Translate

Sunday, May 10, 2015

በመጨረሻም በግብጽ ነጻ ወጡ… እኛ ግን መንግስት አለን እንዴ?

ክንፉ አሰፋ
Egyptian President Abdel Fattah al-Sisi receives an Ethiopian man
የፌስቡክ አርበኛው ቴድሮስ አድሃኖም ቦሌ ሄደው ከሊብያ ነጻ የወጡ ዜጎችን ሲቀበሉ አየን። እፊታቸው ላይ የማፈር ሳይሆን የጀግንነት ስሜት ይነበባል።
አቀባበላቸውም 90 ደቂቃ በእንቴቤ የሚለውን ታሪክ ይመስላል። ኡጋንዳ ላይ የታገቱ ዜጎችዋን ለማስለቀቅ እስራኤል ያደረገችው ገድል። ቴድሮስ አድሃኖምም በኩራት እና በድል አድራጊነት ስሜት ነው ስደተኞቹን የተቀበሉት። መቼም ሼም የሚባል ነገር ከነሱ ዘንድ ጠፍቷል። በስራቸው ማፈር ሲገባቸው አይናቸውን በጨው እያጠቡ የሌላውን ድል እንደራስ ያጣጥሙታል። ህሊና ያለው ሰው ያሳደዳቸውን እና በባእድ ነጻ የወጡ ዜጎቹን ሲመለከት ብርክ ነው የሚይዘው። አልገባቸው ይሆናል እንጂ ክብራቸውን የሚቀንስ ማንነታቸውን የሚፈትን ድርጊት ነው። አስቀድመን በግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዜናውን ባንሰማ ኖሮ ደግሞ ሌላ ታሪክ ይነግሩን እንደነበር ጥርጥር የለውም።

Egyptian President Abdel Fattah al-Sisi receives (R) an Ethiopian man who “rescued” alongside 26 other Ethiopians from war-torn Libya by Egypts security services
ሁኔታቸው አባት እና እናቱን በግፍ ገድሎ ፍርድ ቤት የቀረበውን አይነደረቅ ያስታውሰናል። ወንጀል መፈጸሙን ያመነው ይህ ጎረምሳ የፍርድ ማቅለያ እንዲናገር በመሃል ዳናው በተጠየቀ ግዜ እንዲህ አለ። “ያው አባት እና እናት ስለሌለኝ፤ ለወላጅ አልባ ልጆች እንደሚደረገው ልዩ እንክብካቤ ያስፈልገኛል።”
በአለም-ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደሰማነው እነዚህን ዜጎች ነጻ ያወጣችው ግብጽ ናት። ከአይሲስ ጥርስ ወጥተው ግብጽ ምድርን ሲረግጡ አቀባበል የተደረገላቸው በምንስቴር ደረጃ ሳይሆን በረዕሰብሄር ደረጃ ነው። ከአውሮፕላን ሲውርዱም የግብጽን ባንድራ እያውለበለቡ ነበር። አዲስ አበባ ላይ ግን ባንዲራ አልያዙም። ይህም ትልቅ ትርጉም አለው። ባንዲራ የአገር ክብርና ፍቅር ነው። የህዝብ አንድነት እና ትሰስር በባንዲራ ይገለጻል። አንገት ላለው፤ አንገቱን የሚያስደፋ እውነታ!
በግብጽ መከላከያ ሃይል ነጻ የወጡት እነዚህ 27 ኢትዮጵያውያን ካይሮ ሲደርሱ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ፕሬዝዳንታዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅድምያ ለሰብአዊ ፍጡር ክብርን ከመስጠት የሚመነጭ ተግባር ነው። ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ ቢያገኙበትም ይገባቸዋል። ክቡር የሆነን ሰው ነብስ አትርፈዋልና ይህ ለኛ ትልቅ ትርጉም ነው የሚሰጠን። መልካም ስራ ለክፉ ቀን ስንቅ ነው።
አዲስ አበባ ሲገቡ ግን ሃይለማርያም ደሳለኝ ሊቀበሏቸው አልቻሉም። ምክንያቱም ግልጽ ነው። ለሳቸው ያለገደብ የተሰጠው ስልጣን ተቃዋሚዎችን እና ዲይስፖራውን መሳደብ ብቻ ነው። ምናልባትም ለኚህ አሻንጉሊት ዋነኛው ችግር አይሲስ ሳይሆን አሜሪካ ላይ የተነሳው አልሻባብ ነው። አሜሪካ ባሸተተች የኛዎቹ ያስነጥሳቸዋል። ለዚህ የአሜሪካ ቆሻሻ ጦርነት የኢትዮጵያን ወታደር ለመላክ አላንገራገሩም። የኛ ወገን እንደ ከብት ሲታረድ ግን የመረጡት ብሄራዊ የሃዘን ቀን ማወጅ፣ ከንፈር መምጠጥ፤ ሻማና ጧፍ ማቃጠል …። ምክንያቱ እነሱ እንደሚሉት የድንበር መዋሰን ጉዳይ አይደለም። ይህ ቢሆን አሜሪካ ሽብርተናን ለመውጋት አፍጋኒስታን ወይንም ሶርያ አያዋስናትም። መውረር ባስፈለጋት ግዜ ፓናማንም ግሪናዳንም ወርራለች። ሶማልያ ላይ ከሰፈረው ሰራዊት ስንቱ እንደሞተ በፓርላማ ሲጠየቁ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስተር ሲመልሱ፤ “ይህ ጉዳይ እናንተን አይመለከትም!” ነበር ያሉት። የፓርላማ አባላት ይህንን ወሳኝ ጉዳይ የማወቅ መብት ከሌላቸው ታዲያ ለማን ነበር ሪፖርቱ የሚቀርበው? ለአሜሪካ?
አለም ስለ አይሲስ ጭፍጨፋ ሲጨነቅ፣ እነሱ ግን ምርጫው ነው እንቅልፍ የነሳቸው። እናም በዜጋው ሰቆቃ ሳይሆን በሰላማያዊ ፓርቲ ላይ ተጠምደዋል። አይሲስን ከመዋጋት ሰማያዊ ፓርቲን ማጥፋት ይመርጣሉ። የመከላከያ ሰራዊቱ አንበሳነት በሃገር ውስጥ ብቻ መሆኑን አስመስክሯል። በዜጋው ላይ ኮማንዶ ሲለማመድ አሳዩን።
ለእነሱ ሽብርተንኛ አይሲስ ሳይሆን ጋዜጠኛ ነው። የጸረ-ሽብር አዋጅ አውጥተው ጋዜጠኛ እና ተቃዋሚዎችችን ያፍኑበታል። ሽብርተኛው ዜጋዋ ሳይሆን አይሲስ እንደሆነ ግብጽ ትምህርት የሰጠቻቸው ይመስላል። ከራስዋም አልፋ እኛኑ ስትታደግ አየን።
በዚህ ሰሞን የቴድሮስ አድሃኖም ፌስ ቡክ ገጽ ተጨናንቆ ነው የሰነበተው። የስደት ቀውሱ ያመጣውን ችግር ይዞ ትንሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት መሆኑ ነው። የኝህ ሰው ስራ ጨርሶውኑ በፌስ ቡክ ላይ ሆኗል ያስብላል። ጨጓራው የተቃጠለ ዜጋም ይህንኑ ገጽ የንዴቱ ማብረጃ አድርጎታል።
በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አይቴ ቴድሮስ እንዲህ ብለው ጽፈዋል። “የመጀመሪያ ዙር ከሊብያ ተመላሽ ወገኖች አዲስ አበባ ገብተዋል። መንግስት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።”
ታዲያ ሚኒስትሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ እነዚህ ወገኖች ሲገቡም ሆነ አቀባበል ሲደረግላቸውም አልታየም። እውነት ነው በኢትዮጵያዊነታቸው ሳይሆን በዘር እየተለኩ፣ ለገዢው ፓርቲ ቅርብ የሆኑ፣ ወዘተ በሱዳን በኩል እንዲገቡ መደረጉ ተሰምቷል።
ተስፋዬ ሁሴን የተባለ ወገን በዚያው ጽሁፍ ስር እንዲህ ሲል መለሰላቸው፣ “መቸስ ውሸትህ አያልቅ፣ በቀደም እለት የደቡብ አፍርካ ተመላሾች ብለህ ቀደድክ። ነገር ግን እዚህ ከደቡብ አፍርካ የገባ አንድም ስደተኛ ባልነበረበት፣ ተመላሾች ብለህ ስትዋሸን ዝም አልን። አሁን ደግሞ ከሊቢያ … መጥኔ ውሸትህን ለሚጋቱ አድርባዮች! ጊዜ እየጠበቅህ ብቻ የእንትን ተመላሾች በል። ነገ ደግሞ የሰማይ ቤት ተመላሾች እንደምትለን ተስፋ አደርጋለው። በውሸት፣ በፌዝ 24 ዓመት…”
ቴድሮስ አድሃኖም መጻፋቸውን ቀጠሉ፣ ስለ ሁለተኛው ዙር ተመላሾች። ዙቤር ኡስማን የተባለ መላሽ ደግሞ “አገር የሌለው ሰው የሄደበት ሁሉ አገሩ ነው! ኢትዮዽያውያን ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ግብፅ፤ የግብፅን ሰንደቅ ኣላማ እያውለበለቡ ሲወርዱ! ከሃበሻ ምድር ተሸርፋ “አገር” የሆነችው ግብፅ ዛሬ የእንጀራ እናታችን ሆነች!” ሲል ነበር ቁጭቱን የገለጸው።
እርግጥ ነው። ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ለዜጋው ግድ አይሰጠውም። አንድ ኢትዮጵያዊ ይልቅ አንድ የህንድ ወይንም የሳዑዲ ዜጋ በሃገራችን ትልቅ ክብር አለው። ከዜጋው ይልቅ ለባእዳን “ባለሃብቶች” ደህንነት የሚጨነቅ ስርዓት ነው። ሲጀመር ዜጋው ከሀገሩ እንዲሰደድ ያደረገው ብልሹ የሆነ ስርአቱ ነው። አርሶ አደሩችን ከቀያቸው እያፈናቀለ፣ ለም መሬታቸውን ለህንድ እና ሳዑዲ ባለሃብቶች በመናኛ ዋጋ በመቸበችብ የወጣቱን ተስፋ ገደለው። ወጣቱ አገር የለውም። ለመኖር ሲል፣ ፍትህ ፍለጋ፣ ስራ ፍለጋ፣ እንጀራ ፍለጋ ይሰደዳል።
የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮው አዲሱ አበበ ከሊቢያ ሁለት ስደተኞችን በስልክ አነጋግሮ ነበር። ሁለቱንም ወደሃገር ቤት መመለስ እንደሚፈልጉ ጠይቋቸው የሰጡት ምላሽ “መመለስ አንፈልግም!” የሚል ነው። እነዚህ ወገኖች በሞት ጥላ ውስጥ ሆነው እንዲህ ማለታቸው በሀገር ቤት ያለው ችግር ምን ያህል የከፋ መሆኑን ይጠቁመናል።
ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አዲስ አይደለም። የአይሲሱ ግድያ አለም አቀፍ ትኩረትን ሳበ እንጂ በሳዑዲ አረቢያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በእስራኤል ወዘተ ፍጹም ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት በዜጎቻችን ላይ ተፈፅሟል። ሴቶች እህቶቻችን በጎረምሶች ተደፍረዋል። በአሰቃቂ ሁኔታም ገድለዋል። ለዜጎቹ የሚከራከር አካል ባለመኖሩም የተናቅን ህዝብ አደርጎናል።
እስራኤል ሃገር በፈላሽ ሙራዎች ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር መድልኦ አለም ሲያወግዘው የኛዎቹ ዝም ነው ያሉት። ባለፈው አመት ናይሮቢ ውስጥ ሰባ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተለቀሙ ሲታፈሱ እና ሲታሰሩ እዛ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ኬንያ ውስጥ ጉዳት የደረሰበት ሕጋዊ ዜጋ የለም” ሲል ነበር መልስ የሰጠው። ሊብያ በፈራረሰች ግዜ አፍሪካ ዜጎች በየኤምባሲያቸው ገብተው ሲጠለሉ ኢትዮጵያውያን መሄጃ አልነበራቸውም። በመጨረሻ ግን የናይጄሪያ ኤምባሲ ተቀብላ አስተናገደቻቸው።
አይሲስ ወደ የመን እየገባ መሆኑ በተሰማ ግዜ ሰይፉ ፋንታሁን አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር። በዘገባው ላይ የመን ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስት ከወሬ ያለፈ ምንም ነገር እንዳላደረገ ይናገራሉ። ይልቁንም ዓለምአቀፍ ሞዴልና ተዋናይ የሆነችው የሐረር ወርቅ ጋሻው ስደተኛውን ለመርዳት የአቅሟን እያደረገች እንደሆነ ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ሐይማኖት ተናግሯል።
በየመን እየታየ ያለውም ጉዳይ እርግጥ “ኢትዮጵያ መንግስት አላት ወይ?”..የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው። ጋዜጠኛው የመን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ “እንረዳቸዋለን ወይስ እናርዳቸዋለን?” ነው ያለው ሲል ባሰፈረው ጽሁፉ በዶቺቬሌ ቃላቸውን የሰጡት የኤምባሲው ቃል አቀባይ አቶ አምደሚካኤል ንግግር ኣሳፈሩን ይላል። “ኢትዮጵያዊያኑን እንረዳቸዋለን። ከአይ. ኦ. .ኤም. ጋር በመተባበር ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉትን እንመልሳለን” ብለዋል። … ” አዎ ይረዳሉ ግን ኤምባሲ ውስጥ ላሉ ሰራተኞች ነው። ..እኛን ግን እንረዳለን ማለት ፈልገው ሳይሆን እናርዳቸዋለን ማለታቸው ነው። ሲያርዱ እንጂ ሲረዱ መቼ ታይተው ነው።” ብሎ ነበር የጻፈው።
እውነታው ይህን ይመስላል። አንዳንድ የስርአቱ አጨብጫቢዎች ታዲያ ይህ እውነታ አይወጥላቸውም። ዜጋ እየተሰቃየ እነሱ ግን ስለ ህንጻ ይነግሩናል፤ ስለ ታምራዊው 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይሰብኩናል። … ሕንጻና መንገድንማ ቅኝ ገዥዎችም ሰርተዋል። ለዚያውም እነሱ ከሚነግሩን የበለጠ።
ሕዝብ ደግሞ እያለ ያለው ፣ “ከህንጻ በፊት ነጻ!” እንሁን ነው! ሀገር ማለት መሬት አይደለም። ሃገር ማለት ወንዙ፣ ተራራው፣ ሽንተረሩ፣ አደለም። ሃገር ማለት ሕዝቡ ነው። የህዝቡ ሰቆቃ ግድ የማይለው አካል መንግስት ሊሆን አይችልም።

No comments:

Post a Comment