Translate

Wednesday, December 13, 2017

ከ424 ዜጎች ጭፍጨፋ፤ ከ14 ዓመት መሬት ነጠቃ በኋላ የጋምቤላ “ኢንቨስትመንት” 9ቢሊዮን ብር ያህል ከስሯል

ጋምቤላን በረሃ አድርጎ፤ ሕዝቧን ገድሎ፤ በተለይ የአንድ ክልል “ዜጎችን” ብቻ ጠቅሞ በጋምቤላ የተተገበረው “ኢንቨስትመንት” ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ያህል የማይከፈል ዕዳ ውስጥ መዘፈቁን ህወሓት/ኢህአዴግ አመነ።

ልክ የዛሬ 14ዓመት ነበር መለስ በመራው ስብሰባ ላይ “እንጨርሳቸው፤ አንድም አኙዋክ መትረፍ የለበትም”  የሚለው ትዕዛዝ የወጣው። በዚህም መሠረት 424 ንጹሃን በግፍ ተጨፈጨፉ፤ መሬታቸው ተነጠቀ፤ ለባለሃብቶች በሃያ ብር (በወቅቱ 1 ዶላር) ሒሳብ ተቸበቸበ። ህወሓት ደርግን ሲወነጅልበት የነበረውን ግዳጅ ሠፈራና መንደር ምሥረታ በአኙዋክ ወገኖች ላይ ተፈጸመባቸው። ይህ ሁሉ የሆነው ለ”ልማት” ነው ተባለ።
በጋምቤላ የአኙዋክ ተወላጆች ተጨፍጭፈውና ከመሬታቸው ተፈናቅለው “ለሰፋፊ እርሻ” በሚል ሲቸበቸብ ከነበረው መሬት “ወደ ሥራ የገባው” 15በመቶው ብቻ መሆኑን ህወሃት/ኢህአዴግ ማስታወቁን ጎልጉል የዛሬ ዓመት ዘግቦ ነበር። የጎልጉል ዘገባ ሲቀጥል፤ ለ“እርሻ ልማት” በሚል በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ብድር ተሰጥቷል። የመሬት ካርታ “ከቢሮ ውጪ በመኖሪያ ቤቶችና በጫት ቤት ውስጥ” ሲሰራ ቆይቷል። በብድር አሠጣጡ ላይ ቁልፍ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊ ኢሳያስ ባህረ ከሥልጣኑ ለመነሳት ምክንያት የሆነው “ብድር በመስጠቱ ሂደት ለተወሰኑ የባለሃብቶች ቡድን (ለትግራይ ተወላጆች) በማድላቱ ነው” መባሉን ጨምሮ ዘግቦ ነበር።
በጋምቤላ ይህ ነው የማይባል ግፍና የዘር ማጽዳት ተካሂዶ ከምስኪን ረዳተቢሶች የተነጠቀው መሬት ከጥቅም ውጪ ሆኗል። ገና ከጅምሩ አሠራሩ ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ በተለያዩ ሪፖርቶች ሲነገረው የነበረው ህወሃት/ኢህአዴግ የጋምቤላ አኙዋኮችን ከምድራቸው ላይ በማጥፋት መሬታቸውን ከነጠቀ በኋላ “ሰፋፊ እርሻ” በሚል አንዱን ሔክታር መሬት በሃያ (20) ብር ሲቸበችበው ቆይቷል። በኢትዮጵያ እስከ 3ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከነዋሪዎች እየተነጠቀ፣ ደን እየተጨፈጨፈ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ የህወሃት/ኢህአዴግ ደጋፊዎችን ኪስ ሲያደልብ፤ ድርጊቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ሲነገር፤ “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልሸጥነው መሬት ነው” በማለት ሞት እንደ ቡሽ ክዳን በድንገት የነቀለው መለስ ተናግሮ ነበር።
ዓመታት ተቆጥረው፣ የሰው ነፍስ ከትንኝ ያነሰ ደረጃ ወርዶ፣ በግፍ ተጨፍጭፎ፣ ቀሪው ኑሮው ተመሳቅሎ፣ መሬቱ ተነጥቆ፣ ወደማይፈልግበት ቦታ በግዳጅ ሰፈራ ተወስዶ፣ የተፈጥሮው ደን ተጨፍጭፎ፣ ኑሮው ከሞት በታች ከሆነ በኋላ ህወሃት/ኢህአዴግ አደረግሁ ባለው ጥናት መሬቱም፣ ብድሩም ከንቱ ሆኗል፤ “ኢንቨስተሮቹ” ገንዘቡን አባክነውታል፤ “ለመንግሥት” የገባ ጥቅም የለም፤ ትርፉ ኪሣራ ነው ብሏል።
ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሆነው ተክለወልድ አጥናፉ እነ ኢሳያስ ባህረ እንደፈለጉ ሲያዙበት የነበረው ልማት ባንክ “አጠቃላይ የማይመለስና መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድር ከአጠቃላይ 38 ቢሊዮን ብር” መስጠቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ከዚህ ብድር ውስጥ “25 በመቶ ወይም 8.6 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ያደረገው፣ በጋምቤላ ለተጀመሩ ሰፋፊ እርሻዎች ልማት የተሰጠው ብድር” በማለት ተክለወልድ መናገሩ አብሮ ተዘግቧል።
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የዛሬ ዓመት “በጋምቤላ የከሸፈው ኢንቨስትመንት” በሚል ርዕስ ባወጣው የዜና ዘገባ ላይ ይህንን ብሎ ነበር፤
‹‹በጋምቤላ በሰፋፊ እርሻ ስም ከተሰጠው “630 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ ስራ የገባው ከ15.5 በመቶ” ብቻ ነው። ከዚህ በፊት በእርሻ ንግዱ ላይ የተሰማሩ ተብለው የተጠቀሱት “ባለሃብቶች” 780 የነበሩ ቢሆንም አሁን በፋና ላይ ወጣ በተባለው ሪፖርት 623 ብቻ ናቸው ተብሏል። 157ቱ እንደ ኮንዶሚኒየም ጠፉ ባይባልም “በመረጃ ልውውጥ ክፍተት” ያልተገኙ ተብለው በሙያዊ ቃል ተገልጸዋል። እነዚህ 157 “ባለሃብቶች” ብድር ይወሰዱ፤ መሬት ይረከቡ፤ የፋና ዜና አልጠቀሰም
‹‹ባለፈው “የጋምቤላ እርሻ ባለሐብቶች የሕብረት ሥራ ማኅበር” አቤቱታ አሰሙ በተባለበት ወቅት የማህበሩ ኃላፊ አቶ የማነ አብዛኛው በጋምቤላ በእርሻ የተሰማራው “ባለሃብት ባጋጣሚ የትግራይ ተወላጅ” መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል።
‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲገዛ የነበረው ኢሳያስ ባህረ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ከ623ቱ “ባለሃብቶች” መካከል 200ው 4.96 ቢሊዮን ብር ከባንኩ ወስደዋል። ከእነዚሁ “623 ባለሃብቶች ውስጥ ለ381 ባለሃብቶች ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተደራርቦ” የተሰጠ ሲሆን ባንኩም ለእነዚሁ ድራቢ መሬት ለወሰዱ “ባለሃብቶች” ድራቢ ብድር ሰጥቷል።
‹‹ብድሩ ሲፈቀድ በብድሩ ማመልከቻ ላይ ብድሩ የሚውልበት ዝርዝር ይጠቀሳል፤ ይህም ማለት ብድሩ የተሰጠው “ለመሬት ልማት፣ ለማሽነሪ ግዥ፣ ለካምፕ ግንባታ እና ለስራ ማስኬጃ የተሰጠ ሲሆን፥ ከአጠቃላዩ ብድር ውስጥ” 2 ቢሊየን ብሩ “ለመሬት ልማት ተብሎ ለ194 ባለሃብቶች ተሰጥቷል” በማለት ሪፖርቱ ማስረዳቱን ፋና ዘግቧል።
“ባለሃብቶቹ በዚህ ገንዘብ 314 ሺህ 645 ሄክታር መሬት እንዲያለሙ ቢጠበቅም (እነርሱ) ያለሙት ግን 55 ሺህ ሄክታሩን” ብቻ ነው። እንዲሁም ሰፋፊ እርሻ እናለማለን ብለው መሬትም ብድርም ሲወስዱ ከነበሩት 623 “ባለሃብቶች” መካከል 40 በመቶ ያህሉ (242ቱ) “ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚዎች ናቸው”።››
ከዚህ ሁሉ በኋላ አሁን ወደ 9ቢሊዮን የሚደርስ ብር የማይከፈል ዕዳ ሆኖ ቀርቷል የተባለው። ኢሳያስ ባህረ “ብድር በመስጠቱ ሂደት ለተወሰኑ የባለሃብቶች ቡድን በማድላቱ ነው” በሚል ነበር ከስምንት ዓመት ምዝበራ በኋላ ከሥልጣኑ የተነሳው። አሁን ተክለወልድ ባቀረበው ዘገባ የገንዘቡ መጠን 9ቢሊዮን ብር ነው። የጋምቤላ እርሻ ልማቶች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት የማነ በተናገሩት መሠረት መሬቱንም ብድሩንም የወሰዱት “ባጋጣሚ የትግራይ ተወላጅ” ናቸው። አእምሮ ላለው የገንዘቡ ስሌትና በእነማን ኪስ ውስጥ ገንዘቡ እንደገባ ነጋሪ አያሻውም።
ከጋምቤላ ጋር በተያያዘ ጎልጉል በተደጋጋሚ ሲዘግባቸው የነበሩትን መነበብ የሚገባቸው ሪፖርቶች ከዚህ በታች ሰፍረዋል፤
በጋምቤላ የከሸፈው “ኢንቨስትመንት”
“የመሬት ካርታ ጫት ቤት ተሠርቷል”
ጋምቤላ ልጆቿ በጥይት የተጨፈጨፉበት ምክንያት ይፋ ሆነ!
የካሩቱሪ መሬት ለትግራይ “ባለሃብቶች” ሊሰጥ ነው
ጋምቤላ ከውስጥም ከውጭም የምትለበለብ ለም ምድር!!
ህወሃት በስጋት ትጥቅ እያስፈታ ዜጎችን ለምን ያስጨርሳል?
የጋምቤላ ክልል በህንድና በሳዑዲ ኩባንያዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ
የህንዱ ኩባንያ “ከቆመለት ዓላማ በተቃራኒ ከአካባቢው ደን ጣውላ በማምረት ሲያጓጉዝ በተጨባጭ ተይዟል”

No comments:

Post a Comment