Translate

Tuesday, February 18, 2014

የረዳት አብራሪው እህት መልዕክት በግምገማ አይን…

Abe Tokchaw

የረዳት አብራሪው እህት መልዕክት በግምገማ አይን…
397281_138042889641890_1097458037_nየረዳት አብራሪው እህት በፌስ ቡኳ በኩል እንድ መልዕክት አስቀምጣ አግኝተናል። ይህንኑ መልእክት እንደሚከተለው በገምገማ አይን እናየዋለን!
በመጀመሪያ ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ሰዎች በሙሉ የተዝረከረከ ከሆነባችሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ከትናንት ከሰዐት በኋላ ጀምሮ እስካሁን ኢንተርኔትና ቴለቪዥን ላይ ያለማቋረጥ ተተክየ ስለቆየሁና በጥልቅ ሃዘን ስለተመታሁ አይምሮየ ትክክል ላይሆን ይችላል።
(አይዞሽ እታለም ችግርሽ ችግራችን ነውና እስቲ አውጊን እባክሽ….)
‘የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ሮም ይጓዝ የነበረ አውሮፕላን ጠልፎ ጄነቫ ላይ ያሳረፈው ረዳት አብራሪ እጁን ለስዊዝ ስጠ። ምክንያቱም ስዊዘርላንድ ውስጥ ጥገኝነት ለመጠየቅ ነው ብሏል።’ የሚለውን ዜና በርካታ የዜና ማሰራጫዎች ከየፊናቸው አስተያየት ጋር አቅርበውታል። የዜና ማሰራጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ወገኖች ያሻቸውን ብለዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች የሰብዐዊ መብት ተሟጋቾችና እንደ አቤ ቶኪቻው ያሉ ቀልደኞች የየራሳቸውን ሃሳብ ለማስተላለፍ ተጠቅመውበታል። በጣም አሳዝኝ ነገር ነው። ሁሉም የየራሱን እምነት ለማስተላለፍ እንጂ እሱስ ምን ሆኖ ይሆን ብሎ አለማሰቡ ልብ ይሰብራል።

(ቆይ እማዬ እዝችጋ እኔም አስተያየት አለኝ፤ አንደኛ ነገር በዚህ ሁሉ መሃል እኔ ምስኪኑ እንደ ቀልድኛ የተቆጠርኩበት ምክንያት አልገባኝም።  ሁለትኛው ነገር ግን “ሁሉም የየራሱን መልዕክት ለማስተላለፍ ተጠቀመበት እንጂ እርሱ ምን ሆኖ ይሆን  ብሎ አለማሰቡ ልብ ይሰብራል ላልሽው…”  የጠላትሽ ልብ ስብር ይበልና ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኮ ምን ሆኖ ይሆን ብሎ ሲጠይቅ ነበር። ሲጠይቅ ብቻም ሳይሆን ሲጨነቅም ነበር። በርግጥ አንዳንድ ወዳጆቻችን “መንግስታችንን አዋርደ…. ” በለው ሲቆጡ አይቻልሁ።፡በተረፈ…. እኔም የወንድምሽ እና ወንድማችን ሁኔታ ካሳሰባቸው መካከል ነኝ። እናም በእውነቱ ወቀሳሽ ፍትሃዊ አልምሰለኝም። እስቲ ለማንኛውም ቀጥይልን….)
ወንድሜ ሃይለመድህን አበራ የሰዎችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም እንስሳትን ለመጉዳት የሚፈልግ ሰው አይደልም። ደግሞም ያንን የጨነቀውን ያክል ከፈራው ነገር ለመሸሽ ሞከረ እንጂ ማንንም ባለመጉዳቱና ሃሳብ እንኳ እንዳልነበረው ምንም አይነት ማጥቂያ መሳርያ ባለመታጠቁ አሳይቷል። በሁሉም ዘንድ የሚታወቀው ለተቸገሩ በመድረስና ባዛኝነቱ ነው። ካገር ውጪ ሄዶ ለመኖር የሚፈልግ ሰው ቢሆን ለሱ በጣም ቀላል ነገር ነው። ከጥቂት ወራት በፊትንኳ ዩኤስ ኤ ሄዶ ነበር። ከ አስር ቀናት በላይንኳ መቆየት አልፈለገም። ዝም ብሎ ካገር መውጣት ቢፈልግ ከዛ የተሻለ አጋጣሚ አልነበረም። ደግሞም በኑሮ ደረጃ ውጪ ቢኖር ያን ያክል የሚያሻሽለው ነገር አይደለም። ምክንያቱም የገንዘብ ችግር የለበትም። ከራሱም አልፎ ለብዙ ሰዎች የሚተርፍ ገቢ ነበረው።
(ይሄንን ሁላችንም እናምናለን። እንኳንስ የአውሮፕላን እርዳት እና የታክሲ ረዳትም ዛሬ ግዜ ገቢው ቀላል አይደለም።(እዘችጋ ትንሽ ቅልድ ቀላⷅያለሁ….))
ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ሳይሆን እጅግ በጣም ጎበዝ ጭንቅላት ያለው ወጣት ነው። አብዛኛዎቹን ክፍሎች ሁለት ሁለት እያለፈ አስራ ሰባት አመት ሳይሞላው ሀይስኩል ሲያጠናቅቅ የ አስራሁለተኛ መልቀቂያ ውጤቱ ሁሉም ኤ ነበር። የጀመረውን የ አርክቴክቸር ትምህርት ትቶ ወደ ፓይለትነት የገባው ለሙያው ካለው ፍቅር የተነሳ ነው። ለኢትዮጵያ አየር መንገድም የተለየ ክብር አለው።
(ይሁን…. ይሄንንም ማመን አይቸግረንም…. ቀጥይ እታለም….)
ሃይለመድህን ሁሉንም አስታዋሽ ቤተሰቡን የሚወድና ተጫዋች ሰው ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለኛ ያለውን ፍቅር ደህነታችንን በማረጋገጥና የሚያስፈልገንን ሁሉ በመታዘዝ ቢገልጽም ከዘመድ ወዳጆቹ ጋር መገናኘትና አቆመ። የወትሮው ጨዋታና ደስተኝነቱ ቀርቶ ብቸኝነትን የሚወድ ዝምተኛ ሆነ። ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ። በሁኔታው ተደናግጠን ደጋግመን በመጠየቅ ያወቅነው ሊያጠቁት የሚከታተሉት ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ነው። ስልኩን እንደጠለፉት ያስባል፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን አይከፍተውም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ ጀምሮ ነበር። ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው። ወንድሜ ለሰዎች እርዳታ ለመድረስና የሌሎች አዳኝ ለመሆን የማይታክት ሰውንጂ እንዲህ በሚያንገበግብ ስቃይ ውስጥንኳ ለራሱ አስቦ እርዳታን የሚጠይቅ ሰው አይደለም። ሁኔታውን በደበስባሳው በታወቀበት ጊዜንኳ የሚያስፈልገውን የህክምና በማቅረብ ስላልረዳነው ቤተሰቡ ሁሉ እንደግር ሳት ይከነክነዋል።እሱ ግን እንዲህ ባለ ጥልቅ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥንኳ ለኛ አንድም ቀን ሳያስብ ቀርቶ አያውቅም።
(ውድ እህታችን  ይሄ ነገር አልመስልህ ብሎኛል።  ለምሳሌ ከላይ ካሰፈርሽው አንቅፅ ውስጥ “በሁኔታው ተደናግጠን ደጋግመን በመጠየቅ ያወቅነው ሊያጠቁት የሚከታተሉት ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ነው።” አልሽን። እንደሚያምን ነው ማለት፤ ….ግን ማንም የሚከታትለው የለም ለማለት ነው። ይሄንን በምን አረጋገጥሽ… እንዲህ አይነቱ ጭንቀትስ እንደምን ከባዶ ሜዳ ይመጣል… ሌላው፤ “የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው።” አልሽን ታድያ ወንድምሽ እና ወንድማችን አብራርቶ ያልነገራችሁን ነገር አንቺ ከየት አምጥተሽ አብራርተሽ ነገርሽን…. ?) ከዚህ በተጨማሪ አንድ አጎትሽ የሰጡት መገለጫስ ሰምተሽው ይሆን….  እሰቲ ለማንኛውም… እንስማሽ…)
ይህን የምታነቡ ወገኖች ሁሉ ዛሬ እኔ ይሄን ከምጽፍ እግዚአብሄር ምስክሬ ነው እሱ ወደነበረበት ጤናና ሁኔታ ተመልሶ እኔ ሞቼ ቢሆን እመርጣለሁ። ውሸት ከሆነ ይህንን በማድረግ የውሸቴን መልስ እንዲያሳየኝ አምላኬን እለምነዋለሁ። በኛ አገር መስሪያ ቤቶች የሰዎችን እውቀት ብቃትና ቁመና ሳይቀር ሲመዝኑ የዐይምሮ ጤንነት ሁኔታን አለመከታተላቸው እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው።
(እዝች ጋ ውሸት ከሆነ የምትለውንም ቃል ምን አመጣት ብዬ ማስቤን አልደብቅሽም።  በተጨማሪ ግን  እታልም፤ አንቺ ራስሽ ወንድምሽ እና ወንድማችን እንዲህ ያለ የዕምሮ ስቃይ ውስጥ መኖሩን ያወቅሽው ትላንት አወሮፕላን መጥለፉን ስትሰሚ ካልሆነ በስተቀረ… ቀደመሽ ብታውቂ ኖሮማ ሀክምና ቦታ ሳይሄድ ስራ ቦታ ሲሄድ ዝም አትይም ነበር። ስለዚህ “የተከበረውን” አየር መንገዳችንን መውቅስሽ አልተዋጠልኝም።) .
ወንድሜ ትናንት አውሮፕላኑ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ምን አጋጥሞት ይሆን እነዛ የሚላቸው ሰዎች ሲመለስ ጠብቀው እንደሚገሉት ዝተውበት ያንን ፈርቶ ይሆን ወይም ፓይለቱ ከጠላቶቹ ጋር በመተባበር ሊይጠቃው እንደሚችል ብማመን ሰግቶ ይሆን ሲወጣ ራሱን ለመከላከል በሩን የዘጋው ከሁለቱ አንዱ ወይም ሁለቱም እንደሆነ አምናለሁ። አስቡት በዛች ቅጽበት አለሙን በሙሉ ሊያናጋ የሚችል ምንም አይነት ራሱን ሊከላከልበት የሚችል መሳርያ ሳይዝ ይህንን ድርጊት የሚያስፈጽም ምን ነገር ሊኖር ይችላል ስዊዘርላንድ ገነት አይደለችም። የዐይምሮ ህመም ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለዚያውም በማንም ላይ ምንም ጉዳት ባልፈጸሙበትና ሊፈጽሙም ባላሰቡበት ሁኔታ ወደስር ቤት እንዲወረወሩ ህግ የሚፈቅድ አይመስለኝም። ሃይለመድህን ለህይወቱ ሰግቶ ነበር። የሰው ልጅ ሊቋቋመው በማይችል የመንፈስ ጭንቀት ገሃዱና ሃሳባዊው አለም በተዘበራረቀበት የስቃይ አለም ውስጥ ብቻውን ሲሰቃይ ነው የቆየው። በተስተካከለ የዐይምሮ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው ላይገባው ይችላል። እኔ ግን የሱን ግማሽ ባያክልም የተወሰነ ይህንን መሰል ችግር ስላለብኝ ህመሙን አውቀዋለሁ። ሁሌም በሳት እየተጠበሱ መኖር ማለት ነው
(እህቴ ሙች   እንኳ ምንም እየነገርሽን ያለው የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም፤ ይህንንም አንቀጽ ተጠርጣሪ ሆኖ አግኝቼዋልሁ። አንደኛ ነገር ርስ በርሱ የሚምታታ ሃሳብ ይዘዋል። ቅድም የሚያሳድዱት ሰዎች እንዳሉ ያምናል ያልሽን ልጅ አሁን ደግሞ የሚያሳድዱት ሰዎች ዝተውበት ይሆናል…. ስትዪን በርግጥም የሚያሳድዱት ሰዎች አሉ ወይስ ሃሳቡ የፈጠራቸው ናቸው … የሚለውን ግራ አጋብተሽናል። ሌላው እኔም ከእርሱ ባነስ መልኩም ቢሆን ይሄው ችግር ስላለብኝ ስትዪ የነገርሽን ሃሳብ ችግሩን ቤተሰባዊ ለማድርግ እነ እንትና ሆነ ብለው ያስገቧት ቃል ትመስላለች።)
ወገኖች መልዕክቴን አንብባችሁ በምትችሉት ሁሉ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ፍትህ አግኝቶ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በመጣር እንድትተባበሩን መላ ቤተሰቡ በምታምኑት ሁሉ እንለምናችኋለን! እኛም የሚያስፈልገውን የህክምና እርዳታ አግኝቶ ወደ ቀድሞው ጤናው ከተመለሰ በኋላ ለዚች አገር ባለው አቅም ሁሉ እንዲያገለግል በማድረግ እንክሳለን!
(ይሄንን መለዕክት እኔም እጋራልሁ… ሃይለመድህን አበራ የስዊዝ መንግስት ነፃ ሊለቀው ይገባል። ችግሩ ምንም ይሁን ምንም በርካታ ጥገኝነት መጠየቂያ አማራጮች እያሉት ይህንን እርምጃ የወሰደው የከፋ ነገር ቢደርስበት መሆኑ ግልጽ ነው።)
የኔ ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ ፍትህ ማጣት ብርቅ አይደለም። ባለስለጣኖቻችን የሚያድርሱብን በደል  ለአዕምሮ መታወክ ብቻ ሳይሆን ለሀገር መታወክም ይዳርጋል። ከሃይለ መድን እህት በተጨማሪም፤ አንድ አጎቱም፤  ”ከአንድ ወር በፊት ድንገት የሞቱ አጎቱ ሁኔታ ለከባድ የአዕምሮ መታወክ ዳርጎታል።” የሚል አስተያየት ለአሶሽየትድ ፕሪስ ሰጥተዋል። በርግጥም ይህ መሆኑን የስዊዝ ሃኪሞች ማረጋግጥ ከቻሉ ሃይለመድን ነገሩ ይቀልለታል። እኛም ደስ ይለናል።
ነገር ግን፤ እህቱ እና አጎቱ በተለያይ አገላለጽ፤ ምክትል አብራሪውን የአዕምሮ ህምምትኛ ነው ማለታቸው፤ እንዲሁም እህቱ ጽሁፏን ስትጀምር ግልጽ ባልሆን ምክንያት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችን እና እኛ ቀልደኞቹን ሳይቀር አጓጉል በመተቸት መጀመሯን፤ እንዲሁም የመንግስታችንን የቀደመ ልምድ ልብ በማለት እህትም ሆነች አጎት ልጁን የአዕምሮ ህመምተኛ ያሉት በእነ አጅሬ አስገዳጅነት እንደሆን እጠርጥራልሁ።
ከዚህ በፊት የ የኔ ሰው ገብሬ ቤተሰቦች እንዲሁ አይነት መግልጫ እንዲሰጡ መገደዳቸውን ማስታውሻ የያዝን ሰዎች ነን።
(ዘግ ይቶ በደረሰን ጥርጣሬ ደግሞ እህቱም እህቱ ስለመሆኗ አጎቱም አጎቱ ስለመሆናቸውም እንጠረጥራለን!(ጠረጠሩ መባላችን ካልቀረ ደገሞ እንደ እህት እና አጎት ሆነው የሚጫወቱት አቶ ሬድዋን እና አቶ በረከት ሊሆኑም ይችላሉ))
በመጨረሻም፤
እደግመዋልሁ…
ሃይለመድህን አበራ የስዊዝ መንግስት ነፃ ሊለቀው ይገባል። ችግሩ ምንም ይሁን ምንም በርካታ ጥገኝነት መጠየቂያ አማራጮች እያሉት ይህንን እርምጃ የወሰደው የከፋ ነገር ቢደርስበት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ከጎኑ ልንቆም ይገባል። ለኢትዮጵያ ተላልፎ ከተሰጠ ግን እንደተባለው አዕምሮው የታወከ እንኳ ቢሆን የሚለቁት አይመስልኝም! ሳስብው እኛ ይሄ ሁሉ ዘመን አዕምሯችን ታወኮ መቼ አውሮፕላን ጠለፍን… ብለው ቁም ስቅሉን የሚያሳዩት ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment