Translate

Tuesday, April 28, 2015

አልሸባብ አይሲስን ሊቀላቀል ነው

ተጨማሪ የሽብር ስጋት በኢትዮጵያ

ial

በሶማሊያ የሽብር ተግባራትን በመፈጸም የሚታወቀው አልሸባብ ደመኛና አረመኔውን አይሲስን ሊቀላለቀል መሆኑ ተሰማ፡፡ አገራችንን በተጨማሪ የሽብር ስጋት ውስጥ እነደሚጥላት ተገምቷል፡፡
የሶማሊያን ስፊ ግዛት የሚቆጣጠረው አልሸባብ የማእከላዊ ስልጣኑን ካጣ ወዲህ በደረሰበት ወታደራዊ ኪሳራ የአለም አቀፍ አሸባሪው አልቃይዳ ክንፍ በመሆን እያካሄደ ባለው የደፈጣ ውጊያ ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ርቋት በንጹሃን ደም የታጠበች መንግስት አልባ ጦር ሜዳ ከሆነች ከሁለት ዓስርት አመታት በላይ አስቆጥራለች።

ሟቹ አቶ መለስ የቆሰቆሱት የሶማሊያ ችግር እስካሁን አልበረደም፤ የኢትዮጵያን ጦር ጨምሮ ከተለያዩ አፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ወታደሮች የሶማሊያን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር እያደረጉ ያለው ጥረት መና ቀርቶ የእሳቱ ወላፈን ድንበር ተሻግሮ ለዜጎቻቸው ጦስ እስከ መሆን ርቆ የሄደበት አጋጣሚ የሰላም አስከባሪ ሃገራቱን ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት ደኅንነት ስጋት ውስጥ ጥሎታል።
ሶማሊያ ውስጥ ወታደሮቻቸውን ካሰለፉ ሃገራት መሃከል በዩጋንዳ እና ኬንያ ዜጎች ላይ ይህ እስላማዊ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን “አልሸባብ” ድንበር ተሻግሮ በንጹሃን ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው።
አልቃይዳን በይፋ ከተቀላቀለ ወዲህ ከአለም ህዝብ የተገለለው አልሸባብ አለም አቀፋዊ ትኩረትን ለመሳብ በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመፈጸም እቅድ እንዳለው በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው የዛቻ መግለጫዎቹ ቡደኑ ሃያል ነን ለሚሉ ሃገራት ሳይቀር ራስ ምታት ሆኗባቸዋል።
በኢህአዴግ ድጋፍ ወፌ ቆመ እያለ የሚገኘውን ሞቃዲሾ ላይ የተገደበ በአምሳሉ የፈጠረውን ስርዓት ባለስልጣናት አልሸባብ ሲሻው በሽብር ጥቃት በመግደል አሊያም እርስ በርሳቸው እንዲናቆሩ ጀሌዎቹን አሾልኮ በማስገባት ከሚፈጽመው ደባ ባሻገር ጊዜ እየጠበቀ ከርቀት በሚያስወነጭፋቸው የከባድ ጦር መሳሪያ አረር የቤተመንግስቱን ሰላም መቅኖ በማሳጣት ሶማሊያ ውስጥ  አለ የሚባለውን መንግስት ህግና ስርዓት ትርጉም አልባ አድርጎታል።
የሶማሊያ አለመረጋጋት አገርሽቶ ለጎረቤት ሃገራት ጦስ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ አልሸባብ የሽብር ስትራቴጂውን በመቀየር በቅርቡ ኬንያ ላይ በአንድ ዩኒቨርስቲ ማዕከል በክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት በሌሎች ላይ አጠናክሮ ለመቀጠል አለምአቀፍ አሸባሪ ቡድን ከሆነው አይሲስ ጋር በመዋሃድ እንደ ሊቢያ ቢጤዎቹ የሰው ልጅን አንገት በካራ ለማረድ የነደፈው እቀድ በአልሸባብ የአመራር አባላት መካከል ንትርክን ፈጥሮ መሰንበቱ ይነገራል። አልሸባብ ከቡድኑ ጋር ለመዋህድ ያቀረበው ጥያቄ ወታደራዊ የሎጀስቲክ አሊያም የሰው ሃይል ድጋፍ ከዚህ ከአረመኔ አይሲስ ለማግኘት እያደረገ ያለው ጥረት የአልሸባብን ወታደራዊ አቅም እየተመናመነ መምጣት በግልጽ የሚያሳይ ጣረሞት ነው በማት አንዳንዶች ይገልጹታል፡፡ በአንጻሩ ሌሎች አልሸባብ አለምአቀፋዊ አቅሙን እያጎለበት የመጣውን አረመኔ አይሲስ ተዋጊዎች ሶማሌያ በማስገባት ኢትዮጵያን በማተራመስ ለመበቀል የታቀደ ስትራቴጂ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በሃይማኖት ሽፋን ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሃራም በአካባቢው ሃገራት መንግስታት ወታደሮች በቅንጅት የከፈቱበትን ጦርነት መቋቋም ሲሳነው የቦኮ ሃራም መሪ “ሼካው” ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የዚህ ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው አይሲስ አሸባሪ ቡድን አካል መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። አልሸባብ ሰሞኑን እያሰማ ያለው ጩኸት ቡድኑን ለሁለት መክፈሉን ቢሰማም ይህ አጋጣሚ በአባላቱ መሃከል የተፈጠረው ልዩነት ሰፍቶ ለአልሸባብ ከሶማሊያ ምደር መጥፊያው ምክንያት ካልሆነ የ አይሲስ ዱካ ሶማሊያ ውስጥ ከታየ ኢራቅ፣ ሶሪያንና ሊቢያን እያተራመስ የሚገኘው ሰይጣናዊ ሃይል ለሃገራችን ሰላምና መረጋጋት በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ ከመሆን ሊያግደው የሚችል ምድራዊ ኃይል እንደሌለ በበርካቶች ዘንድ የሚታመን ሐቅ እየሆነ መጥቷል።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!
(Ethiopian Hagere Jed Bewadi ለጎልጉል የላኩት)

No comments:

Post a Comment