Translate

Tuesday, May 5, 2015

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እየታደኑ እየታሰሩ ነው

ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን እንዳይታዘብ እንደሚፈልግ ገለጸ
•የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ፓርቲዎችን አነጋግሯል
• በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ አባላት ላይ የሚፈፀመው ድብደባ ቀጥሏል
• ‹‹የተጀመረውን የሀሰት ክስ እውነት ለማስመሰል የታቀደ ነው››
ethiopia-blue-party-300x164የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ሰበብ እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ሀሙስ ሚያዝያ 22/2007 ዓ.ም ብሌን መስፍንና ተዋቸው ዳምጤ ከመስሪያ ቤት ተይዘው የታሰሩ ሲሆን ሚያዝያ 24/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተደረገውን አመጽ መርታችኋል፡፡›› በሚል ፖሊስ ክስ እንዳቀረበባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ዛሬ ሚያዝያ 26/2007 ዓ.ም ማቲያስ መኩሪያ ቤቱ ውስጥ እያለ በፖሊስ ተይዞ ታስሯል፡፡ ማቲያስ፣ ብሌንና ተዋቸው ወረዳ 10 (ላዛሪስት ፖሊስ ጣቢያ) ታስረው ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የሚደረገው እስርም ‹‹መንግስት በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የጀመረውን የሀሰት ክስ እውነት ለማስመሰል የታቀደ ነው፡፡ ፖሊስ ምርመራ ሳይጨርስ በሀሰት 20 አባላትንና 6 አመራሮችን አስረናል ብለው ነበር፡፡ እነሱ የፈለጉት ይህን ሚዲያ ላይ ወጥተው በሀሰት የፈፀሙትን ውንጀላ ማሰመሰል ነው፡፡›› ሲል አቶ ዮናታን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

በሌላ ዜና በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ደህንነትና ፖሊስ የሚፈፅመው ድብደባ አሁንም መቀጠሉ ተገልጾአል፡፡ በዛሬው ቀን የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው የሀሳብ ጌታቸው ‹‹ለሰማያዊ ፓርቲ ወረቀት በትነሻል›› በሚል ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀሙባት ተገልጾአል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ህብረት 5ኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንዳይታዘብ እንደሚፈልግ ለህብረቱ ታዛቢ ቡድን ገለጸ፡፡ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ ሚያዝያ 26/2007 ዓ.ም በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን በተናጠል በምርጫው ዙሪያ ያነጋገረ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ቡድኑን ያነጋገሩት አቶ ወረታው ዋሴ እና አቶ እምዕላሉ ፍስሃ ህብረቱ ምርጫውን እንዳይታዘብ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡
የህብረቱ ታዛቢ ቡድን ከአሁን ቀደም በተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች መታዘቡን ያወሱት የሰማያዊ ተወካዮች፣ ህብረቱ በሪፖርቱ ለአምባገነኖች እውቅና ከመስጠት ያለፈ አንዳች እውነታውን የሚያሳይ ትዝብቱን አላስቀመጠም ሲሉ ለታዛቢ ቡድኑ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ህብረቱ የአምባገነኖች ስብስብ ነው›› ያሉት የፓርቲው ተወካዮች፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ተስፋ በማጣት በታዛቢነት እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ህብረት ግን ለአምባገነኖች እውቅና ለመስጠት መምጣቱ በሰማያዊ ፓርቲ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቀደምት ፓን አፍሪካኒስቶች አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት ታግለዋል፤ የአሁኖቹ እውነተኛ ፓን አፍሪካኒስቶች ደግሞ አፍሪካን ከአምባገነኖች ነጻ በማውጣት ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል›› በማለት ለህብረቱ ታዛቢዎች የገለጹት የፓርቲው ተወካዮች፣ በዚህ ረገድ ህብረቱ ተገቢውን ስራ እያከናወነ ነው ለማለት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ጋባዥነት 5ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ በቅርቡ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ህብረቱ በዛሬው ዕለት ያነጋገራቸው ፓርቲዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በውል አልታወቀም፡፡

No comments:

Post a Comment