥ በአረብ ስፕሪንግ ባይበላም በህይወት ወጥቶ የመለስ ዜናዊ እንግዳ ሆኖ ነበር። አሁንም በዚያው አካባቢ ብቅ ጥልቅ ይላል። የመንን በተለይ ሆዴይደንና ሳንዓን ከአሰብ ድንጋይ ወርውረህ አንድ ሰው ልታቆስል ትችላለህ። አሜሪካ ደግሞ የእኛ ቤተኛ ስለሆነች ጋሞ ጎፋ (አርባ ምንጭ) በርከት ያሉ ሰው አልባ አዉሮፕላኖች (drones) አሰማርታ እነዚያ እንደዳክዬ ጉብ ጉብ ብለው ተቀምጠዋል። ስድስት ሺህ የአሜሪካ ሰራዊት ጅቡቲ ላይ መሽጓል። ባራክ ኦባማ ደግሞ የተመረጡበት አንድ ዓቢይ ቃል ኪዳን (ፕላትፎርም) በአመራራቸዉ ዘመን አንድ አሜሪካዊ በየትም አገር የጦር ሜዳ ላለማስገባት ስለሆነ ምንደኞችን በበጎ ፈቃድም ይሁን በግዥ ለማሰማራት አዘጋጅታ ያስቀመጠች የሃይለማርያም አስተዳደር አለች። እግረ-መንገዳቸዉን ወሃቢስቶችም ኤርትራን እንዲያግባቡ በዚያዉም (በነካ እጃቸው) ኢሳያስን ከርቀት ሆነው ከሚሳደቡበት አቅጣጫ እንዲመልሱ ልዩ ተልእኮ ተቀብለው ኤርትራዊውን መሪም በሪያድ አነጋግረዋል። ስንቅና ትጥቅ በማቀበል ረገድ (የመንን በኢራኖች ከሚደገፈዉ ደብረ በጥብጥ ኢስላማዊ ሃይል ለመታደግ) ዘመቻ ማስተባበር ያስፈልጋል። ምን ያስፈልጋችኋል? ምን ይሟላላችሁ? የሚል መልእክት ከማስተላለፍ ባሻገር ዌንዲ ሸርዉድ ጥቃቅን የመሰላቸዉን ራሳቸዉ ለመፈጸም ቃል ይገባሉ። ለነገሩ አዲስ አበባ ላይ ብሄራዊ ባንኩ የዉጭ ምንዛሪ የለኝም ማለት ከያዘ ሰንብቷል። አሜሪካ በዓመት የሚሰፍርልን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የት እንደደረሰ እንግሊዝ ብቻ ለበጀት ማስተካከያ፥ ለዕዳ መክፈያና ለመሳሰሉት የምትሰጠዉ ሶስት መቶ ዘጠና ሶስት ሚሊዮን ፓዉንድ የአዲስ አበባን መንገድ አለማየቱን ሴትዮዋ እያወቁ አያውቁም። የአዉሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በአጠቃላይ ለዚያ “ቀበኛ” እያሉ ለሚያሙት መንግስት ከቢሊዮን ዶላርስ በላይ ያፈሳሉ። እዉነትም ቀበኛ? “አየሁን” አያውቅም። ገንዘቡ የሚገባበት የበርሙዳ ትሪያንግል አለ። ለዌንዲ ያ ሁሉ ኢምንት ነዉ። ወያኔ ስለሚያስራቸዉ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎች – በአደባባይ ስለሚረሸኑ ኢትዮጵያዉያን ደንታ የላቸዉም። ያልተነሳም። አይነሳም። ጠባቸው ከአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተከታታይ ሃይላት ጋር ነው። የዌንዲ ደንበኞች አይን ለአይን መተያየት የማይችሉ፥ ለምስክርነት የማይበቁና ከህሊናቸዉም ጋር የተሰነባበቱ ናቸው። ሴቲቱ ግራ የገባቸውና የሚያሳዝኑ ናቸው። ሀይለማሪያምና ጭፍሮቹ በምንም አይነት ሊደገፉ አይችሉም። ለአሜሪካኖቹ ደግሞ ስለነሱ የሚሰጡት ድጋፍ ሁሉ የሚያስገምታቸውና የሚያሸማቅቃቸው ነው። ወራዳና ባለጌ ባቆለጳጰስኸው ቁጥር ውርደቱ ሁሉ ወዳንተ ትከሻ ይዛወራል። ዌንዲ የዚህ ሰለባ ናቸው።
መጽሃፋችን “የሚያበራየዉን ወይፈን አፍ ማሰር አይገባህም” ይላል። የመንግስታችን እምነትም ይኸዉ ነዉ። የዉጭ ምንዛሬ በዉጭ፥ ለዉጭ ይቀመጣል። በአገር ከአገር የሚገኘዉ ገንዘብ ክርስቶስ እንዳለዉ የ “ቄሳር” ነዉ። ያም ሆነ ይህ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ይህን ለመተሳሰብ ስልጣንም ዉክልናም የላቸዉም። ቢሆንም የመንግስታችንን ቀማኛነት፥ ፍርደ-ገምድልነትና፥ ተራ ሽፍትነት ¬– ወደር የሌለው ወንጀለኝነት አያውቁትም አንልም። እኛ እንኳ ማስረጃ ስንጠይቅ ዋቢያችን የዌንዲ መስሪያ ቤት ሪፖርት ነዉ። በአጭሩ በኦባማ ፍልስፍና መመሪያ መሰረት ¬– በተለይ ኦባማ “America should lead the world” የሚል አቋም በሰፊው እያራመዱ እንደ መሆናቸው አለምን የሚመሩበት አንደኛው አቋም የአሜሪካንን ጦርነት ደሀ ልጆቻችን በጦርነት መሰውያዉ እሳት ላይ ማንደድ ብቻ ሊሆን ነዉ::
በወያኔ በኩል አሁንም በመስዋዕትነት የሚቀርብ አለ። ስራዊቱ የእሳት ራትና የመድፍ ቀለብ እየሆነ ይዋጋላቸዋል። አሁንም ይዋጋል። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የወያኔ ባለስልጣኖች ለሴቲቱ ያቀረቧቸዉ ጥያቄዎች ምን እንደነበሩ መገመት ይቻላል። ጠንቋይ በመቀለብ ወይም በጸሎት የሚገኝ አይመስለኝም። ወያኔ ለአሜሪካም ሆነ ለሌላ ሀይል የኢትዮጵያ ልጆች የሆኑትን የሰራዊቱን አባላት በምንደኝነት ለማከራየት ዝግጁ ናቸው። በእውነቱ በእነ ሐይለማሪያም ደሰለኝ በኩል ሳይቀፍፋቸው፥ ለአፍታ እንኳን መንፈሳቸውን ሳይረብሸው ከቶውንም ጮቤ እየረገጡ የሚፈጽሙበት ይህን መሳይ ወራዳ ሰራ ነው። አሜሪካኖች በፈንታቸው ሊያስነኩ የማይፈልጉት እንዲህ ያሉ ወገኖቻቸውን የሚሸጡ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ሕሊና፥ መንፍስና፥ ነፍስ ለመሸጥ የተዘጋጁ ሰዎችን ነው ። እንዲህ ያሉ መሪዎች ከየትም አናገኝም ቢሉ አይደንቀንም። የአሜሪካ ድጋፍ ምክንያት ይህ ነው ።
የእኛዉ መሪዎች ከጦር መሳሪያ ሸመታዉ ዝርዝር፥ በመካከለኛዉ ምስራቅ በተለይም በሶማሊያና በየመን ባህረ ሰላጤ ከአሜሪካ ጋር ለመቆም ከሚያሳዩት ስምምነት ባሻገር ለመሄድ ዝግጁ ናቸው። ዌንዲ እንደሚሰማቸዉ ዛሬ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትፈልገዉን ሁሉ ለማቅረብ የሚችለው ወያኔ ብቻ ነው። ያ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለኢትዮጵያ ያልቆመ በጥቃቅን ጥቅም ሊታለል የሚችልና “ብሄራዊ ክብር” የሚባል እምነት የሌለዉ መሆኑን ያውቃሉ። በገበያ የሚፈለገው አይነት መንግስት ተገኝቷል ማለት ነው። እንዲያም ሆኖ በጊዜ ማህፀን ዉስጥ ያለ መንግስት መፈለጋቸው እዉነት ነዉ። ጨረታው ከወጣ ደግሞ ቆይቷል። የተቃዋሚ ሃይሎችን ባነጋገሩ ቁጥር “ግልፅ አማራጭነታችሁን አረጋግጡ” እንዳሉ ነዉ። በዚህ አንጻር እነሱ ከአሜሪካ የሚያገኙት ጥቅም ሁሉ ተደማምሮ የእነ ብርሃኑ ነጋ ግንቦት ሰባት የማታ ማታ ምን ሊያደርስባቸዉ እንደሚችል አይዘነጉትም። የህልዉና ጥያቄ ነው ለወይዘሮይቱ ያነሱት። አዎን በየቦታዉ ሰራዊቱን እየላኩ የመድፍ ቀለብ፥ የእሳት ራት እያደረጉት ነዉ። ለኢትዮጵያ ጦርነትና ጥቅም ሳይሆን ለትልቁ ወንድም (ቢግ ብራዘር) የመስዋዕትነት ጠቦት እየሆንን ነዉ። በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ለበርካታ አመታት (ከ1945 ወዲህ) የአሜሪካ መሪዎች “ይህ የአሜሪካ ዘመን ነዉ። አሜሪካ ዓለምን መምራት አለባት የሚለዉ የፖለቲካ ፈሊጥ በኦባማ የግዛት ዘመንም የበለጠ እየተራገበ መሆኑ ይደንቀናል። በ21ኛ ምዕተ አመት ሌሎች የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች አሜሪካን ወታደሮችን በጦር ሜዳ እያሰማሩ ሲሆን ኦባማ ግን ለአሜሪካ የዓለም ገዥነት የሌሎችን ሕዝቦች ነፍስና ደም የሚፈልጉ መስለዋል። “አሜሪካ አለምን መምራት አለባት” “America should lead the world” ያለይሉኝታ የሚነገር፥ አለም በሙሉ ለአሜሪካ መገበር እንዳለበት በእብሪት የሚገለጥ መፈክር ሆኗል። ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ወዲህ አሜሪካ ብቸኛዋ ልዕለ-ሃያል በመሆንዋ ዓለም በሙሉ በእስዋ ፈቃድና ትዕዛዝ መሰረት መገዛት አለበት የሚል እብሪት የተሞላዉ አቋም ተፈጥሯል። አዎን! ነፍሰ ገዳዮችና የአራዊት ልብ የገባላቸው አምባገነኖችን አሜሪካ እያደነች በሕዝቦች ላይ በመጫን አለምን የመግዛትዋን አቋም ማንም ህሊና ያለው የአለም ዜጋ አይቀበለውም። በ21ኛው ክፍለዘመን አዲሱን የባርነትና የተራቀቀ ኒዮኮሎኒያሊዝም ለመቀበል ያዳግታል።
ወደ ሚስ ሸርዉድ እንመለስ
ሴቲቱ ከወያኔ መንግስት ባለሟሎች ጋር በሰፊዉ ሲወያዩ በአጀንዳዉ ውስጥ የወያኔ ጠላቶች ጉዳይ እንደሚያዝ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ስለሆነም ግንቦቶችና በዚያ የገለማ ስርዓት ላይ የተነሱ ሃይሎች ሁሉ ስለነሱ የተባለና የሚባል ጉዳይ መኖሩን መገመት አለባቸው። እንዲያዉም ማንም የአሜሪካና የአዉሮፓ መንግስት ባለስልጣን ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝና የወያኔ ሹማምንት ወደ እነዚህ አገሮች ሲሄዱ ከልመናና ከግዥ ሰነዳቸዉ ሊስት ዉስጥ ይህ ጥያቄ ዋነኛዉ መሆኑን መገመት አለ።
የዚህ መጣጥፍ መክፈቻ ካደረግነዉ የአልአህራም ጋዜጣ አዘጋጅ “አንድ ለመንገድ” አንጻር የሚስ ሸርዉድን መግለጫ መውሰድ እያመች ይሆናል። ይሁንና ሴቲቱ ለወያኔ አመራር ከሰጡት ተልዕኮና ሃላፊነት አንጻር የተወሰኑ የወያኔን ጠላቶች ማስፈራራት ትንሹ ውለታ ነበር። ወይም እስከ እናካቴዉ ግሬችኮ ለፋዉዚ የሰጡት የሽንገላ ቋንቋ ይሆናል። ፈረንጅ “የማሾፍ ፖለቲካ” ወይም bluff የሚለዉ ነዉ። ይህንን የፈረንጆች “የማሾፍ ፖለቲካ” ከራሳችን ታሪክ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
የቪክቶር ኢማኑኤልና የቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢጣልያ የመንግስታትን ማህበር ቃል ኪዳን ጥሳ ኢትዮጵያን ስትወረር በደፈጣ ፖለቲካ ውስጥ ገብተዉ የፋሽስቶች ረዳት ለመሆን ከአለም አቀፍ ሴራው ዋነኛ ተዋንያን መካከል የእንግሊዙ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰር ሳሙኤል ሖርና የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒየር ሳቫል ነበሩ። እነዚህ ሁለት ዲፕሎማቶች የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ዋና ጸሃፊና የአንዳንድ ሌሎች መንግስታት ወኪሎች አምታተው ሴራቸውን ተያይዘውታል። በዚሁ መሰረት ፈረንሳይና እንግሊዝ የሙሶሊኒ ሰራዊትና የጦር መሳሪያ በስዊዝ ካናል በኩል ወደሞቃዲሾና ምጽዋ እንደተሸኘ ያውቃሉ። የሙሶሊኒ ሰራዊትና የጦር መሳሪያ፥ የአየር ቦምቦችና የነርቭ ጋዝ በስዊዝ ካናል ፀሃይ እየሞቀዉና 140 የእንግሊዝና የፈረንሳይ መርከቦች እያዩአቸዉ ኢትዮጵያዉያንን ለመጨረስ ተጭኖ አልቋል። በዚህ መካከል ቀና አመለካከትና ሰብዕና የነበራቸዉ በሊጉ የእንግሊዝ ቋሚ መልእክተኛ የነበሩት አንቶኒ ኢደን በሴራዉ በመብሸቅ አንጀታቸዉ ቆስሎ አልሰሩ አላስበላ አላስጠጣ ብሏቸዋል። በመካከሉ ሁሉ ነገር ለኢጣልያ ከተመቻቸና በሽሬና በአምባአላጌ እንዲሁም የጦር ሚኒስትሩ ራስ ሙሉጌታ በነበሩበት ግንባር (50ሺ ጦር) ሩቡ ያህል በቦምብና በጋዝ ሲያልቅ ላቫልና ሖር የፖለቲካ ትርኢት ማሳየት ይጀምራሉ። በዚህም መሰረት ሰር ሳሙኤል ሖር ወደ ጄኔቫ በመሄድ ወደሊጉ ስብሰባ ገብቶ “የሊጉ ቃል ኪዳን ይከበራል! አይታጠፍም! ሊጉ ለቆመለት ቁም ነገርና አላማ አገሮች ማናቸዉንም መስዋዕትነት ይከፍላሉ። እንግሊዝ ወረራውን በቀላሉ አትመለከተዉም” በማለት ጉባዔውን አንጫጫው። አዳራሹ በጭብጨባ ተቃጠለ። በዚሁ ልክ ፒየር ላቫልም ከሊጉ አዳራሽ ውጭ ሆኖ “ፈረንሳይም ከሊጉ ጋር ትቆማለች” እያለ ሲጮህ ዋለ። (በነገራችን ላይ የታሪክ ፍርድ ሲገመገም ሳቫል ማታ ላይ ፓሪስ ውስጥ የተለመደ እንቅልፉን ማለዳ ሲጨርስ ፈረንሳይ የሂትለር ግዛት ሆናለች።)
ሁለቱም የፖለቲካ አሻጥረኞች በጄኔቫ እንዲያ ሲናገሩ ብዙ የመንግስታት ወኪሎች ተቀብለዋቸዉ ነበር። ታዲያ ሳሙኤል ሖር በሊጉ ጉባዔ ላይ ያደረገዉን “ታሪካዊ ንግግር” በተመለከተ በትዝታ መጽሃፉ ውስጥ ማሾፌ ነበር፥ “It was all a bluff” ብሎታል። ራሱ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ሳሙኤል ሖር ያንን ንግግር ካደረገ በኋላ በማግስቱ በእንግሊዙ Morning Star ላይ ባወጣዉ ጽሁፍ “ሰራዊታችን ያለ ችግር ምስራቅ አፍሪካ ገብቷል! ጉዳዩ የሁለት ቢሊዮን ሊሬ ጥያቄ ነበር። ያንን ሁሉ በሰማይ ከዋክብት የሚለካ ገንዘብ ያወጣነዉ ለለበጣ መሰላችሁ?” ብሎአል። በዚሁ አይነት እኒህም የአሜሪካ ዲፕሎማት የተናገሩትን ያናገራቸው የከዋክብት ግምት ያለው ጣጣ ካልሆነ እንዲሁ የፖለቲካ bluff ነው ትላላችሁ? የአዉአሎም ልጆች አካሄድኮ አይታወቅም። በመልካም ልግስና ብዙ ስራ ለመስራት እንደሚፈልጉ አንዳንድ ጊዜም በእህቶቻችንና በሚስቶቻቸዉ አማካኝነት ወፍራም አስበ ደነስ (ግዕዙን ቀሲስ አስተርይ ካልተቃወሙት) እንደሚያፍሱ ይታወቃል። ተክነዉበታልም። እንዲያም ሆኖ እንደ ሳሙኤል ሖር It was a bulff ወይም እንደ ማርሻል ግሬችኮ It was one for the road የሚሉበትም አጋጣሚ አይጠፋም። ኣድሮ ማየት ነዉ። ታዲያ ብዙዎቻችን ሚስ ዌንዲን የወቀስናቸዉንና የተቸናቸዉ፥ “እንዴት ለወያኔ እንዲህ ያለ ምስክርነት ይሰጣሉ?” በማለት ነዉ። ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መግለጫዎች አንዲቱን ይዤላቸዋለሁ። አሜሪካኖች ለመስማት ሲፈልጉ ይሰማሉ፤ ለማየት ሲፈልጉ ያያሉ። ለማየት ሲፈልጉ በሳር ክምችት ዉስጥ ያለች መርፌ ያያሉ። ካልፈለጉ ደግሞ በእልፍኝ ዉስጥ የሚጎማለል ዝሆን አይታያቸዉም ብለዋል። ዌንዲ አስመሳይና የዉሸት ተለማማጅ እንጂ በደደብነት የሚታሙ አይመስለኝም። (በነገራችን ላይ ሴትዮዋ ተገፍተው ወጥተዋል። ዕድል ሌላ ጊዜ ይህን የመሰለ ስራ የምትሰጣቸው አይመስልም። የምዕራቡ የፖለቲካ አምላክ የጻፈላቸው የፈረደባቸው እንዲሁ ዘወር ማለትን ብቻ ነው።
በአለም ዙሪያ በዚህ መልክ ሲያካሄዱ የኖሩትን ለአብነት ማቅረብ ይቻላል። ለቦታና ለጊዜ፥ እንዲሁም ጹሑፍ ላለማንዛዛት ከኢትዮጵያ ሁኔታ አንድ ማስረጃ እናቀርባለን።
በ1950ዎቹ (እስከ 1958 ይመስለኛል) በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ኮሪ ትዝ ይሉኛል። ጆን ኬኔዲ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በሆኑበት ስዓት ከመረጧቸዉ ወጣት የሐርቫርድ ምሩቃን መካከል አምባሳደር ኮሪ አንዱ ናቸዉ። ከንጉሠ ነገስቱ እልፍኝ ከአዳራሽ፥ የዙፋን ችሎትና እንዲያ ባሉ ስፍራዎች የሚሽከረክሩ ናቸዉ። ይህ ብቻም ሳይሆን በመኖሪያ ቤታቸዉ በየጊዜዉ ድግስ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በወር አንድ ቀን የጋዜጦች አዘጋጆች ይጋብዛሉ። እሳት ግር ብሎ ይነድዳል። የፈለገ ጥሬ ስጋ ያወራርዳል። አለዚያ ቄንጠኛ ጥብስ በኮኛክ ይጠበሳል። ፍሌመኞን ነዉ የሚባለዉ? ቲቦን ወዘተ ይቀርባል። ማወራረጃዋ ኮኛክ በእድሜዋ ትመጣለች። ኦን ዘ ራክስ ተለምዷል። በአጭሩ የአምባሳደር ኮሪ ግብዣ የምትናፈቅ ናት። የፕሬዚዳንት ሩዝቬልት የኋይት ሃዉስ “ባህል” እየተባለ በሚጠቀሰዉ ስልት ከመኖሪያ ቤታቸዉ ጎምቱ ጎምቱ የሆኑ ሰዎችን እየጠሩ፥ እያበሉና እያጠጡ ለነገና ለተነገ ወዲያ ስራ የሚጠቅማቸዉን ጉዳይ መተኮሻ ኣድርገዉታል።
አንድ ቀን (1959?) ለጦር አዛዦች የሚሰጥ ግብዣ ነበር። ጄኔራል መኮንኖች በተለይ የሃይል አዛዦች በብዛት እንደነበሩ አይጠረጠርም። ለእነዚህ ደግሞ ወደ አሜሪካ የሚወስድ ስያሜዉ “ሊደርሺፕ ቱር” በተሰኘ ፕሮግራም እየመጣ ሁሉም የአሜሪካ ልጅነት እስኪሰማው ድረስ የሚቀብጥበት አጋጣሚ ነበር። ከዝርዝሩ እንመለስና በአንዱ የግብዣ ወቅት ሁሉም ከንጥረ-ነገሩ ገፋ አድርጎ ሲወስድ አምባሳደሩ ከዋናዉ ጄኔራል ጋር ድምጻቸዉን ቀንሰው ማዉራት ይጀምራሉ። “ሆድ ያባዉን ብቅል ያወጣዋል” የሚባለዉ አነጋገር በፈረንጅም አለ “In wine comes the truth” ። ታዲያ አምባሳደሩ ሌተና ጀኔራሉን ከልብ ማጫወት ይዘዋል። “ጄኔራል ዛሬ እኮ በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ወታደራዊ መፈንቀለ-መንግስት እየተካሄደ ነው። ይህ የወታደር መንግስት መቋቋም ጉዳይ ማቆሚያ አጥቷል። ለዚህም መንግስት ሳያሰጋ አይቀርም። ያስቡበት። ያንን የመሰለ ሁኔታ እንዳይፈጠር እርስዎን ልንረዳዎት እንችላለን” በማለት አንድ ትልቅ ኳስ ከሜዳቸዉ ዉስጥ ይጥሉላቸዋል። ጄኔራሉ ግን ነጋ አልነጋ ብለዉ ወደ ንጉሰ-ነገስቱ ዘንድ ሄደዉ “አሜሪካኖች” ምንኛ የማይታመኑና ወዳጃቸዉ የሆነዉን ይህን መንግስትም እንደምንም ለመለወጥ እንደሚሹ ይገልጡላቸዋል። የፖለቲካው የጊዜ ጨዋታ አጤ ዮሃንስ ወይም አጤ ሃይለስላሴ “ለአሜሪካ ታማኝ አይደሉም” የሚል አይደለም። ዋናው ጉዳይ የሃይለስላሴ መንግስት መገልበጡ የማይቀርና ባይሆን የሚመጣዉን መንግስት አዋላጆች አሜሪካኖች ራሳቸው ይሆኑ ዘንድ የሚቀይስ ፖለቲካ ነዉ። (በነገራችን ላይ አምባሳደር ኮሪን ጃንሆይ ሲያስጠሯቸው ሰዉየዉ ጉዳዩን በመጠርጠር ወደላንጋኖ ሄደዋል አሰኙ፤ ጃንሆይ ደግሞ ለፕሬዚዳንት ጆንሰን ስልክ ደዉለዉ ዲፕሎማቱ ሳይዉል ሳያድር “እንዲጠራ” ተደረገ። ምን ሆነ መሰላችሁ? አምባሳደር ኮሪ ለጥቂት ጊዜ ዋሽንግተን አካባቢ ሲሽከረክሩ ቆይተዉ ሳልቫዶር አየንዴ በቺሌ ሶሻሊስት መንግስት እንዳቋቋሙ ያንን ለመገልበጥ ሁሉንም ሴራ ጎንጉነዉ በመጨረሻ ላይ ያለዉን ምዕራፍ ለናትናኤል ዴቪስ አስረክበዉ ወደዋሽንግተን ተመለሱ። ናትናኤል ዴቪስ ከጄኔራል ፒኖቼ ጋር ሁሉን ነገር ጨርሰዉ ከቅልበሳዉና እልቂቱ አንድ ቀን በፊት ወደ ዋሽንግተን ተመለሱ። ከዚያ አንድ ወር ሳይሞላቸዉ በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሆኑ “አግሪማ” (ስምምነት) ተጠየቀ። በነካ እጃቸዉ አብዮት ይቀለብሱ ዘንድ ነዉ። ይህ እንቅስቃሴ ረጃጅም ጽሁፎች የሚቀርቡበት ሲሆን ምናልባትም ሊሰመርበት የሚገባዉ አንድ ሃቅ አምባሳደር ኮሪ እንዳሉትና እንደፈሩት ሁሉ “የማይታወቁና እንዲያዉም በየጦሩ ካምፕ የተናቁ” ወታደሮች ያንን የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክ ገረሰሱት። ስዩም ሐረጎት “Serving Emperor Haile Selassie” በሚለዉ መጽሃፉ እንደገለጠዉ ደግሞ “የክብረ-ነገሥት ፍጻሜ” ሆነ።
ሚስ ሸርዉድ ግንቦት 7ን ሽብርተኛ አድርገዉ ሲያቀርቡ ከልባቸዉ ላይሆን ይችላል። የምለዉ ይህ እንቅስቃሴ ኣድጎና ተጠናክሮ ይህን ዛሬ የሚረዱትን መንግስት ጨምድዶ ወደታሪክ መጣያ ቅርጫት ሲወረውረው ለማየት ቢችሉ ደስ ይላቸዋል ባይ ነኝ። ከዚያም በፊት ጥንካሬውንና “ግልፅ አማራጭነቱን” በማየት “እሹሩሩ” ቢሉት አይድነቃችሁ። ብቻ ሴቲቱ የእኛ ሰዉ እንደናቃቸዉና እንዳዘነባቸዉ ሁሉ የኦባማም አስተዳደር የፈቀዳቸዉ አልመሰለኝም። በቃሽ ተብለዋል። የታላላቅ መንግስታት ፖለቲካ በመሰረቱ ይህን ይመስላል። ረቂቅ ፖለቲካና ጠለቅ ያለ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ከነዚህ መንግስታት ስትጠብቁ ሳታስቡ አንሰዉ ስታገኟቸዉ አለመደነቅ ነዉ። የሚስ ሸርዉድ መስሪያ ቤት ቢያንስ ባለፉት አስር አመታት ሰለወያኔዎች ፖለቲካ አሳፋሪነት፥ ስለሰብአዊ መብት ሬከርዳቸዉ አስቀያሚነትና ስለ ኢኮኖሚ ያላቸዉ ዝቅተኛ የሞራል ደረጃ የራሳቸዉ መንግስት ያወጣውን ተደጋጋሚ መግለጫ አያዉቁትም፤ አልሰሙትም ብሎ ማሰብ አያመችም። ምናልባትም በዝግጅቱ በስተጀርባም ሊኖሩ ይችላሉ። እኔ የሎርድ Parlmerston “ነፍስ አይማረዉ” የምልበት ጊዜ ሞልቷል። በ 1848 የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረዉ ይህን ግለሰብ ንግስት ቪክቶሪያ “ለመሆኑ በዛሬዉ ዕለት የእንግሊዝ ወዳጆችና ጠላቶች እነማን ናቸዉ?” ብለዉ ይጠይቃሉ። ያን ጊዜ ነዉ “እንግሊዝ የዘለቄታ ጠላትም ሆነ የዘለቄታ ወዳጅ የላትም። የዘለቄታ ጥቅም እንጂ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ስለዚህ በፖለቲካቸዉ ውስጥ ጥቅም እንጂ ሞራሊቲ የሚባል ቅመም የለም። ሰብአዊነት ብርቅ እሴት ነዉ። ይልቁንም ለጥቅማቸዉ መከበር ሚሊዮንና ትሪሊዮን የሆነ ነፍስ ቢጠፋ ቁብ አይሰጣቸውም። የሕዝብ የሕሊና ቁስል አይሰማቸውም። የሚዘረፍ የለም እንጂ ከዚች ደሃ የኢኮኖሚ ቋታችን ኣድፋፍተዉ ቢወስዱብን የሚሰማቸዉ እንዳች የህሊና ወቀሳ የለም። ለነገሩ ታላላቆቹ መንግስታት በፖለቲካ ቀመራቸው ዉስጥ ህሊና የለም። የህሊና ወቀሳ “ላም ባልዋለበት” ነዉ። ሚስ ሸርዉድ እንደሌሎቹ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ሁለት ነፍስ ናቸዉ። በአደባባይ ወያኔ የሚወደዉን በመናገር ሊሸዉዱት ይወዳሉ (ይፈልጋሉ) ። በግል የተወሰኑ ሰዎች ህሊናቸዉን የሚወቅስ ጉዳይ ሲያቀርቡላቸዉ “ወንጀላቸዉን ሁሉ ከእናንተ የበለጠ አዉቃለሁ” የሚሉ ናቸዉ። አንድ ሰዉ አንድ ጭንቅላት ሁለት ምላስ! ይህን መሳይ የፖለቲካ ዘማዊነት ከታላላቆቹ መንግስታት ደጋግማችሁ ትሰማላችሁ። ማፈሪያ! እንዲህ ሲያደርጉ መንግስታቸዉን እንደሚጎዱ ለማወቅ አይፈልጉም። ወያኔዎችን “እሹሩሩ” ካላሉና bluff ካላደረጉ ወደብጫዉ መንግስትና ብጫዉ ጎዳና (ቻይና) ይሄዳሉ ብለዉ ተራ ፍርሃት ይመጣባቸዋል። የፖለቲካው ዘማዊ ባህርይም ይህ ከንቱ ስጋት ነው።
አዎን ትላልቆቹ አገሮች – ድሮ የምናዉቃት ሶቪየት ኅብረትና አሁንም ጣዕሟን የበለጠ እየተረዳን የመጣነዉ አሜሪካም ወሮበላ መሪዎችንና አምባገነኖችን ይወድዳሉ። ያስጠጓቸዋል። እነዚህ ግለሰቦች የሞራል ትልቅነትና የነፍስ ‘ንፅሕና’ ስለሌላቸው ለባርነትና ለአገልጋይነት የተመቹ ናቸው። ዝግጁ ናቸው። የሚዋረድ ኩራት የላቸውም። እንደምታዩት እነ ስብሐት ነጋ ከእንስሳዊ ሰብዕናቸው የት ይወርዳሉ? አንዳንድ ደማካ ነፍስ የሆኑትንም በአምባገነንነት ይቀርጿቸዋል። የእነሱን ተልዕኮ እስከፈጸሙ ድረስ ማናቸዉም ድጋፍ ይሰጧቸዋል። ህዝባዊ ወንጀሎቻቸውን የሚያዩ አይኖች የሏቸዉም። የአሜሪካ ቅምጥሎች የነበሩ እነ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮን፥ እነ ሳሞዛን፥ እነ ባቲስታን፥ እነ ሻህ ኤንድሻህ ፓሕላቪን ይጠቅሷል።
ከዚህ እኩል አምባገነን በመፍጠር ሂደት የአሜሪካኖችን ሚናም እንዲሁ ማንሳት ይቻላል። ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ከሚደነቁት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው መካከል ዲን አክሰን (Dean Acheson) ይገኛሉ። እንደሚታወሰው በ1952 የግብፅ ወጣት መኮንኖች ቡድን ፋሩቅን ከስልጣን አባርሮ የብዙሃን ፓርቲ አመራርን ለማስፈን ይንደፋደፍ በነበረበት ሰዓት ከዲን አኬሰን በኩል የቀረበዉ አሳብ እኔ መልቲ-ፓርቲ በምትሉት ዉዥንብር ዉስጥ ስዳክር አልገኝም። ከሺ ሰዎች ጋር መደራደር አልፈልግም። ይልቁን ከመሃላቸዉ ጉልበት ያለዉ አንድ ሰዉ ይውጣና ልንረዳዉም ልንንከባከበዉም እንችላለን” ብሏል። የዲን አኬሰንን የትዝታ መጽሃፍና በቅርቡ ስለግብጽ ሬቮሉስዮን የተጻፈዉን Soldiers, Spies and Statesmen ይመለከቷል። ናስርን በአምባገነንነት የመፍጠሩን ሃላፊነት የወሰዱት ዲን አኬሰን ነበሩ ማለት ይቻላል።
ራቅ ባለ ዘመን (ምንአልባትም 47 አመት) ያነበብሁት “The Boss” የተባለዉ መጽሃፍም የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (በመንግስት ውስጥ ያለው መንግስት) እና ዲን አኬሰን እንደሚነግሩን ለአሜሪካ ጥቅም ተቀዳሚነት የሚተማመኑበት አምባገነን እስከመፍጠርና እሱንም እስከመንከባከብ የደረሰ (የሚያደርስ) የቅብጠት አያያዝ ሊሰጡ ይገደዳሉ። በካይሮ ለናስር መንግስት በሚሰጡት ክብካቤ በመጀመሪያ ላይ ይህንን አጽንተዋል። በኢራን ህጋዊዉንና በህዝብ የተመረጠዉን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሃመድ ሞስዴህን በመገልበጡና ሻህ ኤንድ ሻህ ፓህላቪን በማንገሡ ሂደት (1953) የአሜሪካ ሲአይኤና የእንግሊዝ መንግስት (ኤም አይ ሲክስ) ሚና በሃፍረት የሚታወስ ነዉ። ቀደም ባለዉ ገለጻ በቺሊ በህዝብ የተመረጠዉን ሳልቫዶር አየንዴን በመግደልና መንግስቱን አስገልብጦ ጨካኝና ጨቋኝ የሆነዉን ጄነራል ኦግስቶ ፒኖቼን መጎለቱን አንስተናል።
እነዚህ አምባገነኖች በህዝቦች ላይ የፈጸሙት ደባ፥ ያቋቋሙአቸዉ የሽብር ሪፐብሊኮች (ግዛቶች) ታሪክ በትክክለኛ መልኩ ተዘግቦ የሚገኘዉ በሲአይኤ መስሪያ ቤት ነዉ። የአሜሪካም የፖለቲካ ነውር ማስረጃ ሁሉ የሚገኘዉ በዚያዉ ባህረ-መዝገብና የፖለቲካ ሰነድ ዉስጥ ነዉ። ሌላዉ ቀርቶ ሲአይኤ ከተመሰረተበት ክ1948 አንስቶ ከ52 የማያንሱ በህግ የተመረጡ የዓለም መሪዎች ለአሜሪካ ጥቅም ባለመመቸት ሰበብ ተገድለዋል። እነ ሉሙምባና የፓናማ ሶስት መሪዎች ከዚህ ተራ ዉስጥ ይመደባሉ። ታዲያ ፕሬዚዳንት ኒክሰን የኒካራጉዋን ህዝብ ደም እያስለቀሰና በአንዳንድ ጸሃፊዎችም አገላለጽ “ደም እየጠጣ” የገዛዉን የአናስታሲያ ሶሚዛን (ደባልዬ) አምባገነንነት ተጠይቀዉ የሰጡት መግለጫ በትምህርት ማዕድ ላይ እንኳን የሚጠቀስ ነዉ። ኒክሰንን እንጥቅሳቸዉ፤ “Yes I know Somosa is a son of a bitch፥ but he is our son of a bitch” ነበር ያሉት።
እኔ የወቅቱን ወንጀለኛና “ማፈሪያ” የኢትዮጵያ መሪዎች (ገዢዎች) በኒክሰን ቋንቋ ላዉቃቸዉ አልፈልግም። ለፕሬዚዳንት ኦባማና ለዌንዲ ግን የግላቸዉ sons of bitches ናቸዉ። አሽከርነታቸዉንና ነፍስና ስጋቸዉን ለእነሱ አገልግሎት ማዋላቸውን እቀበላለሁ። “የዉሻ ልጅ” የምትለዋ ቋንቋ ለአማርኛዉ አገላለጥ ስለማትስማማ ሌላ አማርኛ ልናመጣ እንችላለን (በዚያ ትክ ማለቴ ነዉ)። የዛሬ 267 ዓመት ወደ ፖለቲካዉ መዝገበ ቃላት የገባዉ “ዘላለማዊ የወዳጅነትና የጠላትነት መለኪያና የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ እምብርት የአሜሪካ ወይም የእንግሊዝ ጥቅም” የመሆኑ ጉዳይ ዛሬም እየተሰመረበት ነዉ። ውብ ቋንቋና ጥዑም አነጋገር ያላቸዉ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አሜሪካ አለምን መምራት አለባት” እያሉ ደጋግመው ይነግሩናል። በሚመች ጊዜ ይህን አገላለጥ በራሱ ባሕርያትና ይዘት በሰፊው ብመለስበት ደስ ይለኛል። አገሬ በእድገትና በሰላም ገስግሳ ከአሜሪካ ብትስተካከል እጅግ እደሰታለሁ። የመጨረሻ ህልሜ ግን አለምን ትገዛ ዘንድ አይደለም። የእኛ ከወያኔ ነጻ መዉጣት የአሜሪካንን የአለም መሪነት የሚያቃዉስ መስሎ ከታያቸዉ ግን እዚሁ ዉብ አሜሪካ ሆኜ ያስጠጋችኝን አሜሪካ መንግስት አምርሬ ብፋለመዉ ደስ ይለኛል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን ዘላለም በወያኔ የእሳት መሰውያ ላይ መንደድ መቃጠልና ከስሎ ማለፍ ግዴታችን መሆኑን አልቀበልም በማለት እምዬ አሜሪካን እፋለማለሁ። አገሪቱም እንዲሁ ለወያኔ ቆሌና የወርቅ ጥጃ አምላክ በእሳቱ መሰውያ ላይ እየነደደች ስታልቅ እሳቱን ለማጥፋት የዌንዲን፥ የሱዛን ራይስንና የኦባማን ፈቃድ መጠየቅ እንዳለብን ለማወቅም ለመቀጠልም አልሻም። ይልቁንም እዚህ ላይ ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ከእንግዲህ ወዲያ ህዝባችን ያልተስማማዉንና የሚያፌዝበትን መንግስት ለመቅጣትና ከስራም ማባረር ያለዉን ነጻነት ማወጅ ነዉ። እንደአሜሪካ፥ እንግሊዝ፥ አለም ባንክ፥ የአዉሮፓ ህብረት፥ ወዘተ ያሉ መንግስታትና የቅኝ አገዛዝ ድርጅቶች “የግልና ተወዳጅ የዉሻ ልጆች ወይም የማንወደድ የዉሻ ልጆች” አድርገዉ እንዳያዩን ጠረጴዛዉን ልንገለብጥባቸዉ ይገባናል። ተወዳጅ “የዉሻ ልጅነትም” ሆነ “የማንወደድ የዉሻ ልጅነት” ይቅርብን። በአፍንጫችን ይዉጣ። ከሁለቱ የትኛዉን ትመርጣለህ? ብባል ሁለቱንም መጥላቴን አዉጃለሁ። ኢትዮጵያዊነትን ማንም የሚሰጥህ መብት ወይም የሚነፍግህና የሚነጥቅህ ምድራዊ ሃይል የለም። በእኔ በኩል በወያኔ የዜግነት ሰጪነትና ነሺነት ስልጣን አዋቂነት ባልታማም ይልቅስ እነሱ ኢትዮጵያዊ በመባላቸዉ ብቻ የቆሰለ አንጀት ይዤ ወደመቃብር እሄዳለሁ። እፋለማለሁ! ተፋለሙ!
ዌንዲ ሸርዉድ ግንቦት ሰባትን እንደሚቃወሙና እንደ አልቃይዳና እንደ አይሲስ አሸባሪ ከማለት ባሻገር የሄዱ አይመስለኝም። ለዚህ መግለጫ አጻፋዉን ከግንቦት ሰባት አመራር ብንጠብቅም አቅጣጫዉ ወያኔን የሚቃወምና የሚቋቋም ሁሉ አሸባሪ የሚባል እንደመሆኑ ሁላችንንም በአንድ ቅርጫት ዉስጥ የሚያስቀምጠን ይመስለኛል። ስለሆነም አንድ ግዴታ ዉስጥ ልንገባ የምንገደድ ይሆናል። እኛ አይደለንም የአሜሪካን ጥላቻ የምናተርፈው። አሜሪካ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍቅር ጨርሳ እዳታጣ እፈራለሁ። የዘመኑ ፖለቲካ ይህን እየመሰለ መምጣቱን የአሜሪካ የፖለቲካ መሪዎች ማጤን አለባቸዉ ባይ ነኝ። አሜሪካና እንግሊዝ ከ Palmerston ፍልስፍና (ቋሚ ጠላትና ቋሚ ወዳጅ የለንም፤ ቋሚ ጥቅም እንጂ) ከሚለዉ ወጥተዉ በ21ኛዉ ክፍለዘመን እንኳን በሰዉ ልጆች በአጠቃላይና በመንግስታትም እኩልነት ለማመን አልቻሉም። ፕሬዚዳንት ኦባማ በግልፅ ቋንቋ አለምን እንገዛለን፥ መግዛት አለብን ይሉናል። እዚያ ላይ ልንለያይ ነዉ። ወያኔ ሊገዛ ይችላል፤ እየታየም ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አይገዛም፥ አይነዳም። የመጨረሻዉ ትልማችን የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን ይገዛ – ራሱን ይመራ ዘንድ ነዉ። የመጨረሻው ፈታኝ ችግር ቢመጣ እንኳን፥ ኢትዮጵያ በማንም እንድትገዛ አልስማማም።
ከላይ እንደጠቀስኩት ሴቲቱ የሰጡት መግለጫ አልተቋጠረም። ወያኔን የነካ (ግንቦት ሰባትን ጨምሮ) ምን ይደርስበታል? የተንጠለጠለ አቋም እንጂ በግልጽ የተነገረ ነገር የለም። በመለስ ቋንቋ እንመለስበትና “ጣቶች፥ እጆችና፥ አጽቆች እንቆርጣለን” አላሉም። በዋሽንግተን የሚገኙ የወያኔ መንግስት ጠላቶችን እያነቅን ወደአዲስ አበባ በመላክ እናስደስታቸዋለን እንዳልተባለ እገምታለሁ። እዚህ ላይ ስንደርስ በእርግጥ የአሜሪካን ዲሞክራሲ ዉበት ማሰብ አለብን። የዚችን ታላቅ አገር መስተንግዶ አክብሬና ዲሞክራሲ በስራ ላይ የሚዉልበትን የየቀኑን ህይወቴን እያየሁ፥ አሜሪካንን እያደነቅሁና እያፈቀርኩ እኖራለሁ። ማንም እንዲነካት ነክቶአትም አደጋ እንዲያደርስባት አልሻም። አሜሪካ ለሁላችንም የስደት ቤታችን ናት። እኛም የአሜሪካ ህልም ተቋዳሾች ነን። መንፈሳዊ ቤቴ ናት። በዚህ አንጻር በዲሞክራሲ ስም መሪዎቿ በየአገሩ የሚያደርሱት ጉዳት ይቀፈኛል።
ከህዝብ ይልቅ አምባገነንነት የሚመረጥበትና “በእግዚአብሄር እንታመናለን” (In God we trust) የሚል መሪ መፈክር ያነሳ መንግስት አላማና መርሁ በአሳማ ፊት የወደቀ እንቁ ይሆንብናል። የሴቲቱ ዌንዲ ሸርዉድ ንግግግር በዕንጥልጥል ነዉ የቀረበዉ። ከዉግዘት ባሻገር ሌላ (ሌሎች) እርምጃዎች አሉ? ይኖራሉ? አነጋገራቸዉን በሚመለከት እሸት እሸት የሆነ ማስረጃ በማቅረብ ሰዉ ፊት ለመቅረብ በማይችሉበት ሁኔታ ያሳፈሯቸው ምሁራንና ድርጅቶች ነበሩ። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ያሉ የሚዲያ አውታሮች ሳይቀሩ ከዚህ ሁሉ በኋላ ለወያኔ አገዛዝ መቀጠል ሲባል በኢትዮጵያዉያን ታጋዮችና ተቋሞቻቸዉ ላይ አንድ አይነት ስውር ይሁን ገሃድ ርምጃ ቢወሰድ የአሜሪካንን አመራር ውስልትና የሚመሰክርና በሁላችንም ኢትዮጵያዉያን ላይ የተቃጣ ጥፋት አድርጌ እወስደዋለሁ። አቅሜ ደካማ ሊሆን ይችላል፤ መንፈሴ ጠንካራ ነው።
ለአሜሪካ የምንነግራት ኢትዮጵያውያን ጦርነት ላይ ናቸው። ከእንግዲህ ወዲያ ገላጋይ የሚፈልጉ አይመስለኝም። ይህም ሲባል ሰላምን አንፈልግም ማለት አይደለም። የጦርነት ፖለቲካ መለጠጥና ከሰላም ባሻገር ማደግ መሆኑንም እናውቃለን። ጦርነቶች የሚፈጸሙት እንደገና በሰላማዊ አደባባዮች በሚደረግ ምክክርና ውይይት መሆኑንም አንስተውም። ወያኔ ከዚያ በላይ ሄደ – ከሒትለርም ጉዞ አልፎ ዜጎቻችንን ጨፍጭፏል። አገር ሸጦአል። አንድነታችንን አቃውሶአል። ጦርነት አውጇል። በህዝቡ ላይ። ስለዚህ ግንቦት ሰባትና ሌሎች ሃይሎች ይህን በእግዚያብሔርና በህዝቡ ስም የሚያካሄዱትን ትግል ማንም ለመቃወም የሞራልና የትውልድ መብት የለውም። ተውን!
የኦባማ አመራር በእነ ግንቦት 7 ላይ አንድ አይነት የሚሳዝን አቋም ከያዘ (አያደርገዉም እንጂ) ወያኔን የነካ አሜሪካንን ነካ ማለት ይመስላል። ሐቁ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በግንቦት ሰባት ሆነ በሌላ ድርጅቶቹ ወያኔን ይፋለማል፤ ያንበረክካል። ለታሪክ የፍትህ አደባባይም ያቀርበዋል። ይህንን መሰረታዊ የአገሬን ህዝብ መብት ኦባማ፥ ዌንዲ፥ ካርተር….. ባርተር ሊቀሙ ሊያቆሙ አይችሉም። በየጆሮዎቻቸዉ ሹክ ብለን ሳይሆን በጩኸት ልናስቀር የሚገባን ሐቅ ይህን ይመስላል። አትርዱን፤ አትፍረዱልንም። ግን ትግላችንን አክብሩልን። አትንኩን። ዳግመኛም የአሜሪካ አባቶች ለእዉነት ስለመቆም፥ ከተገፉ ህዝቦች ጎን ስለመሰለፍ፥ በጭቆናና በግፍ ላይ በመዝመቱ ሒደት የነበራቸዉን አቋም መርምሩ። አሜሪካ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment