Translate

Wednesday, May 25, 2016

በጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የቀረበው የሽብር ክስ ዝርዝር

Getachew Shiferawየፌደራል አቃቤ ህግ ግንቦት 10/2008 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ የሽብር ክስ የመሰረተበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የቀረበው ክስ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ የሚል ነው፡፡
ተከሳሹ ከ24/05/2006 ዓ.ም እስከ 13/04/2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ግንቦት ሰባት ከተባለ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስቡክ እና ስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎች በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ፈጽሟል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል፡፡
በአቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሽ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በህግ ተመዝግቦ በሀገር ውስጥ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጋር ያደረገው የመልዕክት ልውውጥ ክስ ሆኖ ቀርቦበታል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ከተለያዩ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ሚዲያዎች ባለሙያዎች በተለይም ኢሳት ጋር ያደረጋቸው ቃለ-መጠይቆችና የመረጃ ልውውጦችም በሽብር ክስነት ቀርበውበታል፡፡ ተከሳሹ በሽብርተኝነት ክስ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ቤተሰቦቻቸውን እንዴት ማገዝ ይቻላል በሚል ከዳያስፖራ አባላት ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ የተለዋወጣተቸው መልዕክቶችም በክሱ ላይ ተካተው ቀርበዋል፡፡
በአጠቃላይ ጌታቸው ‹‹…በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር እየተገናኘ መረጃ በመሰብሰብ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በማስተላለፍ….›› በሽብር ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለአምስት ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ክስ ተመስርቶበት ቂሊንጦ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ግንቦት 26/2008 ዓ.ም የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሊነበብለት ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment