Translate

Wednesday, December 13, 2017

የተማሪዎች ዓመጽና የየአካባቢው አጫጭር መረጃዎች

አክሱም ዩኒቨርሲቲ
አክሱም ዩኒቨርሲቲ በየግማሽ ቀኑ ሲነሳና ሲበርድ ነው የሰነበተው። በካፌ ሰዓት ብዙ ጊዜ ድንጋይ ይወረወራል። ማምሻውን በራት ሰዓት በተፈጠረው ብጥብጥ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትና መውጣት አይቻልም ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው ቢሔዱም እስካሁን መውጣት የሚፈልጉ ከሁለት ሺህ በላይ የዐማራ ተማሪዎች አሉ።


አዲግራት ዩኒቨርሲቲ
ዛሬ ጠዋት በነበረው ብጥብጥ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባትና መውጣት አይቻልም ነበር። በአዲግራት እስካሁን የተረጋገጠ 9 ያክል ተማሪዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካቶች ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ወደ 30 የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በአዲግራት የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው ቶርች ተደርገዋል፤ እስካሁንም አልተፈቱም። ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሔድ ቢፈልጉም አልተቻለም። ገዳም እንገባለን ብለው የወጡ ተማሪዎችም የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል።

መቀሌ ዩኒቨርሲቲ
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ግቢ ማምሻው ግጭት እንደተፈጠረ መረጃዎች ቢወጡም ዝርዝር ማግኘት አልተቻለም። ዘግይቶ በመጣ መረጃ ደግሞ ግቢው ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ ደርሶ መብራት ጠፍቶ የተማሪዎች ጩኸትና ለቅሦ እንደሚሰማ ነው የገለጹልን።
(ተጨማሪ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ግቢ ማምሻውን እንዳልከው ከባድ የፍንዳታ ድምፅ ተሠምቶ መብራት ተማሪዎቹ መጮህ እንደጀመሩና ወዲያው የፌዴራል ፖሊሥ ጊቢው ውስጥ መግባቱን ዶርማቸው ውስጥ ሆነው ያዩ ልጆች ነግረውኛል። ይሄንን ስፅፍ በድጋሚ በሜሴጅ በላኩልኝ መልእክት መብራቱ አልመጣም ግቢው ግን መረጋጋቱን ነግረውኛል ። Abate Azagae)

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ
ትናንት በማራኪ ካምፓስ ተማሪዎች ሰላማዊ ተቃውሞ ጀምረው ነበር፤ “አዲግራት ያሉ ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ ይቁም!” “የዐማራ ደም መፍሰስ ይቁም!” ወዘተ የሚሉ ተቃውሞዎች በማራኪና ቴዎድሮስ ካምፓሶች ቀጥለው ከሕዝብ ጋር ሊደባለቁ ሲል በአጋዚ ከግቢ እንዳይወጡ ተደርገዋል። ዛሬም ከሆስፒታሉ ውጭ በሁሉም ካምፓሶች ተቃውሞዎች ቀጥለው ነበር፤ ነገር ግን የጠዳው ግቢ የአጋዚ ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። በጥይት የተገደሉ ተማሪዎች ሁሉ እንዳሉ ነው የተገለጸው።

ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ
ትናንት ሌሊት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የነበረውን የዐማራ ጭፍጨፋ በማውገዝ የተጀመረው ተቃውሞ የትምህርት መማር ማስተማር ሒደቱን ሙሉ በሙሉ አቋርጦታል። ከአዲግራት የተገደለ አንድ ልጅ አስከሬን የሚመጣ አለ መባሉ የበለጠ ችግሩን አባብሶታል። አጋዚ ወደ ግቢው መግባቱንም ሰምተናል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ጠዋት ዘንዘሊማ ኮሌጅ የጀመረው ተቃውሞ ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፖሊን፣ ፔዳንና ይባብ ኮሌጆችን ጭምር አዳርሷል። የትግራይ ተማሪዎች አዲስ ዓምባ የተባለ ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላቸው ሲሆን የፌደራል ፖሊስና አጋዚ ቀሪ ተማሪዎችን እያሰረ ነው። ምሽት ላይ ፖሊ ግቢ መጠነኛ ቃጠሎ ደርሶ ወዲያውኑ ጠፍቷል።

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ
በደብረ ማርቆስ ማምሻውን ነው የተማሪዎች ተቃውሞ የጀመረው። ሆኖም በዝግጅት ሲጠባበቅ የነበረው የፌደራል ፖሊስና አጋዚ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ተብሏል።

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ
በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ተቃውሞ እስካሁን አልበረደም። የትግራይ ተማሪዎች በወልዲያ ስታዲየም ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው፤ ከዩኒቨርሲቲው በመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ነው ተመርጠው የወጡት። ሌሊት አንድ ሕንጻ በእሳት ጉዳት ደርሶበታል። በወልዲያ ትምህርት ቤቶችም ዝግ ሆነው ውለዋል።
ዛሬ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው መርሣ ካምፓስ አዲስ ተቃውሞ ጀምሯል።

ውጫሌ ውርጌሳ
በውጫሌና ውርጌሳ የተጀመረው ተቃውሞ ትናንት ነው። “ልጆቻችን ሳይመለሱ ወደ መሀል አገር ወይም ከመሀል አገር ወደ ትግራይ የሚሔድ መኪና መኖር የለበትም” በሚል ነው ተቃውሞው የተነሳው። አንድ ልጅ ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተገደለ አለ መባሉ የበለጠ ጉዳዩን አወሳስቦታል። ጥቂት መኪናዎች ተቃጥለዋል። የሰላም ባስ ተሰባብሯል።
ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ውለዋል።

No comments:

Post a Comment