Translate

Sunday, May 24, 2015

ሥልጣን ወደ ህወሃት?!

“በሃይለማርያም አፈርኩባቸው” - በየነ ጴጥሮስ

tplf haile debretsion
* “ግምገማ!” የኢህአዴግ ስድብ ሃይማኖት
“ምግባረ ብልሹዎች ናችው፤ የሚታፈርባቸው ናቸው። እነሱን ብሆን ራሴን እንዳዋረድኩ ነው የምቆጥረው” ሲሉ የመድረክ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ ሃይለማርያምንና “ሌሎችም ቢሆኑ” ሲሉ የገለጹዋቸውን ባለሥልጣናት ምግባር ተቹ። ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቢኖር ኢህአዴግ እንደሚሸነፍ ከ፱፭ በመቶ እርግጠኛ መሆናቸውንም አመለከቱ።

ተቃዋሚዎችን ሕዝብን ወዳልተፈለግ አቅጣጫ እየመሩ ነው በማለት በመወንጀል የማስጠንቀቂያ መልእክት ያስተላለፉትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ተከትሎ ቪኦኤ ያነጋገራቸው  ዶ/ር በየነ “የሞራል ብቃት የላቸውም” ሲሉ ሃይለማርያምን ክፉኛ ተችተዋቸዋል። “ለፓርላማ” ማብራሪያ ሲሰጡ “አንተ በምትሰጠው ውሳኔ እንገዛለን” በማለት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ሃይለማርያም የሰላ ወቀሳ ደርሶባቸዋል
ባለሙሉ ሥልጣን መሪ ባይሆኑም ኢህአዴግን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ሃይለማርያም፣ አገዛዙ ምርጫውን ተከትሎ እየፈጸመ ያለውን ተግባር እያወቁ ያቀረቡትን መሃላ “ሸፍጥ፣ ምግባረ ብልሹነት የሞላበት፣ ቅንነት የጎደለው” ሲሉ ያጣጣሉት የመድረኩ ሊ/መንበር በየነ፣ ሕዝብ ስለ ኮሮጆ ስርቆት፣ ስለ ፩-፭ ቅስቀሳ፣ ስለ ሸፍጥና ስለ ምሬት በግልጽ በሚናገርበት በአሁኑ ወቅት ሃይለማርያም ይህንን ጥሪ ማቅረባቸው አሳፋሪ እንደሆነ አመልክተዋል። በድርጊቱም እንደሚያፍሩ አስታውቀዋል።
የሰሞኑን የምርጫ ሁኔታና በረከሱ ቃላቶች የታጀበውን ድርጅታዊ ግምገማ የተከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች  አቶ ሃይለማርያም ሳይወረወሩ ራሳቸውን በ“በቃኝ” ቢያሰናብቱ ቢያንስ “ለንስሃ ይቀላቸዋል” ሲሉ ተደምጠዋል። ሥልጣኑ ተመልሶ ወደ ህወሃት ይገባል በሚባልበት ወቅት ጓድ ሃይለማርያም ለምርጫው ደፋ ቀና ቢሉም በግምገማ የደረሰባቸው መዓትና ይህንኑ ተከትሎ ሰሞኑን ቁም ስቅላቸውን እያዩ ነው።
ራሱን በንብ የመሰለው ኢህአዴግ ማር እያላሰ የሚናደፍበት አንድ “ሃይማኖት” አለው – “ግምገማ”! በዚህ ሃይማኖታዊ ሥነስርዓት ወቅት ካድሬዎቹ ተሰብስበው ሌላውን ካድሬ ይወቅጣሉ፤ ይሸከሽካሉ፤ ይፈጫሉ፤ ያቦካሉ፤ ይጋግራሉ፤ ወዘተ። የዚህ “ሃይማኖት” ፈጣሪዎች አገርን “በነጻ አውጪ” ስም የሚመራው የህወሃት ሰዎች ናቸው። እንደ ክዳን ቆርኪ ተስፈንጥረው ሞት ቀደማቸው እንጂ አቶ መለስ የዚህ “ሃይማኖት” አናዛዥ “መንፈሳዊ አባት” ነበሩ። ሲፈልጋቸው በፓርላማ “ስኳር እወዳለሁ፤ የስኳር ሌባ” ነኝ ያስብላሉ። ሲያሻቸው ደግሞ በፓርቲያቸው “የማናዘዣ ክፍል” ካድሬዎቻቸውን አስጠንተው አስገብተው የፈለጉትን ያስወቅጣሉ።
meles and hailemariamአገር እናስተዳድራለን የሚሉት የኢህአዴግ ሰዎች ባለፈው ሰሞን ተሰብስበው ጓድ ሃይለማርያምን መውቀጣቸውን ኢሣት ምንጮቹ ጠቅሶ ተናግሯል። ሙሉ ቀን ፈጀ በተባለው ግም-ገማ ሃይለማርያም በህወሃት በተቀነባበረ የኑዛዜ “ሃይማኖታዊ ሥነስርዓት” ላይ እስኪያለቅሱ ድረስ ተወቅጠዋል፤ ተሸክሽከዋል፤ ተፈጭተዋል፤ … “አትረባም” ተብለው እንደ ሸንኮራ ተመጥጠው ተተፍተዋል፤ እንደ ሲጃራ ፊልተር ከከንፈር ወርደው ተረግጠዋል።
በሚኒስትር ስም የተቀመጡት የኢህአዴግ ጓዶች አንድ አገር ከሚመራ ሹም ፈጽሞ የማይጠበቁ፤ እጅግ የወረዱ፤ ጸያፍና አስደንጋጭ ቃላትን እየተናገሩ ሃይለማርያምን ሲወርፉ መዋላቸው ተሰምቷል። በአገር በጀትና ጊዜ ተጠቅመው የራሳቸውን ተራና እጅግ የዘቀጠ አሉባልታቸውን አሰምተዋል። “ባለራዕዩ” መሪያቸው ያወረሷቸውን በተግባር በመፈጸም “የስድብ ሌጋሲያቸውን” እንደሚቀጥሉ በገሃድ አረጋግጠዋል።
“ውጭ አገር እንዳልሄድ ተከለከልኩ”፤ “አዲስ ቃል አልፈጠርክም”፤ “ትንቀኛለህ”፤ “ትሳደባለህ”፤ “ለጴንጤ ታደላለህ”፤ “ውጭ አገር ስልጠና አልላከኝም”፤ “ለወላይታዎች ታደላለህ”፤ “ተንኮለኛ ነህ”፤ “ዕውቀት የለህም”፤ ወዘተ እየተባሉ የኮሌጅ ደጃፍ ሳይረግጡ “ዲግሪያቸውን”ከየወፍጮ ቤቱ በሸመቱ ካድሬዎች በፈረቃ ተሰድበዋል፤ ተሞልጨዋል።
ይህንን እጅግ የወረደ ተራ አሉባልታና ሃሜታ ኢህአዴግ “ዴሞክራሲያዊ ውይይት፤ ግምገማ” እያለ ቢጠራውም ለእያንዳንዳችን እንደ ኢትዮጵያዊ እጅግ የሚያሳፍርና አንገት የሚያስደፋ ነው። በሚኒስትር ማዕረግ የተቀመጡ ሰዎች አንዳች ማስረጃ ማቅረብ በማይችሉበት ሁኔታ እንደ ክፍል ተማሪ “እኔ፤ እኔ” እያሉ እጃቸውን እያወጡ ሲሳደቡ መዋል ቢያንስ ዕድሜያቸው ሊፈቅድ የማይገባ ተግባር ነበር። የመለስን ሬሣ እና አጽም እስካሁን በመፍራት የሚሽቆጠቆጡት ካድሬዎች፤ ሃይለማርያምን ጨምሮ በየንግግራቸው ሁሉ “እርሳቸው እንዳሉት፤ እርሳቸው እንደተናገሩት” በማለት የዓርፍተነገር መጀመሪያና መጨረሻ የሚያደርጓቸውን መለስ ከ20 ዓመታት በላይ የህወሃት ሊቀመንበር፤ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፤ ፕሬዚዳንት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ … በመሆን በአምባገነንነት ሥልጣኑን እየቀያየሩ “ሲዋቡበት”፤ “ሲኳሉበት”፤ “ሲሳደቡበት”፤ “ሲያፏጩበት”፤ አብሮ ከማፏጨትና ከማጨብጨብ በስተቀር የሚናገራቸው አልነበረም።hailemariam speaking
ለመሆኑ “ለትግሬ ታዳላለህ”፤ “ብቃት ያንስሃል”፤ “ውጭ አገር ስትሄድ እኔን ወደ ክልል ላከኝ”፤ “ተንኮለኛ ነህ”፤ “መሰሪ ነህ”፤ ወዘተ ብሎ መለስን ተናግሮ ወይም “ገምግሞ” ከዚያች ክፍል በህይወት የሚወጣ ማነው!? ለነገሩ “የግምገማው ካህን” ጓድ መለስ ለማን እና በማን ይወቀሳሉ? በማንስ ይገመገማሉ? እርሳቸውም በደህና ጊዜ “ከውጭና አገር ውስጥ ወፍጮ ቤቶች” ያመረቷቸውን አጠገባቸው በማድረጋቸው ሞተውም ሬሣቸውና አጽማቸው ይመለካል፤ ይሰገድለታል።
ከመለስ ሞት በኋላ አገሪቱ በደቦ ወይም በቡድን እንደምትመራ ሲናዘዙ የቆዩት ሃይለማርያም ግምገማውም በዚሁ መልኩ ቡድኑን በሚገመግም ሁኔታ ይደረግ አለማለታቸው ሲቆጫቸው የሚኖር ይመስላል። መለስ ስብስብ፤ ጥቅልል አድርገው ይዘውት የነበረውን ሥልጣን ሲሞቱ ህወሃት እየሸራረፈ ለነደብረጽዮን “ክላስተር” እያለ ሲሸነሽን እንዳልቆየ አሁን ሥልጣኑ በአንድ ሰው የተያዘ ይመስል በግም-ገማ ስም ይህንን ሁሉ ማለት ምክንያቱ ሌላ እንደሆነ ግልጽ ነው።
በአገር ውስጥና ውጭ አገር ታዋቂነት ባላቸው የትምህርት ተቋማት ተምረው የተመረቁት ጓድ ሃይለማርያም “የወፍጮ ቤት ተመራቂዎች” ተሰብስበው “ብቃት የለህም” እያሉ ሲፈጯቸው እርሳቸውም መጽሐፍ ማንበብ አልወድም፤ ዕቅድ ማዘጋጀት አልችልበትም፤ ለውጥ ማድረግ ያቅተኛል፤ … እያሉ “ለካህናቱ” መናዘዛቸው የተማሩባቸውን ከፍተኛ ተቋማት የሚያዋርድ ነው። ውርጅብኙና አሉባልታው ሲዘንብባቸው “አሞራ በሰማይ ሲያየኝ ዋለ፤ አንዣበበኝ” እያሉ ከማልቀስ ይልቅ “እዚህ ያላችሁ እያንዳንዳችሁ እኔን የመገምገም አንዳች ብቃት የላችሁም፤ ከተገመገመም የቡድን አመራሩ ነው መገምገም ያለበት” በማለት ቆራጥ ውሳኔ ሰጥተው አፍ ማስዘጋት ሳይችሉ ቀርተው ሲያለቅሱ አምሽተዋል።
ለነገሩ ኢህአዴግ “ግም-ገማ” ይበለው እንጂ ይህች ጨዋታ የማይፈለገን ካድሬ መብያ፤ መቀርጠፊያ ስልት መሆኑ በውል ይታወቃል። “መበስበስ የጀመረ ካድሬ” እንደ “bad apple” ቶሎ ወደ ቆሻሻ መወርወር አለበት። ያልበሰበስ ከሆነ ደግሞ በግም-ገማ እዚያው በስብሶ እዚያው ገምቶ እዚያው ይጣላል። “እኛ ምንም አላደረግነውም” ለማለትም ግለሰቡ ራሱ “እኔ ግም ነኝ፤ ብስብስ ነኝ” በማለት ራሱን እንዲያዋርድ ይደረጋል። ይህ ኢህአዴግ ነው እንግዲህ አገር የሚመራው፤ አሁንም እቀጥላለሁ የሚለው።
የህወሃት/ኢህአዴግ አፈቀላጤዎች፣ ካድሬዎች፣ ሹምባሾች፣ ልክስክሶች፣ ወዘተ እንዲህ የዘቀጠውን የኢህአዴግ ማንነት በንብ ማር መስለው፤ ግም-ገማውን “ዴሞክራሲያዊ አሠራር አስመስለው” ሕዝብ ሊያሳምኑ ሲጥሩ መታየታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ያሉት ካድሬዎች የሚናገሩት አንድ ሃቅ ግን አለ፤ መንገድ መሰራቱን፤ ፎቅ መገንባቱን፤ … ያትታሉ። ቅኝ ገዢዎች ይህንን በሥርዓት የሚያደርጉት ተግባር ነው። ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ሥርዓት እየተመራች በጣም የተዋበች አገር ነበረች፤ ጎረቤት ኬኒያም የቅርብ ምሳሌ ናት። ጣሊያንም ለአምስት ዓመታት በቆየበት ጊዜያት በዚያ ሁሉ ተጽዕኖና የአርበኞች ተጋድሎ እስካሁን ድረስ የሚጠቀሱ በርካታ መንገዶችን፣ ህንጻዎችን፣ … ሠርቷል። በዘመኑ የነበሩ ባንዳዎችም ይህንኑ እያወደሱ ቪክቶር አማኑኤልን፣ ቤኒቶ ሙሶሊኒን እና አዶልፎ ግራዚያኒን ሲያገዝፉ፤ ሲያሞካሹ፤ በጸሃይ ሲመስሉ ኖረዋል። በነጻ አውጪ ስም እስካሁን ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር” – ህወሃት – ወኪሎችም ይህንኑ ሲደሰኩሩ፤ ፎቶ ሲለጥፉ፤ መለስን ከፍ ከፍ ሲያደርጉ፤ ኢህአዴግን የሚያሾረው ህወሃት – ቅኝ ገዢ፤ እነርሱ ደግሞ ባንዳዎች መሆናቸውን በማስረጃ እየመሰከሩ ነው።
“ሥልጣን ወይም ሞት” ብለው ሞት የቀደማቸው መለስ ከተሸኙ በኋላ የሃይለማርያም በሥልጣኑ መንበር መቀመጥ የህወሃት ሰዎችን ሲያንገበግብ የቆየ አጀንዳ ነው። ጎልጉል በዚህ ጉዳይ ላይ “በህወሃት “የትግራይ ኩራት ተነክቷል” ባዮች አይለዋል” በሚል ርዕስ በዘገበበት ወቅት ሃይለማርያም ከኦባማ ጋር ሆቴል ቤት በአቻነት ያደረጉት ስብሰባ መለስ ለዚህ “ክብር” ሳይበቁ በመሞታቸው “የትግሬ ክብር” ወርዷል የሚለውን ቁጭት እንዲያይል ማድረጉን አትቷል። ውጭ አገር ስብሰባ ሲሄዱ በተለይ ራት ግብዣ ላይ “ሥርዓት ያዝ!” እንደተባለ ህጻን ጠረጴዛ ጠርዝ ብቻቸውን እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው አገር ቤት ሲደርሱ የሚሳደቡትን የሚያስቡ የሚመስሉት መለስ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር ሃይለማርያም እንዳደረጉት ዓይነት የፊትለፊት የአቻ ስብሰባ ለማድረግ አንድ ጊዜ እንኳን አልቻሉም፤ አልበቁም፤ አልታደሉም።meles at g20
በተለይ ከዚህ የሃይለማርያምና ኦባማ ስብሰባ በኋላ በህወሃቶች ዘንድ እየከረረ የመጣው ሃይለማርያምን የማንሳት ዘመቻ በቅርቡ በተካሄደው “ግም-ገማ” ወቅት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ የተደረገ ይመስላል። ህወሃት ሁሉንም ዓይነት አሉባልተኞች እና ሃሜተኞች ሰብስቦ ሃይለማርያምን አዋርዷል፤ ሰድቧል፤ ብቃት አልባ አድርጓል። “የተመከረው ለራሱ ነው”፤ “ከፈለገ ይስማ ካልፈለገ …” ተብሏል። ካልሰማስ?
በቀጣይ የሚሆነው ህወሃት በጠ/ሚ/ሩ ቢሮ አካባቢ ካስጠጋቸው አንዱ “የትግሬን ኩራት” የሚመልስ፤ “በመለስ ምላስ አዲስ የስድብ ቋንቋ ፓርላማ ውስጥ የሚፈጥር”፤ “ደምመላሽ” መንበሩ ላይ ማስቀመጥ ነው። ብአዴን ሲያምረው ይቅር፤ ኦህዴድ የፊንፊኔ ከንቲባነትና ለቅሶ ደራሽ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን በዝቶበታል፤ ደቡብ ዕድሜ ለሃይለማርያም “ብቃቱን” አሳይቷል። ስለዚህ “አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር” ሰልሎም ይሁን ፌስቡክ ላይ ፈልጎ የማግኘቱ ኃላፊነት ህወሃት ላይ ወድቋል፤ “እውነተኛ ወያኔ” መሆኑን የሚያምንና ባደባባይ የሚመሰክር ዘመናዊ የህወሃት ሰው ለቦታው “ብቁ” ሊሆን ይችላል።
ለጎልጉል ቅርብ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ዜና አቀባይ ግን ህወሃት በዚህ አቋሙ ከአሜሪካ ጋር እንዳልተስማማ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ለህወሃት መሰጠት የለበትም በሚል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አውጪዎች ለህወሃት ሰዎች ተናግረዋል። አሜሪካ ይህንን አቋም የያዘችው ለኢትዮጵያ በማሰብ ሳይሆን ከትግሬ ውጪ በሆነ ሰው ሥልጣኑ ተይዞ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ጥላቻ እንዲረግብና የራሷን ጥቅም ለማስቀጠል እንደሆነ በውል የሚታወቅ ነው። “የትግሬ ኩራት ተነክቷል” ባዮቹ የህወሃት ነፍጥ አንጋቢዎችም ይህንን ለማስታረቅ ቢያቅታቸውም በአንጻሩ የጌቶቻቸውን የአሜሪካውያኑን ሃሳብ መቀበልም እጅግ አዳግቷቸዋል።haile meeting
የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጓድ ሃይለማርያም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ በቀጣዩ ምርጫ ለጠ/ሚ/ርነት ይወዳደራሉ? ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ድርጅታቸው “የጋራ ውሳኔ የሚሰጥ ድርጅት” መሆኑን በመጥቀስ ድርጅታቸው “በሚመድባቸው ቦታ” የሚሠሩ መሆናቸውን አስቀድመው ተንብየው ነበር። ትንቢቱን ሲያጠናክሩም እንዲህ አሉ “ይህ ድርጅት 20 ዓመታት ሙሉ ሲመራ ይህንን (የምደባ) አሠራሩን ለማወቅና ለመገንዘብ ይቸግራል የሚል ግምት የለኝም። በድርጅታችን ውስጥ መዳቢ ኮሚቴ አለ። እኔንም ጨምሮ የሚመድብ ማለት ነው። ይህ ኮሚቴ እዚህ ቦታ ትሠራለህ ሲል እኔም እሠራለሁ። ድርጅታችን ከዚህ ተነስተህ ወረዳ ታገለግላለህ የሚለኝ ከሆነ የወረዳ ሊቀመንበር ሆኜ እሠራለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነህ ብታገለግል የተሻለ አስተዋጽኦ ታበረክታለህ ከተባልኩ ደግሞ አገልግሎቱን እሰጣለሁ። ታላቁ መሪያችን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድርጅቴ ሊስትሮ ሁን ብሎ የሚመድበኝ ከሆነ ሊስትሮ ለመሆን ዝግጁ ነኝ ብለው ነበር። እኛ እንደዚያ ነን።” (ምንጭ፤ ሪፖርተር 12 February 2014)
“ሥልጣንህን መቼ ነው የምትለቀው?” ተብለው በተጠየቁ ቁጥር “ድርጅቴ ልቀቅ ካለኝ፤ ፓርቲዬ አትፈለገም ካለኝ፤ …” እያሉ ከ20 ዓመት በላይ ሲያሾፉ የነበሩት አራዳው መለስ ሊስትሮ ሳይሆኑ አልፈዋል። ሃይለማርያም ግን ከዚህ የሚያመልጡ አይመስሉም። ምናልባትም ጠ/ሚ/ር በመሆን ካገኙት ዝና ይልቅ በዓለም ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ሊስትሮነት የተሸጋገረ የመጀመሪያው ሹም በመሆን በጊነስ መጽሐፍ ላይ ስማቸውን በማስመዝገብ በህወሃትንና በገምጋሚዎቻቸው ላይ በቀል ያደርሱ ይሆን?!
ህወሃት ሥልጣን ለመልቀቅ አንዳችም ሃሳብ እንደሌለው በግልጽ ይናገራል፤ ሊሾማቸው ያዘጋጃቸውና ሲያሰለጥናቸው የሰነበተው “ወያኔዎችም” እንዳሉ በግልጽ የሚታይና ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ሕዝብ ድምጹ ቢከበርለት ማን እንዲያስተዳድረው እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ በምርጫ ድምጹን መስጠቱ በፍጹም የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ በኮሙኒስታዊ አሠራር የዳበረው ህወሃት/ኢህአዴግ ምርጫ ቢልም የሚያደርገውን ያውቃል፡፡ ከዚህ በፊት ከነበሩት ኮሙኒስቶች ተምሯል፡፡ ስለዚህ በምርጫ ወቅት የሚያደርገው ዮሴፍ ስታሊን ያስተማረውን ነው፤ እንዲህ ብሎ ነበር “ምርጫ እንደነበር ሕዝቡ ካወቀ በቂው ነው፤ ድምጻቸውን የሚሰጡ ምንም የሚወስኑት ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የሚወሰነው ድምጽ በሚቆጥሩት ነው”፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰሞኑን እንዳሉት ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዝ አሉት – ጠመንጃና ምርጫ ቦርድ!

No comments:

Post a Comment