Translate

Tuesday, February 11, 2014

አንድ ቁምነገር፤ የብሄራዊ ቋንቋ ያለህ…!!! ( አቤ ቶኪቻው)

በነገራችን ላይ ብሄራዊ ቋንቋ የሚባል ነገር የለንምኮ… አማርኛ ለረጅም ጊዚያት የሀገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኖ አግልግሏል። አሁን ግን አማርኛ በአማራ ክልል እና በፊደራል አስተዳደሮች (አዲስ አበባ እና ድሬደዋ እንዲሁም ይሁንልን ባሉ አንዳንድ ከልሎች) ብቻ ተውስኖ ይኖር ዘንድ ተፈርዶበታል። ሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ተማሪዎች በገዛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ። እንዲሁም እንደየ ክልሎቹ ሁኔታ ‘የፌደራሉን’ ቋንቋ (አማርኛ) ከተወሰነ ክፍል በኋላ መማር ይጀምራሉ። (የፌደራል ቋንቋ ስል የፌደራል ፖሊስ ቋንቋ ማለቴ አይደለም ካነሳናቸው አይቀር ግን የእነርሱ ቋንቋ ራሱ መቀየር እንዳለበት ጠቁሞ ማልፉ መልካም ነው እስከመቼ ድረስ ቆመጥ እና ክላሽ ለመግባቢያ ቋንቋ ይጠቀማሉ… ) ሃሃ… ብለን ወደ ቁምነገራችን ስናሳልጥ፤

በኬኒያ የስደት “ኬዝ” ጋገራ
በግሌ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውን አሳምሬ እድግፈዋለሁ። በአፍ መፍቻ ቋንቋ አለመማር አቀበቱ ብዙ ነው። ለምሳሌ፤ አንድ በጉራግኛ አፉን የፈታ ልጅ በሳይንስ ትምህርት ክፍለ ጊዜ በቅጡ በማይርዳው ቋንቋ የእጅ መታጠብ ጥቅም ቢነገረው ቋንቋውን ለምዶ መምህሩ ምን እያለው እንደሆነ እስኪገባው ድርስ ፊቱን ሳይታጠብ ወደ ትምህርት ቤት ሊመጣ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ድሮ አርስናልን እድግፍ ከነበረው በላይ የምደግፈው ነገር ነው።
(እኔ የምለው አርሴ ገሰገሰች…. አሁንም ድጋፌን ለጅምርላት ወይስ አርፌ ሲቲዬን አይዞሽ… ልብል…)
ያም ሆኖ ግን ኢትዮጰያን የመሰለች ሀገር፤ እንዴት ብሔራዊ ቋንቋ አይኖራትም… ይሄን ጊዜ አንስተኛ እና ጥቃቅን የኢህአዴግዬ ካድሬዎች “ኢትዮጵያ የሚባል ብሄር ስለሌለ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ አያስፈልጋትም” ሊሉ እንደሚችሉ ይጠረጠራል ተጠርጥሮ ታድያ እንዴት ዝም ይባላል…
አሁን ‘በስራ’ ላይ የሚግኘው የኢትዮጵያ ህግ መንግስት፤ አንቅጽ አራት ላይ የኢትዮጰያ ብሄራዊ መዝሙር፤ በሚለው ርዕስ ስር “የኢትዮጰያ ብሔራዊ መዝሙር የህገ መንግስቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዘቦች በዴሞክራሲ ስርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፤ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል።” ይላል። ይህም ሕግ መንግስቱ ራሱ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መኖሩን ያመለክታል ማለት ነው።  ስለዚህ ኢህአዴግ መስተፋቅር እና መስተ ነዋይ ያስነካቻችሁ በሙሉ “ኢትዮጵያዊ ብሄርትኝነት የለም” ስትሉ ከህገ መንግስቱ ጋር እየተላተማችሁ እንድሆነ ታውቁት ዘንድ ይሁን፤ (መላተም ብርቃችን አይደለም ካላችሁንም እንግዲህ በቴስታ በሉትና የግንባራችሁን ታገኛላችሁ!)
ሀገር በብሔራዊ መዝሙር ብቻ አትኖርም በብሄራዊ ቋንቋም እንጂ… ብለን በአዲስ መስመር ስንቅጥል፤
አሁንም ህግ መንግስቱን ስናየው፤ አንቅጽ አምስት ላይ ስለ ቋንቋ ሲደነግግ፤ “ማናችውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራችዋል” ይላል… እስይ የኔ አንበሳ ብለን ስንወርድው፤ በዚሁ አንቅጽ ቁጥር ሁለት ላይ “አማርኛ የፌድራሉ ቋንቋ ይሆናል” ይላል።  እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የምንቀውጠው፤ (አራዳ “ቀወጠው” ብሎ ሲል፤ አጥብቆ ተከራከረ አለቀም እምቢኝ አለ፣ በጉዳዩ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ  ሲል ተጨቃጨቀ። የሚል ትርጉሜ ይይዛል።)
“አማርኛ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ ይሆናል” ሲል የደነገግውን ሕገ መንግስት አፍ ካለው ይናገር ዘንድ ከሌለውም በተወካይ በኩል እንዲመልስልኝ ሁለት ጥያቄዎችን እጠይቀዋለሁ፤ አንደኛው አማርኛ ብቻውን ምን እዳ አለበት እና ለብቻው የፌደራሉ ቋንቋ ይሆናል… የሚለው ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ፤ ብሄራዊ መግባቢያ ቋንቋችንስ ምንድን ነው… የሚል ይሆናል።
እንደ ሀገር የሚያስትሳስርን የሚያግባባን ሁለትስ፣ ሶስትስ ቋንቋ ቢኖርን የሚጎዳው ማነው… በባቢሎን ዘመን ስራ ፈቶች እግዜርን ላይ ለመድርስ ግንብ ሲገነቡ የልባቸውን ክፋት ያየው አምላክ ቋንቋቸውን ደበላልቀው የሚል ሃይማኖታዊ ትምህርት ሰምቼ አውቃለሁ፤ ታድያ መንግስታችን በልባችን ምንም ክፋት የሌለብንን ዜጎቹን በቅጡ ተግባብተን በቅጡ ተባብረን ትልቅ ሀገር ብንገንባ ምን ይጎድልበታልና ብሔራዊ ቋንቋ አሳጣን…. (የጥያቄ ምልክት በብዛት)
እናም፤ ጆሮ ያለው ይስማ አንድ የሚያደርጉን ቋንቋዎች ያስፍልጉናል። ሶስት እና አራት ቋንቋዎቸን ብብሔራዊ ቋንቋ ደርጃ የሚጠቅሙ ሀግሮች ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱበትም። ስለዚህ እየተግባባን እንድንገነባ ዛሬውኑ ብሔራዊ ቋንቋዎቻችንን አሳውቁን እና  አስትምሩን፤ የዚህ ቁምነገር ፀሀፊ፤ አንጅት ላይ ጠብ በሚሉ አጥጋቢ ምክንያቶች፤ ቢያንስ አማርኛ እና ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ሆነው ግልጋሎት መስጥት እንዲጅምሩ በብርቱ ይውተውታል።
ተቃዋሚዎች ሰምታችኋል!
ኢህአዴግም ሰምተሻል!

No comments:

Post a Comment