Translate

Monday, February 4, 2013

አንድነታችን ከእምነት ቤታችን ይጀምራል


ከታዛቢ (መንግስቱ ሙሴ)

የተከበሩ ዶክተር ጌታቸው ሐይሌ ቤተክርስቲያንን አስመልክቶ በወጣ ወቅታዊ ድርሰታቸው ቤተክርስቲያን አልተከፈለችም የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። በእርግጥ በቀኖናም ሆነ በዶግማ ቤተክርስቲያን ልዩነት አለመኖሩ ለማንም ሰው የተሰወረ አይደለም። እናም ያንን አስመልክቶ እስካሁን የተነሳ ጥያቄም ሆነ አለመስማማት ስለሌለ ውይይትም አያስፈልገውም ማለት ነው። ሆኖም ለአለፉት 21 አመታት ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲያስጨንቅ የኖረው ቀኖና ቤተክርስቲያን በመጣስ የፖለቲካ መንበሩን የያዘው ሐይል የራሱን ደጋፊ ወይንም አባል አስቀመጠ በማለት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖረው የአቡነ ጳውሎስን ህጋዊነት አልተቀበለም። ሆኖም በአገር ውስጥ አማራጭ ስለሌለና በኃይል የታፈነ በመሆኑ ምርጫ አልነበረውም ዛሬም የለውም። ያም ሲሆን የአበባ ጉንጉን ይዞ ተቀበላቸውም ማለት እንዳልሆነ ባሳለፍናቸው 21 አመታት ሁላችንም እንደታዘብነው በሄዱበት ሁሉ ክብርና ሞገስ ሳይሆን ስድብና ጥላቻ እንዳጋጠማቸው ትክክል ነው። በዚህ በውጩ አለም ግን ሁኔታው ከአገርቤት በእጅጉ የተለየ ነበር:: አሁንም በቀጣይነት ያለው ያለፈው አቡነ ጳውሎስ የፈጠሩት ነው። ልዩ የሚያደርገውም ምእመኑ ከሶስት ቦታ መከፈሉ ብቻ ሳይሆን፤ የውስጥ ሲኖዶስ ደጋፊወችም ከስርአቱ ጋር በመተባበር አቢያተ ክርስቲያናትን ወደ ፍርድ ቤት በመጎተት ሕዝበ ክርስቲያኑ እየተማረረ ቤተክርስቲያንን እንዲተው ወይንም ወደሌላ እምነቶች እንዲዞር ማድረጋቸው ነበር። ለፍርድቤትና ለእርስ በርስ ሽኩቻ ሰለባ የሆኑትም “ገለልተኛ” ነን የሚሉት ለመሆናቸው በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ምእመናንና ቦርድ ሦስት ተከታታይ ክሶች ደርሰውበት ምንም እንኳን ሚካኤል ቢያሸንፍም፤ በዶክተር ጌታቸው ለቀረበው የገለልተኝነት ሀሳብ መልካም ምሳሌ ነው። የእምነት ቤት የጭቅጭቅ መሆኑ ያሳዘናቸው ብዙ ምዕመናንም እቤታቸው መቀመጥን መርጠዋል።

የተከበሩ ዶክተር ጌታቸው ክፍፍል የለም ሲሉ ይህንን ከላይ የጠቀስኩትን እውነታ በምን ተመልክተውት ይሆን? የፍቅርና የሰላም ቤታችን በጥላቻና እረብሻ ሲተካ፤ ምእመኑ ተማሮ ወደሌሎች ወደማያምንባቸው ቤተክርስቲያኖች ሲሄድ፤ ክፍፍል የለም፤ ሁኔታውም አልጎዳንም ማለት እንዴት ይቻላል? ዛሬ እንኳን አዋቂ፤ ልጆቻችን ያደጉባቸው ቤተክርስቲያኖች ያሉበትን ሁኔታ በቅጡ ተገንዝበዋል። በዚህ የዶክተር ጌታቸው አባባል ብዙሀን ዜጋ ተሳስቷል ወይንም መከፈል የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጓሜ የለውም አሁን ላለው ሁኔታ ማለት ነው። አለያም በአባትነት ለማጽናናት የተጠቀሙበት ቃል ነው። በእርግጥም የእምነት ልዩነት አለመፈጠሩና ምእመናን የትኛውም ቤተክርስቲያን (ውስጥ ወይም ውጭ) ሄደው ጸሎት መድረጋቸውን አላቆሙም። ሁሉም እንደሚረዳውና ከፍ ዝቅ ተብሎ የተጨነቀበት አገር ውስጥ ባለው ምእመን ሳይሆን እዚ በስደት በምንኖረው መካከል ያለው መለያየት ተቃልሎ የሚታይ መሆን የለበትም። በአገር ውስጥ የሕዝብ መብት የሚያከብር ሳይሆን በሀይል የሚገዛ አስተዳደር በመኖሩ መንግስት በእምነቶቻችንም ጣልቃ በመግባት መንበሩን የተቆጣጠረበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ በመጠቀም በውጭ ያሉ አንዳንድ አድባራት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ስር ነን ሆኖም ሁለት ሲኖዶስ በመፈጠሩ ከሁለቱም መሆን አንፈልግም በማላት “ገለልተኛ” የሚል ስም በመስጠት ላለፉት አያሌ አመታት ሦስተኛ መንገድ ተከትለዋ። ይህ አሰራር በእርግጥም ከኦርቶዶክሳዊነት ውጭ ከመሆኑ ባሻገር ልክ እንደ ፕሮቴስታን አቢያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሀይ ባይ የሌላቸው ቀሳውስትን እንደፓስተሮች በአሻቸው እንዲሰሩ ፈቅደውላቸዋል። ከዶክተር ጌታቸው መጣጥፍ እንደተረዳሁት የቆየውን የ”ገለልተኛነት” ለማስቀጠል አሁንም ቅድመ ምክንያት አድርገው በዚህ መልክ አቅርበዋል።
“ችግራችን በአንድ፤ዘመን ሁለት ፓትርያርኮች መኖር ነው– በአንድ አካል ላይ ሁለት እራስ። ፓትርያርኮቹ አንዱ ኢትዮጵያ አንዱ አሜሪካ ሆነው፥ “ያንኛውን ትታችሁ እኔን ተከተሉ” ስላሉን ግራ ተጋባን። ግማሾቻችን አንዱን፥ ግማሾቻሻችን ሌላውን ተከተልን፤ ሌሎቻችን ማንንም አልተከተልንም። ሆኖም፥ የአንዱ ፓትርያርክ ተከታይና የሌላው ፓትርያርክ ተከታይ ወይም ገለልተኛው የሃይማኖት ወንድማማቾችና እትማማቾች ናቸው።”
ከዚህ የገለልተኛ ነን ባይ አቢያተ ክርስቲያናት መቀጠል ብሎም መባዛት ተጠቃሚው ሕዝብን በመንደርና በቋንቋ እየከፋፈለ በማባላት ስልጣኑን ለማራዘም ደፋ ቀና ለሚለው ቡድን ነው። “ገለልተኛ” ነን የሚሉት የውጮቹ ምእመናን ብዙወቹ እስከ ሰሞኑ ተንኮሉ ያልገባቸው፤ አለያም ሕዝቡ በአንድ እንዳይሆን የሚደክሙት የገዥው ቡድን ደጋፊወች ናቸው። ዛሬ የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ላለፉት ሁለት አመታት ያላቋረጠ መብታችን ይከበር ጥያቄ አንግበው የሚሞቱትና የሚታሰሩት ሁሉን ጠቅልሎ በያዘው አናሳ ቡድን የደረሰባቸውን ጭቆና በመቃወም ነው። በክርስትና እምነት ተከታዮች። በተለየም በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ላለፉት 21 አመታት የደረሰው በደል ይህን ያክል ተብሎ ለሚዛን የሚቀርብ አይደለም። እንዴው ለአንብነት በዋልድባ ገዳም መነኩሳት እየደረሰ ያለን በደል በአንድ ቆመን እንዳንጮህ ያደረገን የመለያየት መጋረጃ በመኖሩ አይደለም?
በዶክተር ጌታቸው ጽሁፍ ማንም ሰው እንደታዘበው አንድ ሲኖዶስ ብቻ ነው ሊኖር የሚችለው የሚለው አስተሳሰብ፤ የውስጡን ሕገወጥ ምርጫ ከመቀበል የሚያልፍ አይደለም። አምስተኛውም ይሁኑ መጭው ስድስተኛ ፓትሪያርክ ኃይልን መከታ ያደረጉ እንጅ በመለኮት ደጋፊነት የተመረጡ አይደሉም። እናም ዶክተር ጌታቸው “እዚህ በውጭ ያሉት እና አገር ውስጥ የሚኖሩት እኔን ተከተሉኝ ስላሉን ለሦስት ተከፍለናል” ብለዋል። መጠየቅ የምፈልገው በጽሁፋቸው ደጋግመው የአቡነ ጳውሎስ መመረጥ ቀኖና ቤተክርስቲያንን ያፈረሰ ሕገ ወጥ ነው ካሉ፡ ተከተሉኝስ ቢሉ ሕገወጥ ያሉትን ለምን ማዳመጥ አስፈለገ?  የውጭ አባቶች በምንና እንዴት ተከተሉን ብለው ሊያስገድዱ እንደቻሉ ግልጽ አይደለም።
ከዚህ አጣብቂኝ ያደረሰንን ምክንያት ሁሉም ቢያውቀውም፥ በአጋጣሚው እንደገና በአጭሩም ቢሆን ማንሣት ይገባል። ወያኔዎች የፖለቲካውን ሥልጣን እንደያዙ፥ ቤተ ክርስቲያኗንም ተቆጣጠሯት። መንበረ ፓትርያርኩን የያዘውን ርእሰ ቤተ ክርስቲያን (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን) ገፍተው የራሳቸውን ሰው (ዶክተር አባ ገብረ መድኅን ይባሉ የነበሩትን አስከድተው) አስቀመጡበት። በዚህም ሁለት ታላላቅ ብሔራዊና ታሪካዊ ወንጀል ፈጸሙ። (1 “ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም የሚለውን የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ጣሱት፤ (2) በሀገሪቷ ላይ የዘሩትን ጎሰኝነት ዘረኝነት ከማታውቀው ቤተ ክርስቲያን አስገቡት። ኅብረተ ሰባችንን በዚህም በዚያም አፈረሱት፤ አፈራረሱት። ያልታመመውን ሁሉ በሽተኛ አደረጉት።
የወያኔወች የጎሰኝነት በሽታ በውጭ የሚንጸባረቀውም ሆነ ትልቅ ሚና የተጫወተው በቤተክርስቲያንና በኮሚውኒቲ ተቋማት ነው። የሰሞኑ አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ለብዙ ምእመናን መልካም ትምህርት ሰጧል። የተቻቸውንና የተቃወማቸውን “ፖለቲከኛ” እያሉ የተመጻደቁት ልብ አውልቅ የዘረኛው ቡድን ደጋፊወች እንደምርጫ የወሰዱት ገለልተኛ የሚልውን ነው።
ቤተክርስቲያኗ የደረሰባትን የሕገ ቤተክርስቲያን ጥሰትን ከላይ እንዳስቀመጡት ተጠብቆ፤ ከአገር ተገፍተው እንዲሰደዱ የሆኑት አባቶች ምእመኑን ወደኛ ኑ ብለው የጠየቁበት ጊዜ አይታሰበኝም። አገርቤት የሚኖረው ወገናችን የተጣለበትን ተገዶ ከመቀበል ውጭ ምርጫ የለውም። ከሁሉም የመለያየቱ ጉዳት የሚታየው በውጩ ወገን ላይ ሆኖ ሳለ። እየፈራረሱ ያሉ አድባራትን ማገዝ ሲችል፤ በደል እየደረሰባት ላለችው ቤተክርስቲያን ደጋፊና አለኝታ ሊሆን ሲገባው ከሁለት አልፎ ሦስተኛ ጎዳና እንዲከተል መደረጉ፤ ገዳማት ሲፈርሱ በአንድ መነሳት ያለመቻሉ አንድ ትልቅ ጉዳት ነው።
የዋልድባ መነኩሳት የደረሰባቸውን ግፍና፤ በገዳሙ ላይ እየደረሰ ባለው በደል ከዚህ በውጭ ከምንኖር አንድ ድምጽ ማሰማት ያልተቻለው የወያኔው ቡድን ከውስጥ ዘሎ በውጭም ካድሬ ቀሳውስትንና ሰላይ ከፋፋዮቹን አሰማርቶ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር ገለልተኛ ተብሎ ሦስተኛው ጎዳና ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም። እናም የተከበሩ ዶከተር ጌታቸው ይህ በውጭ የቆየው የሶስት ጎራ ቤተክርስቲያን እዲቀጥል ይፈልጋሉ ማለት ነው? መቸም በወያኔው አስተዳደር ድጋፍ የሚተዳደሩትን አቢያተ ክርስቲያናት የሚጠቅም ካልሆነ የሚጎዳ ነገር የለውም። ለዚህ መልስ ቢሰጡኝ በትህትና እጠይቃለሁ።
የአንድ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ማእከል ከሕዝቡ ማእከል መሆን እንዳለበት መካድ አይቻልም። ስለዚህ፥ በሕዝብ ማህል ያለውን የኢትዮጵያውን ጭቁን ሲኖዶስና የቤተ ክርስቲያንን አመራር ታግሎ፥ ከወያኔ እጅ ነፃ አውጥቶ፥ ከመውሰድ ይልቅ፥ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋም ሕጋዊ አለመሆኑን ሲኖዶስ አቋቋሚዎች ያውቁታል።
ከዚህ አባባል ምን እንውሰድለት? በአቦይ ፀሐየና መሰል የሕወሓት አመራር ቁጥጥር ስር የዋለውን ጉባኤ ጭቁን እንበለው? ወይንስ መሰል አስተሳሰብ እያራመዱ በውጭ ሲኖዶሳችን አገር ነው። እኛ ያባ ጳውሎስን ስም ሳንጠራ ግን በጳውሎስ ስር ነን ይባል የነበረውን አሁንም በቀጣይ ለሚመረጠው ገለልተኛ ነን እያልን ግን ህጋዊነቱን እንቀበላለን ለማለት ነው?የተከበሩ ዶክተር ጌታቸው ጭቁን ያሉት ከትግራይ ሜዳ ጀምሮ የተቋቋመውን ሲኖዶስ ከሆነ፤ በምንና እንዴት ጭቁን ሊሆን ቻለ የሚለው ማብራሪያ ይፈልጋል። መረሳት የሌለበት ላለፉት የወያኔ የስደትና የጭቆና አመታት በውጭ የሚኖረው ሕዝበ ክርስቲያን አንድ እንዳይሆን ይህ ከላይ የተቀመጠ አባቶችን አታስጠጉ አይነት አባባል ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም። እንደሚመስለኝ በወያኔ የተጎዳነው እንዳናገግም አንቆ ይዞን በመሰል ወገኖች ሌላ መለያያ መዘየዱ አግባብነት የለውም። ያለው መንገድ ሁለት ነው። አንድም በዶክተር ጌታቸው “ጭቁኑን ሲኖዶስ” የተባለውን መከተል፤ አለዚያም ከተገፉ አባቶች ጎን ቆሞ ይህን የስደትና የጭቆና ዘመን ከሕዝባችን እንዲነሳ ማገዝና መተባበር ነው።
ይህችን አጭር ጽሁፍ ያቀረበው ሰው ለአለፉት አመታት “ገለልተኛ” በተባለ ቤተክርስቲያን አባል የሆነ ግለሰብ ሲሆን። የገለልተኝነት ጉዳቱን መልካም አድርጎ ተገንዝቧል። ቤተክርስቲያን የፍቅር ሳይሆን የጭቅጭቅ ሲሆንም አይቷል። በገለልተኛ ቤተክርስቲያናት ውስጥ የሚያገለግሉ ቀሳውስት ባሻቸው አዳሪ በመሆናቸው የችግሩ ሁሉ ምክንያቶችም እነሱው ሆነዋል። ወደው ሳይሆን ከሚያውቁት አሰራርና ደንብ ውጭ ያገኙት ቁጥጥር አልባ ሁኔታ የፈጠረው በመሆኑ ነው። አሁን ከማንኛውም በላይ “ገለልተኛ” መሆንን የሚመርጡት እንዲህ ወደዚህ በስደት እየጎረፉ ያሉት ቀሳውስት ናቸው።
“ገለልተኛ” የሚለው አስተሳሰብ የውስጥ ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጭ በፖለቲካው ተጽእኖ የሚመረጥን አባት መደገፍ ነው። ከአሁን በኋላ በውጭ ያለው ምእመን ይህን ክፍፍል አቁሞ አራተኛውን ህጋዊ ፓትርያርክ በአባትነት መቀበል ነው የሚበጀውና ትክክለኛው የእምነት ጎዳና። ጥቅሙም አንድነትን፤ ሕብረትንና ትብብርን ያመጣል። ከመሀላችን የተለየውን ፍቅር ይመልሳል። ለወገንና ለቤተክርስቲያን የተሻለ ያግዛል። ለተበደሉት በጸሎትም ሆነ በተግባራዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሦስት መንገድ የለም። ትክክለኛው አንድ ነው።
ለቅድስ ቤተክርስቲያን መልካም መሪ ይስጣት
yberhanie@gmail.com

No comments:

Post a Comment