Translate

Tuesday, April 22, 2014

ስለፍትህ ሲባል ስርዓቱ ይፍረስ! ክፍል ሶስት (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

Temesgen Desalegn "Fact" Ethiopian Amharic newspaper editorልዕለ ኃያሏ ሀገረ-አሜሪካን ዛሬ ለተጎናፀፈችው የሕግ የበላይነት የተከበረበት ሥርዓት መሰረት የጣሉት እነ ቶማስ ጃፈርሰን በነፃነት አዋጃቸው ላይ ‹‹ሁሉም ሰዎች በእኩልነት የተፈጠሩ ናቸው›› በማለት ሲደነግጉ፤ እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ደግሞ “Animal Farm” በሚለው መፅሐፉ፣ ጉልበታም ‹‹ገዥ›› አድርጎ በሳላቸው ገፀ-ባሕሪያት አማካኝነት ‹‹…አንዳንድ እንስሳት (ሰዎች) ግን የበለጠ እኩል ናቸው›› ይለናል፡፡ በርግጥ ሁለቱም አይነት አስተዳደሮች መሬት ወርደው ዓለማችንን ዲሞክራት እና አምባ-ገነን በማለት በሁለት ጎራ የከፈሉ የመሆናቸው ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ ራሷ አሜሪካንን ጨምሮ አብዛኛው የአውሮፓ አገራት ከሞላ ጎደል በዜጎች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ማሕበረሰብ መገንባት ከቻሉት ውስጥ ሲመደቡ፤ ብዙሃኑ የአፍሪካ እና የእስያ መንግስታት ደግሞ ‹‹አንዳንድ ሰዎች ይበልጥ እኩል ናቸው›› በሚል መንፈስ የተቃኘ አገዛዝ አንብረው፣ የትኛውንም ተግዳሮት በጠብ-መንጃ ዓይን መመልከትን ፈቅደዋል፡፡ ከእነዚህኞቹ መካከል የእኛይቷ ኢትዮጵያ ዋነኛዋ ናት፡፡

ባለፉት ሁለት አስርታት በጠቅላይነት የጨዋታ ሕግ እየተመራ፣ ከሰሜን-ደቡብ የተንሰራፋ መዋቅር መዘርጋቱ የተሳካለት ኢህአዴግ፤ የፖለቲካ ሳይንስን በአብዮታዊነት ለውጦ፣ ሀገሪቱን ለጥቂቶች የፌሽታ፣ ለብዙሃኑ የዋይታ መድረክ ሲያደረጋት አንዳች ኮሽታ ያለመሰማቱ መነሾም ይኸው ነው፡፡ ለሕግ ከማይገዙ ፖለቲከኞች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው አንስቶ፣ በአንድ ጀንበር ሰማይ-ጠቀስ ህንፃን እንደጓሮ አትክልት የሚያፀድቁ ‹‹አባ-መላዎች›› መበርከታቸው አስማታዊ-ጥበብ ያልሆነብንም ለዚሁ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳ ያላጠናቀቁ አፍላ-ወጣቶች ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ባላቸው መኪኖች መምነሽነሻቸውም ሆነ፣ ለአቅመ አዳም ሳይደርሱ ግዙፍ የአስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤት ሆነው ማየታችን ይህንኑ ያስረግጥልናል፡፡
አብዮታዊ ግንባሩ ከፊተኞቹ ንጉሳዊም ሆነ ወታደራዊው አስተዳደር የሚለይበት ክፉ ገፅታዎች አሉት፡፡ ለአብነትም ከአጀንዳችን ጋር በሚዛመደው የፍትሕ ሥርዓት ማነፃፀር ይቻላል፡፡ በአፄው ዘመን በአንፃራዊነት የሰፈነው የሕግ የበላይነት በሂደት ተንኮታኩቶ ቢወድቅም፤ ደርግ በጎዳና ላይ የፈፀመው ዘግናኙ የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ምዕራፍ ከተዘጋ በኋላ ባሉት የሥልጣን ዘመናቱ፣ በእውቀት የበቁ እና ከአድሏዊነት የራቁ ሊባሉ የሚችሉ ዳኞች እና ዐቃቢያነ-ሕግ በመሾም፣ ዛሬ ካለው የተሻለ ተቋማዊ የፍትሕ ስርዓት ለመገንባት መሞከሩን የጊዜው መዛግብት ያወሳሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በሕግ ባለሞያዎች እንደመልካም ነገር የሚጠቀሰው ‹‹ጠቅላይ ዐቃቤ-ሕግ›› ተብሎ አንድ ሰው ተመርጦ የሚሾምበት አሰራር ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቦታ የሚመደብ ግለሰብ የሀገሪቱን መሪዎችን ጭምር መክሰስ የሚችልበት ተቋማዊ ሥልጣን ያለው ከመሆኑም በላይ ‹‹አደገኛ ናቸው›› የተባሉ የህትመት ውጤቶችንም ሲያምንበት ሳይሰራጩ ቀድሞ እስከማገድ የሚያደርስ ሥልጣን ነበረውና፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር በምዕራባዊያን ሀገራት የተለመደ ሲሆን፤ የቀጥታ ሥርዓታዊ ተጠያቂነትንም ስለሚያስከትል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሕግ ለማስከበር ጠቃሚ መሆኑ በዘርፉ ምሁራንም ዘንድ የታመነበት ነው፡፡ በደርግ ዘመን (ለርዕሰ-ብሔሩ ታማኝ የመሆን ግዴታውን ሳንዘነጋ) ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ ካገኘ፣ በየትኛውም የሥልጣን እርከን ላይ ያለ ሹመኛን በሙሉ ፍርድ ቤት ከመገተር የማያስመልስ ሥልጣን እንደነበረው ይነገራል፡፡
ይሁንና ይህ ሁናቴ የግርንቢጥ ተመንዝሮ የፍትህ ስርዓቱን ከማፀየፍም ተሻግሮ፣ በሕግ ፊት እኩል ያልሆኑ ወይም በኦርዌላዊያን ቋንቋ ይበልጥ እኩል የሆኑ ‹‹ዜጐች› ተበራክተው የታዩት በዘመነ-ኢህአዴግ ነው ብል ብዙም ስሁት ድምዳሜ አይሆንም፡፡ ከዓመታት የጥምዝምዞሽ ጉዞ በኋላም የተቀደሰችዋ የፍትሕ ምኩራብ ረክሳ፣ የዜጎች መብት ተደፍጥጦ፣ ‹‹ሕገ-አራዊት›› ገንግኖ፣ ጠብ-መንጃ መንገሱ ሊስተባበል የማይችል ሀቅ ሆኗአል፡፡በርግጥ ከሁሉም አስከፊውና አሳሳቢው ጉዳይ የፍትሕ ሥርዓቱ ለዝግመታዊ ሞት መዳረጉ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ፕሮፍ መስፍን ወልደማርያም ‹‹አገቱኒ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው የነገሩን ግላዊ ገጠመኝ በሚገባ ከማስረዳቱም ባሻገር፤ ይህን ዘመን ካለፈው ዘመን እንድናነፃፅረው ዕድል ይሰጠናልና ልጥቀሰው፡-
“ሁለት በጣም የተለያዩ አሰራሮች አጋጥመውኛል፤ መጀመሪያ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ተይዤ ነበር፤ በአንድ መጻሕፍት ቤት ቆሜ ስመለከት አንድ ሰው መጣና መታወቂያውን ከአሳየኝ በኋላ መጥሪያ ወረቀት አሳየኝ፤ እንሂድ ብሎ ይዞኝ ሄደና በወንጀል ምርመራ አንድ ክፍል ውስጥ አስገባኝ፤ ሁለተኛው በወያኔ ዘመን በ1992ና በ1998 የተያዝኩበት ነው፤ ሁለቱንም ጊዜ ከአስር እስከ አስራ አምስት የሚሆኑ የታጠቁ ወታደሮች ነበሩ፤ በ1992 የተያዝኩት አንድ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ ቆሜ ነበር፤ ከአስር እስከ አስራ አምስት የሚሆኑ የታጠቁ ወታደሮች በአካባቢው ተበታትነው ለጦርነት የተዘጋጁ ሆነው ሲጠብቁ ሶስት ያህሉ በመጻሕፍት ቤቱ ገብተው ይዘውኝ መኪና ውስጥ አስገቡኝ፤ በጥቅምት 22/1998 ግን ታምሜ ተኝቼ ነበር፤ ብርቱካንና ሙሉነህ ሊጠይቁኝ መጥተው ቁጭ ብለን እናወራ ነበር፤ በድንገት የቤቱን በር ሊያፈርስ የተቃጣ ድብደባ ሰማሁና ስከፍት ጠመንጃውን ደግኖ ‹ኑ ውጡ!› እያሉ ማንገላታት ጀመሩ፤ ልብሴን እንድለብስም አልፈቀዱልኝም፤ ማዕከላዊ ወስደው በአንዳንድ ክፍሎች ውስጥ ቆለፉብን፡፡” (ገፅ 54)
መንግሥታዊው ሙስና
በደርግ ዘመን ከጥሬ ስጋ እና ከውስኪ ግብዣ ያላለፈው ሙስና፤ ዛሬ በቢሊዮን ደረጃ የሀገር ሀብትን እስከ ማስበዝበር ተደርሷል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት የተባበሩት መንግስታት፣ በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን ከሀገሪቱ 8.6 ቢሊዮን ዶላር በሕገ-ወጥ መንገድ ተዘርፎ በአንዲት የላቲን አሜሪካ ደሴት መደበቁን በሪፖርቱ መግለፁ አይዘነጋም፡፡ በአናቱም ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› እንዲሉ፤ ምንም እንኳን የዛሬው ቁጭታቸው አግባብ ባይሆንም፣ አንድ የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣን፣ ከእስር በተለቀቁ ማግስት ማረፊያ የማጣታቸው ነገር አንገብግቧቸው እንዲህ ብለውኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡- ‹‹(ከኢህአዴግ ጉምቱ መሪዎች አንዱ የነበረና በሙስና የተከሰሰን ሰው በስም ጠቅሰው) እስር ቤት ካየሁት በኋላ፣ አንዳች ነገር ከዚህች ሀገር ባለመውሰዴ ይቆጨኛል፡፡ እርሱ ስለታሰረ ቤተሰቦቹ ምን ሆኑ? በደህና የስልጣን ጊዜው ባካበተው ሀብት ለልጆቹም መትረፍ ችሏል፡፡ እኔ ግን የምኖረው በሌሎች ሰዎች ደግነት ነው››፡፡ ይህ የሰውየው ፀፀት ያረበበበት አስተያያት በጥቂቱም ቢሆን የደርግና የዚህን ሥርዓት የሙስና ሁለንተናዊ ሥርዓት መጠቆሙ አይቀርም፡፡
በርግጥ ኢህአዴግ አራት ኪሎን በተቆጣጠረ ማግስት የግንባሩ ቀዳማይ መሪዎች (የተከሰሱትም፤ ያልተከሰሱትም) ‹ኢትዮጵያ አጣዳፊ ዕዳ ውስጥ ገብታለች› በሚል ሰበብ ‹ሙስናን በግላጭ ጀመሩ› ከሚባሉት አንስቶ፤ የኮንትሮባንድ፣ የንግድ ማጭበርበርና የታክስ ስወራና ቅነሳን ጨምሮ፣ ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለአራጣ ብድር የመዋሉ እውነታ አገዛዙ ከጥቂት ባለሀብቶች ጋር በጥቅመኝነት የተሳሰረ መሆኑን ይነግረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ምሳሌ ከአራጣ ብድር ጋር ተያይዞ የተከሰተውን አስደንጋጭ ጉዳይ ብናነሳው ውንጀላውን ምክንያታዊ ያደርገዋል፡፡
እንደሚታወሰው በ2001 ዓ.ም የጌታነህ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ጌታነህን ጨምሮ የ‹‹አሴ ማርብል›› ድርጅት ባለቤት አቶ ምክንያቱ ኃይሌ ራሳቸውን መግደላቸው፣ ጉዳዩን ከጓዳ ወደ አደባባይ አምጥቶታል፡፡ በወቅቱም አሳዛኙን ክስተት ተከትሎ ወሬው ከቁጥጥር ውጪ በመውጣቱ በማሕበረሰቡ ውስጥ የፈጠረው ውዥንብርና ጉሩምሩምታን ለማለዘብ፣ መንግስት በአራጣ ማበደር የጠረጠራቸውን ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ከማዋል አልፎ፣ በኢቲቪ በኩል ዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅቶ የአንድ ሳምንት ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነዝቶበታል፡፡ ‹‹ማነህ ባለሳምንት?›› የሚል የምስጢር ኮድ (ርዕስ) በተሰጠው በዚህ ዶክመንተሪ ፊልም፤ የዛሬን አያድርገውና ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የዘመቻው ፊት-አውራሪ መስሎ በመቅረብ ‹‹ጀብዱውን›› አለቅጥ አጋንኖ እንደተረከልን
እስታውሳለሁ፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ‹ባለሳምንት፣ በል አንተም ግባ!› ከመባሉ በፊት፤ የሙስና-ፀር፣ የሙሰኞች ቀንደኛ ጠላት መስሎ በመተውን ብቃቱ የሚታወቀው ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በዶክመንተሪው ‹ለሙሰኞች ምንም ምህረት የለንም!› እያለ ሲዝት የተመለከተው ሕዝብ በእጅጉ አድንቆት ነበር (በነገራችን ላይ በዶክመንተሪው ፊልም ውስጥ ከገብረዋህድ እኩል መሬት አልበቃው ብሎት የነበረው የገቢዎችና ጉምሩክ ዓቃቢ-ሕግ እሸቱ ወ/ሰማያት ከእነ ገብረዋህድ ጋር አብሮ የታሰረ ቢሆንም፤ አሁን ከእስር ተፈትቶ በቀድሞ አለቆቹ ላይ ምስክር እንዲሆን መደረጉን ከምንጮቼ አረጋግጫለሁ)፡፡ የሆነው ሆኖ አሳማው ናፖሊዮን ‹‹አንዳንድ ሰዎች ግን ይበልጥ እኩል ናቸው›› እንዲል፤ በወቅቱ እነ ገብረዋህድ ከተከሳሾቹ መካከል ለፍርድ እንዳይቀርቡ ያደረጓቸው ጥቂት ወንጀለኞች መኖራቸውን ማወቅ የምንችልበት የነብይነት ፀጋ አልነበረንም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነው፡፡ ለአብነትም በጊዜው በስፋት ያነጋገረው የዮሐንስ ጌታነህ ራስን የማጥፋት ወንጀል፣ ከኬኬ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ‹‹ጉዳዩ ይመለከተኛል›› ለሚለው ጉምሩክና ገቢዎች መረጃው ቢደርሰውም ተጠርጣሪው በነፃ መለቀቁን መጥቀስ ይቻላል፡፡ጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ከዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዮሀንስ ህልፈት በኋላ በሐምሌ 13 ቀን 2001 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን‹‹ጉዳዩ፡- መረጃ ስለመስጠት›› በሚል ርዕስ ሥር የፃፈውን ደብዳቤ ቀንጭበን እናንብብ፡-
‹‹ድርጅታችን ጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአራጣ አበዳሪዎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትና በአሁኑ ጊዜም ለከፋ ኪሳራ የተዳረገ ሲሆን፣ ከአራጣ አበዳሪዎች መካከል የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ዋና ስራ አስኪያጅ እና የድርጅቱ ባለቤት አቶ ከተማ ልጅ የሆኑት ወ/ት ትዕግስት ከተማ አንዱ ናቸው፡፡ …በኚህ ግለሰብ የጭካኔ ተግባር ኩባንያውን በፍትሐ ብሔር ክስ መስርተው ከማዋከብ በተጨማሪ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አጥናፉ ጌታነህን በእጃቸው በሚገኝ ቼክ /በአራጣ ዋስትና/ በወንጀል በመክሰስ የ6 ወር እስራት በማስፈረድ፤ እንዲሁም በኩባንያው ስራ አመራሮች ላይ ከፍ ያለ የሥነ ልቦና ጫና በመፍጠር በምናካሄደው የንግድእንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ኪሳራና በደል አድርሰውብናል…››
ከጉዳዩ ሰለባ ይህ አይነት ተጨባጭ መረጃ፣ የደረሰው ገቢዎችና ጉምሩክ ግን፣ በወቅቱ አቶ ከተማ ከበደ ላይ ክስ ለመመስረት አልደፈረም፡፡ እኮ ለምን? ለዚህ ጥያቄ፣ የምናገኘው ብቸኛ ምላሽ ከሙስና ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ፣ ራሱ የተቋሙ የወቅቱ ዳይሬክተርአቶ መላኩ ፈንቴ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ለመርማሪዎች ከሰጠው ቃል ውስጥ፡-
‹‹ሳሙኤል ታደሰ የተባለና በመሥሪያ ቤቱ የሕግ ምክር ቡድን ዐቃቢ ሕግ የሆነው ግለሰብ እቢሮዬ መጥቶ ‹የከተማ ከበደን ክስ ገብረዋህድ በገንዘብ ተደራድሮ ክሱ እንዲነሳ እያደረገ ነው› አለኝ›› በማለት መጠቀሱን ተመልክቻለሁ፡፡
በርግጥ ይህን መሰል አደገኛ የሕግ ጥሰት እየተፈፀመ ስለመሆኑ የሚያመላክት ከባድ መረጃ ለመላኩ ፈንቴ የሰጠው የበታች ሰራተኛው አቶ ሳሙኤል ብቻ አይደለም፤ በፓርቲውም ሆነ በፖለቲካው ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነው በረከት ስምኦንም ጉዳዩን አንስቶለት ነበር፡-

‹‹አቶ በረከት ቢሮ በአካል እንድገኝ ጠርቶኝ በሄድኩበት ወቅት ‹የከተማ ከበደን የአራጣ ኬዝ ገብረዋህድ ተደራድሮ ክሱን አንስቶለታል ይባላል፣ ጉዳዩን ታውቀዋለህ ወይ?› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ‹ግለሰቡ ተደጋጋሚ ጊዜ እንደስራ {እንደ መደበኛ ሥራ} አድርጎ መስራቱን የሚያሳይ ማስረጃ ስላልተገኘ ክስ አልመሰረትንበትም› አልኩት፡፡ ‹ኬዙን የምታውቀው ከሆነ ጥሩ ነው› ብሎኝ ተለያየን፡፡ እኔም አቶ ገብረዋህድ ማስረጃ አልተገኘም ስላለኝ ኬዙን አልተከታተልኩትም፤ የት እንደደረሰም አላውቅም››
 ማለቱን የምርመራ መዝገቡ ላይ ተጠቅሷል (በነገራችን ላይ በዚሁ ርዕሰ-ጉዳይ በሚያጠነጥነው ክፍል አንዱ ጽሑፍ ላይ፣ አቶ ኮነ ምህረቱ ከእስር የተለቀቁት ‹‹መረጃ ስለሰጡ ነው›› በሚል የጠቀስኩት የአቶ መላኩ ቃል በምርምራ መዝገቡ ላይ ቢኖርም፤ አቶ ኮነ ነፃ የወጡት በፍርድ ቤት እንደሆነ ከሌላ ሰነድ ላይ ተመልክቻለሁ)
እንግዲህ እነዚህ የመረጃ ምስክሮች ሁለት ታላላቅ እውነቶችን ያስረግጡልናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የመጀመሪያው ሙስና በዚህች ሀገር እጅግ ጠልቆ ሥር መስደዱንና ሥርዓቱ ራሱ እጁን ከቶ የሚያቦካበት ተጨባጭ እውነታ መሆኑን አምነን እንድንቀበል መገደዳችን ጋር ይያያዛል፡፡ ምክንያቱም የጌታነህ ዮሐንስ ቤተሰቦች የድርጅቱ ህጋዊ ማህተም በታተመበት ደብዳቤ ላይ በአራጣ ብድር ከነበራቸው ዕዳ 10 ሚሊዮን ብር ውስጥ ግማሹን ለአቶ ከተማ ድርጅት መክፈላቸው እና ለቀሪው 5 ሚሊዮን ብር ደግሞ የጌታነህ ትሬዲንግ ንብረት በሀራጅ እንዲሸጥ መወሰኑን መግለፃቸው፤ እንዲሁም እንደ አቶ በረከት ስምኦን ያለ ወሳኝ ባለሥልጣን ስለጉዳዩ መስማቱን በቀጥታ ለአቶ መላኩ መናገሩ ነው፡፡ መቼም በረከት ‹‹መረጃ አገኘሁ›› የሚለው ከአልፎ ሂያጅ መንገደኛ አለመሆኑን መገመት አይሳነንም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በ2001 ዓ.ም ማስረጃ የቀረበበትን ተጠርጣሪ ከአራት ዓመት በኋላ ያንኑ ክስ እና ማስረጃ በመቁጠር ወደ ፍርድ ቤት ሊወስድ የሚችልበት ያልተሰማ ተአምር የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ምን አልባት የዚህ ምስጢር በሁለተኛነት ከምጠቅሰው ጭብጥ ጋር ሊተሳሰር ይችላል፤ ይኸውም ሥርዓቱ የራሱን ሰዎች በ‹‹ሙስና›› ወደ እስር ቤት የሚወረውረው ሙስናን ለመዋጋት ባለው ተነሳሽነት ሳይሆን፣ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ የተፈጠረበትን የውስጠ-ፓርቲ ክፍፍል ለማብረድ ‹እንደ አጀንዳ ይጠቅመኛል› ብሎ ሊሆን የሚችልበት ገፊ-ምክንያት መታየቱ ነው፡፡ በተለይም የህወሓት አመራር አባላት ‹‹የመቀሌው›› እና ‹‹የአዲስ አበባው›› በሚል በወቅቱ መከፈላቸው፤ እንዲሁም ብአዴን ከመቀሌው ቡድን ጎን መቆሙ እና ለእስር የተዳረጉት ባለሥልጣናትም በዚሁ መስመር የተሰለፉ መሆናቸው ከሹክሹክታ ያለፈ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም ሁሉም ተከሳሾቹ የተጠየቁበት ወንጀል በአቶ መለስ ዘመን ተፈፅሞ፣ የተከሰሱት ግን ከሞቱ በኋላ መሆኑ ጉዳዩን ሙስናን ከመታገል ለይተን እንድንመለከተው ያስገድደናል፡፡
እዚህ ደርሰናል¡
ይህ ስርዓት ከቀደሙት ያፈነገጠበት አንዱ መለዮው፣ የጥቅመኝነት ሰንሰለቱን ተቋማዊ ቅርፅ መስጠቱ ነው፡፡ ከስልጣን ፒራሚዱ አናት ላይ የተቆናጠጡት ገዢዎች፣ በጥቅም የሚደልሏቸውን ከስራቸው እየሰበሰቡ በ‹‹እከክልኝ…›› ጥብቅ ዝምድና ውስጥ ይጋመዱና፣ ግንባሩ ቢነካ የእነርሱም ህልውና እንደሚናጋ በማመን አንዳች ክፉ ነገር እንዳይደርስበት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ዳሩ ግን፣ የሀገሪቷ ብሄራዊ ኬክ በእጅጉ አነስተኛ ነውና፤ አንደኛው የበለጠ ድርሻ ሲሻ፤ ከሌላኛው ጥቅመኛ ጋር መናረቱ እውነት ሆኗል፡፡ በመንግስታዊው ሙስናም እያየን ያለነው ይኸው ነው፡፡ አሁን በእስር ላይ ያሉት የቀድሞ ባለስልጣናትም ሆኑ፤ በድሆች ጉሮሮ ላይ የቆሙት አራጣ አበዳሪ እና ‹‹ልማታዊ ባለሀብቶች››፣ እነርሱን ከሚበልጡ ጥቅመኞች ጋር የገጠማቸው ግድድር ለወህኒ እንዳበቃቸው መጥቀስ አንደኛው የመከራከሪያ ጫፍ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በሙስና በተዘፈቀ መንግስት ውስጥ፣ ማንም ማንንም በሙሰኝነት ሊከስስ የሚችልበት የሕግ መሰረት አለመኖሩ ግልፅ ነው፡፡ ይሁንና ቻርለስ ዳርዊን ‹‹ጉልበታሞቹ ደካሞቹን እየዋጡ ይቀጥላሉ›› እንዲል፤ ምንም ያህል አምባገነን እና ጨቋኝ ስብስብ ቢሆንም ራሱን በራሱ ከመበላት ለማዳን ‹‹የእርምት እንቅስቃሴ›› ማድረግ አለበትና፤ ጥቂት ሙሰኞችን ሰብስቦ እስር ቤት ቢከት እልል በቅምጤ አያስብልም፡፡
ሌላኛው ነገሩን ሊያብራራልን የሚችለው ጉዳይ፣ የሙስና ክስ እና የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ለዚህ መሰሉ ሰበብ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያልነው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በርዕስ-ጉዳይ ዋነኛ ማጠንጠኛ ባደረኳቸው ጽሑፎቼ በሙስና ተከሰው ዘብጥያ የወረዱት ባለስልጣናት፣ በውስጠ-ኢህአዴግ ለተፈጠረው የስልጣን ትንቅንቅ ማብረጃ የተመረጡ መሆናቸውን በአመክንዮ አስደግፌ ለማስረዳት መሞከሬ አይዘነጋም፡፡ መቼም መላኩ ፈንቴም ሆነ ገብረዋህድ፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በነፃነት እንዳይጎለብት ከማድረግ አልፈው፣ የህወሓት የንግድ ተቋማት የሀገሪቱን ሁለንተና እንዲቆጣጠሩ ከፍ-ዝቅ እያሉ ሲለፉ መቆየታቸውን በማስታወስ፣ ዛሬ ስለገጠማቸው መንከራተት ሀዘኔታ ሊኖረን የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ይህ ጉዳይ አሉባልታ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ለማስረዳት ሁለት ሰነዶችን ልጥቀስ፡፡ የመጀመሪያው ራሱ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን መርማሪዎች አቶ መላኩንም ሆነ አቶ ገብረዋህድን ከመረመሩበት መዝገብ ላይ የተገኘ ነው፡-
‹‹1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች (መላኩና ገብረዋህድ) በተለያየ ጊዜ ለ5ኛ ተከሳሽ (እሸቱ ግራፍ ይባላል፤ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አቃቂ ቅርንጫፍ የሕግ ማስከበር ኃላፊ እና በሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ-አስኪያጅ የነበረ) ትዕዛዝ በማስተላለፍ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የትራንዚት ፍቃድ ተሰጥቷቸው በጅቡቲ በኩል ከውጪ አገር ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሚሌ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ከሚደርሱት መኪኖች (ዕቃዎች) ውስጥ፡- መቴክ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢኒጅነሪንግ፣ ሜድሮክ፣ ኒያላ ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያና መለዋወጫ ዕቃ አስመጪ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ድርጅቶች የሚያስመጡትን ዕቃዎች በ5ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ተመርጠው ሳይፈተሹ፣ ‹ተፈትሸዋል› የሚል ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማስደረጋቸው››ይላል፡፡
ሁለተኛው ሰነድ ደግሞ ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ገቢዎችና ጉምሩክ ለፀረ-ሙስና የላከው ደብዳቤ ሲሆን፤ እንደሚከተለው እንቀንጭብለት፡-
‹‹ከ2003 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም በቅ/ጽ/ቤታችን ሥራ-አስኪያጅ በኩል በተለያዩ ጊዜያት በተቋቆሙ የመረጣ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተለያዩ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ጭነቶች በመረጣ ኮሚቴው እየተመረጡ ሳይፈተሹ እንደተፈተሸ ምልክት ተደርጎ የፍተሻ ማሕተም እየተደረገባቸው ሲተላለፉ የነበረ ሲሆን፤ ይህም አግባብነት የሌለው መሆኑን እንገልፃለን፡፡ ከእነዚህም ጭነቶች ውስጥ ለአብነት መስፍን ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ሜድሮክ፣ ሳሊኒ፣ መተሃራ ስኳር… የሚጠቀሱ ናቸው›› (ማሕተም አለው፤ ስለ ሥራ-አስኪያጁ በሚል አቶ አበበ ሚሻሞ የተባለ ሰው ፈርሞበታል)
መቼም በእነዚህ ሰነዶች ከተጠቀሱት ድርጅቶች ውስጥ ቢያንስ እነ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ እነ ስኳር ኮርፖሬሽንን ማን እንደሚቆጣጠራቸው መታወቁም ሆነ፤ የቱጃሩ ሼኸ መሀመድ አላሙዲን ሜድሮክ የዚሁ ነውረኛ አሰራር ተጠቃሚ መሆኑ፣ ዛሬም ድረስ በቸልታ የምናልፋቸውን አያሌ ጉዳዮች እንድናሰላስል ያደርገናል፡፡ እነ መላኩ ፈንቴም፤ በተለይ ከኤፈርት ድርጅት እና አባይ ፀሀዬ በሚኒስትር ማዕረግ ይመራው ከነበረው ስኳር ኮርፕሬሽን፤ እንዲሁም እነ ሳሞራ የኑስ ከሚያስተዳድሩት የመከላከያ ቴክኖሎጂ ተቋም ሊያገኙ የሚችሉት ግላዊ ጥቅም ይኖራል ተብሎ አይታሰብምና፣ የተከሰሱበትን ሕገ-ወጥ ትዕዛዝ ከማን በምን መልኩ እንደተላለፈ ደፍሮ በማጋለጥ ኢህአዴግ ካዘቀጠው ፍትሕ ሥርዓት ይልቅ፣ ለሕዝባዊ ፍርድ ቢታመኑ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መቼም አገዛዙ እንደሆነ አንደ አላቂ ዕቃ ተጠቅሞ በፈለገው ሰዓት ወደ እስር ቤት መወርወርን የተለመደ ተግባሩ አድርጎታል፡፡ እናስ ወንድሞች! ዛሬም በጥቂት የህወሕት ሰዎች ትዕዛዝ በፈፀማቸሁት ወንጀል ዝምታን በመምረጥ ስቃይን መቀበል ብልህነት ነው ትላላችሁ?!
ምን ይሻለናል?
ባለሀብቶቹም ቢሆኑ እንደ ባለሥልጣናቱ እስረኞች ሁሉ ተመሳሳይ መልክ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ እስር ያልደረሰባቸው አራጣ አበዳሪዎቹም ሆኑ በሙስና መበልፀጋቸው የሚታወቅ ትላንት የተወለዱ ከበርቴዎች፤ ከስርዓቱ ሰዎች ጋር ባላቸው የተሻለ የጥቅም አልያም ብሄር-ተኮር ግንኙነት መትረፋቸው፣ ልክ እንደአሳሪና ታሳሪዎቹ ገዢዎቻችን ሁሉ፣ የእነዚህም ባለተራነት የጊዜና ከገዘፉት የፓርቲ መሪዎች ጀርባ የመደበቅ ወይም ያለመደበቅ ጉዳይ ብቻ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ወታደራዊ መኮንኖቹም ቢሆኑ፣ በሀገር አውዳሚው ተግባር መሳተፋቸው በስፋት ይሰማል፡፡ በርግጥም የአንድ ጄነራል መንግስታዊ ደመወዝ ስንት እንደሚደርስ በሚያውቅ ህዝብ መሀል፣ የአዲስ አበባን አስፓልት ግራ-ቀኝ በፎቆች መሙላት፤ የመኮንኖቹን ስርዓታዊ ትምክህተኝነት በሚገባ ይናገራል፡፡ የነገሩ ውስብስብነት የሚታየው ደግሞ፣ የከፍተኛ ማዕረግ መኮንኖቹ የሙስና ዝፍቀት፣ ከጉምሩክ እስከ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማትን አስተሳስሮ፤ የንግድ ማህበረሰቡን አባላትም አካትቶ የያዘ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በአም-ባገነን መንግስታት እንደ ‹‹ነብይ›› የሚቆጠረው ኒኮሎ ማኪያቬሊም ‹‹The Prince›› በተሰኘው ዘመን አይሽሬ መጽሐፉ፤ ገዥዎች ከሕዝባቸው በተጓዳኝ የጉልበተኛ መኮንኖችን ፍላጎት ማሟላት እንደሚኖርባቸው ይመክራል፡፡ የዚህ መደብ ወካዮች ጥቅም ለማግበስበስና መረን ለወጣው ጭካኔያቸው መሰረት ለማስያዝ፣ አገዛዙ ክፉ ባህሪያት እንዲኖረው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በማኪያቬሊ አስተምህሮ መሰረት፣ በውስጣዊ ተቃውሞ የሚናጥ ሥርዓት ዕጣ-ፈንታውን ከሕዝብ ይልቅ ከወታደራዊ መኮንኖቹ ጋር ማስተሳሰሩ ከመአቱ የሚያመልጥበትን ዕድል ያሰፋዋል፡፡ ይህንን መርህ ትላንት አቶ መለስ ዜናዊ፣ ዛሬ ደግሞ እነ አባይ ፀሀዬ እና በረከት ስምኦን የመጫወቻ ካርድ ቢያደርጉት የሚገርም አይሆንም፡፡ እናም የተመሰረቱ ክሶችን እያቋረጡ ከአገር የሚሰደዱ ዐቃቢያነ-ሕግ እና በፖስታ የተላከላቸውን ፍርድ የሚያነበንቡ ዳኞች የሞሉበት የፍትህ ተቋም ሊያያቸው ያልተቻለው የእነዚህ ‹‹የጦር መሪ›› ሙሰኝነት፣ አንድ ነገር እስካላደረግን ድረስ ሀገሪቷን ከሥርዓቱ እኩል ገዝግዞ ከመጣል የሚመለስ አይሆንም፡፡
መንግስታዊ ሙስና እንዲህ እንደ ኢህአዴጓ ኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ትልቁን ጨቋኝ ከትንሹ የሚያባላበት ጥግ ሲደርስ፤ የፍትህ ስርዓቱም በዚሁ ስርዓታዊ ክስረት መበከሉ አልቀረም፡፡ ከከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ የወረዳ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ድረስ፣ ፍትህ የሚያገኙት የተከበረውን መቅደሰ ማዘሞት የሚችሉት ብቻ ሆነዋል፡፡ ማህበረሰቡን የሚያናውጡ ወንጀሎች የሚፈፅሙ፣ ህፃናትን በጨቅላነታቸው ለሚያስቀጥፍ ኃጢያት የሚዳርጉ ሞራለ-ቢስ የንግድ ሰዎችም ክሶቻቸውን የሚያቋርጡበት፣ ምስኪን ሀገር ይዘን ቀርተናል፡፡ እናም መሰረታዊው ጉዳይ ፍትህ የተጨፈለቀባትን ሀገር፣ እንዴት ወደፊት መውሰድ ይቻላል? የሚለው ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ስለርትዕ ልዕልና ስንል፣ ከስርዓቱ ውስጥም ሆነ ውጪ ሆነን የየድርሻችንን ብናዋጣ፤ ቅፅሩን አፍርሶ ሀገሪቷን ለማሰንበት አድካሚ መንገድ እንደማያስጉዘን ማመን፣ የዘመኑን ድምፅ መስማት እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment