Translate

Saturday, December 16, 2017

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የሽግግር መንግስት ሰነድ ማዘጋጀቱን ገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና

ናትናኤል ኃይለማርያም
የኢትዮጵያን ጉዳይ አስመልክቶ በአውሮፓ ፓርላማ የተጠራ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ አመራሮች በቦታው በመገኘት ኢትዮጵያ አሁን ስለገጠማት ፈታኝ እና አስፈሪ ጉዳዮች በማንሳት ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለኢሳት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ለማወቅ ተችሏል።

ፕሮፌሰሩ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የሕወሓት መንግስት እስከ ዛሬ ድረስ ለአውሮፓም ይሁን ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚሰጠው የውሸት እድገት እና የዲሞክራሲ አስተዳደር ዛሬ ላይ ሊሸፍነው በማይችለው ሁኔታ በአለም አደባባይ ተጋልጦ የታየበት ጊዜ ላይ መድረሱን በአገር ውስጥ እየተካሔደ ያለው ድርጊት ይመሰክራል ብለዋል።
ይህም በመሆኑ አገዛዙ ሲያወራ የነበረው ተራ ፕሮፓጋንዳ በሙሉ እንዳልሠራለት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተረዳው መጥቷል። በመሆኑም፣ ይህ አገዛዝ እስካለ ድረስ የአገሪቷ ችግር ወደ በለጠ ቀውስ የሚሔድ እንጂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ቁመና የሌለው እንደሆነ በግልጽ እየታየ እንደሆነም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የአውሮፓ ሕብረት በጠራው ስብሰባ የተካሔደው ውይይት ትኩረት የሰጠው፣ የዲሞክራሲ ሃይሎቹ እንዴት ወደፊት መራመድ እንደሚችሉ እና ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር እንዴት እናወጣታለን? ለችግሩ መውጫስ ማመላከቻ አለን ወይ? በሚል ዙርያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ ስብሰባ በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ እንዳውጠነጠነ የገልጹት ፕሮፌሰሩ፣ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ ቢመጣ የአገራዊ ንቅናቄው ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት ለመመልከት እና ኢትዮጵያውያኖች በጋራ እያደረጉ ያለውን ትግል ለመመልከት ያሰቡ እንደሆነም አርበኛ ብርሃኑ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄም አገራችን አሁን ላለችበት ውስብስብ ችግር ያዘጋጀውን የሽግግር ሰነድ ለአውሮፓ ሕብረት ማቅረቡን እና ይህንንም ሰነድ በተለያዩ የአገራችን ቋንቋ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘጋጅተን ለህብረተሰባችን ለውይይት እናቀርባለን በማለት ገልጸዋል።
አገራዊ ንቅናቄዉ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ የኢትዮጵያን ችግር እንዴት መክተን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ በማምጣት በአገራችን ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ በምንም መልኩ አምባገነን መንግስትን እንደማታስተናግድ እና አሁን ያለው የዘረኛና አምባገነን መንግስት የመጨረሻው እንደሚሆን አረጋግጠው ለዚህም በጋራ እየሠሩ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ጉዳይ ይከታተሉ ከነበሩት የፓርላማው አባል አንዱ በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የዛሬ አመት እንደዚሁ ስብሰባ ተደርጎ አስተያየት ሰጥቼ ነበር፣ ያልኩትም የኢትዮጵያን ጉዳይ በደንብ ካላየነው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል ተናግሬ ነበር፣ በማለት አሁን አገሪቷ እየሔደችበት ያለው ነገር አሳሳቢ እና አስፈሪ መሆኑን አሳውቀዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የአገራዊ ንቅናቄው ተባባሪ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሲገኙ የገዢውን መንግስት ወክለው ዶ/ር ሰሎሞን ነጋሽ መገኘታቸውም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment