Translate

Thursday, February 14, 2013

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የሶማሊ ልዩ ሚሊሺያዎች በነዋሪዎች ላይ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ ይፋ አደረገ


የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የሶማሊ ልዩ ሚሊሺያዎች በነዋሪዎች ላይ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በትናትናው እለት የስርጪት ፕሮግራሙ የሶማሊ ልዩ ሚሊሺያዎች በነዋሪዎች ላይ የፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያ ይፋ አድርጓል። ኢሳት ይፋ ባደረገው በዚሁ በምስል የታገዘ ዘገባ እንደተገለጸው በምእራባዊያን አቆጣጠር ማርች 16፣ 2012 በኢትዮጵያዋ የሶማሊ ክልል ፣ በጋሻሞ ወረዳ በክልሉ መንግስት የሚተዳዳሩት ልዩ ሚሊሺያዎች አንድ ወጣት ይገድላሉ። የወጣቱን መሞት ተከትሎ ከወረዳው ህዝብ የተውጣጡ ሰዎች “አሁንስ በቃ” በማለት ገዳዩን የሚሊሺያ አባል ተከታትለው ይገድሉታል። ይህን ተከትሎ የልዩ ሚሊሺያ ሀይሉ አባላት በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው በመሄድ ነዋሪዎችን ሲገድሉ፣ ሴቶችን ሲደፍሩና ንብረት ሲዘርፉ መቆየታቸውን የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ማጋለጣቸውን ዘገባው አውስቷል። እንደ ኢሳት ዘገባ “ህዝቡ በቃን” ብሎ እንዲነሳ ያደረገው ዋና ምክንያትም የግፉ ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ መሆኑን ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ታውቋል።
በማግስቱ ማርች 17፣ ከ2 ሺ በላይ የሚሆኑ ልዩ የሚሊሺያ አባላት ወደ ወረዳው ተመልሰው በመሄድ ሰዎችን ከቤት እያወጡ ሰዎችን ገደሉ። ኢሳት የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ እንደገለጸውና የአካባቢው ነዋሪዎች በፎቶግራፍ አስደግፈው በላኩት መረጃ ከቤታቸው እየተለቀሙ የተገደሉት ሰዎች ብዛት 23 ነው። የልዩ ሀይሉ ድርጊት ያስቆጣው የወረዳው ነዋሪ መሳሪያ አንስቶ ከልዩ ሀይሉ ጋር መታኮስ በመጀመሩ፣ 17 የልዩ ሀይል የሚሊሺያ አባላት ተገድለዋል። የህዝቡ ቁጣ ያስፈራቸው የልዩ ፖሊስ አባላት አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል ብሏል። ይሁን እንጅ ውጥረቱ አሁንም ድረስ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ ብሏል ኢሳት።

የኢትዮጵያ ሶማሊ የጦርነት ቀጣና ተብሎ በመከለሉ አንድም ጋዜጠኛ ወይም የሰብአዊ መብት ድርጅት ወደ አካባቢው በመሄድ በክልሉ ያለውን ችግር ለማጣራት አልቻለም ያለው ኢሳት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሺን በአካባቢው ገለልተኛ አለማቀፍ አጣሪ ቡድን እንዲላክ ቢወስንም፣ ውሳኔውን በወያኔው አገዛዝ እምቢተኝነት የተነሳ እስካሁን ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም ብሏል።
ቀጣፊው መለስ ዜናዊ ከ7 አመታት በፊት በሶማሊ ክልል የሚካሄደው ጦርነት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል በማለት ለፓርላማ ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል።
በሌላ ዜና ከዋልድባ ተሰደው በጎንደር መድሀኒዓለም ቤ/ክ የተጠለሉ 48 ባህታዊያን ታፍሰው መወሰዳቸውን ኢሳት በትናንትናው እለት ገልጿል። የኢሳት የጎንደር ዘጋቢ በስፍራው ተገኝቶ እንደዘገበው ባህታዊያኑ ከጥር 2 ቀን 2005 ዓም ጀምሮ መድሀኒአለም ቤ/ክርስቲያን ውስጥ በሚገኝ አንድ አዳራሽ ውስጥ ከሰዎች ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ በጥብቅ ቁጥጥር ሲጠበቁ መቆየታቸው ታውቋል።
በትናንትናው እለት ባህታዊያኑ ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ በአውቶቡስ ተጭነው ወደ አልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል ያለው ኢሳት የአካባቢው ወጣቶች ከባህታዊያኑ ጋር አብረን እንሄዳለን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ አካባቢው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር ታውቋል።
መነኮሳቱ ገዳሙን ለቀው የተሰደዱት የጸለምት አስተዳዳሪ የትግራይ ተወላጅ እስካልሆናችሁና የክልሉን መታወቂያ እስካላወጣችሁ ድረስ በገዳሙ አትኖሩም በሚል ስላባረራቸው መሆኑን 31 ባህታዊያን በጋራ ጽፈው ያወጡት መግለጫ እንደሚያሳይ የኢሳት ዘጋቢ መግለጹንና የዚህንም ዘገባ ሙሉ ዝርዝር በዛሬው እለት እንደሚያቀርብ ኢሳት ገልጿል።

No comments:

Post a Comment