Translate

Wednesday, June 17, 2015

እባብ ሲደበደብ ራሱን ይከላከላል፡፡ ለምን?

አማካሪዎቹ ከቤተ መንግሥቱ ወጥተው ለአራት ወራት ያህል መከሩ፡፡ አነሡ ጣሉ፤ በመጨረሻም የደረሱበትን ሐሳብ በብራና ጽፈው ወደ ንጉሡ ዘንድ መጡ፡፡ የተጠቀለለውንም ብራና ሰጡት፡፡ ንጉሡም ገለጠና አነበበው፡፡ እንዲህ ይል ነበር ‹‹ይህም ያልፋል››፡፡
ለምን? አላቸው ንጉሡ፡፡
በየትኛውም የሥልጣንና የሀብት ከፍታ ላይ ብትሆን፣ በየትኛውም የዝናና የክብር ሠገነት ላይ ብትደላደል፣ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ግፍ አትሠራም፣ ፍትሕ አታዛባም፣ ድኻ አትበድልም፣ ከልክህም አታልፍም፡፡ ራስህን ዘላለማዊ አድርገህ ካሰብክ፣ ጊዜ የማይቀየር ዓለምም የማትዞር ከመሰለህ ግን ራስህን ለማስተካከል እንኳን ጊዜ ሳታገኝ ነገሮች ይቀየሩና በሠራኸው ወኅኒ ትወረወራለህ፣ ባወጣኸው ሕግ ትቀጣለህ፣ በቆረጥከው ዱላ ትመታለህ፣ ባሳደግከው ውሻ ትነከሳለህ፡፡ ስለዚህ አሁን የተቀመጥክበትን ዙፋን፣ የምታንቀጠቅጥበትንም ሥልጣን፣ ‹ይህም እንኳን ያልፋል› ብለህ አስበው፡፡

ተቀናቃኞችህን ድል እንዳደረግክ፣ አገሩን ጠቅልለህ እንደያዝክ፣ ሁሉ በእጅህ ሁሉ በደጅህ እንደሆነ፣ በለስ እንደቀናህ፣አንደኛ እንደወጣህ፣ እንደ ተጨበጨበልህ፣ እንደታፈርክና እንደተከበርክ፣ አትቀርም፡፡ ይህም በጊዜው ያልፋል፡፡ እነዚህ ዛሬ በዙሪያህ ሆነው የሚያፍሱልህ የሚያጎነብሱልህ፣ ሳታስነጥስ ይማርህ፣ ሳትወድቅ እኔን የሚሉህ፤ ሳይበርድህ ካልደረብንልህ ሳታዝን ካላለቀስንልህ የሚሉህ፤ ሳትጠራቸው አቤት፣ ሳትልካቸው ወዴት የሚሉህ፣ ይኼ ሁሉ ሲያልፍ ያልፋሉ፡፡
ካንተም በፊት ሌሎች ነበሩ፣ ካንተም በኋላ ሌሎች ይመጣሉ፡፡ ከፊትህ ሌላ ባይኖር ኖሮ ከኋላህ ሌላ ባልመጣም ነበር፡፡ በጊዜ ውስጥ ትናንት ዛሬና ነገ አሉ፡፡ ዛሬ ትናንት፣ ነገ ዛሬ እየሆኑ ያልፋሉ፡፡ አንተ ሌሎችን እንደተካህ ሁሉ የሚተካህም የግድ ይመጣል፡፡ አንተ ሌሎችን እንደረታህ ሁሉ የሚረታህም ነገ ይመጣል፡፡ አንተ ሌሎችን እንዳሠርክ ሁሉ የሚያሥርህም ነገ ይመጣል፡፡ አንተ እንደቀበርክ ሁሉ ቀባሪህም ነገ ይመጣል፡፡ እስኪ ለቀስተኞችን እይ፤ የዛሬ ቀባሪ ሁሉ ነገ በተራው ተቀባሪ ነው፡፡ ማንም ራን የሚቀብር የለም፡፡ ሌላውን እንደቀበረ ሁሉ እርሱን ሌላ ይቀብረዋል እንጂ፡፡ ‹ይህም ሁሉ ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ሁሉን በልኩ፣ ሁሉን በደንቡ ታደርገዋለህ፡፡
የሌሎችን ታሪክ አጥፍተህ፣ የሌሎችን ሐውልት ሰብረህ፣ የሌሎችን ዋጋ አርክሰህ፣ የሌሎችን ስም ገድለህ መኖር ትችላለህ፤ ዐቅሙና ሥልጣኑ እስካለህ ድረስ፡፡ ነገር ግን ይህም ያልፋል፡፡ ያንተንም ታሪክ የሚያጠፋ፣ ያንተንም ሐውልት የሚሰብር፣ ያንተንም ስም የሚያጎድፍ፣ ያንተንም ዋጋ የሚያረክስ በተራው ይመጣል፡፡ የሚተካህን የምትፈጥረው ዛሬ በምታደርገው ተግባር ነው፡፡ ክፉ ከሆንክ ክፉ ይተካሃል፣ ርቱዕ ከሆንክ ርቱዕ ይተካሃል፡፡
ይኼ ሁሉ ዓለም አልፎ ብትወድቅ፣ ብትሰበር፣ ብትታሠር፣ ብትረሳ፣ ብትሰደድ፣ ብታጣ፣ ብትነጣ፣ ከላይ ወደታች እንዳየኸው ሁሉ ከታች ወደ ላይ የምታይበት ዘመን ቢመጣ፣ ያሰብከው ቀርቶ ያላሰብከው ቢሆን፣ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ አስብ፡፡ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ተሥፋ አትቆርጥም፣ ነፍስህ ሳትወጣ አትሞትም፣ ራስህን ለብስጭትና ንዴት፣ ለቁጣና ትካዜ አሳልፈህ አትሰጥም፡፡ ከሞት በኋላ ትንሣኤ፣ ከእሥር በኋላ መፈታት መኖሩን ታያለህ፡፡ የድል ጫፉ ሽንፈት እንደሆነው ሁሉ የሽንፈት ጫፉ ድል ነው፡፡ የሥልጣን ጫፉ መውረድ እንደሆነው ሁሉ የውርደት ጫፉ ሥልጣን ነው፡፡ የብርሃን ጫፉ ጨለማ፣ የጨለማም ድንበሩ ብርሃን ነው፡፡ የበሽታ ጫፉ ጤና፣ የጤናም ጫፍ በሽታ ነው፡፡
ዓለም ቋሚ አይደለቺም፡፡ ጊዜ ወደ ፊት ብቻ ነው የሚሄደው፡፡ እሥር ቤቱ ሲተከል የነበሩት አሁን የሉም፤ ስለዚህም አንተም እዚያ እሥር ቤት አትኖርም፡፡ ችግር ሲጀመር የነበሩት አሁን የሉም፤ አንተም ችግር ውስጥ የግድ አትሰምጥም፡፡ እንደሚያልፍ ካመንክ፡፡ እንደሚያልፍ ካመንክ ለማሳለፍ ትጥራለህ፡፡ እንደሚያልፍ ካላመንክ ግን ያለህበትን ትቀበለዋለህ፡፡ የተቀበልከውን ነገር ደግሞ አትለውጠውም፡፡ ችግርን ያልፋል ብለህ ከተቀበልክ ወደ ውጭ ታያለህ፣ ወደ ውጭ ታስባለህ፣ ወደ ውጭም ትመኛለህ፡፡ ከአጥሩና ከድንበሩ አልፈህ ታልማለህ፡፡ ሰው የሚኖረው ከሥጋው በላይ በኅሊናው ነው፡፡ ውድቀት በሥጋ መኖር ሲጀመር ይመጣል፡፡ ክብርና ድል ደግሞ በኅሊና መኖር ሲጀመር ይመጣሉ፡፡
እባብ ሲደበደብ ራሱን ይከላከላል፡፡ ለምን? ራሱ ካለ የተቆረጠ አካል ቢኖረው እንኳን ይቀጠላል፣ የተጎዳ አካል ቢኖረው እንኳን  ይፈወሳል፡፡ ራሱን ከተመታ ግን አለቀለት፡፡ ሰውም ኅሊናውን ከተመታ ሞተ ማለት ያን ቀን ነው፡፡ ኅሊናህ እንዳይመታ ከፈለግክ ‹‹ይህም ያልፋል› ብለህ አስብ፡፡ የቆምክበት ቦታና ጊዜ አስመራሪ፣ አታካች፣ አንገሽጋሽ፣ ከባድና ጽኑ ቢሆን እንኳን ግን ያልፋል፡፡ አንተ ያንን መከራ እየቀመስክ ባለህበት ጊዜ እንኳን እያለፈ ነው፡፡
ለዚህ ነው ይህንን የሰጠንህ፡፡ በጥጋብም ሆነ በረሃብ፣ በሀብትም ሆነ በድህነት፣ በሥልጣንም ሆነ በውርደት፣ በድልም ሆነ በሽንፈት፣ በጤናም ሆነ በሕመም፣ በዝናም ሆነ በክስረት፣ የሚመጣ መከራ አለ፡፡ ከዚያ መከራ መውጣት ከፈለግክ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ አስብ፡፡ ይኼ መንገዱን መመልከቻ መነጽርህ ነው፡፡ ከሠገነቱ እንዳትወድቅ መውረጃህ፣ ከጉድጓዱም እንድዘቅጥ መውጫህ መሰላል ነው፡፡
ንጉሡ ምክራቸውን ሰምቶ በቤተ መንግሥቱ፣ በፍርድ ቤቱ፣ በግብዣ ቤቶቹ፣ በባለሥልጣናቱ እልፍኞች፣ በጦር አዛዦች ሠረገሎች፣ በባዕለ ጸጎች አዳራሾች፣ በወኅኒ ቤት ግድግዳዎች፣ ‹‹ይህም ያልፋል› የሚለው ምክር እንዲለጠፍ አዘዘ፡፡ እርሱም ሲነጋ ሲጠባ፣ ሲወጣና ሲገባ፣ ሲፈርድና ሲወስን ሁሌ ያየው ጀመር፡፡ ‹ይህም ያልፋል› እያለ፡፡

No comments:

Post a Comment