Translate

Wednesday, February 12, 2014

አንዲት ሀገር፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ሀይማኖት፣ ብዙ ሃሳብ ፤ ትንሽ ሂሳብ!

konso-strawberry-fields-ethiopiaአንዲት ሀገር፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ሀይማኖት፣ ብዙ ሃሳብ ፤ ትንሽ ሂሳብ!
ብዙ ሃሳብ የተባለው ፈረንጆቹ “አይዲያ” የሚሉትን እንጂ እኛ “አይ እዳ” እያልን የምንጨነቅበትን ሃሳብ ያብዛው ለማለት አይደለም። ትንሽ ሂሳብ የተባለው ደግሞ የዋጋ ንረት የሌለባትን ሀገር ለመመኘት የተቀመጠ መሆኑ ይታውቅ፤
በመጀመሪያም፤ አባቴ የነገረኝ ተረት…
አንድ ሰውዬ ነበር… ሲኖር ሲኖር ሲኖር ከዕለታት በአንዱ ቀን በጣም ራበው። ሲርበው ጊዜ መንገድ ላይ ካገኘው አንዱ የባቄላ ማሳ ዘሎ ገባ፤
ማሳው ውስጥ ቁጭ ብሎም እጁ እንደያዘለት እሸቱን ነጨት እያደረገ ከነ ቅርፊቱ ወደ አፉ ይሰደው ጀመር።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ ትንሽ ከበላ በኋላ ርሃቡ መለስ ሲልለት ጊዜ እሽቱን በቅጡ እየፈለፈለ ይበላ ጀመር። ትንሽ እንደበላም (“እንዲህ ልጠግብ ነው በሬዬን ያርድኩት…” እንዳለው ሰውዬ አይነት መጥገብ ጠገበ።) ሆዱ ሙልት ካለ በኋላም ግን መብላቱን አልተወም። እሸቱን ፈልፍሎ ከዛም ከፈለፈለው በኋላ ያለችውን ቅርፊትም ልጦ ቀስ እያለ ከውስጥ ያለችውን የባቄላ ፍሪ መብላቱን ቀጠለ።
የሰውዬውን ሁኔታ ተደብቆ በአንክሮ ሲከታትል የነበረው የማሳው ባለቤት ታድያ ካለ ፈቃዱ እሸቱን በመብላቱ አልትቆጣውም፤ ይልቅስ መከረው፤ “ወንድሜ በማሳዬ ስትገባ ጀምሮ አይቼህ ነበር፤ ርቦህ ነውና እሸቴን በላህ ብዬ አልቀየምህም። ይልቅስ ልምከርህ፤ አለው….፤ እሺ አለ በላተኛው፤ (….ሰው ማሳ ዘሎ ገብቶ በምክር መለቅቀ ከየት ይገኛል…?) መካሪወም እንዲህ መከረው… “እንደ መጀመሪያውም አይደለም። እንደ መጨረሻውም አይደለም። እንደ መካከለኛው ብላ” ብሎ አለው።
መቼለታ ስለ ብሔራዊ ቋንቋ ጥቂት አውርተን ነበር። በርካታ አስተያየቶች ደረሱኝ። ሁሉንም እያመሰገንኩ ወጋችን ግር ያላቸው ግለሰቦች እና ድርጅቶች ስለተገኙ፤ ማብራሪያ የምትመስል ነገር እንደሚከተለው እንጨምራለን። ማብራሪያ ያልናት ማረሪያ እንዳትሆንም እንፀልያለን፤
እንጸልያለን ብል ጊዜ፤ ከነገሬ ጋር የምትያያዝ አንድ ቆየት ያለች ዜና ትዝ አለችኝ፤ “መጽሐፈ ቅዳሴ በኦሮምኛ ቋንቋ ተተረጎመ” ትላለች ዜናዋ። ታዋቂው አንድ አድርገን ሃይማኖታዊ ድረ ገጽ ነበር የዘገበው። ድረ ገጹ በዘገባው፤ “ይህ መጽሐፈ ቅዳሴ በኦሮምኛ ቋንቋ መተርጎሙ አባቶች ቅዳሴን በኦሮምኛ ቋንቋ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል” ሲል ያትታል። አያይዞም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዘመናት አማርኛ እና ግእዝን ለቅዳሴ ትጠቀም እንደነበር አሁን ደግሞ በኦሮምኛ ቅዳሴ ሊጀመር መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ይነግረናል። እዝች ጋ ሲጫኑየድረ ገጹን ሙሉ ዘገባ ያገኙታል።
አንዳንድ ወዳጆቼ የብሄራዊ ቋንቋ ያለህ… ብዬ ኡ ኡ ካልኩ በኋላ አማርኛ እና ኦሮምኛን በአጥጋቢ ምክንያቶች ብሄራዊ ቋንቋዎቻችን ይሆኑ ዘንድ እውተውታለሁ ማለቴ አላጠገባቸውም። (ኧረ አለተዋጠልንም ያሉኝም አሉ) ከላይ የጠቅስነው ዘገባ ስናየው፤ ውትውታው የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች መሆኑን ያሳያል። ከዛም በተጨማሪ በርካታ ተቃዋሚ ድረጅቶች አንድነት እና ሰማያዊን ጨምሮ በፕሮግራማቸው ውስጥ አማርኛ እና ኦሮምኛ የሀገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ይሆናሉ የሚለውን ሃሳብ ማካተታቸውን ሰምቻለሁ።
በቅርቡ የግንቦት ሰባቱ ዋና ጸሐፊ ሲናገሩ እንዳድመጥናቸውም ጎንደር ያለ ተማሪ ትምህርቶቹን ለማለፍ ኦሮምኛ ማለፍ ግዴታው እንዲሆን ወለጋ ያለ ተማሪም ከክፍል ክፍል ለመሸጋገር አማርኛ ማለፍ ግዴታው እንዲሆን በማድረግ ሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ከገዛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ሁለቱን ቋንቋዎች በቅጡ ቢናገሩ ሁላችንም የምንተሳሰርብት (የአይቲ ተማሪዎች “ሊንክ” የሚሉት አንዳች መስተዋድደ “ኢንስቶል” ተደረገልን ማለት ነው።) ሲሉ ነበር። ያው ያሉትን ቃል በቃል ስለዘነጋሁት በራሴ ቃል ጻፈኩት እንጂ እንዲሁ ነው ያሉት።
የኦነጉ ጄነራል ከማል ገልቹም ይሄንኑ ሃሳብ ሲናገሩ ሰምቻቸው አውቃለሁ። ይቺ አይንቷን ማዋደጃ ሲናገሩ ያልሰማሁት ነፍሳቸውን እንዴት እንዳደረገው እንጃ እርሳቸው ብቻ ናችው።
እንግዲህ ይህንን ሁሉ መዛበሬ ለምንድነው… የተባለ እንድሆን፤ ይህ ሃሳብ የእኔ ብቻ አይደለም ለማለት ነው። የሚለው መልስ ይሆናል።
መረጃው ለሌላችሁ ወዳጆቼ እደግመዋልሁ …ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ብሄራዊ መዝሙር እና ብሄራዊ ቡድን እንጂ ብሄራዊ ቋንቋ የላትም። (ለዚህ ማመሳክሪያ ህገ መንግስቱን ማየት የሚፈልግ ካለ ኮፒ አድርጌ ለመላክ ዘግጀቴን አጠናቅቄያለሁ…ሃሃ) በህገ መንግስቱ ላይም ሆነ በሌሎች ህጎች፣ አዋጆች እና ደንቦቻችን እንኳንስ ብሄራዊ ቋንቋ ሊኖረን ይቅርና “ብሔር” የሚልው ቃል ራሱ እጅጉን ተጎሳቅሎ ነው የምናገኘው።
ህገ መንግሰቱ “ብሄራዊ መዝሙር” ሲል ስለ ኢትዮጵያ የሚያዜም ሆኖ መታውቂያ ላይ “ብሄር” ስንባል ኢትዮጵያ ያልን እንደሆን እንደ ሽብርተኛ እንታያለን። ወድያው ደግሞ፤ “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አንድ ጎል አገባ” ሲል ጋዜጠኛው ይናገራል። ኢትዮጵያ የሚባል ብሄር ከሌለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚባል ከየት መጥቶ ነው አንድ ጎል የሚያገባው…?
ለማንኛውም ብሄራዊ ቋንቋ ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት አልነበረንም። እርግጥ የፌደራሉ ቋንቋ አማርኛ (ነፍሴ) በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይነገራል። ኦሮምኛም (ነፍሴ) እንደዛው በስፋት የሚነገር የሀገራችን ቋንቋ ነው። (አማርኛ እና ኦሮምኛ ለብሄራዊ ቋንቋነት ይታጩ ብዬ የምቀውጥውም ክዚህ መነሻነት ነው።)
ታድያ እነዚህን ነፍስ የሆኑ ቋንቋዎች ከሌሎቹ ጣፋጭ ቋንቋዎቻችን በተጨማሪ ብንማራቸው እና የጋራ ማንነታችን ብናደርጋቸው “ማነው ሚለየው ሚደፍርው የኢትዮጵያ ልጅ ፍም እሳት ነው!!!” ብሎ ከዳር ዳር የሚያስተጋባ ለጠላት ግራ የሚያጋባ አንድነት ፈጠርን ማለት አይደለምን!?
እናም እላልሁ፤ በዛኛው ጽንፍ ያሉም ልብ ይግዙ፤ በዚህኛው ጽንፍ ያሉም ይውገዙ “እንደ መጀመሪያውም አይደለም፣ እንደ መጨረሻውም አይደለም፣ እንደ መካከለኛው ብላ” እንዳለው ሰውዬ፤ ይህ የተናገርነው በግራ እና በቀኝ ያሉ ጽንፎችን የሚያስማማ አማካይ ሃሳብ ነው:: ይህንን በፕሮግራማችሁ የነደፋችሁ ተቃዋሚዎች እናንት የተባረካችሁ ናችሁ!
በዚሁ አጋጣሚ የሁዳዴ ጾም መዳረሻ ላይ ለምትግኙ ክርስትና እምነት ተከታይ ወዳጆቼ አንድ ኦሮምኛ ዝማሬ እጋብዛችኋለሁ፤
አሁን ርዕሳችን ይደገማል፤
አንዲት ሀገር፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ሀይማኖት፣ ብዙ ሃሳብ ፤ ትንሽ ሂሳብ!

No comments:

Post a Comment