Translate

Tuesday, October 29, 2013

የጤና ጥበቃን ሙስና ማን አቤት ይበለው?


Author, Demesew Desta
ደምሰው ደስታ
የፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የተካሄደን የሙስና ምዝበራ በሪፖርቱ መጠቀስ ያለበትን ሳይጠቀስ ማለፉ አግራሞትን አጭሮብኛል። ነገሩ እንዲህ ነው ለረጅም አመት በመድሀኒት ዘርፍ የኢትዮጵያ መድሀኒትና የህክምና መገልገያ እቃዎች በማስመጣት ለመላው ሀገሪቱ በማከፋፈል (ፋ.ር.ሚ.ድ) በመባል የሚታወቀው ድርጅት ጉለሌ ጳውሎስ ሆስፒታል ፊት ለፊት የሚገኝ መስሪያ ቤት ሲሆን በሀገሪቱ በሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ቅርንጫፎች ያሉትና በጣም ጥሩ አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚሰጥ ተወዳዳሪ የሌለው መስሪያ ቤት ነበር።

ሆኖም ህወሀት መራሹ መንግስት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ጥሩ በሚባል መልኩ ስራውን ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2001 የመስሪያ ቤቱ ስም እንዲቀየርና ተጠሪነቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር ሆኖ የሀገሪቱ የእርዳታም ሆነ በግዢ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለተለያዪ ለጤና ተቋማት መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በማቅረብ ስሙም የመድሀኒት አቅርቦትና ፈንድ ኤጀንሲ (መ.አ.ፈ.ኤ) ሆኖ ከዚህ ቀደመም የመንግስት የልማት ድርጅት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ሙሉ በሙሉ ወደ መንግስት ድርጅት እንዲቀየር ተደርጓል።
የዚህ ጽሁፍ አላማ የመስሪያ ቤቱ አወቃቀርና ስለሚሰጠው አገልግሎት ለማስቃኘት ሳይሆን በመድሀኒት አቅርቦትና ፈንድ ኤጀንሲ ተቋም ውስጥ የተፈጸመን የሙስና ተግባር የጸረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርት መንግስታዊ የሆኑ ድርጅቶች በተለያየ ምክንያት መመዝበራቸውን ሪፖርቱ አንድን ብቻ የሀዋሳ ቅርንጫፍ የመ.አ.ፈ.ኤ በእምነት ማጉደል ወንጀል ግምቱ ብር 1 ሚሊየን 7 መቶ ሺ የሆነ መድሀኒት ተመዝብሮ ለግል ጥቅም መዋሉ በሪፖርቱ ገልጿል።
ሆኖም ይህ የጸረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ የሀዋሳን ቅርንጫፍ ነጥሎ ቢጠቅስም ነገር ግን በሀላፊነት የተጠየቀ አለመኖሩ እራሱ አነጋጋሪ ነው። የሚገርመው ደግሞ የአዲስ አበባው ዋናው መስሪያ ቤት እና የጅማው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በባሰ ሁናቴ መመዝበሩ የተለያዩ መረጃዎች ስላሉኝ ቀጥሎ በዝርዝር እሄድበታለው።
የዚህ የሙስና ተግባር ባለቤቶች በመጀመሪያ ፋ.ር.ሚ.ድን ወደ መ.አ..ፈ.ኤ ለመቀየር ከመብቃቱ በፊት በሁሉም ክልል ያሉት የመድሀኒት ማስቀመጫ መጋዘኖች በጣም በጥሩ ሁናቴ የተያዙ እንዲሁም በሚገባ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው እኔው እራሴ ምስክር ነኝ ምክንያቱም በአንድ ወቅት እዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ እሰራ ነበር።
ሆኖም ይህ ዘረፋ በሶስቱም መስሪያ ቤት የተካሄደ ቢሆንም  የሀዋሳውን ብቻ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በሪፖርቱ መጥቀሱ የሚገርም ነው። ምክንያቱም አንድ አይነት በሚመስል ሁኔታና በተቀነባበረ መልኩ በዋናው መስሪያ ቤት አዲስ አበባ በሚገኘው እና በቅርንጫፍ ጅማና ሀዋሳ ዘረፋ ተካሂዶባቸዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የነበሩት ዶክተር ቴውድሮስ አድሀኖም ጨምሮ በተለያዪ የጤና ዘርፍ ላይ ያሉ ሀላፊዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት ደብዳቤ ለዘረፋው የመንግስት ተገን ያላቸው ግለሰቦች ይህንን ደብዳቤ በመያዝ ወደ መ.አ.ፈ.ኤ ድርጅት ለዘረፋው የሚተባበሯቸው የስራ ሀላፊዎች እነሱም፤
1, አቶ ሀይለስላሴ ቢሆን (የመ.አ.ፈ.ኤ ዋና ዳይሬክተር)
2, አቶ የማነ ብርሀን ታደሰ (የመ.አ.ፈ.ኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር)
3, ወ/ሮ ዝናብ ተክሊት (የጉለሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ)
4, ወ/ሮ ሶፋኒት (የምግብና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ሀላፊ)
ጋር በመሆን በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች መዝብረዋል።
እነኚ ዘራፊዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት ደብዳቤና የመድሀኒቱ ይዘትና መጠን የሰፈረበት ሰነድ በእጄ ላይ ይገኛል ሆኖም ይህንን መረጃ ላቀበሉኝ ሰዎች ደህንነት ስል ላልተወሰነ ጊዜ ከማውጣት ተቆጥቤአለው።
እስቲ ስለ ዶክተር ቴውድሮስ አድሀኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስተር በነበረበት ወቅት ያሳይ የነበረው ታይታ (showing) ጥቂት ነገር ልበላቹ። ወቅቱ ገና ተሹሞ እንደመጣ በሀገራችን ላይም የሞባይል ስልክ አገልግሎት ጥቅም ላይ ውሎ ነበር እናም ይህ ሚኒስቴር ያንን ወቅት በመጠቀም ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የጤና ሰራተኛ ቅሬታ ወይም ችግር ካለ በሞባይል ስልኩ ደውሎ ቅሬታውን እንዲያቀርብ ፍቃድ ቢሰጥም ስልኩ ግን ለታይታ እንጂ የእውነት አገልግሎት ለመስጠት የቀረበ አልነበረም።
ለምሳሌ በዛህ ወቅት የጳውሎስ ሆስፒታል ዶክተሮች አንድ የወያኔ ካድሬ ተነስቶ የሰአት ፊርማ ካልፈረማቹ በሚል አስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጦባቸው ዶክተሮቹም ቅድሚያ ህሙማንን መጐብኘት ይቀድማል ወይስ ፊርማ ጋር መሰለፍ በሚል ትልቅ አለመግባባት ተከስቶ ነበር። ይህን ጉዳይ ወደ ሚኒስቴሩ ጋር ቅሬታቸውን ለማሰማት በተቀመጠላቸው ስልክ ቢደውሉ እንዲሁም በአካል ቢሄድም መልስ ሳያገኙ ቀርተዋል።
ሌላው ደግሞ ሚኒስቴሩ የዳቦ ስሞች በማውጣት ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ጤና ጥበቃ ሲሰራበት የነበሩትን ስሞች ፕራይመሪ ሀልዝ ኬርን ወደ ጤና ኤክስቴንሽን፤ ጤና ረዳትን ወደ ጤና ሰራዊት የመሳሰሉት በማለት ስም ቀያየረ እንጂ በፊትም የነበረ ፕሮግራም ነው። አሁን ደግሞ በቲወተር ተያይዞታል። ይህ ሁሉ የታይታ ምልክት ዶክተሩ የራሱን ስም ከመገንባት ውጪ በጤናው ዘርፍ ላይ ምንም ያመጣው ለውጥ  የለም።
በእርግጥ ለህወሀት ትልቅ ስራ ሰርቶላቸዋል ይህም በጤና ጥበቃ ስም የሚመጣውን ማንኛውም የእርዳታ ገንዘብና መድሀኒቶች ወደ ህወሀት ድርጅቶች ካዝና እንዲገባ አድርጏል፣የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ባለቤት ወ\ሮ አዜብ መስፍን በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ ላይ የሚመደበውን ከፍተኛ የውጭ በጀት እንድትመዘብር ሁናቴዎችን አመቻችቶላታል፣ የጤና ጥበቃ ሰራተኞችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአስገዳጅ ሁናቴ የወያኔ አባል የማድረግ ስራ ሰርቷል እና በዙሪያው ከአንድ ዘር በተውጣጡ ግለሰቦች በጤና ጥበቃ ሀላፊነት ላይ አስቀምጧል።
በመቀጠል በዋናነት ስለተነሳሁበት የሙስና ዋና ተዋናይ ስለሆነው አቶ ሀይለስላሴ ቢሆን ላስቃኛቹ። ለ20 አመታት ያህል ይህ ግለሰብ በመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ በሀላፊነት የቆየ ሲሆን በተለያየ ጊዜ ከህወሀት ድርጅቶች ጋር መድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች በህገ ወጥ መልኩ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ደጎስ ያለ ገንዘብ ሲመዘብር የቆየ ነባር የህወሀት ታጋይ ነው።
ይሁንና የጸረ ሙስና ኮሚሽኑ በዚህ ይብቃህ ብሎ ሳይከሰው አሁንም በሀላፊነት መ.አ.ፈ.ኤ በዋና ዳይሬክተርነት በመምራት ለህወሀት ድርጅቶች ለሆኑ የመድሀኒት አስመጪዎችና የመድሀኒት ፋብሪካዎች በህገ ወጥ የጨረታ አሰራር መድሀኒቶችን በግዢ መልክ ለ መ.አ.ፈ.ኤ እንዲያቀርብና ያለማንም ከልካይነት የመስሪያ ቤቱን ገንዘብ ያለ አግባብ በመጠቀም ላይ ይገኛል።
ይህ ግለሰብ በአንድ ወቅት እንደሰማነው እራሱ ዶክተር ቴድሮዎስን እንደሚያዝ እና የፓለቲካ ስውር እጅ ያለው በጤናው ዘርፍ ያሉትን ከፍተኛ የሙስና ተግባራት በመሪ ተዋናይነት የሚመራ ነው። ይህንን ትልቅ ዘረፋ የሚፈጽመው ግለሰብ የሚያስቆምም ሆነ ወደ ህግ የሚያቀርበው አለመኖሩ ምን ያህል ሀገራችን ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር እጦት ውስጥ እንዳለች ማሳያ ነው።
ቁም ነገሩ ተጠቃሎ ሲታይ የህዝብና የመንግስት ንብረት ያለ አግባብ ተመዝብሯል ተሰርቋል ስለዚህ ለፓለቲካና ለተለያዪ ማህበራዊ ጉዳዮች በጋራ እንደምንቆመው ሁሉ ያለአግባብ የሚመዘበሩ የሀገሪቱ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ዘረፋ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትና እንዲሁም በያለንበት ሙሰኞችን ማጋለጥ የዜግነት ግዴታ ነው።
ቸር እንሰንብት።

No comments:

Post a Comment