Translate

Monday, February 18, 2013

አባት ያቆየውን በማፍረሱ የሚመፃደቅ ሰራዊት!


አባት ያቆየውን በማፍረሱ የሚመፃደቅ ሰራዊት!

ጌታቸው, ከኦስሎ
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
የሰሞኑ የአዲስ አበባ ከራሞት እና የቴሌቭዥን ጣቢያዋ የዜና ርዕስ ”የመከላከያ ሰራዊት ሳምንት” ተከበረ የሚል ነበር። በ አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ሰራዊት” የደረሰበት የእድገት ድረጃ”
Ancient Ethiopian army
ጥንታዊው የኢትዮጵያ ወታደር
ተብሎ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰሩ፣ የተገጠሙ፣ እየተባሉ የተነገሩ አውደ ርዕዮች ከመታየታቸውም በላይ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ስታድዮም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም በተገኙበት ኢህአዲግ ለመጀመርያ ጊዜ ወታደራዊ ትርኢት አሳይቷል። መቸም ማንም ዜጋ የሀገሩ ሰራዊት ጠንካራ መሆኑን እና ሃገርን የመጠበቅ አቅም እንዲኖረው ይመኛል። ይህ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው።

አሁን ባለንበት አለም ውስጥ የወታደራዊ ጥበብ የጉልበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውስብስብ እውቀትን እና ግንዛቤን የሚጠይቅ ሳይንስ ነው። ወደሚፈለገው የእውቀት ደረጃ ለመድረስ ግን አንድ ሰራዊት ማሟላት የሚገባው ብዙ ነገሮች አሉ። በኢህአዲግ የተደራጀው የኢትዮጵያ ሰራዊትን ሳስበው ብዙ ያልተመለሱልኝ  ጥያቄዎች አሉ። ከእነኝህ ጥያቄዎች ውስጥ -
  • ሰራዊቱ የቆመው ለስልጣን መጠበቅያነት ነው ወይንስ ለሕግ እና ለስርዓት ብቻ?
  • ሀገር የመከላከል ሥራ እግረመንገድ የሚስራ ሥራ ነው ወይንስ ቅድምያ የሚሰጠው?
  • ሉአላዊነት (soverginity) የሚለውን ቁልፍ ቃል ሰራዊቱ ከከፍተኛ መኮንኖች እስከ የመስመር መኮንኖች ብሎም እስከ ተራው ወታደር ድረስ በምን ያህል የዲግሪ ደረጃ ይረዳዋል?
  • ሰራዊቱ ኢትዮጵያን እንዴት ነው  የሚገልፃት?
  • ሰራዊቱ በምን ያህል ደረጃ ከአካባቢያዊ የወንዝ ስሜት እርቆ በብሔራዊ ስሜት ውስጥ ነው? መኮንኖቹ ምን ይህል አለምአቀፋዊ ስልታዊ (strategic) የኃይል አስላለፎችን ይረዳሉ? የመተንተን አቅማቸውስ? ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የምነሱብኝ ጥያቄዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ውስጥ ነፃነት እና ሉአላውነቷን አስከብራ የኖረችው በእየዘመኑ የነበሩት መሪዎቿ ለሁለት ነገሮች ተገዢ ስለነበሩ ነው። ይሄውም አንዱ ለእግዚአብሔር ሁለተኛው ለሀገራቸው ፍቅር። ዛሬ ላይ ሆነን አፄ ምኒልክን ”ለምን ማይክሮሶፍት ኮምፕዩተር አልተጠቀሙም? አፄ ዮሐንስ ለምን በዶዘር  የሊማሊሞን አቀበት አላፈረሱም? ”መሰል ጥያቄ ካልጠየቅን በስተቀር በዘመናቸው መስራት የሚገባቸውን በነበረው ቴክኖሎጂ፣የአቅም ውሱንነት፣ብድር እና እርዳታ ከመላው አለም እየጎረፈላቸው ሳይሆን በባዶ እግሩ የሚሄድ ሰራዊት ይዘው ይችን ሀገር እንደ ሀገር ከሙሉ ክብር እና ማዕረግ ጋር አስረክበውናል።
መደነቅ ከተገባን ከየትኛውም የወታደራዊ የትምህርት ተቁዋም ሳይመረቁ አለምን ባስደነቀ የወታደራዊ ስልት አድዋ ላይ ድል ያደረጉትን፣ ዶጋሊ ላይ ያንቀጠቀጡትን፣ ምፅዋ ላይ የተናነቁትን ማሰብ እና መዘከር ተገቢ ነው። ኢህአዲግ የኢትዮጵያ ሰራዊት በዓል ብሎ ለማክበር ብቻ ሳይሆን ለማሰብ እራሱ ሃያ አንድ አመት ስለፈጀበት የሚያዝኑ የመኖራቸውን ያህል። ለምን አሁን? የሚሉ ጥያቄዎች ግን በብዛት የሚነሱ ናቸው።
ወንድምን ገድሎ ሃውልት መስራት 
TPLF statue in Mekele Ethiopia
መቀሌ የሚገኘው ወንድማማቾች ደም መፋሰስ ተምሳሌት (የኢህአዲግ የ ”ድል” ሃውልት)
ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ የመጀመርያውን ወታደር (ወጥቶ አደር) በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን መመስረቷ እና በኃላ በፋሺሽት ጣልያን ላይ ከአርበኞች ጋር የተፋለመው የጥቁር አንበሳ ጦር ቀጥሎም በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ በምድር ጦር፣በ አየር ኃይል እና በ ባህር ኃይል ደረጃ መዋቀሩ ይታወቅል። ኢህአዲግ እንግዲህ ይህንን ለዘመናት የተገነባውን ሰራዊት በ1983 ዓም  አዲስ አበባን ሲቆጣጠር መበተን የመጀመርያ ስራው ነበር። ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አውጥታ ያስተማረቻቸው ምርጥ መኮንኖችን ”የታገሉት ለህዝብና ለ ሃገር  ነው” ብሎ በሥራ ገበታቸው እንዲገኙ ከማድረግ ይልቅ በእየእስርበቱ ‘ጉዳያችሁ እስኪጣራ’ እያለ አጎራቸው። የተቀሩት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገር ትተው እንዲሄዱ ተደርጉ የተረፉት ደግሞ በሀገርቤት ከግል ንግድ እስከ በመንገድ ላይ ወጥቶ እስከመለመን ደረሱ። በሽምቅ ውግያ እና በቆረጣ የሚታወቁት የኢህአዲግ ሰራዊት በተቀረው አለም ከሃያ አምስት እስከ ሰላሳ አመት የሚፈጀውን የከፍተኛ መኮንነት ማአረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጎናፀፉ ተደረጉ። ጀነራሎች፣ ኮለኔሎች ሆኑ።
ይህ ብቻ አይደለም የሰራዊቱ ቤተሰቦች ከሁለት እና ከእዛም በላይ ትውልድ ይኖሩበት የነበሩትን ቤቶች በተለይ በካምፕ አካባቢ የነበሩትን በሙሉ በአንዲት ጀንበር እንዲለቁ ተደረጉ። ቤተሰብ ተበተነ ልጆች ለጎዳና ተዳዳሪነት ተጋለጡ። የቀድሞ ሰራዊት አባላት የነበሩት   ምንም አይነት የዘር እና የወንዝ ስሜት የሌላቸው የሀገር ፍቅር እና ሉአላዊነት በሚል ፍቅር የተቃጠሉ ዜጎች በሜዳ ተበተኑ። ከኢህአዲግ ባለስልጣናት አንድም እነኚህ እኮ የሀገር ሰራዊት ናቸው። ዛሬ እንድንቆም ያደረጉን ከሱማሌ ጋር ተናንቀው ሀገር ያዳኑ ናቸው ያለ አልነበረም።
በእዚህ ብቻ አልተገታም ኢትዮጵያ ሃውልት የምትሰራው ከባእዳን ጋር ላደረገችው ጦርነት እንዳልነበር ኢህአዲግ ወንድም ከወንድሙ ጋር  ለተጋደለበት አሳፋሪ ታሪካችን እንደ ትልቅ ገድል ሃውልት አቆመ። ሃውልቱንም ”ድላችን” አለው። ሆኖም ግን ከወንድምህ ጋር ላደረከው ጦርነት ሃውልት ማቆም መጪው ትውልድ  እንዲቆስል  ነው? ቀድሞ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ጊዜም ሆነ ከእዛ በኃላ ብዙ የእርስ በርስ ጦርነት ነበሩ። ግን ነገሥታቱ ወንድሜን ገድልኩ ብለው ሃውልት ሰርተዋል? ብሎ ለሚጠይቀው ኢህአዲግ መልስ የለውም። እውነት ግን የትኛው ንጉስ የቱን ደጃዝማች ገደልኩ ድል አደረግሁ ብሎ ሃውልት ሰራ? ኢህአዲግ ግን ከወገኑ ጋር ላደረገው ደም መፋሰስ አድርጎታል።
እንግዲህ የኢትዮጵያ የሰራዊት ቀን ሲከበር  ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ሁሉ መታሰብ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ብለን ስንጠራ ከሙሉ አካሏ እና ታሪክዋ ጋር መሆን አለበት። አንዲትን ሴት እጇን ትተን ወይንም እራሷን ቆርጠን ሌላ አካሏን እያነሳን ሴት ብለን መጥራት እንደማንችል ሁሉ ኢትዮጵያንም መነሻዋን ያወቀ ሰራዊት መድረሻውን የሚረዳ መኮንን ሲኖራት ነው ሰራዊቱ የሕዝብ ስሜትን የተጋራ አብሮት ሊሞት የቆመ ልብ ማግኘት የሚቻለው። ከ እዚህ ውጭ እንዴት ነው ገና በሀገሪቱ ያለፈ ታሪክ ላይ ሙሉ በሙሉ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን መተማመን ላይ  ያልደረሱ መኮንኖች   የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚያስከብሩት?
አባት ያቆየውን  በማፍረሱ የሚመፃደቅ ሰራዊት
የኢትዮጵያ ሰራዊትን ከጅቡቲ እና ሱዳን ጋር እያወዳደርን አድገናል ተመድገናል  ማለት ተገቢ አይደለም። በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የነበሩ እና ነፃነታቸውን ካገኙ ገና አመታት ያስቆጠሩ ሃገራት የኢትዮጵያ መለክያ እና ማነፃፅርያ ሊሆኑ አይችሉም። በመጀመርያ እኛ ማን ነን? የት ነበርን? አሁን የለንበት መድረስ የሚገባን እና ልካችን ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው።
አንድ ብርጭቆ ውሃ ያለውም ሆነ አንድ ባልዲ ውሃ ያገኘ ሁለቱም ብዙ ውሃ አለኝ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ግን ባለ ብርጭቆው ብዙ ውሃ አላኝ ያለው አቅሙን እና ሊኖር የሚገባውን
Ethiopian National Defense Force - Ethiopian navy
የኢትዮጵያ የባህር ኃይልን አፄ ኃይለ ስላሴ ሲጎበኙ
ካለመረዳት ከሆነ ችግር ነው።ኢትዮጵያ በአየር ኃይልም ሆነ በባህር ኃይል አቅሟ ሌላው ቀርቶ ስጋት ብላ ታስብ የነበረው ከ መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የሚሰነዘረውን ጥቃት እንጂ በጎረቤት ደረጃ አልነበረም። በ1969 ዓ.ም ሱማልያ በኢትዮጵያ ላይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ያነሳችው በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ ውስጣዊ ችግር የልብ ልብ መስጠቱ እንጂ የ ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም ከሚገባው በታች ወርዶ አይደለም። እርግጥ ነው በወቅቱ የአሜሪካ መንግስት እስካፍንጫው በቀድሞዋ ሶቭየት የታጠቀውን የሶማልያ ጦር ኢትዮጵያ እንዳትዋጋ የጦር መሳርያ ግዢ ማዘግየት መፈፀሙ በወቅቱ ቶሎ ወደውግያው ላለመግባት የቀረቡ  ምክንያቶች ነበሩ። ሆኖም ግን በአየር ኃይሉም ሆነ በምድር ጦር ደረጃዋ ጥሩ ነበር። ለእዚህም ነው ኢትዮጵያ ሱማልያን ባብዛኛው የተዋጋችው በሚሊሻ ጦር የሆነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከአነሳሷ ጀምሮ ኢህአዲግ ሰራዊቱን በትኖ ወደኃላ ባይወስዳት ኖሮ ዛሬ መወዳደር ያለብን ከደቡብ አፍሪካ እና እንደ ቱርክ ከመሰሉ ሀገሮች ጋር ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።
ለእዚህ ማስረጃ የሚሆነው የባህር ኃይላችን የነበረበት ደረጃ ነው። የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አቅም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጋር የሚወዳደር እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በተደጋጋሚ ከሻብያ ጋር በተደረገው ውጊያ በሰው ኃይልም ሆነ በማቴርያል እያገዘ የኢትዮጵያን የባህር ኃይል ያዘጋው ኢህአዲግ ዛሬ የኢትዮጵያ የሰራዊት ቀን ብሎ ሲያከብር አያምርበትም።
ኢትዮጵያ በዘር በጎሳ የሚያስብ ሰራዊት ኖሯት አያውቅም። ዘራይ ድረስ እና አብዲሳ አጋ ጣልያንን በሀገሯ ያንቀጠቀጧት፣ አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን የተዋጉት፣ ምፅዋ ላይ በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ የረገፉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከምንም በላይ ክልላዊ ስሜት ሳይሆን ክብርት ለሆነች ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መሆኑ መጀመርያ ማመን ከሁሉ በፊት ይቅደም። ወደድንም ጠላንም ዛሬ ላለንበት እኛነት  መሰረቶቻችንን  ማክበር ካልቻልን የሚያከብረን አለመኖሩን ማሰብ አለብን።
በመጨረሻም ከኢህአዲግ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከመኮንን እስከ ተራ ወታደር የሀገር ፍቅርን ቅድምያ የሚሰጥ የወንዝ ስሜት ያልገዛው መሆኑን ለመረዳት የ1953ዓም የ መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በአፄ ሃይለስላሴ ላይ ያደረጉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እና በ1981ዓም በኮለኔል መንግስቱ ላይ የተሞከረው የመፈንቅል ሙከራ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል። ይሄውም ሰራዊቱ ምን ያህል የህዝብን እና የሀገርን  ጉዳይ ከንጉሡ እና ከኮለኔል መንግስቱ በላይ እንደሚመለከት  አመላካች ነው።
ለእዚህ ማሳያ የሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶን ታሪክ በትንሹ የሚያሳይ ቪድዮ ማየቱ ጠቃሚ ነው። ሜጀር ጀነራል ደምሴ የኢትዮጵያን አየር ወለድ  ከመሰረቱት አንዱ ናቸው። በሱማሌም ሆነ በኤርትራ ጦርነት ላይ ሲዋጉ የኖሩ በኃላ ግን በኮሎኔል  መንግስቱ ላይ የመፈንቅለ መንግስት  ሙከራ ሲያደርጉ በእራሳቸው በመሰረቱት የ አየር ወለድ  የተገደሉ የጦር መኮንን ነበሩ።
ዛሬ የኢትዮጵያ የሰራዊት ቀን የሚከበረው እንዲህ አይነት ለሀገር የሞቱ ደርግን እራሱን ሲዋጉ የነበሩ ጀግኖች ተረስተው ነው። ባጭሩ ግን ኢህአዲግ የአትዮጵያን የሰራዊት ቀን ሲያከብር አላማረበትም።
አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ

No comments:

Post a Comment