Translate

Thursday, February 14, 2013

በአልቃይዳ ሰበብ ቻይናን መቆጣጠር


በአልቃይዳ ሰበብ ቻይናን መቆጣጠር

የኦባማ አስተዳደር መጪው የአፍሪካ ዕቅድ
us china
የአገራቸውን አጠቃላይ ሁኔታ እና መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል፤ የአገራቸውን የወደፊት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ … ሁኔታ እንዲሁም አሜሪካ በቀጣይ ዓመታት የምትከተለውን የአጭርና የረጅም ጊዜ የውጪ ፖሊሲ ዕቅድ በተመለከተ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማክሰኞ ምሽት ለምክርቤቱ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኦባማ በርካታ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ አፍሪካና ቻይናም የንግግራቸውን ሙሉ ቀልብ የሳቡ ነበሩ ባይባልም ሳይጠቀሱ አልታለፉም፡፡ በተለይ ስለአፍሪካ እንዲህ ብለዋል፤-
‹‹… የተለያዩ አፍቃሪ የአልቃይዳ ወኪሎችና አክራሪዎች ከአረብ ምድር እስከ አፍሪካ ብቅ እያሉ መጥተዋል፤ እነዚህ ቡድኖች ሊያመጡ የሚችሉት አደጋ እንደዚያው እያደገ መጥቷል፡፡ ይህንን አደጋ ለመቋቋምም በአስር ሺዎች የሚጠጉ ልጆቻችንን በመላክም ሆነ አገራትን መቆጣጠር አያስፈልገንም፡፡ ይልቁንም እንደ የመን፤ ሊቢያ እና ሶማሊያ ያሉት አገሮች የራሳቸውን ደኅንነት እንዲያጠናክሩ እንረዳቸዋለን፤ በማሊ እያደረግን እንዳለነው አሸባሪዎችን እየተዋጉ ያሉትን ወዳጆቻችንንም እንደግፋለን፡፡ እንደአስፈላጊነቱም ባለን አቅም ሁሉ በአሜሪካውያን ላይ አደጋ ሊጥሉ በሚችሉ አሸባሪዎች ላይ ቀጥተኛ እርምጃ እንወስዳለን፡፡››
የማሊ ጉዳይ
የፈረንሣይ ወታደሮች ባማኮ ማሊ አየርማረፊያ (ፎቶ: ሬውተርስ)
በአፍሪካዊቷ ማሊ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ አሸባሪነትን ማክሸፍ አለብን ብለው የተነሱት ምዕራባውያን ማሊን ከተለያየ አቅጣጫ እያዋከቧት ይገኛሉ፡፡ የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጦር በመላክ ውጊያውን እየመራች ነው፡፡ ሁሉም እየተጫወቱት ያለው ሙዚቃ ‹‹በአሸባሪነት ላይ ጦርነት ከፍተናል›› የሚል ነው፡፡
እንግሊዝ ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ቢፈጅም በዚሁ መቀጠል እንዳለበትና አስፈላጊውም ሁሉ መስዋዕትነት መከፈል አንዳለበት በየሚዲያው እያስተጋባች ትገኛለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ዴቪድ ካሜሮን የማሊው ቀውስ ‹‹ወራትን የሚጠይቅ ምላሽ ሳይሆን ዓመታትን እንዲያውም አስርተ ዓመታትን የሚጠይቅ›› እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ የአገራቸውን ሃሳብ በመደገፍ የብሪታኒያ ልዩ ኮማንዶ ወደ ማሊ በመሄድ የፈረንሣይን ጦር የሚያግዝ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሰው ዓልባ የቦምብ ጥቃትና የአየር ላይ ስለላም ታካሂዳለች፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አሜሪካም ለጦርነቱ ሙሉ ድጋፍ እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ዋሽንግተን ፖስት በቅርቡ እንደዘገበው የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ከፈረንሣዩ አቻቸው ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት በአፍሪካ የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ዕዝ ማዕከል (አፍሪኮም) ለፈረንሣይ የጦር አውሮፕላኖች አየር ላይ ነዳጅ የመሙላት ድጋፍ እንዲሠጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ እንዲሁም አሜሪካ ከቻድና ቶጎ ወታደሮችን በማጓጓዝ ተግባር ላይ እንደምትሰማራ ታውቋል፡፡
ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኦባማ በማሊ የሚገኙ አክራሪዎችን ለመዋጋት እንዲያስችል በሚል የአሜሪካንን ምክርቤት (ኮንግሬስ) 32ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ጥያቄ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በማሊ ለሚገኘው የፈረንሣይ ጦር ከምትረዳውና ከምትሰጠው ድጋፍ ውጪ መሆኑ ነው፡፡
የፈረንሣይ የጦር ሄሊኮፕተሮች በማሊ ክልል ከአየር ላይ የሚያደርጉትን ጥቃት ቀጥለዋል፡፡ መጠለያና መሸሸጊያ የሌላቸው ንጹሃን በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ማሊያውያን በየጊዜው እያለቁ ይገኛል፡፡ በጥር ወር መገባደጃ አካባቢ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት የዘገበው የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ እንዳለው ከአየር በተካሄደ ጥቃት 11 ሰዎች በአንድ ጊዜ ሲገደሉ አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡ የዓይን ምስክር ጠቅሶ የዘገበው ጋዜጠኛ ከሟቾቹ ውስጥ ህጻናት እንደሚገኙበትም ተናግሯል፡፡
አሸባሪን በመዋጋት በቻይና ላይ መዝመት
ምንም እንኳን ምዕራባውያን በማሊም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚያካሂዱት የቀጥታ ወረራ ከአሸባሪነት ጋር ለማያያዝ ቢሞክሩም ሁኔታው ግን ሌላ ትርጉም እየተሰጠው መጥቷል፡፡
(Photo: thenakedconvos.com)
በቅርቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የለቀቁት ሒላሪ ክሊንተን በአንድ ወቅት ሲናገሩ ‹‹የእስያን ዕድገትና ታታሪነት መግታት የአሜሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚና የስትራቴጂ ፍላጎት ነው›› ብለው ነበር፡፡ በዚህ ንግግራቸው ‹‹እስያ›› ብለው በደፈናው ይጥቀሱት እንጂ ዋንኛ የንግግራቸው ዓላማ ቻይና ላይ ያተኮረ እንደሆነ በርካታ የአሜሪካንና የቻይናን የበላይነት እሽቅድምድም የሚያጠኑ የሚናገሩት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ቻይና ከአፍሪካ ጋር እየመሠረተች ያለው ግንኙነት እየጨመረ ብቻ ሳይሆን እየረቀቀም መጥቷል፡፡ ቀድሞ የምዕራብ አሸርጋጅ የነበሩ የአፍሪካ አምባገነኖች በአሁኑ ወቅት ከኮሙኒስት ቻይና ጋር በንግድና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በአፈና፣ በስለላ እንዲሁም በሙስና እጅና ጓንት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በርካታዎቹ መሪዎች አፍቃሪ ምዕራብ ለመሆን ቢሞክሩም የኮሙኒዝም አራማጅ እንደመሆናቸው የቻይና ወዳጅነት በውጭ ከሚታየው በላይ ውስጣቸው የዘለቀ እንደሆነ በብዙ ፈርጁ እየተመሰከረ ያለ ሁኔታ ነው፡፡
በተለይ ከስድስት ዓመት በፊት ‹‹የቻይና እና የአፍሪካ የትብብር መድረክ›› በማለት ቻይና ወደ ሃምሳ የሚጠጉ መሪዎችንና ሚኒስትሮችን በቤጂንግ በመጥራት ታላቅ ስብሰባ ካካሄደች ወዲህ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ጀመረች፡፡ ወዲያውም የአፍሪኮም ኅልውና ይፋ ሆነ፡፡ ዓላማውም በውጭ ከሚታየው ሌላ በዋንኛነት ቻይና በአፍሪካ የምታደርገውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጽዕኖ መከታተል እንደሆነ እምብዛም የተሰወረ አልነበረም፡፡
ቻይና ግን በበኩሏ በአፍሪካ ያላትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀጠል አቶ መለስን ጨምሮ በርካታ ቀን ምዕራባዊ ማታ ኮሙኒስታዊ የሆኑ መሪዎችን ማሽሞንሞን ቀጠለች፡፡ የሙሉ ቀን የቻይና ወዳጅ ለማድረግም በሁሉም ዘርፍ እንቅስቃሴዋን ገፋች፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ቻይና በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ማስፈጸሚያ የሦስት ዓመት ዕቅድ በማውጣት ሦስት ቢሊዮን ዶላር መደበች፡፡ ይህም ቻይና አስቀድማ ከመደበችው ሦስት ቢሊዮን ብድርና ሁለት ቢሊዮን የውጭ ንግድ ዱቤ ሌላ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሁ ጁንታዖ በወቅቱ ስምንት የአፍሪካ አገራትን በጎበኙ ጊዜ ያስታወቁት ጉዳይ ነበር፡፡
ቻይና በዚህ አልተገታችም፤ በ2003 መገባደጃ ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ወደ 170ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ አፍሪካ ለቻይና ኢንዱስትሪዎችን የምትልከው ግብዓት ከ5.6 ቢሊዮን ዶላር ወደ 93ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ በሐምሌ 2004ዓም ደግሞ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ቻይና ለአፍሪካ አገራት ልትሰጥ ያሰበችውን ብድር በእጥፍ በማሳደግ 20ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መወሰኗን አሳውቃለች፡፡
ይህ እጅግ አሳሳቢ የሆነው ቻይና በአፍሪካ ላይ እያደረገች ያለው ተጽዕኖ ምዕራባውያን በዝምታ የሚያልፉት አይደለም፡፡ በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ጆን ኬሪ በአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክርቤት ለጥያቄ በቀረቡ ጊዜ በተለይ የቻይና እና የአፍሪካን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገሩ ‹‹ቻይና በመላው አፍሪካ ተሰራጭታለች – እውነቴን ነው የምለው በአፍሪካ በሙሉ! በመዓድንና በሌሎች … ጠርታችሁ በማትዘልቁት መስኮች በሙሉ የረጅም ጊዜ ስምምነቶች እየፈረመች ትገኛለች፡፡ እኛ ደግሞ ከጨዋታው ውጪ የሆንባቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ፤ እንደዚህ ማለቱን ባልወደውም፤ ወገኖቼ በጨዋታው መሳተፍ አለብን›› ብለው ነበር፡፡ አሜሪካና ምዕራባውያን ባጠቃላይ ወደ ጨዋታው ለመግባት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡
ይህ ደግሞ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ‹‹በአሸባሪነት ላይ ጦርነት›› የሚል የሽፋን ስዕል ሲሰጠው ብቻ ነው፡፡ በአፍሪካ ይህንን የሽፋን ስዕል የመጽሐፋቸው መለያ ያደረጉ አገራት ጥቂት አይደሉም፡፡ መንገዱ ሲጨልምበት ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ጊዜያዊ ጥቅሙን ብቻ በማየት የሚጓዘው ህወሃት/ኢህአዴግ አገራችንን በዚህ ሽፋን ውስጥ ካስገባትና የቅርብና የሩቅ ጠላቶች በግድ ከፈጠረልን ቆይቷል፡፡ ዞር ብሎ ደግሞ ከቻይና ጋር ተጋብቷል፡፡
‹‹ባለራዕዩ›› መለስ ለሁለቱም ታዛዥና ታማኝ ሆነው የትኛውን አብልጠው እንደሚታዘዙና ለየትኛው እንደሚገዙ ውሉን ሳይዙ አገራችንን ውል አልባ አድርገው አልፈዋል፡፡ የኅልፈታቸውም መነሻ ይህ ነው ባይባልም ከጅምሩ ኮሙኒስታዊ መሆናቸውና ዞረው ወደ ማዖ አገር ፊታቸውን ማቅናታቸው የምዕራባውያን ወዳጅ ሆነው እንደማይቀጥሉ ጉልህ ማስረጃ ነበር፡፡ ምርጫቸውን ሳያስተካክሉ ተሰናበቱ እንጂ፡፡
የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካና የቻይና ፍጥጫ በአፍሪካ ዙሪያ በዚህ መልኩ የጎሪጥ በመተያየት የሚቀጥል አይሆንም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኞች በተለይ በፕሬዚዳንት ኦባማ ሁለተኛ የአስተዳደር ዓመታት ወደ ተጨባጭ ደረጃ እንደሚያድግ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ አፍሪካ የአሜሪካና የቻይና ሁሉንዓቀፍ ጦርነት የምታስተናግድ ሆና ስትቀጥል የአገራችንስ መጻዒ ዕድል ምን ይሆን?
(ይህንን ዘገባ ለማጠናቀር በርካታ የሚዲያ ውጤቶችን በዋቢነት ተጠቅመናል፤ ለሚጠይቀንም እናሳውቃለን:: ፎቶ: ጂ. አር)

No comments:

Post a Comment