Translate

Monday, October 14, 2013

የሀገሩን ችግር ሁሉ ለኦሮሞ ልጆች ብቻ እየሰጠ ሆድ የሚስብሰን ተስፍሽ… ተስፋው ምን ይሆን!

የሀገሩን ችግር ሁሉ ለኦሮሞ ልጆች ብቻ እየሰጠ ሆድ የሚስብሰን ተስፍሽ… ተስፋው ምን ይሆን!
መቅድም
ውድ የድረገጻችን ተከታታዮች ራሴን አሻሽላለሁ ብዬ ትምህርት ጀመሬ ስጠፋ ጊዜ ራሴን ያሸሸሁ መስሏችሁ ምነ ነካህ… ብላችሁ መጨነቃችሁን በተለያየ መልኩ አድርሳችሁኛል፤ ለተጨነቃችሁ እንደተጨነቃችሁልኝ አንድዬ ይጨነቅላችሁ!!! ብዬ መመረቅ እወዳለሁ፤ እነሆ ዛሬ በወዳጃችን ተስፍሽ ማስታወሻ ምክንያት ተከስቻለሁ አንብቡልኝማ፤
OromoWomanበ1992 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ማዕከላዊ ስታስቲክስ የሚባል መስሪያ ቤት እሰራ ነበር፡፡ ያኔ “ፈላ” ነበርኩ፡፡ በምሄድባቸው የገጠር ቀበሌዎች የሚያገኙኝ እናቶች በሙሉ መጀመሪያ የሚጠይቁኝ “እናት አለችህ…” ብለው ነበር፡፡ “አዎ” ስላቸው፤ “እንዴት አምና ላከችህ…” ብለው ቀጣይ ጥያቄ ያነሱ ነበር፡፡ አባቶቹም፤ “ይቺ እሳት የሆነች ልጅ” እያሉ የሚያደንቁኝ ከጩጬነቴ ጋር እያያዙ ነበር፡፡  እንደውም ይፋት ውስጥ የሚገኙ የዳውድ አምባ ቀበሌ ሰዎች፤ “በስምንተኛው ሺህ ሽንብራ ጥላ ስር ሆኖ የሚፈርድ ዳኛ ይመጣል” የተባልከው አንተ ነህ ይሉኝ ሁሉ ነበር፡፡ (ለእነርሱ የመንግስት ሰራተኛ ሁሉ ዳኛ ነው) …አስቡትማ የሽንብራን ተክል እንደዛፍ ጥላ የምጠለልበት ምን ያህል ሚጢጢ ብሆን እንደሆነ….!
ታድያ በዛን ወቅት አብዬ ዘውዴ የነገሩኝ መቼም አይረሳኝም፡፡
ለስራ አብዬ ዘውዴ ያሉበት ቤት ጎራ ስል ዕለቱ ሰንበት ነበርና በርካታ ሽማግሌዎች እና ሙሉ ሰዎች ተሰብስበው ወግ ይዘው ነበር፡፡ ታድያ ከመንገድ መሪዬ “ሚሊሻ”  ሙሉጌታ ጋር ሆኜ እነ አብዬ ዘውዴን ያሉበት ስደርስ “ኖር” ብሎ ከመቀመጫው ያልተነሳው ራቁቱን መሬት ላይ ቁጭ ብሎ ሲጫወት የነበረው ህፃኑ የአብዬ ዘውዴ የልጅ ልጅ ብቻ ነበር፡፡
እኛም በአካባቢው ባህል መሰረት በእግዜር ብለን ሰዎቹ ብዙ እንዳይቆሙ ፈጠን ብለን ተቀመጥን፡፡ እኔ የተቀመጥቁት ከአብዬ ዘውዴ አጠገብ ነበር፡፡
“ከአዲሳባ መምጣትህን ሰምተናል፡፡ መንግስት እንዲህ እንዳንተ ያሉ አአንድ ፍሬ ልጆችን አምኖ ስራ ብሎ መላኩ ይገርማል” አሉኝ፡፡

እኔም አንድ ፍሬ አለመሆኔን ለማስረዳት ጥረት አደረግሁ፡፡
በጨዋታ መሃል ታድያ አብዬ ዘውዴ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ጠየቁኝ፡፡
“እኔ የምልህ ጋሽ አበበ” አሉኝ…
አቤት አብዬ ዘውዴ
“እናንተ ከአዲሳባ ስትመጡ እኛ ህፃን አዋቂ ሳንል አክብረን ጋሼ ብለን ጠርተን ኖር ብለን ተነስተን በአክብሮት እና በእንክብካቤ እናስተናግዳችሁ የለም እንዴ… ”
አረ በደንብ እንጂ አብዬ በእውነቱ እግዜር ያክብርልኝ እንጂ ሌላ ምን እላለሁ… አልኩ የምለው ጠፍቶኝ፡፡
“ቆይማ… እስቲ ልጠይቅህ ታድያ እኛ አዲሳባ ስንመጣ ምነው እንዲህ አትንከባከቡን… ምነው እንዲህ አታከብሩን ምነው… እስቲ ንገረኝ!” አሉኝ፡፡
አረ እናከብራለን አብዬ ዘውዴ… ብዬ ለክፍለ ከተማዬ ልከራከር ቃጣኝ፡፡
“የለም የለም…. እርግጥ አንተ እንዳየንህ ጥሩ ልጅ ነህ ነገር ግን ብዛቱ አዲሳቤ ምን እንደበደልነው እንጃ የገጠር ሰው ሲያይ በንቀት ነው፡፡ ትልቅ እንኳ ቢሆን፣ በሀገሩ የተከበረ እንኳ ቢሆን፣ አንቱ የተባለ እንኳ ቢሆን፣ ምን ብርቱ ገበሬ ቢሆን፤ አዲሳቤ ሲጠራው “አንተ” ብሎ አቃሎ ነው፡፡ አረ ጭራሽ እናንተ ዘንድ “ገበሬ” ማለት ስድብ ነው አሉ… ለመሆኑ ምን በድለናችሁ ነው… አርሰን ባበላ ገበሬን የስድብ ቃል ያደረጋችሁት…  አረ ምን አጥፍተን ነው ባላገር እያላችሁ የምትሰድቡን… ምን አጥፍተን ነው…? እስቲ ታውቀው ካለህ ንገረኝ…”
ብለው አፋጠው ያዙኝ፡፡
መልስ አልነበረኝም፡፡
የተስፋዬ ገብረአብ መፅሃፍ ላይ ያለችውን “ጫልቱ እንደ ሄለን” ን አነበብኳት፡፡ ተስፍሽ መፅሃፉን በነፃ ለመበተኑ ምክንያት ይቺ ምዕራፍ ከመጽሀፉ ትውጣ ብለው አሳታሚዎቹ ስለጠየቁ መሆኑን ነግሮናል፡፡ እነርሱም አበዙት፡፡ በሰለጠነ ሀገር ቁጭ ብለው የሰው ስራ ሳንሱር ማድረግ ነውር አይደለም እንዴ! እነዚህ አታሚዎች በርግጠኝነት ድሮ ኩራዝ አሳታሚ ሲሰሩ የነበሩ እና የሳንሱር ስራ ልምዳችን ከንቱ ከሚቀር ብለው የሚተጉ መሆን አለባቸው፡፡
የተስፋዬ ገብረአብ ጫልቱ ሚዴቅሳን ታሪክ ካነበብኩ በኋላ ደግሞ ተስፋዬም አበዛው ብያለሁ፡፡
“ጫልቱ” ስሟ “ሄለን” ከተባለ ወዲህ፤ “አዲሳባዎች ይሄ ስም ምን በደላቸው…” ብላ አጥብቃ ስታማርር ተስፋዬ ያስነብበናል፡፡ አማርኛዋም በኦሮምኛ ቃና የተላቆጠ በመሆኑ ስትሸማቀቅ ያሳየናል፡፡ አረ እንደውም የሆነው ቦታማ የጫልቱ  አክስት፤ “አማርኛሽን እንደምንም ብለሽ ካቀላጠፍሽ ንቅሳትሽ ችግር የለውም ምክንያቱም ጎንደሮችም ይነቀሳሉ” ብለው ስለ ተስፋዬ ሲናገሩለት አነበብኩ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ…. የጎንደር ንቅሳት እና የኦሮሞ ንቅሳት በአዲሳቤዎች የተለያየ ቦታ ነው እንዴ የሚሰጠው!???
ይሄኔ ነው ተስፍሽ አበዛው ያልኩት፡፡
እውነቱን ለመናገር አብዬ ዘውዴ በፅኑ እንደወቀሱኝ የአዲሳባ ሰው ባላገር አያከብርም፡፡ ኦሮሞም ይሁን አማራ ትልቅም ይሁን ትንሽ ወንድም ይሁን ሴት ጫልቱም ትሁን ትንቧለል ብቻ ከባላገር ከመጡ ለአዲሳቤ መቀለጃ መሆናቸው ነው፡፡
በርካታ “ዙሪያሽወርቆች” በአዲሳቦች ተረብ የተነሳ ወርቅ የሆነ ስማቸውን ትተው ሜሪ ተብለዋል፡፡ በርካታ “ጃለሌዎች” በአዲሳቦች ፉገራ የተነሳ ፍቅር የሆነ ስማቸውን ቀይረዋል፡፡
አዲሳቤ ተረብ ይወዳል አንዳንዴ በሀገሩ የተከበረ ሰው ባላገር ስለሆነ ብቻ በአዲሳቤ ዘንድ የተቀበረ ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ አሁን አሁን ሻል እያለው ቢሆንም ጨርሶ መጥፋቱን እንጃ…
በነገራችን ላይ እኔ ድል በትግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር ጓደኞቼ በሙሉ የሚጠሩኝ በአባቴ ስም “ቶላ” እያሉ ነበር፡፡ ሲጀምሩት በአባቴ ስም ማሾፋቸው ነበር፡፡ በበኩሌ አንድም ቀን ከፍቶኝ አያውቅም፡፡ በምትኩ እኔም ጓደኞቼን በአባታቸው ስም ነበር የምጠራቸው፡፡ ለምሳሌ፤ “ጎንባ” የምንለው ልጅ ነበር፡፡ አሁንም ለምሳሌ “ብርመጂ” የምንለውም ልጅ ነበር… አሁንም ለምሳሌ “ብርሌ” የምንለው ልጅ ነበር፡፡ እነርሱም ሌሎችን በአባት ስም እየጠሩ አንድ ሰሞን በአባት ስም መጠራራትን ፋሽን አድርገነው ነበር፡፡ በአዲሳባ የኦሮሞም ይሁን የአማራ ለየት ያለ ስም ከተሰማ ምን ማለት ነው ብሎ ከመመራመር አንስቶ እስከ ማንጓጠጥ መድረስ ብርቅ አይደለም፡፡ ተስፋዬ ግን ይሄንን ለኦሮሞ ልጆች ብቻ የተሰጠ የአዲሳቦች ቁጣ አድርጎ ያስነብበናል፡፡
እኔ የምለው የሀገሩን ሁሉ ችግር የኦሮሞ ልጆች ብቻ ችግር እንደሆነ አድርጎ እየፃፈ ሆድ የሚያስብሰን ምን ተስፋ ሰንቆ ይሆን!

No comments:

Post a Comment