Translate

Tuesday, April 22, 2014

ሁለት : ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? እሱ ሲፈቅድ ነው? ወይስ ጌታው ሲፈቀድለት? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)


Prof. Mesfin Woldemariamአንድ በሀርቫርድ የኒቨርሲቲ ያጋጠመኝን ነገር መግቢያ ላድርገውና ልቀጥል፤ በአንድ ሴሚናር (የጥናት ውይይት) ላይ አንድ ጥቁር አሜሪካን ፕሮፌሰር ወደአሜሪካ በባርነት በመጡት አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ በመዘርዘር አስረድቶ አሁን ለእነሱ ልጆችና የልጅ ልጆች ካሣ መከፈል አለበት የሚል ክርክር አነሣ፤ ካሣውን የመክፈል ግዴታ የሚጣለው ማን ላይ ነው? ካሣውንስ የመቀበል መብት የሚሰጠው ለማን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሳናነሣ ብዙ ሌሎች ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ — እነዚያ ከአፍሪካ በባርነት ተይዘውና ተሸጠው የመጡት ሰዎች ዛሬ የሉም፤ እነሱ በባርነት ሞተዋል፤ ዛሬ በሕይወት የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻነታቸውን አግኝተው ባለሙሉ መብት ዜጎች ሆነዋል፤ በአንጻሩ ደግሞ ለባሪያዎች ነጻነት የተጋደሉ ነጮች አሉ የእነዚህ ልጆች ከባሪያዎቹ ወይንስ ከጌቶቹ ወገን ይመደባሉ? ዛሬ ለልጆቻቸው ካሣ ይከፈል ማለት ልጆቹ የራሳቸውን ነጻነት ችላ ብለው ከአባቶቻቸው ባርነት ጋር እንዲቆራኙ ማድረግ አይሆንም ወይ? የባርነት ምልክቶችን ሁሉ ደምስሰው ነጻ ሰዎች ለመሆን የመጀመሪያው ግዴታ ራስን ችሎ በሁለት እግሮች መቆም ነው፤ ካሣ ክፈሉን ማለት አንደኛ ዋጋ ለማይሰጠው ነጻነት ዋጋን በማውጣት ማርከስ ነው፤ ከሰውነት ወደቤት እንስሳነት መውረድ ነው፤ ሁለተኛ በጌታና በባርያ መሀከል ያለው ግንኙነት መልኩን ለውጦ እንዲቀጥል መድረግ ነው፤ የውይይቱ ባለቤት እኔ ያቀረብሁትን ሀተታ እንዳላሰበበት ቢናገርም የእኔ ጥያቄ የተወደደ አልመሰለኝም፤ ካሣ ተቀባዮች ባርነታቸውን ካሣ ከፋዮች የባሪያዎች ባለቤትነታቸውን ጠብቀው እንደተቆራኙ መቀጠላቸው ባርነትን አያጠፋም፤ ለእኔ ጤናማ አልመሰለኝም።

ባሪያና ኃላፊነት አይተዋወቁም፤ ባሪያ ለገዛ ራሱ ኑሮም ቢሆን ኃላፊነት የለውም፤ ለምግቡም ሆነ ለልብሱ፣ ለመጠለያውም ሆነ ለቀብሩ ኃላፊነት የለበትም፤ ለሁሉም ነገር ኃላፊነቱ የጌታው ነው፤ ከባርነት መውጣት ማለት፣ ከባርነት መላቀቅ ማለት ነው፤ ለገዛ ራስ ሕይወት፣ ለገዛ ራስ ኑሮ ሙሉ ኃላፊነትን መሸከም ነው፤ ስለዚህም ከባርነት ወደነጻነት መሻገር ከግድዴለሽነት ወደኃላፊነት መሻገር ነው፤ ስለዚህም ከግዴለሽነት ወደኃላፊነት ሳይሻገሩ ከባርነት ወደነጻነት መሻገር አይቻልም! ኤልሪድጅ ክሊቨር የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው (Soul on Ice) የሚል መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አፍአዊ ምልክቶችን ዘልቆ የሚገባ የነጻነትንና የባርነትን ባሕርያት ያሳያል፤ በአንድ በኩል በሴት ባርያና በወንድ ጌታ መሀከል ያለውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንድ ባርያና በሴት እመቤት በኩል ያለውን ግንኙነት በግላጭ ያወጣዋል፤ ባርነትን የባሕርዩ ያደረገ መገለጫው ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑ ነው፤ ለምንም ነገር ሳያስብ፣ በትእዛዝ ብቻ መመራት የተመቸው ባርያ ነው።
ደግ ጌታ በራሱ ተነሣሺነትና በራሱ ፈቃድ ባሪያውን ነጻ ቢያወጣው ባሪያው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚሆን አይመስለኝም፤ በሕግ ነጻ ይሆናል፤ በውስጡ ግን ገና ከባርነት አልተላቀቀም፤ ከጌታው ጥገኛነት ለመውጣት ባለመዘጋጀቱ በኑሮውም ቢሆን ከጌታው አልተላቀቀም፤ ሳይለቀለቅ ከነእድፉ እንደተሰጣ ልብስ ነው፤ ተፈቅዶለት ከባርነት የወጣ ገና ነጻነትን አላገኘም፤ ከባርነት ለመላቀቅ በፍላጎቱና በፈቃዱ ወስኖ ነጻነቱን ከጌታው በግድ ፈልቅቆ ማውጣት አለበት፤ ለምን? የነጻነቱንና የሰውነቱን ቁርኝት ተገንዝቦ፣ የዜግነት እኩልነቱን ተረድቶ፣ በሰውነትም በዜግነትም ጌታህ-ነኝ ከሚለው የማያንስ መሆኑን አምኖ በቆራጥነት ሲነሣ ነው፤ የሰውነቱንና የዜግነቱን ልክ፣ የነጻነትን ትርጉምና ጣዕም አውቆ በትግል ነጻነቱን ሲያገኝ ያለጥርጥር ከባርነት ወጣ ማለት ይቻላል፤ አለዚያ ነጻነቱን በስጦታ፣ በጌታው መልካም ፈቃድ የሚያገኘው የነጻነት ሙሉ ባሕርይ አይኖረውም።
የአፍሪካን አገሮች ብንመለከት የመረረ የነጻነት ትግል የተካሄደባቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አልጂርያ፣ ዚምባብዌ ናቸው፤ እንደሚታወቀው እነዚህ አራቱም አገሮች ለአውሮፓውያን ሰፈራ የታጩ ነበሩ፤ ምናልባት በእነዚህ ዘገሮች ለነጻነት የተደረገውን ትግል መራራ ያድረገው ዋናው ምክንያት አፍሪካውያኑ አገር-አልባ ሆነው እንዳይቀሩ የነበረው ስጋት ሊሆን ይችላል፤ በአንጻሩ ሱዳን የነጻነት ትግል አልነበረም፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት ስለሆነ ቶሎ ነጻነትን በመስጠትና ወዳጅ በመፍጠር፤ በሶማልያም በኩል እንዲሁ ቶሎ ነጻነትን በማሸከም ምዕራባውያን ወደፊት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እየቀረጹ ነበር ለማለት ይቻላል፤ ግብጾች ከስንት ሺህ ዓመታት በኋላ ነው አሁን በዘመናችን ወንዶችና ሴቶች በአደባባይ ወጥተው እምቢ! በማለት ሙባረክን ያስወረዱት! ለነጻነት የመታገሉ ልምድ ስለሌላቸው፣ በዚያም ላይ ባህልና ሃይማኖት ተጨምሮበት ሙባረክን አስወርደው ነጻነትን አላገኙም፤ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ሕዝብም አጼ ኃይለ ሥላሴን አስወርዶ ነጻነቱን አላገኘም::
እያንዳንዱ ሰው የተፈጠረው ከነፍላጎቱና ፍላጎቱን ለማሟላት ካለው አዛዥነት ጋር ነው፤ ባርያ ፍላጎቶቹን ለማሟላት አዛዥነቱ የለውም፤ አዛዡ የራሱ ፈቃድ ነው፤ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሰው ወና ሰው ነው፤ ዋናውን የሰውነት ባሕርዩን ያጣ ባዶ ዕቃ ነው፤ ከባዶ ዕቃ ውስጥ የሚወጣ ነገር የለም፤ ለዚህ ነው ለነጻነቱ መታገልና በራሱ ጥረት ድልን ለመጎናጸፍ የማይችለው።

No comments:

Post a Comment